>

የጊዜ፣ የምድሪቱ፣ የእኛ፣ እና የሁሉ ነገር - አጭር የህይወት ታሪክ! (አሳፍ ሀይሉ)

የጊዜ፣ የምድሪቱ፣ የእኛ፣ እና የሁሉ ነገር – አጭር የህይወት ታሪክ!

አሳፍ ሀይሉ

«This book marries a child’s wonder to a genius’s intellect. We journey into Hawking’s universe while marveling at his mind. » 
 
         (- The Sunday Times, London)

በብዙ ቅዱሳት መጻሕፍትና የሐይማኖት ሰዎች ሰበካ እንደምናገኘው ሰው ትህትናን ለመላበስ፣ ራሱን ዝቅ ለማድረግ፣ ከእርሱ በላይ እጅግ ታላቅ ኃይልና ጥበብ እንዳለ ይገነዘብ ዘንድ – እንዲያደርግ የሚመከረው አንድ ነገር አለ፡፡
ያም ምድርና ሠማያትን የዘረጋውን፣ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ያሉ ፍጡራንን የሚገርም ረቂቅ ተፈጥሮ አላብሶ የፈጠረውን፣ ይህችን ዓለም፣ ህዋውን፣ ከዋክብቱን፣ ባህሩን፣ ሠማዩን፣ የብሱን፣ አዕዋፉን፣ አበባውን ሁሉ እጅግ ውብና ማራኪ አድርጎ በረቂቅ ጥበቡ ያነፀውን ታላቁን ፈጣሪ ማሰብ፣ የፈጣሪን ታላቅነት፣ የፈጣሪን አዋቂነት፣ የፈጣሪን ቻይነት ማሰብ ነው፡፡
ያን ስታስብ – አንተ ምን ያህል አንድ ተራ ኢምንት ፍጡር እንደሆንክ ትረዳለህ፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ የምናገኛቸው ብዙ ነብያት፣ ንጉሣንና ወንጌላውያን – የፈጣሪን ንፅህና ባየሁ ጊዜ ምን ያህል የረከስኩ እንደሆንኩ ተረዳሁ – ሲሉ ነው የምናገኛቸው፡፡ በፈጣሪ ፊት እንደ ትል ያነስሁ ሆኜ ተገኘሁ ነው የሚሉት፡፡
የፈጣሪ ታላቅነት፣ የራሳችንን ማንነት አሳይቶን፣ ትሁቶች ያደርገናል፡፡ በሰውኛ ከታሰበ – ምናልባት ብዙ ወደ መንፈሳዊ ሕይወት የቀረቡ ሰዎች በትህትና የተሞሉ የመሆናቸው ምክንያቱ ይህ ሳይሆንም የሚቀር አይመስለኝም፡፡
አንዳንዴ ግን ትሁት ሆነህ ለመገኘት፣ ከእብሪትህ በረድ ለማለት፣ የቱን ያህል አላዋቂ እንደሆንክ ለመረዳት፣ የግድ ወደ ፈጣሪ ተንጠራርተህ መመልከት አይጠበቅብህም፡፡ ራስህን ከኮፈስክባት ትንሽዬ የሙያ ጉሮኖ ውጣ፡፡
ራስህን ከፍ አድርገህ ከምትመለከትባት ትንሽ የዕውቀት መስክ ወጣ በል፡፡ ራስህን ታላቅ አዋቂ አድርገህ ከቆጠርክበት የተሰማራህበት የሕይወት መስክ ትንሽ ወጣ በል፡፡ እና ፍፁም ጨዋነትህን ወደምትረዳባቸው ለጆሮህ ባዳ፣ ለዓይህን እንግዳ ወደሆኑ ሙያዎች ጎራ በል፡፡
ያን ጊዜ አንተ ምን ያህል አላዋቂ እንደሆንክ ይታወቅሀል። ምን ያህል እጅግ ብዙ የማታውቃቸው ነገሮች እንዳሉ፣ በተለያዩ የዕውቀት መስኮች፣ በተለያዩ ሳይንሶች፣ በተለያዩ ልምዶች – ከአንተ እጅግ እጅግ እጅግ (ሚሊዮን ጊዜ) የሚበልጡ ሰዎች እንዳሉ ይገባሀል።
ብዙ የታላላቅ ዕውቀት ባለቤት የሆኑ፣ የብዙ አስደናቂ ጸጋ ባለቤቶች የሆኑ ሰዎች እንዳሉ ትገነዘባለህ፡፡ እና ትዕቢትህ ሳይወድ በግዱ ይለዝባል፡፡ ትህትናን ትላበሳለህ፡፡ ለሌሎች አክብሮት ይኖርሃል፡፡ አንገትህን ትሰብራለህ፡፡ በትህትና፡፡
ትህትና የገነት ቁልፍ ነች፡፡ ትህትና የዕውቀትም፣ የጥበብም ቁልፍ ነች፡፡ “የማላውቀው ነገር አለ” ብለህ ካላመንክ፣ ለማወቅ አትነሳሳም፡፡ ትህትና ሲርቅህ፣ አለማወቅህን መረዳት ሲሳንህ ብዙ ዕውቀቶች፣ ብዙ ትምህርቶች፣ ብዙ ልምዶች፣ እና ብዙ ጽድቆች ያመልጡሃል፡፡ በብዙ ነገሮች መሞላት ስትችል፣ እዚያው በዚያው እየረገጥክ ባለህበት የምትንሿሿ የጸናጽል ሻኩራ ሆነህ ትቀራለህ፡፡
እኔ ብዙ ጊዜ የምለው ነው፡፡ የፈጣሪን ታላቅነት ለማወቅ የግድ መንፈሳዊ መጻሕፍትን ማገላበጥ አይጠበቅብህም፡፡ ናሽናል ጂኦግራፊክ (“National Geographic”) የሚለውን አስገራሚ የምድሪቱን ፍጡራን የሚያስቃኝ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ማየት በቂህ ነው፡፡
የፈጣሪን ተዓምር ለመረዳት፡፡ እመነኝ፡፡ ናሽናል ጂኦግራፊክ ፈጣሪ በኪነጥበቡ ወደዚህች ምድር ያመጣቸውን ጉድ የሚያሰኙ ፍጡራን እያሳየህ የወጣልህ በፈጣሪ አማኝ ሰው ያደርግሃል፡፡
ትህትናን ትላበስ ዘንድ ደግሞ የግድ ወደ መንፈሳዊ ሰበካዎች መሄድ አይጠበቅብህም፡፡ አንዳንድ ድንቅ መጽሐፎችን ገልበጥ ማድረግ ይበቃሃል፡፡ አላዋቂነትህ የቱን ያህል እንደሆነ አሳምረው ይነግሩሃል፡፡ እና አደብ ያስገዙሃል፡፡ ትሁት ትሆናለህ፡፡
ለእኔ ይህ የቲዎረቲካል ፊዚክስ ሊቅ፣ የማቴማቲክስ ሉካሲያን ፐሮፌሰርና፣ ዓለም ያደነቀው ምናባዊ ጭንቅላት ባለቤት የሆነው – የስቴፈን ሃውኪንግ መጽሐፍ – እንዲያ ነው ያደረገኝ፡፡
በዚህ በዓለም ከመጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ እጅግ ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ ታትሞ በመነበብ ብዛት ከፍተኛውን ደረጃ እንደያዘ በሚነገርለት ታዋቂ መጽሐፉ – በ ‹‹ብሪፍ ሂስትሪ ኦፍ ታይም›› – ስቴፈን ሃውኪንግ – እንደዚያ ነው ያደረገኝ፡፡ የአላዋቂነቴን ግዝፈት በመረዳት ብዛት አንገቴን በሃፍረት አስደፋኝ፡፡
ስቴፈን ሃውኪንግ በዚህ መጽሐፉ የኳንተም ፊዚክስን፣ የሪሌቲቪቲን፣ የብላክ ሆልን፣ የጊዜን ዑደትና አቅጣጫ፣ የዩኒቨርስን ሁለመና፣ የስበትን ህዋዊ መርሆዎች፣ የከዋክብትና የጸሐይን ጠባይና ዕድሜ፣ የኬሚካሎችንና ሞለኪውሎችን ባህርያት ይተነትናል።
ሁሉንም ነገር የሚመለከቱ ዘርፈ-ብዙ ትንታኔዎችንና ዕይታዎችን፣ ከዓለሙ ፈጣሪ ከእግዜሩ ጋር የሚሟገትባቸውን መሠረታዊ የምድርና ህይወታውያን አፈጣጠር ጥያቄዎች፣ እና ሌሎች እልፍ አስደናቂ ፅንሰ ሃሳቦችና ቀመሮችን ደርድሮ ጠበቀኝ ሃውኪንግ፡፡
ምንም አላልኩም፡፡ ምንምም ማለት አልቻልኩም፡፡ ብቻ ከፍ ባለ የእንግድነት፣ እና የትህትና መንፈስ ተሞልቼ – በጥምር ጦር እንደተወረረችው እንደ ባግዳድ ከተማ ‹‹ሰጥ-ረጭ›› ብዬ አንብቤ በትህትና ከደንኩ፡፡ መጽሐፉን፡፡
ምን ተሰማኝ? ወደ አዲስ የማላውቀው እንግዳ ዓለም የመምጣት፡፡ የዕውቀት እንግዳ፡፡ የፊደል ባዳ፡፡ እና በጣም ትሁት የመሆን መንፈስ፡፡ ኧረ መሸማቀቅ ሁሉ ያለበት ትህትና፡፡
ልክ ራሱ ስቴፈን ሃውኪንግ ወደፊት ይቻል ይሆናል ብሎ በመጽሐፉ መጨረሻ እንዳካተተው ‹‹ታይም ትራቭል›› ሁሉ – ይህ መጽሐፉ ከማስደመም አልፎ መቼ ነው እንዲህ ተደምሜ የማውቀው? አሰኝቶ – በ”Time Travel” (በታይም ትራቭል የጊዜ ሠረገላ) ወደ ኋላ አክንፎ መለሰኝ፡፡
በዚህ መጽሐፍ ከመደመሜ የተነሳ ያደረብኝን እጅግ ብዙ ሚሊዮን ትህትና – እና መሸማቀቅ – ሳጤነው – አዲስ አልሆንብህ ብሎኝ ግራ ገባኝ መጀመሪያ፡፡ የት ነው የማውቀው ይሄን መሸማቀቅ? ‹‹ደዣቩ›› ይሆን? መስሎኝ ነበር፡፡ ግን አይደለም፡፡ አስታወስኩት፡፡ ከዚህም በፊት እንዲህ ዓይነት የመደመም፣ እና አንገት የመድፋት ስሜት ሁለመናዬን አልብሶት ነበር፡፡
ድሮ ገና በ3 ዓመት ዕድሜዬ ይመስለኛል፡፡ ሀሁ ፊደል ልቆጥር፣ ለመጀመሪያዋ ዕለት – አባባ ይብዛ ጋር አልሄድም ብዬ እያለቀስኩ – እርጥቡ እንባዬ ከፊቴ ላይ ሳይደርቅ፣ በአንድ ትልቅ የዋርካ ዛፍ ጥላ ተጠልላ፣ ወደ ቀኝ ጎን አዘምማ ወደቆመችው፣ የቆርቆሮ መማሪያ ክፍል ደርሼ – ወደ ውስጥ ስገባ – እና አለፍ አለፍ ብለው በተደረደሩ የድንጋይ እግሮች ላይ በተጋደመው ረዥሙ ጠፍጣፋ አግዳሚ ጣውላ ላይ – ከሌሎች ህጻናት ጎን ተኮራምቼ ቁጭ ስል፡፡
በፊደል ቤት ቁጭ ብዬ – እነዚያን ፊት ለፊቴ በግድግዳው ላይ በተሰቀለው የፊደል ገበታ ላይ ለጉድ የተሰረደሩትን – ያኔ ብዛታቸው የሠማይ ከዋክብትን ያህል የመሰሉኝን – የአማርኛ ሆሄያት – እንደ ጉድ ስመለከት፡፡
እና መቼ ይሆን እነዚህን ሁሉ አጥንቼ ከዚህች ክፍል በሠላም ተርፌ የምወጣው – እና ወደ ቀጣዮቹ የአቡጊዳ፣ የመልዕክተ ዮሐንስና የዳዊት ክፍሎች የምሸጋገረው? በሚሉ ሥጋቶች በተቀሰፍኩበት ቅጽበት፣ የተሰማኝ ባይተዋርነት፣ የወረሰኝ አላዋቂነት፣ ያላበሰኝ ትህትና፣ እና ኩምሽሽ አድርጎ ያስቀረኝ የመሸማቀቅ ስሜት ጭምር፡፡ ትዝ አለኝ፡፡ ልክ እንዲህ እንደ አሁኑ፡፡ በጣም አድርጎ ትዝ፡፡ ነው ያለኝ እንጂ፡፡
ስቴፈን እግዜር ይይልህ፡፡ እንደ ገሞራው – “አንተ የብላክ ሆል ሳይንቲስት – ነፍስህን አይማረው”፡፡ ልለው ፈለግኩ፡፡ እና ተውኩት፡፡ ትዕቢቴ አልበረደልኝም ማለት ነው? ብዬ ድጋሚ ሽምቅቅ፡፡
አንዳንዴ ግን እነዚህን ቲዎረቲካል ፊዚሲስቶች፣ ማቴማቲሺያንስ፣ እና ሌሎች ብዙ ሳይንሳዊ ኤክስፐርመንቶቻቸውንና ትንታኔዎቻቸውን በጥቃቅን ላብራቷሮቻቸውና በግዙፍ የኤሌክትሮን ኮላይደር ፉጋቸው ውስጥ ተቆልፈው የሚመረምሩ ያለም ሳይንቲስቶችና ሊቃውንት ግን – አንድ የጋራ ነገራቸው ይገርመኛል።
በቁጥር እጅግ አብዝተው ያምናሉ፡፡ በሚያዩት ናሙና እጅጉን ይንተራሳሉ፡፡ በሚሰሩት ምናባዊ ስሌት እጅጉን እርግጠኞች ናቸው፡፡ ይሄ ነገራቸው ግን ብዙ ጊዜ ይገርመኛል፡፡
በእርግጥ ለእኔ በልጅነቴ የቀሰምኳቸው ሆሄያት ወደፈለግኩት ዓለም በሃሳብ የምቀዝፍባቸው ውቅያኖሶቼ ሆነው እንደሚያገለግሉኝ ሁሉ – እነዚህ ሳይንቲስቶች ደግሞ ቁጥር ነው መጓጓዣቸው፡፡ ካለ ቁጥር ስሌት አይንቀሳቀሱም፡፡ ቁጥሩን የሚፈልጡት ለጉድ ነው፡፡
42 (አርባ ሁለት ተከታታይ) ዜሮ ዜሮ ዲጂቶች ያሉትን ቁጥር – የሚሊዮን ሚሊዮንኛ ሚሊዮንኛ ሚሊዮንኛ ሚሊዮንኛ… ጊዜ እያሉ ያባዛሉ፣ ያካፍላሉ፣ የከዋክብትንና የጨረቃን፣ የሞለኪውሎችንና የራዲዬሽኖችን፣ የፍጥረትንና የጥፋትን ጉዞዎች በቁጥር ይደረድራሉ፡፡
በቁጥር ይቀምራሉ፡፡ በቁጥር ይተውራሉ፡፡ በቁጥር ቴረም ሠርተው ያመሳክራሉ፡፡ በቃ ቁጥር ነፍሳቸው ነው፡፡ ቁጥርን እንደ እግዜሩ ሊያምኑት ምንም አይቀራቸውም፡፡ ይገርመኛል፡፡ ለምንድነው ግን እንዲህ ለቁጥር የተገዙት? ለምንድንስ ነው በቁጥር ሁሉ ነገር ላይ እንደርሳለን ብለው የልብ ልብ የተሰማቸው?
አልበርት አንስታይን፣ ኒውተን፣ ዳልተን፣ ኦፐንሃይመር፣ ፌርሚ፣ ወይ ኤዲንገርና ጄጄ ቶምሰን፣ ወይ ሌሎች ብዙዎች በቁጥር ተመሥርተው ተዓምራዊ የምድሪቱን ኃይል ቀስቅሰው ስላሳዩ ይሆን? ወይስ አንስታይን የአቶሚክ ቦምብን ከስቶ የቁጥሮችን ተዓምር ስላሳየ?
በሰው ልጅ የቁጥር ስሌት የተዋቀሩ ሰው ሠራሽ የሃይድሮጂን ቦምቦች – ፈጣሪ ከዘረጋት ከፀሐይዋ በላይ አንድ ሺህ ሚሊዮን ጊዜ የሚልቅ የሙቀት መጠን አመንጭተው የቀረባቸውን ሁሉ አቅልጠው ወደ ትነትነት እንደሚቀይሩት ስላረጋገጡ? ይህ ሁሉ ቁጥርን ከእግዜሩ በላይ ለማመን – ወይ ይህ ሁሉ የቁጥር ተዓምር የእግዜሩን ተዓምር እንዲሞግቱ አድርጓቸው ይሆን?
ይገርመኛል ይሄ ነገራቸው ብቻ፡፡ አንዳንዶቹ ሊቃውንት ፈጣሪ አምላክ ፍጥረተ ዓለሙን ‹‹ሀ›› ብሎ አልጀመረም – ለማለትም ይቃጣቸዋል፡፡ ቢግ ባንግ – የፍጥረተ ዓለም መጀመሪያ ይሁን – ተቀብዬአለሁ – ስለ ቢግ ባንግ ምንነት ግን አትመርምሩ – ብለው የካቶሊኩ ጳጳስ በኮስሚክ ሳይንቲስቶች የጥናት ጉባዔ ላይ ቀርበው ባደረጉት ተማጽኖ – ሳይንቲስቱ ስቴፈን ሊሳለቅ ጥቂት ይዳዳዋል፡፡
ሐይማኖቶች ሳይንሳዊ ለመሆን የሚያደርጉት ሩጫ፡፡ ሣይንሱ ዘልሎ ከሐይማኖት ጋር የሚያደርገው ፍልሚያ፡፡ ይሄ ሁሉ ይገርመኛል፡፡ ቁጥሮች ፈጣሪን ሊተኩ ይችላሉን? እኚያ ጳጳስ የፈሩት ይህ ጉድ እንዳይከሰት ይሆን? አልመሰለኝም፡፡
ችግሩ ግን እነርሱ በቁጥሮቻቸው ተዓምራትን ሰርተው ያሳዩ ሳይንቲስቶች ናቸው፡፡ እኔ ደግሞ በእነርሱ ፊት እንደ ህጻን የምቆጠር አንድ ተራ አላዋቂ ነኝ፡፡ “ውሃ ቁልቁል እንጂ ሽቅብ አይፈስም”፡፡ ትቀበላለህ እንጂ አትሰጥም፡፡ ይህ ነው? ይህም አልመሰለኝም፡፡
አንድ ሥፍራ ላይ ስለ ብዙ የምድሪቱ አፈጣጠር (እና አጠፋፍ) መላምቶችን በብዙ የቁጥር ቀመሮችና ማስረጃዎች አስደግፎ በሳይንሳዊ መንገድ እየተነተነ ግን – አስቦትም ሆነ ሳያስበው – በመሐሉ – ስቴፈን ሃውኪንግ ጠብ ያደረጋት አንዲት ሃሳብ እጅጉን ማርካኝ ቀረች፡፡ ከሃሳቦቹ ሁሉ መሐልም መዝዤ ለስንብቴ አስቀረኋት፡፡
ስቴፈን ሃውኪንግ የቴርሞዳይናሚክስን ሁለተኛውን ህግ እያስረዳ ነበር፡፡ የዚህ ዓለም ነገሮች ሁሉ ጊዜ በሄደ ቁጥር ይበልጡኑ ወደ ተበላሸው፣ ወደ ተዘበራረቀው፣ እና ወዳልተስተካከለው ነገር አቅጣጫ የመጓዝ ዝንባሌ አላቸው – የሚል ነው ይሄ ‹‹የመርፊ ህግ›› ተብሎም የሚታወቅ የተፈጥሮ ህግ፡፡
ለምሳሌ ድንጋይ ቢኖር – በጊዜ ብዛት ድንጋዩ እየተሸረፈ፣ እየተቀረፈ፣ እየተሰነጠቀ፣ እየወየበና፣ እየተሸረሸረ ነው የሚሄደው፡፡ እንጂ እየተሞላ አይሄድም፡፡ ዛፍ ቢኖር እንዲሁ አድጎ አድጎ እያረጀ፣ እየጎበጠ፣ እየተሰባበረ ነው የሚሄደው፡፡ ብዙው ተፈጥሮ እየተራቆተ ነው የሚሄደው፡፡
በዚህ ህግ መሠረት የሻይ ሲኒህ ከጠረጴዛው ላይ ቢወድቅብህ የመሰባበር እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ እንጂ ወደ ኋላ ተመልሶ የተሰባበረው ተገጣጥሞ አንድ ወደ መሆን አይሄድም፡፡
ሲኒው ከወደቀበት ጊዜን ወደኋላ ጠምዝዞ ሽቅብ ነጥሮ ወደነበረበት አዲስነት ራሱን ገጣጥሞ ሲመለስ ካየህ – ይልሃል ስቴፈን ሃውኪንግ – ወይ የቪዲዮህ ፊልም እያጭበረበረህ ነው – ወይ የ”ታይም ትራቭል” ሳይንሳዊ ልብወለድ መጽሐፍ ወይ ፊልም እያየህ ነው፡፡
ከዚህ የተፈጥሮ ህግ ስንነሳ – በቢግ ባንግ ጊዜ ከአስር ሺህ ሚሊዮን ዓመታት በፊት የተፈጠረችው ምድራችን – በጣም የተበሻቀጠች፣ በጣም የተፍረከረከች፣ በጣም የተበታተነች፣ እና ብዙ ነገሯ ያልረጋ ነበረች፡፡
ምድሪቱ በዚያ ዓይነቱ “ዲስኦርደርሊ ስቴት” ውስጥ ከነበረች ታዲያ – እንዴት በጊዜ ብዛት ወደ ባሰ ዲስኦርደር፣ ወደ ባሰ መበላሸት፣ ወደ ባሰ ግልብጥብጥነትና መላቅጥ መጥፋት እንጂ – እንዴት ወደተስተካከለ ምድርነት ልትቀየር ቻለች?
በቢግባንግ ፍንዳታ ፍንክትክቷ የወጣው ምድራችን፣ እንዴት በጊዜ ሂደት ይበልጥ መላቅጧ እየጠፋና እየተሸሬረፈች በመምጣት ፋንታ ወደ ተስተካከለና አንጎላቸው እየመጠቀ የሚመጡ ፍጡራንን ወደምታስተናግድ – የተሻለ የተፈጥሮ ሥርዓት ወደተገነባባት ዓለምነት፣ እና የተሻሉ ፍጡራንን ወደምታስተናግ ምድርነት እንዴት ተቀየረች?
በድንገተኛ ፍንዳታ የተጀመረች ዓለም – እንዴት እየተስተካከለች ትመጣለች? ይሄ የቴርሞዳይናሚክስን ህግ የሚጻረር ነው፡፡ … እንዲህ እያለ እየጠየቀ.. እስከዛሬ የሰው ልጅ የደረሰባቸውን የስነፍጥረት ቀመሮችና ሳይንሳዊ ድምዳሜዎች.. በጥያቄ ምልክት ውስጥ አስገብቶ ያስቀምጥልናል፡፡ እና እንዲህ ይላል፡-
‹‹ቆይ እሺ ምድር የሆነ ፈጣሪ አምላክ አስተካክሎ፣ አቀናብሮ፣ አቅዶ፣ ሁሉን ነገር አሰካክቶ ያስቀመጣት ካልሆነች፣ ፍጡራኑም በ”ናቹራል ሴሌክሽን”ና “ኢቮሉሽን” እና በ”ኮስሚክ ኤግዚስተንስ” አካሄዶች በደመነፍሳዊ ሂደት በህይወት የሰነበቱ ከሆኑ፣ እና የሰው ልጆች ሁሉ እንዲሁ ወዲህ ወዲያ እየተካለቡ የሚኖሩባት፣ እንደ ዝንጀሮ ከቦታ ቦታ እንደሚዘልሉ ዝንጀሮዎች ሆነው ለሚሊዮን ዓመታት የዘለቁባት አውድማ ከነበረች ይቺ ዓለም-
‹‹አንድ ነገር ብቻ አይዋጥልኝም – ያም – በእነዚህ ቲዎሪዎች መሠረት ያ ዝንጀሮ የሆነ ፍጡር በምድሪቱ ላይ ያሳረፋቸው አሻራዎች ሁሉ – ልክ ፊደላቱን እየረጋገጡ በታይፕራይተር ላይ ግርር ብለው ከሚያልፉ ዝንጀሮዎች እንደሚገኘው ዝብርቅርቅ ያለ አይነት ጽሑፍ መሆን ነበረበት!
“ግን የዓለም ሁኔታ የሚያሳየን ከዚያ በተቃራኒው ከሆነስ? ያ ዝንጀሮዎች እየረጋገጡ ያለፉበት ታይፕራይተር፣ ጽሑፍ አኑሮት የተገኘው ነገር  ሲታይ የሼክስፒርን ዓይነት በጥበብ የተተየበ ጽሑፍ ሆኖ ስታገኘውስ? ያንን በምን መልክ ነው፣ በምን ዓይነት የፊዚክስ ወይ የኮስሚክ ቀመር ነው ልታስረዳው የምትችለው?››
ብሎ ይጠይቃል፡፡ እኔም ከብዙ ፈጣሪን ከሚፈታተኑ አስደናቂ ቀመሮቹና ጥያቄዎቹ መሐል ይህቺኑ ጥያቄ ይዤ ተሰናበትኩ፡፡
ብዙ መንፈሳውያን ሰዎች ስለ ፈጣሪ መኖር ሊያስረዱን ሲፈልጉ “የዓይንን አፈጣጠር ተመልከቱ” ይሉናል፡፡ እና ያ የረቀቀ የዓይን አፈጣጠር በዝም ብሎ የዝንጀሮ ታይፕ ተጽፎ ታነፀ? ቁጥርን ስናከብር፣ ሳይንሳዊ ቀመሮችን ስናከብር፣ የጥበብን ሁሉ ፈጣሪ፣ የስሌቶች የቀመሮች ሁሉ ሊቅ የሆነውን የታላቆች ታላቅ ፈጣሪንስ ማክበር ለምን ተሳነን?
ስቴፈን ሃውኪንግ ደስ ያለኝ – ፈጣሪን አክብሮ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ ለነገሩ ስቴፈን የሚከተለው አልበርት አንስታይንም – ምንም እንኳ የምድሪቱን ጅማሮም ፍጻሜም በጄነራል ሪሌቲቪቲ ቲዎሪው ተንብዮ ቢያልፍም – ፈጣሪን ግን ፊት ለፊት አይጋፋም ነበር፡፡
እነዚህ ባለ ዕውቀቶች አንገቴን በትህትና አስደፉኝ፡፡ የተወሰነ የፈጣሪ ትህትናም አላጣሁባቸውም፡፡ እስቲ ከየተለቅንበት የሙያ ጉሮኖ ውስጥ እንውጣና ጥቂት ወደ ሌሎች የሙያ ዓለም ውስጥ ዘለቅ ብለን ያላቸውን፣ የሚሰጡትን እንመልከት፡፡ ከትህትናቸው ጭምር፡፡ ትህትና፡፡ የበዛ ትህትናን እንድንላበስ ያግዙናል፡፡ ከዕውቀት ጋር፡፡
የስቴፈን ሃውኪንግ ‹‹ኧ ብሪፍ ሂስትሪ ኦፍ ታይም›› በታተመ በ10ኛ ዓመቱ በ1996 በስቴፈን ሃውኪንግ ዳግመኛ ጭማሪዎችና ማስተካከያዎች ታክሎበት የወጣ ኤዲሽን ነው ይህ፡፡ ለእንደ እኔ ዓይነቱ የቲዎረቲካል ፊዚክስ ጨዋ እንዲሆን እና እንዲገባ ተደርጎ የተጻፈም መጽሐፍ ነው፡፡
በሶፍት ኮፒ እንደ ልብ የሚገኝ በመሆኑም፣ ማንም ትንሽ ቀለም የቆጠረ ሰው አግኝቶ ቢያነበው ስለሚኖርባት ዓለም ብዙ ሳይንሳዊ እሳቤዎችን ይገበይበታል፡፡ ብዙ ዕውቀትን፣ ከብዙ ትህትና ጋር ይጎነጭበታል።
በበኩሌ ወደ መጽሐፉ ሳይንሳዊ ይዘቶች ገብቼ በድፍረት ከምቀላምድ – ይዘቱ ከመጽሐፉ አሊያ በዘርፉ ከሚያውቅ ሰው አንደበት ቢነገር መልካም እንደሚሆን ተገንዝቤ – ለራሴ ብዬ ካነበብኩት ከላይ ባለው መልኩ ብቻ አስተማሪ ናቸው ያልኳቸውን የበኩሌን እይታዎች አንጸባርቄ ማለፉን መረጥኩ፡፡
አካላዊ ውሱንነት ሳይበግረው፣ ከቀሰፈው ህመም ጋር እየታገለ፣ የምሬት መንፈሱን በአዝናኝ መንፈስ ቀይሮ፣ ለብዙ ዓመታት ስለ ዓለማችንና ስለ ሰው ልጅ ዕጣ ፈንታ የቻለውን ሁሉ ተመራምሮ፣ ያለውን ሁሉ አበርክቶ ህይወቱ ላለፈችው የዓለማችን ዕውቅ የሂሳብ ሊቅና የፊዚክስ ቀማሪ ስቴፈን ሃውኪንግ – ፈጣሪ ነፍሱን በሠላም ያሳርፍለት ብዬ – በትህትና ምስጋናዬን አቅርቤ አበቃሁ፡፡
ጊዜን የፈጠረ አምላክ፣ ጊዜያችንን አብዝቶ ይባርክ!
በኃያላን ያልተረታች፣ በጊዜ ያልተፈታች፣ ዕፁብ ምድራችንን ኢትዮጵያን፣ ድንቅ፣ መካር፣ ኃያል አምላክ አብዝቶ ይባርክ!
የጥበብ ሁሉ ፈጣሪ – ስሙ የተመሰገነ ይሁን!
Filed in: Amharic