>

"ቀሳፊውን የሞት ወንበር የደፈሩ ጀግና ንጉስ....!!! " (አሳፍ ሀይሉ)

“ቀሳፊውን የሞት ወንበር የደፈሩ ጀግና ንጉስ….!!! “

አሳፍ ሀይሉ

ስለ ወንበር ካነሳን አንድ መታለፍ የሌለበት ወንበር አለ። ይህ በፎቶው የሚታየው ወንበር አፄ ምኒልክ የንግስና ወንበራቸው አድርገው የተጠቀሙበት ታሪከኛ ወንበር ነው፡፡ ከአውሮፓ የመጣ፡፡
በዚህ ወንበር ላይ አውሮፓ ውስጥ ሞት የተፈረደባቸው ሰዎች ቅጣታቸውን በሚቀበሉባት ዕለት፣ ተደላድለው ይቀመጡበትና በራስ ቅላቸው የኤሌክትሪክ ኃይል የሚተላለፍለት የብረት ባርኔጣ ይገባላቸዋል። እና በተቀመጡበት የቅርብ ወዳጅ ዘመድ እና የፍርድ አስፈፃሚ ባለሥልጣናት በተገኙበት፣ ፈጣን ሞታቸውን ይቀበሉበታል፡፡
ይህ ወንበር ብዙዎችን በቁም እያቃዠ ወደ ወንጀል ድርሽ እንዳይሉ ያደረገ ( እና በያገሩ ወንጀልን የቀነሰ) ነው እየተባለ ይሞካሻል። አሁንም ድረስ በአንዳንድ የአውሮፓና አሜሪካ ግዛቶች ለሞት ቅጣት በጥቅም ላይ ይውላል። ብዙዎች ግን በዘግናኝነቱ የተነሳ፣ የሞትን ቅጣት ወደ መርፌ በማሻሻል ይህን አስፈሪ የኤሌክትሪክ ወንበር አስቀርተውታል።
ታዲያ፣ ዘመናዊ የተባለች የሰሟት ነገር ሁሉ ወዳገሬ ትምጣልኝ የሚሉት ዘመናዩ ንጉሥ ምኒልክ የዚህች አስፈሪ ወንበር ዝና ከጆሯቸው ደረሰ። ወዲያውም “እኔም ሃገር ወንጀለኛ ከሚሰቀልና ከሚሠየፍ ዘመናዊ የሆነ አውሮፓዊ ሞት ይሙት” አሉና – ይህን ዘመናዊ የሞት መቀመጫ አስመጡ፡፡
ያኔ ለአድዋ ገና ስድስት ዓመታት ይቀሩታል፡፡ ይህ ወንበር በአውሮፓ ጥቅም ላይ ከዋለ ጥቂት ወራት ተቆጥረዋል። ወንበሩ አውሮፓ ጥቅም ላይ በዋለ ማግሥት በማስመጣት በአፍሪካ የመጀመሪያዎቹ ሳንሆን አንቀርም በዚህም ወንበር፡፡
ሶስት ወንበሮች ናቸው ወዳገራችን የመጡት፡፡ ምኒልክም የወንበሩን ግርማ ሞገስና ሁናቴ እንዲሁም የሞት ወንበር ስለሆነ እንዳይጎትተን እያለ ሁሉም ባለሟል ሊጠጋው ራሱ መፍራቱን ሁሉ አስተዋሉ፡፡ እና እጅግ ወደዱት፡፡ ማለፊያ ነው በሉ ሥራ ይጀምርልኝ አሉ፡፡ ከዚያ ግን ጉድ ፈላ!
ለካንስ ኢትዮጵያ ውስጥ ያኔ የኤሌክትሪክ ኃይል አልነበረም፡፡ እና  በጉጉት ባህር ተሻግሮ የመጣው ዓለምን ያንቀጠቀጠው የኤሌክትሪክ ወንበር እኛ ምድር ሲመጣ መግደያነቱ ከሸፈ።
ተመስገን ነውኮ አንዳንዴ ስሙ “ኋላቀርነት” ይባላል እንጂ ከቴክኖሎጂ ጦስ ለመትረፍ መቻልምኮ ያልታወቀበት ምርቃት ነው። የሆነው ሆኖ ሰው ግን ዝናውን ሰምቶ እየፈራው፣ ይህን የሞት ወንበር ከተቀመጠበት ተጠግቶ የሚነካው ጠፋ፡፡ እንደ ታቦት ተፈራ። ይሄን ሰምተው “በሉ አምጡልኝ” አሉ እምዬ ምኒልክ፡፡
“አንዱን ለዙፋኔ የእልፍኝ ወንበር አድርጉልኝ፤ ሁለቱን ደግሞ በወይኑና በጥዱ ጥላዎች ሥር አኑሩልኝ፤ እኔ ብቻ የምቀመጥባቸው፤ የንጉሠ-ነገሥት መንበሮች ይሆናሉ” – ሲሉም አዘዙ፡፡ እንዳሻቸውም ተደረገላቸው። አይቀሬው ሞት በላያቸው አፈር ሊያለብስ ሳይመጣ በፊት፣ ቀድመው በዚያ የሞት ወንበር ላይ ጀግነው ለዓመታት ተቀምጠውበታል። እምዬ ምኒልክ፡፡ ሞትን የደፈሩ ጀግና፡፡
ለመሆኑ የውጭ እንግዶች መጥተው የእምዬን ወንበር ቀርበው ሲያዩት እንደምን ያለ ቀዝቃዛ የፍራቻ መንፈስ ለቅቆባቸው ይሆን? ከሞት ጋር ያን ያህል ቅርበት? ለምን? ምናልባት ዘወትር ሟች፣ ዘወትር አላፊ መሆናቸውን እንዲያስታውሳቸው ይሆን?  ወይስ የሥልጣንን ምንነት ለማመልከት አስበው ያደረጉት ይሆን?
የሞትን አይሸሼነት፣ ከሞት ጋር የመጋፈጥን ጀግንነት፣ ሞትን የመናቅ አይበገሬ ኢትዮጵያዊ ሰብዕና፣.. ለቀረባቸው ሁሉ እያሳዩ ይሆን?
የኢትዮጵያ ነገሥታት አንበሣ የሚያለምዱት ለዚሁ ዓላማም አይደል? ከሞት ጋር ፊት ለፊት መጋፈጥን፣ የማይደፈረውን መድፈርን፣ ሞትን ባለመፍራት ድል መንሳትን፣ ይህን ኢትዮጵያዊ ሰብዕና የተላበሱ ነበሩ። እምዬንም ይህ የሞት ወንበር ያን ዓይነቱን አይበገሬ የቀደምቶቻቸውን ሰብዕና አላብሷቸው ይሆን?
ወይስ የተከተሉት ትውልዶቻቸው ሁሉ በእርሳቸው ወንበር ሙጭጭ ብለው እንደሚሟሟቱበት በድርጊት የገለፁበት የሆነ አስፈሪ ክፉ ንግርት ይሆን? ወይስ ምን? አንድዬ ይወቅ እንግዲህ! እውነታው ግን ያ የምኒልክ ቤተመንግሥት ወንበር እስከዛሬም በጥቂቱም ቢሆን ያን ባህርዩን አለመተዉ ነው፡፡
አንዳንዴ አንዳንድ ነገሮችን እያነሱ እንደ ሻይቡና መጫወቱ ደስ ይለኛል። በያንዳንዱ ግርምታችን ልክ አንዳንድ ቁምነገር አይጠፋም የሚል እምነት አለኝ። ሞትን ለደፈሩት የኢትዮጵያ ጀግና ንጉሥ ለእምዬ ምኒልክ ታላቅ ክብርና የነፍስ ሰላምን ተመኝቼ አበቃሁ።
“እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት
አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፡፡ እኔም
እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡
እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉ ነውና
ስለ እኔ ሞት አላዝንም፡፡ እንግዲህም
ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡”
 – የዓፄ ምኒልክ ክተት ዐዋጅ፣ የመጀመሪያው ዐረፍተነገር።
     (መስከረም 1888 ዓ.ም.)
Filed in: Amharic