>

የፕሮፌሰሩ የፓርላማ አባል ማሳሰቢያ!!! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

የፕሮፌሰሩ የፓርላማ አባል ማሳሰቢያ!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

በዛሬው የፓርላማ ተብየው ውይይት ጥያቄያቸውን መጨረሻ ላይ እንዲያቀርቡ የተደረጉት አንድ ፕሮፌሰር ያቀረቡት ማሳሰቢያ ነበር፡፡ እሱም ምንድን ነው “በአንድ የፓርላማ ሴሽን ላይ ጥያቄ እንዲያቀርብ የሚፈቀደው ለሃያ ሰው ብቻ ነው፡፡ ይሄም ማለት በአምስት ዓመቱ የፓርላማ ቆይታ ሁለት መቶ ሰው ብቻ ነው ጥያቄ ማቅረብ የሚችለው ማለት ነው፡፡ 547 የሕዝብ ተወካዮች ባሉት ፓርላማ ውስጥ በሥራ ዘመኑ ዕድል የሚሰጠው ለሁለት መቶ ሰው ብቻ ነው ማለት የተቀረው የሕዝብ ተወካይ የወከለውን ሕዝብ ጥያቄን የማቅረብ ወይም የመጠየቅ ዕድል ሳያገኝ የሥራ ዘመኑ ይጠናቀቃል ማለት ነው፡፡ ይሄ ተገቢ አይደለምና ሌሎች ተጨማሪ informal sessions እንዲኖሩ ቢደረግ???” የሚል ማሳሰቢያ አቅርበው ነበር!!!
የአገዛዙ ፓርላማ የይስሙላ መሆኑን ከሚያሳዩ ነገሮች አንዱ ይሄ ፕሮፌሰሩ ያነሡት ጉዳይ ነው፡፡ ፓርላማው ላይ ሊኖር ይገባው የነበረ አሠራር ወይም ዲሞክራሲ በሰፈነባቸው ሀገሮች ያለው የፓርላማ ልምድ ግን ተውሎ ይታደራል እንጅ በአንድ ጉዳይ ላይ ጥያቄ ያላቸው የፓርላማ አባላት እያሉ “ሰዓት የለም!” በሚል ፈሊጥ “አትጠይቁም!” ተብለው ታፍነው እንዲያልፍ ወይም እንዲጸድቅ የሚደረግ ጉዳይ አለመኖሩ ነው፡፡ ይሄ እንዲሆን ፈጽሞ አይፈቀድም!!!
የት ሊደረስና ከፓርላማው በላይ  የሚመለከተው ማን አለና ነው “ሰዓት የለም!” በሚል ፈሊጥ የሕዝብ ድምፅ የሚታፈነው??? የፓርላማ አስፈላጊነት ምን ሆነና ነው ያውም ከዓመት አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ብቻ በሚደረግ ውይይት ላይ ሁለት ሰዓት ለማይሞላ ጊዜ እየተደረገ “ሰዓት የለም!” በሚል ፈሊጥ ጥያቄ የሚታፈነው???
ልብ በሉ ያውም እኮ ጥያቄ ለመጠየቅ ነው፡፡ መሆን የነበረበት ግን በአገዛዙ ፓርላማ ጥያቄ አንሥቶ ዝም ማለት ብቻ ሳይሆን እንደገናም ለጠያቂው ዕድል ተሰጥቶ ጥያቄው ተገቢው መልስ ማግኘት አለማግኘቱ ተጠይቆ “ጥያቄየ በአግባቡ አልተመለሰም!” ካለ ከዚያ በኋላ ክርክር ተደርጎበት ነው አንድ ጉዳይ በፓርላማው የሚያልፈው ወይም የሚጸድቀው እንጅ በአገዛዙ የይስሙላ ፓርላማ እንደምታዩት ጥያቄ አቅርቦ ዝም ማለት ብቻ አይደለም!!!
ፓርላማ ማለት የአንድ መንግሥት የመጨረሻው ወይም ከፍተኛው ሥልጣን ያለው የመንግሥት አካል ማለት ነው፡፡ ይሄም በመሆኑ ውሳኔውን በሚሹ በሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ በሰፊውና በጥልቀት ተወያይቶና ተከራክሮ በቀረበው ጉዳይ ላይ መንግሥት ተግባራዊ የሚያደርገውን የመጨረሻ ውሳኔ እንዲያሳልፍ የሚደረግበት መድረክ ነው፡፡ ስለሆነም አስፈላጊ ከሆነ በአንድ ጉዳይ ላይ አስፈላጊው ውጤት እስኪገኝ ድረስ እየተወያየና እየተከራከረ ይከረምበታል እንጅ ከፓርላማ የሚቆጠብና የሚሰሰት ሰዓት ኖሮ “ሰዓት የለም!” በሚል ፈሊጥ ፓርላማው በቅጡ ሳይመክርበትና ሳይከራከርበት አንድ ጉዳይ አልፎ ከፓርላማ ውጭ ያሉ ሥራ አስፈጻሚዎች የፈለጉትን የሚያደርጉበት አሠራር የለም፡፡ ዲሞክራሲ በሰፈነባቸው ሀገራት የሚሠራበት አሠራር ይሄ ነው!!!
እዚህ ሀገራችን ውስጥ ግን ፓርላማ የይስሙላ በመሆኑ አገዛዙ እንደምታውቁት በፊትም ሆነ አሁን ፓርላማ ተብየው በበቂ ያልመከረበት፣ ያልተወያየበት፣ ያልተከራከረበትና ያልወሰነባቸው ጉዳዮችን በፓርላማ ተብየው ማጽደቅና ማሳለፍ ብቻ ሳይሆን ጭራሽ እንዲያውም በአብዛኛው ጨርሶ ለፓርላማ ተብየው ያልቀረቡ ጉዳዮችን አገዛዙ በማንአለብኝነት ሲያደርግና ሥራ ላይ ሲያውል ኖሯል አሁንም እንደዚያው እያደረገ ይገኛል!!!
ዲሞክራሲ በሰፈነባቸው ሀገራት ግን ፓርላማው ሳያውቀውና ሳያሳልፈው የምትደረግ አንዲትም ሀገራዊ ጉዳይ የለችም፡፡ ተደርጎ ቢገኝ ያን ያደረገው አካል በወንጀል ይጠየቃል ከሥልጣኑም ይሻራል!!! በሀገራችን ግን በፊትም ሆነ አሁን ፓርላማ ተብየው “እኔ የማላውቀው ወይም ያላጸደኩት ውሳኔ ተላልፎ ሥራ ላይ ውሏል ወይም ተፈጻሚ ሆኗል!” በማለት ውሳኔውን ሲሽርና ያንን ያደረጉ አካላትን ተጠያቂ ሲያደርግ ታይቶና ተሰምቶ አይታወቅም!!!
ታስታውሱ እንደሆነ ወያኔ/ኢሕአዴግ ለውጥ ብሎ የኢትዮጵያን ሕዝብ በሚያጃጅልበት ወቅት ኩሊውን አቶ ዐቢይ አሕመድን የኢትዮጵያን ሕዝብ መደለያ ብዙ እንዲቀባጥርባቸው ካደረጋቸው ነገሮች አንዱ ሕዝቡ ሁሉንም ነገር እያወቀና እየተከታተለ፣ ፍላጎቱ እየተጠበቀ የመንግሥት ሥራ የሚሠራ መሆኑን በመግለጥ የፓርላማው ይቅርና የካቢኔውና የሥራ አስፈጻሚው ውይይት እንኳ ሳይቀር በቀጥታ ስርጭት ለሕዝብ እየታየ ግልጽነትና ተጠያቂነት በሰፈነበት መልኩ እንደሚሠራ ተናግሮ ነበር!!!
ወያኔ/ኢሕአዴግ በአቶ ዐቢይ አሕመድ በኩል እንዲህ ብሎ ሕዝብን ካጃጃለ በኋላ ግን ሆኖ ያየነው አፈናና የአንድ ሰው አንባገነን ግለኛ አኪያሔድ ወይም አሠራር ከወትሮው በከፋ መልኩ የከፋ ሆኖ እንዲሰፍን ነው የተደረገው!!!
ሕዝቡ ሁሉንም ነገር እያወቀና እየተከታተለ፣ ፍላጎቱ እየተጠበቀ የመንግሥት ሥራ ሊሠራ ይቅርና “ለምን እነ አቦይ ስብሐትን ከሕግ ውጭና ከሕዝብ ፍላጎት ውጭ ፈታህ?” ተብሎ ሲጠየቅ እንኳ የሚመልሰው ቢያጣ “እኔ እናንተ የምትሉኝን አልሰማም አምላኬን ነው የምሰማው፡፡ አምላኬ የሚለኝን ነው የማደርገው!” ብሎ ያላገጠበትና ከሕግና ከመንግሥት አሠራር ውጭ የሆነ መልስ በመመለስ ከተጠያቂነት ለመሸሽ ወይም ለማምለጥ የሞከረበት ሁኔታ ነው ያለው!!!
አቶ መለስ የፈለገውን ያህል የpersonality cultን የመፈለግ ወይም መመለክ የመፈለግ ችግር ተጠቂ ቢሆንም እና አንባገነን ቢሆን ፓርላማውና ካቢኔው ቢቀር እንኳ የሕወሓትን ሥራ አስፈጻሚ ሳያወያይ፣ ሳያማክር፣ ሳያስወስን አንዲትም ነገር አያደርግም ነበር!!!
አጭበርባሪውና መሠሪው ወያኔ በዚህ ለውጥ እያለ ምስለኔውን አቶ ዐቢይን አስቀምጦ በሚያጭበረብርበት የድራማ ዘመን እንደፈለገ ማወናበድ እንዲመቸውና ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዳይሰፍን አቶ ዐቢይን ምን እያደረገ እንዲተውን አደረገው ለከት የለሽ የpersonality cultን የመፈለግ ወይም መመለክ የመፈለግ ችግር ተጠቂ እና በግሉ የፈለገውን የሚያደርግ አንባገነን አድርጎ እንዲተውን በማድረግ ካቢኔውን ወይም ሚንስትሮችን አይደለም የፓርቲውን ሥራ አስፈጻሚ እንኳ ሳያወያይ ሳያማክር ከሕግና አሠራር ውጭ በግሉ የፈለገውን እየወሰነ የሚሠራ አድርጎ እንዲሠራ አደረገው!!!
ወያኔ ኦሕዴድን፣ ብአዴንን፣ ካቢኔውን “ለምን? እንዴት?” ብለው እንዳይጠይቁት በማድረግ አቶ ዐቢይን በዚህ መልኩ ግልጽነትና ተጠያቂነት በሌለበት፣ ከሕግና አሠራር ውጭ በሆነ መልኩ ብቻውን የፈለገውን እየወሰነ እንዲሠራ የሚያደርግበትን አሠራር ወይም አኪያሔድ አመቻችቶ እንዲተውን ባያደርገው ኖሮ ከዐቢይ ጀርባ ሆኖ ዐቢይን “እንዲህ አድርግ!” እያለ የፖለቲካ ቁማር እየቆመረ ማድረግ የሚፈልገውን ነገር በማድረግ ሁሉም ነገር ባሰበውና በሚፈልገው መልኩ እንዲሔድ፣ ድራማው በደንብ እንዲተወን ማድረግ ባልቻለ ነበር!!!
መንጋው ግን አቶ ዐቢይ በዚህ መልኩ ለምን እንደሚሠራ ወይም እንደሚተውን አይገባቸውም፡፡ የራሱ የዐቢይ ችግር ይመስላቸዋል እንጅ ሆን ተብሎ ዐቢይ በዚህ መልኩ እንዲተውን መደረጉ አይገባቸውም!!!
Filed in: Amharic