ጋዜጠኛ ፤ የታሪክ ፤ ተመራማሪ ፣ ደራሲ አምባሳደር ዘውዴ ረታ…!!!
ታሪክን ወደኋላ
አምባሳደር ዘውዴ ረታ ከአባታቸው ቀኝአዝማች ረታ ወልደአረጋይ ከእናታቸው እማሆይ አፀደ ረድኤቱ በወርሃ ነሐሴ 7 ቀን 1927 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ፡፡ እድሜያቸው ለአቅመ ትምህረት ሲደርስ በዘመኑ በነበረው ማህበረሰባዊ ልማድ መሰረት የአማርኛ እና የግዕዝ ቋንቋ ትምህርታቸውን በሚገባ ከተማሩ በኋላ በ 7 አመት እድሜያቸው በ 1934 ዓ.ም በቀድሞ መጠሪያው ደጅአዝማች ገብረማሪያም በኋላ ደግሞ ሊሴ ገብረ ማሪያም ተብሎ የሚጠራው ዛሬም ድረስ በዚህ ስያሜ የሚታወቀው የፈረንሳይ ትምህርት ቤት ገብተው እስከ 1945 ዓ.ም ተምረዋል ፡፡
አምባሳደር ዘውዴ ረታ ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ ባደረባቸው የደራሲነት ፍላጎት፡ እኔ እና ክፋቴ ፣ የገዛ ስራየ ፣ ፍቅር ክፉ ችግርና እንግዳሰው የቡልጋው በሚሉ ርዕሶች አራት ቲያትሮችን ራሳቸው ፅፈውና አዘጋጅተው ለህዝብ ዕይታ አብቅተዋል። ከእነዚህ ቲያትሮች መካከል በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ የታየው እኔ እና ክፋቴ የተሰኘው ትያትር ከፍተኛ አድናቆትን አትርፎላቸዋል ፡፡
ይህ የስነ ፅሁፍ ዝንባሌያቸው እና አዳዲስ ነገሮችን የማወቅ የነጠረ ፍላጎታቸው በወቅቱ ከ ነበሩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፎላቸዋል፡፡ በጊዜው የገንዘብ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህዝብ የአገር ፍቅር ማህበር የበላይ ኃላፊ በነበሩት በአቶ መኮንን ሀብተወልድ ድጋፍ ገና በ18 ዓመታቸው በዚያን ጊዜ የጋዜጣና የማስታወቂያ መስሪያ ቤት እየተባለ ይጠራ በነበረው የመንግስት ተቋም በጋዜጠኝነት ሥራ ለማገልገል በ 1945 ዓ.ም ተቀጠሩ፡፡
የታሪክ አጋጣሚ ሆነና አምባሳደር ዘውዴ የሬዲዮ ሥራቸውን የጀመሩት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን በተቀላቀለችበት የመጀመሪያ ዕለት ማለትም መስከረም 1 /01/ 1945 ዓ.ም ነበር። በዚህም የተወሰኑ ጊዜያት የሥራ ልምምድ ካደረጉ በኋላ ባሳዩት የሥራ ብቃት ብሎም በነበራቸው ጥሩ ድምፅ የዚያን ጊዜ ገነተ ልዑል ያሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እየተባለ ይታወቅ በነበረው ቤተ መንግስት የመጀመሪያው የቤተ መንግስት ዜና መዋዕል ዘጋቢ ሆነው ተመደቡ ፡፡
ይህ የሥራ መደባቸውም ከሞዓ አንበሳ ዘ እምነገደ ይሁዳ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ጋር በቅርብ ለመተዋወቅ ብሎም አጠቃላይ የቤተ- መንግስቱን ዕለታዊ መስተጋብርና ትዕይንተ ውሎ ለማጤን መልካም አጋጣሚውን አበጀላቸው ፡፡
የያኔው ዜና መዋዕል ዘጋቢ የዛሬው አምባሳደር ዘውዴ ይህ የሥራ ዘርፍ ምቹ ሁኔታዎችን አመቻቸላቸው የነበረውን የመንግስት የሥራ አካሄድ ፤ ሀገሪቱ በውስጥም በውጭም ታካሂደው የነበረውን የፖለቲካ ፣ የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ከውስጥ ለመከታተልና ሁነቶችን ለማስተዋል ከፍ ያለ ዕድል ፈጥሮላቸዋል፡፡ ከዚሁ ስራቸው ጋር በተደራቢነትም በኢትዮጵያ ሬዲዮ ዜና አቅራቢነት ለሦስት አመታት ያህል አገልግለዋል፡፡ በእነዚህ አመታት ባሳዩት የሥራችሎታና ብቃት በንጉሠ ነገሥቱ ትዕዛዝ ወደ ውጭ ሀገር ተልከው ከፍተኛ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ተደርጎ ከ 1948 እስከ 1952 ዓ.ም ድረስ በፈረንሳይ ሀገር ፓሪስ ትምህርታቸውን ተምረዋል ፡፡
የጋዜጠኝነት ትምህርታቸውን በማጠናቀቅ ከአራት አመት ቆይታ በኋላ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ገና በልጅነታቸው የጀመሩትን የህዝብ አገልግሎትና ሙያ እንደገና ቀጠሉ፡፡ በ 1952 ዓ.ም በኢትዮጵያ ህዝብ የሀገር ፍቅር ማህበር ስር ይዘጋጁ የነበሩት የኢትዮጵያ ድምፅ ፣ መነን መጽሔት የዝግጅት ክፍል ዋና ዳይሬክተር በመሆን እስከ 1954 ዓ.ም ድረስ አገልግለዋል፡፡ ከዋና ዳይሬክተርነት ጎን ለጎን የእነዚሁ ሚዲያዎች የአማርኛ ቋንቋ አዘጋጅ ሆነው ከፍተኛ አስተዋፆኦ አበርክተዋል፡፡ ከዚያም ባሻገር በ 1954 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሬዲዮ የብሔራዊ ፕሮግራም ዳይሬክተር ሆነው እስከ 1955 ዓ.ም የሰሩ ሲሆን በተለይ በዚህ ስራቸው ሚኒስትሮችንና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችን በየ ሳምንቱ እየጋበዙ ስለ መስሪያ ቤታቸው አሰራር ቃለ መጠይቅ ያደርጉ ነበር፡፡
አምሳዳር ዘውዴ ረታ በጋዜጠኝነት ህይወታቸው የፓን አፍሪካን ዜና አገልግሎት ማህበር ፕሬዝዳንት በመሆን ከ 1956 – 1962 ዓ.ም አገልግለዋል፡፡ በዚህ ሥራቸው የግብፁን ፕሬዝዳንት ጋማል አብደል ናስርን የሴኔጋሉን ሊዮፖል ቴዳርሴንጎርን ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ችለዋል፡፡ ከ 1962ዓ.ም ጀምሮ ወደ ዲፕሎማሲ ሥራ በመዛወር በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስር በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኢንባሲ ሚኒስትር ካውንስለር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ምክትል ሚኒስትርና በመጨረሻም በኢጣልያ እና በቱኒዚያ የኢትዮጵያ መንግስት ልዩ መልዕክተኛ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር በመሆን ለ ሀገራቸው እና ለመንግስታቸው በቅንነት በብቃትና በትጋት አገልግለዋል፡፡
➻ የማወቅ የላቀ ፍላጎትንና አስተውሎትን ወደ መጽሐፍ መቀየር ፤
አምሳዳር ዘውዴ በነበራቸው የሀገራቸውን ታሪክ የማወቅና የማሳወቅ ከፍተኛ ፍላጎት በስደት ላይ እያሉና ከተመለሱም በኋላ ጥልቅ በሆነ ጥናትና ምርምር ሦስች መጽሐፍቶችን አሳትመዋል፡፡ የመጀመሪያው ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መጽሐፍ ” የኤርትራ ጉዳይ ከ 1941-1963 እ.ኤ.አ ” ሲሆን ስለ መጽሐፉ አፃፃፍ ቅድመ ታሪክ አምሳደር ዘውዴ ቃል በቃል እንዲህ ብለው ነበር”የኤርትራ ጉዳይ መጽሐፍ መቼም! ብዙ ሀገሮች ሄድሁ ምክንያቱም የኤርትራ ዶክመንት የሚገኘው በመጀመሪያ ደረጃ እንግሊዝ ዘንድ ነው። እንግሊዝ አገር ብዙ ቆየሁ ፡ ጣሊያኖች ዘንድ ነው በጣሊያን አገር የምኖርበትም ቢሆን ብዙ ሰራሁ ከዚያ ደግሞ አሜሪካን አገር ነው አሜሪካን ብዙ ቆየሁ በመጨረሻ ግን የኤርትራ ጉዳይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቀርቦ ያ ሁሉ ክርክር ሲደረግ የነበሩትን ፋይሎች ሁሉ በሙሉ ለማጥናትና ለመያዝ ያቻልሁት ኒዮርክ ነው፡፡ስለዚህ 7 አመት መፍጀቱ ምንም አያስደንቅም በጣም ሰፊ ዶክመንት ስለሆነ ይሄው ዛሬ ለኢትዮጵያ ትልቅ ሪፈራንስ ሆኖ እንጠቀምበታለን፡፡”ብለዋል፡፡ ይህ መጽሀፍ በተራኪ ተፈሪ አለሙ ተተርኮ በተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በድምጽ መጽሀፍ በሲዲ የወጣ ሲሆን በህዳር 2011 ለምረቃ የበቃ ነው፡፡
ወደ ሁለተኛው መጽሐፋቸው ስንመጣ ደግሞ ” ተፈሪ መኮንን ረዥሙ የስልጣን ጉዞ ” የሚለውን እናገኛለን፡፡ ይህን መጽሐፍ በተመለከተ አምሳደር ዘውዴ ይህን ብለው ነበር “ተፈሪ መኮንን አምስትአመት ነው የፈጀብኝ፡፡ ምክንያቱም አባቴ ቀኝ አዝማች ረታ ወልደ አረጋይ የንግስት ነገስት ዘውዲቱ ምኒልክ ልዩ ጸሃፊ ሆነው ብዙ አመት የሰሩ ስለሆነ ብዙ ያስጠኑኝ ፣ ያስተማሩኝ ነገር ስላለ እንደምንም ከሌላው ዶክመንቶች ካሉት ሰነዶች ጋር በማሰባጠር በማመዛዘን ይህንን መጽሐፍ ጽፌ አቀረብሁ፡፡” ሦስተኛው መጽሐፋቸው ደግሞ “የቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ መንግስት አንደኛ መጽሐፍ” ይጠቀሳል፡፡
ሥራዎቻቸውን አስመልክቶ በርካታ በሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር መድረኮች የህዝብ መገናኛ ብዙኃን በተለያዩ ጊዜያት እየቀረቡ ትምህርትና ገለፃ ሰጥተዋል ፡ ለዚህ ሥራቸውም ከልዩ ልዩ የሀገርና የውጭ ተቋማት እውቅና እና ሞገስ ያገኙ ሲሆን ከ እነዚህም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦
➻ ከንጉሠ ነገሥት መንግስት የምኒልክ የመኮነን ደረጃ ኒሻን ፤ የኢትዮጵያ የክብር ኮኮብ አዛዥ መኮነን ኒሻን ፤ ከ 25 ከተለያዩ የአፍሪካ ፣ የአውሮፓ እና የእስያ አገሮች የተበረከቱ ኒሻኖች ናቸው፡፡
አምባሳደር ዘውዴ ረታ እስከ ህይወታቸው ፍፃሜ ካልተለዩአቸው ከወ/ሮ ገሊላ ተፈራ ጋር መስከረም 21/01/ 1959 ዓ.ም በህግ ተጋብተው የሁለት ሴቶች እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበሩ፡፡ አምሳደር ዘውዴ ረታ አስቀድሞ ለሥራ ጉዳይ ሄደው በነበሩበት የለንደን ከተማ በድንገት በመታመማቸው እዚያው በሚገኘው የቅድስት ማሪያም ሆስፒታል ከፍተኛ የህክምና ክትትል ቢደረግላቸውም ሊድኑ ባለመቻላቸው መስከረም 26/01/ 2008 ዓ.ም በተወለዱ በ 80 ዓመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡
የሀገርና የህዝብ ሀብት የወገንም መኩሪያ የነበሩት ክቡር አምባሳደር ዘውዴ ረታ ዛሬ በህይወት ባለዩንም ሥራዎቻቸው ግን አነሆ ህያው ናቸው፡፡