>

ፋኖን  የሰላምና ደህንነት አጋር ማድረግ ያልተቻለው ለምንድነው ? (ቴዎድሮስ ሀይለማርያም)

ፋኖን  የሰላምና ደህንነት አጋር ማድረግ ያልተቻለው ለምንድነው ?

ቴዎድሮስ ሀይለማርያም

   1. የመንግሥት  ተፈጥሯዊ ባላንጣነት 

ዘመናዊ መንግሥት ሙሉ ቁመና የተላበሰበት የቅርብ ታሪክ  ፣ ፋኖ እንደ አንድ የታጠቀ ህዝባዊ ኃይል ከመንግሥት ጋር ያለው ግንኙነት የጠራና በመተማመን ላይ የተመሠረተ አይደለም።  መንግሥት ማንኛውንም የአመፅ መሣሪያዎች ለመቆጣጠር ካለው ፍላጎት የተነሳ ፋኖን በሽፍታነት ፣ በአመፀኝነት ፣ በፅንፈኝነት እየፈረጀ ሲያሳድደው ኖሯል።

በተለይ አማራ ጠልነት የመንግሥት አገዛዝ ዘይቤ ላይ ጥላውን ባጠላበት  በወታደራዊው መንግሥትም ሆነ  ስጋና ደሙ ፀረ አማራ  በሆነው በዘመነ ኢህአዴግ ወብልፅግና  ዋነኛ የጥቃት ዒላማ ከሆኑት የአማራ መገለጫዎች አንዱ ፋኖነት ነው። ፋኖ  ከሰላምና የደህንነት አጋርነት ይልቅ የአገዛዞች ባላንጣና ስጋት ሆኗል።

2. ፋኖን ጥርስ የማስገባት አደገኛ  ዘመቻ

በአሁኑ ወቅት በፋኖ ላይ ከያቅጣጫው  የተከፈተው  የጠላትነት ዘመቻ ስር የሰደደና በርካታ ተዋናዮች ያሉበት ነው፡፡ የፌዴራሉም ሆነ የአማራ ክልል መንግሥታት ፋኖን  በጥርጣሬ ይመለከቱታል። የህወሓት ድንገተኛ ወረራና የመንግሥት አቅመ ቢስነት አልፈቅድ ብሎ እንጂ ይህን ህዝባዊ  ኃይል ለማዳከምና ቢቻል ለማጥፋት ያልፈነቀሉት  የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።

በሌላ በኩል  ህወሓትን ፣ ኦፌኮን ፣ ጀበላውያንን ፣ የአገው ሸንጎን ፣ የኦሮሞ ብልፅግናን ፣  ኦነግንና  መላውን አማራ ጠል ኃይሎችን  የሚያስተሳስራቸው በፋኖ ላይ  ያላቸው የማይሞት ጥላቻ ነው።  ሱዳንን ፣  ግብፅን ፣ አውሮፓና አሜሪካንና ግዙፍ ዓለማቀፍ ተቋማቶቻቸውን  ጨምሮ አንድ የሚያደርጋቸው ቃል ‹‹ፋኖ›› የሚል ሆኗል፡፡

3. የፋኖ ሃጢአቱ አማራነቱ ❗️

ፋኖ የሚጠላውና የሚዘመትበት  በምን ምክንያት ነው?የሀገርን ህልውና ፣ የመንግሥትን ሥልጣን ፣  የህዝቦችን አብሮነት አደጋ ላይ ስለጣለ ነው? አይደለም ! በተቃራኒው ሀገር ስትወረር ፣ ድንበር ሲደፈር ፣  መንግሥት ሲንገዳገድ ፣ ህዝብ  ሲዋረድ በአጭር ታጥቆ እየደረሰ  የታደገ ባለውለታ ነው።

ፋኖ  የሚዋከበውና የሚዘመትበት የወንጀል ፣ የሥርዓት አልበኝነትና የግጭት ምንጭ ስለሆነ ነው? በፍፁም። እንደ ተቋም ፋኖ በጠንካራና እድሜ ጠገብ የአንድነት ፣ የመስዋዕትነት ፣ አይበገሬነት ፣ ፍትሃዊነት ፣ ግብረ ገብነትና የሰላም ጠበቃነት እሴቶች የሚገለፅ ነው።  ፋኖ በራሱ ስንቅና ትጥቅ ለትልቅ ዓላማ ለመሞት የተማማለ ጓዳዊ  ተቋም ነው።

ፋኖ የአማራ ህዝብ  ታሪክ ፣ ባህል ፣ እሴትና ሥነልቡና ነፀብራቅ የሆነ ተቋም ነው። ከአማራ ህዝብ አብራክ የተከፈለ ፣ ለህዝብ የቆመ ፣ በህዝብ የሚደገፍ ተቋም ነው።  በዋነኝነት የፋኖ ጥላቻ መነሻ የሆነውም ይህ አማራዊ ተፈጥሮውና ባህሪው ነው። በአጭሩ   ፋኖ የአማራ ጥላቻና ፍራቻ ምህፃረ ቃል ሆኗል።

4. ሰላምና ደህንነት በጉልበት አይመጣም

እንደ ማንኛውም ሰው ሰራሽ ተቋም ግላዊም ቡድናዊም ችግሮችና እልፊቶች እዚህም እዚያም በፋኖ ውስጥ  አሉ ይኖራሉም። ይህን በመጀመሪያ ደረጃ እርምት የሚሰጥ  በዘመናት የተካበተ አስተማማኝ ሥርዓት ያለው አካል  ራሱ ፋኖ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ  የተቋሙን ተክለ ስብእና የሚያስጠብቀው ያፈለቀውና  አቅፎ ደግፎ የሚያኖረው ህዝብ ነው። በሶስተኛ ደረጃ ፋኖ በሰላም ጊዜ ገበሬ ፣ በቀውስ ጊዜ ወታደር እየሆነ ማህበራዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ  የመንግሥት ሚና ቀላል አይደለም።

የአማራ  ክልል መንግሥት በክልሉ እያካሄድኩት ነው ያለው የሰላምና ደህንነት የማስከበር እርምጃ  ከነዚህ ተደጋጋፊ  የእርምትና ሚዛን  (check and balance)  ሥርዓቶች ይልቅ በኃይል ማንበርከክ ላይ የተመሠረተ ፣ ባለድርሻ አካላትን ያላሳተፈ ፣ ግልፅነትና ተአማኒነት የጎደለው መሆኑ ከጅምሩ ለውድቀት የተጋለጠ ያደርገዋል።  ዘላቂ ሰላምና ደህንነት በአንድ ወገን የዘመቻ ርብርብ አይመጣም።

5. በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ  እንዳይሆን

የአማራ ክልል የሰላምና ደህንነት ሁኔታ በቋፍ ላይ የሚገኝ ነው። ህዝባችን  የትግራይ ወራሪ ኃይል ካደረሰበት ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት ገና አላገገመም፡፡  በአሁኑ ወቅት የአማራ ፖለቲካዊና ህዝባዊ ቁመና በከፍተኛ ማዕበል እየተናጠ ነው፡፡ አማራው የትግራይ ወረራን ለመመከት በጋራ የከፈለው መስዋዕትነት እንኳን ወደ ጠንካራ አንድነት አላመራም፡፡

ሆን ተብሎ በሚመስል ቸልተኝነት የክልሉ መንግሥት ትኩረት መሠረታዊ ባልሆኑ የእሳት ማጥፋት ስራዎች ተጠምዶ ከርሟል።  በጦርነቱ አስገዳጅነት ከተፈጠሩት የታጠቁ ኃይሎች  ጋር አዎንታዊ ግንኙነት ሊፈጥር አልቻለም፡፡ በዚህ ላይ  ወቅቱን በትክክል ያልዋጀና በተለይ በፋኖ ላይ  ያነጣጠረ ዘመቻ ህዝባዊ ቁጣ በመቀስቀስ ክልሉን ለወያኔና አጋሮቹ ጥቃት ወለል አድርጎ የሚከፍት ይሆናል።

Filed in: Amharic