>
5:13 pm - Wednesday April 20, 3211

የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል-አቀባይ ኢሳት ወይስ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት? [ኤሊያስ ገብሩ-ጋዜጠኛ]

(ወሳኝ ሀገራዊ መረጃዎችን ከመንግሥት መጠበቅ የለብንም ይሆን?)

በእያንዳንዱ ሀገር ያለ ገዥ መንግሥት የየራሱ መረጃ ለህዝቡና ለዓለም-ዓቀፍ ማኅበረሰብ የመስጠት ባህሪ፣ ልምድና ባህል አለው፡፡ ወሳኝ የሆኑ ሀገራዊ፣ መንግሥታዊና ኅብረተሰባዊ መረጃዎች በሚመለከታቸው የመንግሥታት የመረጃ ሰጪ አካላት በኩል መረጃው ለሚያስፈልገው ሁሉ መድረስ እንደሚያሻ እሙን ነው – በተለይ በዘመነ ግሎባላይዜሽን እና በ21ኛው ክ/ዘመን!

ኢትዮጵያን በተለያዩ ጊዜያት ያስተዳደሩ መንግሥታት ‹‹እየመራነው ነው፤ እያስተዳደርነው እንገኛለን›› ለሚሉት ሕዝብ መረጃን የሚሰጡበት የየራሳቸው አካሄድ ነበራቸው፡፡ በአሁን ወቅት ሀገራችንን እያስተዳደረ የሚገኘው ገዥ ፓርቲ ኢህአዴግ ነውና በእሱ ላይ ማተኮር ተገቢ ነው፡፡
ሕወሃት/ኢህአዴግ ከጫካ ጀምሮ ሀገሪቷን ተቆጣጥሮ ማስተዳደር እስከጀመረበትና አሁን እስካለበት ድረስ ‹‹አስተዳድረዋለሁ›› ለሚለው ሕዝብ መረጃን የሚያደርስበት የራሱ መንገድ እንዳለው ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ በሕዝብ ሀብት የሚንቀሳቀሱት የቴሌቭዥን እና የሬዲዮ ጣቢያዎቻችን ለሥርዓቱ በግልጽ ወግነው የሥርዓቱ የፕሮፖጋንዳ መሳሪያ ሆነው ለዓመታት ማገልገል መቀጠላቸው፤ የአደባባይ ሃቅ በመሆኑ ልለፈውና ወደዛሬ ጽሑፌ አንኳር ነጥብ ላምራ፡፡
ዛሬም በከተማ እየኖሩ በጫካ ባህል መታነቅ!

፩. የጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ህመም
በሽግግሩ መንግሥት ጊዜ ለአራት ዓመታት ፕሬዚዳንት በመሆን፣ ከዚያም በኋላ በጠ/ሚኒስትርነት ለ17 ዓመታት ኢትዮጵያን በበላይነት የመሯትን የሟቹ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን ማንሳት ዛሬ ግድ ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ በግንቦት ወር 2003 ዓ.ም ለዓለም ዓቀፍ ስብሰባ ሄደው ከተመለሱ በኋላ ጤንነታቸው ታውኮ እንደነበር ውስጥ ውስጡን ይወራ ነበር፡፡ በዚያው ሰሞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ አዘጋጅቶ መግለጫ ሰጥቶ ነበር፡፡ በአቶ መለስ ጤንነት ዙሪያ የሚናፈሱ ወሬዎችን ተከትሎ ከሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች ጥያቄ ቀረበ፡፡ የጽ/ቤቱ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ሽመልስ ከማልም አቶ መለስ በመልካም ጤንነት ላይ መሆናቸውን ጠቁመው ‹‹ይኼ የኢሳትና የእሳት ወሬ ነው›› በማለት መልስ ሰጡ፡፡ በሂደት ይኼ ምላሻቸው እውነት አለመሆኑ ታየ፡፡ አቶ ሽመልስስ ቢሆኑ የተጠየቁትን እውነተኛ ጥያቄ ከመመለስ ባሻገር የኢሳትን ዘገባ ወደማጣጣል ለምን አተኮሩ?
Elias Gebiru 02.01.2014የኢትዮጵያ መንግሥት የጠ/ሚ/ሩን መታመም አፍኖ ቢቆይም፣ በሰኔ ወር 2003 ዓ.ም በተካሄደው 19ኛው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ስብሰባ ላይ ተካፋይ የነበሩት የሴኔጋሉ ፕሬዚዳንት ማኪይ ሳል አቶ መለስ መታመማቸውን ተናግረው ምሕረትን ተመኙላቸው፡፡ ስለመሪያቸው ጤንነት ማወቅ የፈለጉ ኢትዮጵያውያኖችና ትክክለኛውን እውነት አውቀን ለሕዝብ ተገቢውን መረጃ ማድረስ የፈለግን የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፤ በገዛ ሀገራችን ባይተዋር ሆነን ከሌላ ሀገር መሪ መስማታችን በወቅቱ አሳዛኝ ክስተት ነበር፡፡
ቀናቶች ካለፉ፣ በጉዳዩ ዙሪያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ወሬዎች ከተናፈሱ በኋላ ‹‹አውቆ ከተኛበት›› በመነሳት መግለጫ መስጠት ግድ የነበረበት መንግሥት ሀሙስ ሐምሌ 15 2003 ዓ.ም ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገራት ጋዜጠኞች መግለጫ መስጠት ግድ ሆነበት፡፡ እኔም በወቅቱ ‹‹ፍትህ›› ጋዜጣ ላይ ዘገባ ለመስራት ከቀኑ 9፡20 ሰዓት ገደማ በመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከታደሙ የሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች ጋር ተቀላቀልኩ፡፡ ከአፍታ ቆይታ በኋላ ሚኒስትር አቶ በረከት ስምኦን ገቡና ቦታቸውን ያዙ፡፡ አጠር ያለ ጋዜጣዊ መግለጫም ሰጡ፡፡ ከጎናቸው አቶ ሽመልስ ተቀምጠው ነበር፡፡
የአቶ መለስ መታመም የመግለጫው ዓላማ ዋናውና ቀዳሚው መሆኑን አቶ በረከት ጠቆሙና፤ ጉዳዩ በይፋ ያልተነገረበት እና ከአንድ ወር በፊት በጋዜጠኞች ቀርቦ የነበረው ጥያቄ የተስተባበለበትን ምክንያት አስረዱ፡፡ አያይዘውም ‹‹የገዥውን ባህል ማወቅ ጠቃሚ ይመስለኛል›› ገዥው ፓርቲ አብዛኛውን ጊዜ ዕድሜውን በበረሃ ያሳለፈ በመሆኑ በማንኛውም ሁኔታ መስዋዕትነት እየከፈለ ችግሮችን ተሸክሞ ማለፍ የሚችል ነው፡፡ በግለሰቦች ላይ የሚጋጥም ጉዳይ እንደ ትልቅ ነገር ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም፡፡ ሕመምና የመሳሰሉት ችግሮች የአብዛኛው አመራር የሕይወት አካል ነው፡፡›› በማለት መልስ ሰጡ፡፡ በወቅቱ አቶ በረከት ‹‹የገዥውን ባህል ማወቅ ጠቃሚ ይመስለኛል›› የምትለዋ አገላለጽ ጥያቄ ፈጥራብኝ ነበር፡፡
እንደሀገር ካየነው የአቶ መለስ የጤና ሁኔታ፣ የሀገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደመሆናቸው የሁሉም ሰው ጉዳይ ነበር፡፡ ይህ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 12 [የመንግሥት አሰራር እና ተጠያቂነት] ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ ‹‹የመንግሥት አሰራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት›› ከሚለው ጋር በግልጽ የሚጣረስ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የሕወሃት/ኢህአዴግ የጫካ ባህል ሕገ-መንግሥትን እንደሚንድ ማወቅ ያስፈልጋል!
የአቶ መለስን መታመም ቀድሞ የነገረን የኢትዮጵያ መንግሥት ሳይሆን ኢሳት መሆኑን ልብ ማለት ያሻል፡፡
ሌሎች ሁለት ምሳሌዎችን ላክል፡-

፪. የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መያዝ
በ2006 ዓ.ም ሰኔ ወር ላይ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ ትልቅ የመነጋገሪያ ርዕሠ ጉዳይ የነበረው በአሸባሪነት የተፈረጀው የግንቦት ሰባት ዋና ጸሐፊ የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓ.ም በየመን ሰነዓ አውሮፕላን ጣቢያ በየመን የጸጥታ ሃይሎች ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ቀድሞ የዘገበው ኢሳት ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ የተለያዩ መረጃዎች በተለያዩ መንገዶች ሲወጡ ተስተውሏል፡፡
ስለጉዳዩ የኢትዮጵያ መንግስት መረጃ እንዲሰጥ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ቢጠየቅም፡- ‹‹የምናውቀው ነገር የለም፤ ጉዳዩን በማኅበራዊ ድረ-ገጾች እንደማንኛውም ኅብረተሰብ ነው የሰማነው፡፡ …›› ወዘተ የሚል ምላሾች ከጠ/ሚ/ሩ አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ በአሜሪካ ድምጽ ላይ አደመጥን፡፡ በአቶ አንዳርጋቸው መያዝ ብዙ ከተባለለት፣ የተለያዩ አስተያየቶች እና ግምቶች ከተሰጡበት በኋላ ‹‹አውቆ ከተኛበት›› መነሳት የሚችለው የኢህአዴግ መንግሥት ረዥም ቀናቶችን በዝምታ አሳልፎ አሸባሪ ብሎ የፈረጀው የግንቦት ሰባት ጸሐፊ፣ በየመን የጸጥታ ሃይሎች ቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና ለኢትዮጵያ መንግሥትም ተላልፈው መሰጠታቸውን በይፋ ገለጸ፡፡ አቶ አንዳርጋቸውም በፖሊስ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ላይ ቀርበው ድምጹ እንጂ ምስሉ ከማይታይ መርማሪ ጋር የተነጋገሩት ሀሳብ ለህዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ ታየ፡፡ [በዚህ ቃለ-ምልልስ ላይ ተቆራርጠው የተቀጠሉ የቃላት ፍሰቶች እንደነበሩ ይህም በወቅቱ ሰፊ የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ማለፉ ይታወሳል]
የአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይ ከተነሳ አይቀር፣ በአሁን ወቅት የት ታስረው እንደሚገኙ፣ በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ በቅርቡ አቶ አንዳርጋቸውን ለ40 ደቂቃ ያህል ለሁለተኛ ጊዜ እንዳገኟቸው የተገለጸው የእንግሊዝ አምባሳደሮች ዝርዝር ጉዳዮችን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ የዚህስ አንድምታ ከገዥው ፓርቲ የጫካ ባህል የተወረሰ ይሆን?

፫. ከድሬደዋ ተነስቶ አሰብ ያረፈው የጦር ሄሊኮፕተራችን ጉዳይ
ባለፈው ሳምንት አርብ ታህሳስ 10 ቀን 2007 ዓ.ም ለኢትዮጵያ መንግሥት አሳዛኝ እና አስደንጋጭ ሁነት ተፈጥሮበት ነበር፡፡ በበረራ ልምምድ ላይ የነበረች፣ 30 ሚሊየን ዶላር የምትገመት MI-35 የጦር ሄሊኮፕተር፣ ሁለት አብራሪዎችና አንድ ቴክኒሺያንን እንደያዘች ከኢትዮጵያ ድንበር በመውጣት፤ በሀገረ-ኤርትራ አሰብ ወደብ አቅራቢያ ማረፏ እርግጥ ሆነ፡፡ ይህንንም ተከትሎ፣ ቅዳሜ ታህሳስ 11 ቀን 2007 ዓ.ም ኢሳት ‹‹ሰበር ዜና›› በማለት ሁለት የጦር ሄሊኮፕተሮች ከኢትዮጵያ ከድተው ኤርትራ ማረፋቸውን ደጋግሞ ዘገበ፡፡ የድረ-ገጾች የዜና ዘገባ በዚህ ተጨናነቀ፡፡ ዘገባው በማህበራዊ-ሚዲያው ከዳር ዳር ተሰራጨ፡፡ እንደተለመደው የተለያዩ አስተያየቶች፣ ግምቶችና መላ-ምቶች ተደመጡ፤ ተነበቡ፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤት ለሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ መረጃ መስጠቱን ትቶ የትግል ወቅት ባህሉን በመጠቀም ድምጹን አጥፍቶ ጸጥ አለ፡፡ በመሰል ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተራዘሙ ቀናቶችን በማሳለፍ ‹‹አውቆ ከተኛበት›› መነሳት የሚያውቅበት መንግሥታችን ሶስት ቀናቶችን ብቻ ካሳለፈ በኋላ ግን ከዜና አቀራብ እና አገላለጽ ፍጹም በራቀ መልኩ ዋና አብራሪውን ‹‹ከሃዲ›› በማለት ጭምር እውነቱን በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በኩል አመነ፡፡
ከዜና ዘገባው በመቀጠልም የሥርዓቱ ደጋፊ የሆነው ትግራይ ኦንላይን (Tigray online) ሄሊኮፕተሯ ኤርትራ ከማረፏ ጋር ተያይዞ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ሄሊኮፕተሩን ለማስመለስ ሀይል የጨመረ እንቅስቃሴ ማድረግ አለበት›› የሚል ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወሰድ የሚያሳስብ ሃሳብ ማቅረቡ አይዘነጋም፡፡ የሄሊኮፕተሯም ጉዳይ አሁንም ድረስ መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ መሆኑን ቀጥሏል፡፡
ሥርዓቱ ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ወቅታዊ መረጃን ለመስጠት ያለበትን ለዓመታት የዘለቀ ንፍገት፤ ከላይ ባቀረብኳቸው ሶስት ምሳሌዎች ውስጥ አቀረብኩ እንጂ ሌሎች ብዙ ነገሮችን መዘርዘር ይቻልም ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ አንድ የመጨረሻ ማሳያ ላክል፡-
ባለፈው ዓመት ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ጣሊያን ሮም ማረፍ የነበረበት አየርመንገዳችን ቦይንግ አውሮፕላን በረዳት አብራሪው ኃይለመድህን አበራ አማካኝነት ተጠልፎ ስዊዘርላንድ ጄኔቭ ሲያርፍ፤ የወቅቱ የመንግሥት ጉዳዮች ኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ረፋድ ላይ ለጋዜጠኖች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ‹‹ጠላፊዎቹ (አውሮፕላን ለትራንዚት ሲያርፍ) ከሱዳን ካርቱም የተሳፈሩ አሸባሪዎች ናቸው›› በማለት የተሳሳተ መረጃ መስጠታቸውም አይዘነጋም፡፡
መንግሥት ለህዝቡ ወሳኝ መረጃዎችን በጊዜውና በአግባቡ እውነት ላይ ቆሞ መረጃን ከማያደርስባቸው ምክንቶች መካከል ዋነኛውና ቀዳሚው፡- ነገሮችን ከፖለቲካ ትርፍ እና ኪሳራ አኳያ የሚያይበት፣ ብሎም የሚመዝንበት ራስ-ወዳድ ሥነ-ልቦናው ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ወሳኝ መረጃችን በይፋ ከመግለጹ በፊት ፖለቲካዊ ችግር፣ የሥልጣን መናጋትና ህልውናውን ስጋት ውስጥ ይከትቱብኛል ብሎ የሚያስባቸውን ነገሮች ካስተካከለ በኋላ መረጃውን ወደማመን ያመራል፡፡ መረጃውን ይፋ ከማድረጉ በፊት ‹‹ውሸት አዘል›› መልሶችን እንዲመልሱ ባሰናዳቸው ሰዎች በኩል ሲያስተላልፍም እፍረት የሚሰማው አይደለም፡፡ በዋኝነት ‹‹አስተዳድረዋለሁ›› ለሚለው ሕዝብ መረጃን በዝምታ ውስጥ መንፈጉም ለሕዝብ ያለውን ንቀት የሚያሳይ አድርጌ በግሌ እወስዳለሁ፡፡
ለዚህ ነው ወሳኝ ሀገራዊ መረጃዎችን በትኩስነታቸው እየሰጠን የሚገኘው ኢሳት እንጂ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ባለመሆኑ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ቃል አቀባይ ኢሳት ወይስ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት?›› በማለት በርዕሴ ጥያቄ ያቀረብኩት፡፡
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የንድፈ-ሀሳብ መጽሔት ‹‹ዳንዲ›› አዘጋጅ የሆነው አናንያ ሶሪ በሰጠው አስተያየት ጽሑፌን ልደምድም፡፡
‹‹ይህ የመንግሥት ባህሪ የመነጨው አንድም ከአጠቃላዩ የኢትዮጵያ የቆየ የድብቅነት ባህል ሲሆን፤ በሌላም በኩል ገዥው ፓርቲ ነጻና ታማኝ መረጃን ለሕዝብ በማቅረብ አደጋ ውስጥ ሊወድቅ የሚችለውን በቋፍ ላይ ያለ ሕልውናውን ለማስጠበቅ ከሚያደርገው መውተርተር ነው፡፡ ይህም ሲባል፡- በሁለንተናዊ የቅቡልነት ቀውስ (Overall Legitimacy Crisis) ውስጥ ላለ አፋኝና ከህዝብ የተነጠለ ሥርዓት፤ ትክክለኛ መረጃን በአግባቡና በወቅቱ ለሕዝብ ማድረስ ምን ያህል የከፋ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል ማንም በመረጃ ጭለማ ውስጥ የተቀመጠ ዜጋ የሚረዳው ነው፡፡ አምባገነንነት የሚያፍነው የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ብቻ ሳይሆን፤ ዜጎች ሥለሀገራቸው ጉዳይ የማወቅና መረጃ የማግኘት መብትም ጭምር ነው፡፡ ይህም፡- ‹ሥለ ሀገራችሁ አያገባችሁም!› ከሚል ትዕቢት የሚመነጭ ነው፡፡ በመሆኑም የሕዝብን እውነተኛ ድምጽ የሚያሰማ እንጂ፤ መንግሥት ነኝ ያለ ቡድን ሁሉ የህዝብ እውነተኛ ቃል አቀባይ አይደለም!››

Filed in: Amharic