ጎንደርን አንድነት አስመልክቶ ከእስክንድር ነጋ (የአፋህድ ስብሳቢ) የተላለፈ የደስታ መልዕክት።
ጥቅምት 05፣ 2018 ዓ.ም።
/
ጤና ይስጥልኝ።
የፋኖ አንድነት የአማራ ህዝብ የህልውና ትግልን ጥንካሬ፣ ተሰሚነት፣ ተዓማኒነት እና የመጨረሻ እጣ ፋንታ የሚወስን ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ ለሁሉም ግልፅ የሆነ እውነታ ነው።
የአማራ የህልውና ትግል ጠባብ የፖለቲካ ጥያቄዎችን ለማስፈፀም የሚደረግ ትግል አይደለም። ለአማራ ህዝብ የጄኖሳይድ የህልውና አደጋ ምንጭ ሆኖ የተገኘው ዘረኛው ህገ መንግሥት እንደ መሆኑ መጠን፣ ዓላማ እና ግቡ አሁን ያለውን ዘረኛ ሥርዓት ነቅሎ በአዲስ ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓት መተካት ነው።
ከዚህ አኳያ፣ ስለህገ -መንግስት ጉዳዮች ዓለም አቀፋዊ መርሆች እና መለኪያዎች ባሉበት ዘመን የምንኖር እንደ መሆናችን መጠን፣ ለፋኖ አንድነት መሠረት የሚሆኑት መርህዎች በአብዛኛው ተሠርተው ያለቁ ናቸው። እንደ አዲስ ተሠርተው ስምምነት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች በቁጥር ትንሽ እና ቀላል የሆኑ ናቸው።
ይህ መሠረታዊ እውነታ ጎልቶ በሚታይበት የትግል አውዳችን የፋኖ አንድነት እስካሁን እውን መሆን አለመቻሉ የፋኖ መሪዎችን በታሪክ ሲያስወቅስ የሚኖር ጥቁር ነጥብ ነው።
“መልካም ነገር ከሚቀር፣ ረፍዶም ቢሆን መሆኑ ሰናይ ነው” እንደሚባለው ፣ አብዛኞቻችን የፋኖ መሪዎች በታሪክ ተጠያቂነት እንዳለብን ከተገነዘብን ውለን አደረናል። በሁሉም ወገን ይበል የሚያሠኙ ጅማሮዎችም አሉ።
በዚህ መንፈስ፣ “እከሌ ነው ንፁህ፣ እከሌ ነው ጥፋተኛ” ሳይባባል፣ የአለፈውን ነገር ሁሉ ትተን ወደፊት ብቻ እየተመለከን ባለንበት ጊዜ፣ የአፋህድ እና የአፋብኃ አመራሮች በጎንደር ጠቅላይ ግዛት ጥቅምት 04፣ 2018 ዓ.ም ተገናኝተው፣ ከዚህ በኃላ በአንድነት ለመሥራት ሁላችንም ደስ የሚያሠኝ ተግባራዊ ሥራ ጀምረዋል ። መላው የአማራ እና የኢትዮጲያ ህዝብ እንካን ደስ ያላችሁ።
ግን ስራው ተጀመረ እንጂ አላለቀም። በጎንደር ያየነውን በአማራ ማሳደግ ይጠበቅብናል። በዚህ ረገድ የተጀመሩ የአንድነት ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ዘረኛው ስርአት በቀዳሚነት አማራን ለጅምላ ማንነት ተኮር ፍረጃ፣ ጥላቻ፣ መገለል፣ መፈናቀል እና ጭፍጨፋ ሰለባ ቢያደርግም፣ መርዝነቱ ግን ለመላው ኢትዮጲያዊያን ነው። ስለዚህም በጎንደር የተጀመረው አንድነት ፣ ወደ አማራ ካደገ በኃላ መቋጫው በኢትዮጲያ ይሆናል።
አመሰግናለሁ።
ድል ለአፋሕድ እና ለአማራ ፋኖ ሁሉ!!!!
ድል ለአማራ ሕዝብ !!!
ድል ለኢትዮጲያ ሕዝብ !!!!
ክብር ለሰማእታት !!!!
ዘላለማዊ ክብር ለፈጣሪ !!!!
እስክንድር ነጋ፣
ከአፋሕድ።