ኢትዮ-ምኅዳር ጋዜጣ ቅጽ 03፣ ቁጥር 101፣ ረቡዕ መጋቢት 23 ቀን 2007 ዓ.ም የተደረገ ቃለ ምልልስ፤
ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፡– ለዚህ አባባል መልስ ከመስጠቴ በፊት፣ ከትምህርቴም ኾነ ከአስተዳደጌ የተማርኹትና አብሮኝ የኖረ ቁልፍ የሞራል አስተምህሮ አለ፡፡ ይኸውም፣ በማናቸውም ጊዜ ግጭት፣ ፍልሚያ ወይም ክርክር በምንገጥምበት ጊዜ፣ በተቻለን መጠን እውነትን ጨብጠን መሔዱ በጣም አስፈላጊ ነው የሚል ግንዛቤ አለኝ፡፡ እውነትን ሰለባ በማድረግ ጊዜያዊ ድልን ለመጎናጸፍ መሞከር በራሱ ለምንቃወማቸው ድርጊቶች እና ሰዎች ተላልፎ በመሰጠት ተሸናፊ ስለሚያደርገን፣ በሐሰት ድልን ለመጎናጸፍ መሞከርን የመሰለ ሽንፈት የለም ብዬ ስለማምን ነው፡፡
ዶ/ር አድማሱ፣ ‹‹የትምህርት ክፍሉ በቂ መምህራን አሉኝ ካለ ግለሰቡ ኮንትራቱ አይታደስለትም›› ያሉት እውነት ነው፡፡ ኾኖም ዋናው ጥያቄ፣ የትምህርት ክፍሉ እኔን በሚመለከት አገልግሎቴን አልፈልግም ብሏል ወይ፤ የሚለው ነው፡፡ ይህን ጥያቄ በተመለከተ እኔ እንዲህ ነው ወይም እንዲያ ነው ከምል፣ የትምህርት ክፍሌ የእኔን አገልግሎት በጥብቅ እንደሚፈልግና ኮሌጁም (የሶሻል ሳይንስ) እንደተስማማበት ለፕሬዝዳንቱ የቀረበውን ደብዳቤ በማረጋገጫነት ልታቀርቡት ትችላላችኹ፡፡ የፕሬዝዳንቱን አቀራረብ የቱን ያህል ከእውነት የራቀ መኾኑን አንባቢ አይቶ ፍርዱን እንዲሰጥ እጋብዛለኹ፡፡
ኢ.ም፡- ሰሞኑን ‹‹ተወይኖብኛል›› ብለው ባስነበቡት ቃለ መጠይቅ ላይ ‹‹ብጣሽ ወረቀት ስጠብቅ አልኖርም›› ብለዋል፡፡ እስኪ ስለዚህ ወረቀት ትንሽ ያብራሩልኝ፡፡
ዶ/ር ዳኛቸው፡- ከዚኽ ቀደም እንደገለጽኩት፣ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል የእኔን ተጨማሪ የሥራ ዘመን አገልግሎት እንደሚፈልግ ለሶሻል ሳይንስ ኮሌጁ ዲን እና በበላይነት ለሚሰበስበው አካዳሚክ ኮሚሽን የፍልስፍና ትምህርት ክፍል ሊቀ መንበር በአካል ተገኝተው ከማስረዳታቸውም በተጨማሪ በደብዳቤም ጠይቀዋል፡፡ የሶሻል ሳይንስ ኮሌጁም ቢኾን የፍልስፍና ትምህርት ክፍልን ጥያቄ ተቀብሎ የሥራ ውሌ እንዲታደስ፣ በፕሮፌሰር ወልደ አምላክ በዕውቀት (የኮሌጁ ዲን) በኩል ለዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አድማሱ ጸጋዬ እንዲያጸድቁት በደብዳቤ ጠይቀዋል፡፡
ኾኖም ፕሬዝዳንቱ አራት ወር ሙሉ ይኾናልም – አይኾንምም ሳይሉ ለደብዳቤው መልስ ሳይሰጡ በእጅጉ በመዘግየታቸው የእርሳቸውን ቅን ልቡና የጎደለው እና ተንኮል ያዘለ አካሔድ ለመግለጽ ‹‹ብጣሽ ወረቀት አልጠብቅም›› የሚለውን ሐረግ ተጠቅሜአለኹ፡፡ ፕሬዝዳንቱ መልስ አለመስጠታቸው ከሕግ እና ከሞራል አገባብ ውጭ እንደኾኑ ቀደም ሲልም ለማብራራት ሞክሬያለኹ፡፡ነገሩን ለማጠቃለል ያኽል፣ የእናንተ አንባቢዎች በጉዳዩ ላይ የራሳቸውን ግንዛቤ እና ፍርድ እንዲሰጡ ለፕሬዝዳንቱ የተላከውን ደብዳቤ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚኽ ቃለ ምልልስ አጋጣሚ ላቅርብ፡፡ ከማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ዲኑ በእንግሊዝኛ የተጻፈው የደብዳቤው ይዘት የአማርኛ አቀራረቡ በአጭሩ የሚከተለውን ነው፡-
የፍልስፍና ዲፓርትመንት፣ ለዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ የኹለት ዓመት ኮንትራት እድሳት እንዲያገኙ ጠይቋል፡፡ ስለ ኮንትራት እድሳቱ አስፈላጊነት ዲፓርትመንቱ ያቀረባቸው ምክንያቶች፡-
– ዶ/ር ዳኛቸው ሦስት የድኅረ ምረቃ ትምህርቶች (ኮርሶች) እና የቅድመ ምረቃ ዲግሪ ኮርሶችንም ስለሚያስተምሩ፤
– በርካታ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎችን (ከ12-15 ተማሪዎች) የመመረቂያ ጽሑፎችን ስለሚያማክሩ፤
– ከፍልስፍና ዲፓርትመንት ውጭ በርከት ያሉ ኮርሶችን በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት፣ በሰብአዊ መብቶች ተቋም የትምህርት ክፍል፣ በቴክኖሎጂ ኢንቲትዩት እና የሕግ ትምህርት ቤት ስለሚያስተምሩ፤
– በቅርቡ ለሚጀመረው የሦስተኛ ዲግሪ (ፒ.ኤች.ዲ) መርሐ ግብር የዶክተር ዳኛቸው አገልግሎት በእጅጉ አስፈላጊ ነው ብሎ ዲፓርትመንቱ ስለሚያምን፣
የሚሉት ናቸው፡፡
የአካዳሚክ ኮሚሽኑ በህዳር 24 ስብስባው ወቅት በዚኽ የዲፓርትመንቱ ጥያቄ ላይ ተወያይቶ የዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ የኮንትራት ቅጥር ውል ከታኅሣሥ 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ለኹለት ዓመት እንዲራዘም ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በመኾኑም የሰው ሀብት አስተዳደርና ልማት ቢሮው፣ ለውሉ መራዘም የዩኒቨርስቲውን ፕሬዝዳንት ይኹንታ በማረጋጥ የውል እድሳት ሒደቱን እንዲያስፈጽምልን በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡
ደብዳቤው በአድራሻ የተላከው ለዩኒቨርስቲው ለሰው ሀብትና ልማት አስተዳደር ቢሮ ሲኾን፣ ላኪው ደግሞ የአካዳሚክ ኮሚሽኑ ነው፡፡ ይኸው ደብዳቤ ለፕሬዝዳንቱ ቢሮ፣ ለአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ቢሮ፣ ለአካዳሚክ ጉዳዮች ቢሮ፣ ለፍልስፍና ትምህርት ክፍል እና ለማኔጂንግ ዳይሬክተሩ በግልባጭ እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡
ኢ.ም፡- እርስዎ እንዳሉት፣ ጥያቄዎ ሕግና ደንብን ጠብቆ ከቀረበ፣ ችግር ፈቺ እንዲኾን ከሚጠበቅ ዩኒቨርስቲ አስተዳደር ምላሽ የተሰጠበት አግባብ ስለ አገራችን ኹኔታ ምን አንድምታ እና ማሳያ ሊሰጠን ይችላል?
ዶ/ር ዳኛቸው፡- ከኹሉ አስቀድሞ የአንድ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ለኹለት ዓበይት ጉዳዮች ተጠሪ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ አንደኛና ተቀዳሚው ተጠሪነቱ ዩኒቨርስቲው ለቆመለት ተቋማዊ መርኆ (አይዲያል) ነው፡፡ በኹለተኛው ደረጃ ደግሞ ለዩኒቨርስቲው አጠቃላይ ማኅበረሰብ (ኮሚዩኒቲ) ተጠሪ መኾን አለበት፡፡
እኔ፣ ዶ/ር አድማሱ ጸጋዬ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ከኾኑ ጀምሮ የታዘብኩትና ያየኹት፣ እንደ ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ተጠሪነታቸው ለዩኒቨርስቲው ርእይ ሳይኾን መንግሥት ለሚያወጣው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ዕቅዶች (social and political policy) መኾኑን አያለኹ፡፡ ከዚኽም ባሻገር ለዩኒቨርስቲው ማኅበረሰብ በጎነት ከመቆም እና የአካዳሚክ ነፃነት እንዲከበር ከመጣር ይልቅ ለሾሟቸው የፖለቲካ ኃይሎች በተደጋጋሚ ተጠሪነታቸውን በጉልሕ አሳይተዋል፡፡
በእርሳቸው አመራር አንድ ትጉህ አስተማሪ የሚዳኘው በአካዳሚያዊ መሥፈርት ሳይኾን፣ በብሔር ተዋፅኦ፣ በፓርቲ ተሳትፎ እና የመንግሥት ፖሊሲን ለማስፈጸም በሚያሳየው ተነሳሽነት ነው፡፡ ለማጠቃለል ያኽል፣ ዶ/ር አድማሱ ከሚዘነጓቸው ነገሮች መካከል፣ አንድ የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የመንግሥት ተከፋይ ቢኾንም ቅሉ፣ የመንግሥት ሠራተኛ (ሲቭል ሰርቫንት) እንዳልኾነ ነው፡፡
ኢ.ም፡- በዩኒቨርስቲው ውስጥ እርስዎ የሚሉት ዓይነት ድባብ እንዴት ሊሰፍን ቻለ? በዚኽ አኳኋንስ የዩኒቨርስቲ ምሁራን ለመጠየቅ እና እውነት ላይ ለመድረስ የሚጥሩ ወጣት ዜጎችን እንደምን ሊያፈሩ ይችላሉ?
ዶ/ር ዳኛቸው፡- ጥያቄው ኹለት ጉዳዮችን የያዘ ይመስለኛል፤ ተራ በተራ ለመመልከት እሞክራለኹ፡፡ አንደኛ፣ እንዲኽ ዓይነት የማይጠይቅ፣ ተቀባይነት እና የፖሊሲ አስፈጻሚነት መንፈስ ከዬት መነጨ ብለን በምንፈትሽበት ጊዜ፣ ጉዳዩ በማወቅና ባለማወቅ፣ ግንዛቤ በማግኘትና በማጣት (Epistmic) ምክንያት ብቻ ሳይኾን ከግል ጥቅምና ከፍቅረ ንዋይ ጋር የተሳሰረ ስለኾነ ነው፡፡ እንዲኽ ዓይነት ፖሊሲ አስፈጽሙ ሲባል፣ ትእዛዙ የሚመጣው ብቻውን ሳይኾን ከብዙ ዓይነት ዳረጎት (ኮሚሽን) ጋር ስለኾነ፣ ሳያቅማሙ እና ሳይፈትሹ ወደ መቀበልና መተግበር ይገባሉ፡፡
በዩኒቨርስቲው ውስጥ ያሉትን መምህራን በሙሉ ሳይተቹ ተቀባይ እና ፖሊሲ አስፈጻሚ አድርጎ መመልከቱ አግባብነት አይኖረውም፤ እንዲያውም በዩኒቨርስቲው ለሰባት ዓመታት በቆየኹባቸው ጊዜያት ከአገኘኋቸውና ከተዋወቅኋቸው የግቢው ሊቃውንት ብዙ ትምህርት እንደቀሰምኹ ለመግለጽ እወዳለኹ፡፡
ነገር ግን፣ ጠያቂና ተቺ የኾኑ ዓይናማ ሊቃውንት በግቢው ውስጥ እንዳሉ ኹሉ፣ በርከት ያሉ ካድሬዎችም በምሁራን ስም ተቀጥረው ግቢውን እያጣበቡት እንደኾነ ማንም አይስተውም፤ ፕሬዝዳንቱም አንድ ለአምስት በሚል የጥርነፋ ፕሮግራም መምህራኑን እያስቸገሩ አትኩሮታቸውን ለመማር ማስተማር ሒደቱ በቅጡ እንዳያውሉ እና የትምህርት ድባቡን እያስተጓጎለ እንደሆነ በግቢው ውስጥ በሰፊው እየተወራ ነው፡፡
በጥያቄህ ላይ በእንዲህ ዓይነት ድባብ ውስጥ የሚወጡት ተማሪዎች ምን መልክ ይይዛሉ ብለኽ ለጠየቅኸኝ፣ ኹኔታው ጥሩ ተማሪ ለማፍራት ተግዳሮት ቢኾንም፣ ጥቂት የማይባሉት መምህራን በግላቸው ሞያዊ ግዴታቸውን ለመወጣት በእጅጉ እየጣሩ ይገኛሉ፡፡
ኢ.ም፡- እኔ እንደሰማኹት፣ በመስከረም 2007 ዓ.ም መንግሥት ለዩኒቨርስቲው ማኅበረሰብ ለዐሥር ቀናት የዘለቀ ሥልጠና በሰጠበት ወቅት፣ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አድማሱ ጸጋዬ መምህራንን የመቅጠር ሒደትና ሌሎችንም ዋና ዋና ሥልጣኖች ከዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንቶች ይልቅ ወደ ዩኒቨርስቲ ኮሌጆችና ዲፓርትመንቶች ተሰጥቷል ሲሉ ተደምጠዋል፤ እንዲያውም ኮሌጆችና ዲፓርትመንቶች መምህራንን ለመቅጠር ፈቃደኛ ባለመኾናቸው ከፍተኛ በጀት ለመንግሥት ተመላሽ እየተደረገ ነው በማለት አማርረው ነበር፡፡ በአንጻሩ እርስዎንና ዶ/ር መረራን ዲፓርትመንቱና ኮሌጆቹ እንፈልጋቸዋለን እያሉ ፕሬዝዳንቱ ግን ቅጥራችኹ የሚራዘምበት ይኹንታን ፈቃደኛ አልኾኑም፡፡
ዶ/ር ዳኛቸው፡- በመሠረቱ በወቅቱ እኔ በሥልጠናው ላይ ለመገኘት ስላልፈለግኹ በስብሰባው አልተሳተፍኩም፤ ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ ከቀድሞው የዩኒቨርስቲው አስተዳደር በተለየ መልኩ ለኮሌጆችና ለዲፓርትመንቶች ሥልጣን አውርጃለኹ በማለት እየተኩራሩ ሲናገሩ በሌላ አጋጣሚ ሰምቻለኹ፡፡ ይኹንና ወደ ተጨባጭ እውነታው ስንመጣ፣ ከነቢብ አልፎ በገቢር ባለመተርጎማቸው፣ ፕሬዝዳንቱ ተቀዳሚ የሚያደርጉት የዩኒቨርስቲውን ጥቅምና ፍላጎት ሳይኾን፣ የራሳቸውን የግል ፍላጎት ለመኾኑ ከዚህ የበለጠ ማረጋገጫ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡
ኢ.ም፡- በደብዳቤው እንደተገለጸው፣ ኮሌጁና ዲፓርትመንቱ አጥብቆ በሚፈልግዎት በእርስዎ ላይ ፕሬዝዳንቱ እንዲኽ ዓይነት ርምጃ ለመውሰድ ያበቃቸው ምን ሊኾን ይችላል ብለው ያስባሉ?
ዶ/ር ዳኛቸው፡– ይኸውልህ ነገሩ የተጀመረው ፕሬዝዳንቱ ተሹመው በመጡ ማግሥት ነው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ማኅበረሰብ በጠቅላላ ሰብስበው ለዓባይ ግድብ ምን አስተዋፅኦ ማድረግ እንችላለን ብለው ከመድረክ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ አንድ- አራት- አምስት ሰዎች ተነሡና እኔ እንዲኽ አደርጋለኹ፤ እኔም እንዲኽ አደርጋለኹ ብለው ተናግረው ሲያበቁ፣ የተሰበሰብነው ሰዎች በሺሕዎች ብንቆጠርም ፕሬዝዳንት አድማሱ፣ ‹‹የምትሉት ገብቶኛል፤ የወር ደሞዝ እንሰጣለን ነው የምትሉት፤›› በማለት ቀድሞ የተጻፈ የአቅዋም መግለጫ አስነብበው ስብሰባውን በዚኹ ቋጩት፡፡
እኔም በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ፣ አራትና አምስት ሰው ብቻ በተናገረው እንደምን የብዙኃኑን ሰዎች ፍላጎት አገኙት በማለት ግልጽ ሒሳዊ ደብዳቤ ጻፍኹላቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ መተቻቸት በአካዳሚያዊ ተቋማት የተለመደ ቢኾንም፣ እርሳቸው ግን፣ እኔ ባቀረብኹላቸው አስተያየት አቂመው ቆይተዋል፡፡ ይህን የሚያስረግጥ ሌላም ጉዳይ ልጠቀስልኽ፤
የቀድሞው የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ በነበሩበት ጊዜ፣ 19ኛው የዓለም አቀፍ የትምህርት ፍልስፍና ጉባኤ (International Network of Philosophers of Education Conference) ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲኾን ተወሰነ፡፡ ጉባኤውን የዩኒቨርስቲው የትምህርት ክፍል ለብቻው ማዘጋጀት ቢፈልግም፣ ፈረንጆቹ የፍልስፍና ዲፓርትመንትም መካፈል አለበት ስላሉ፣ በዚያን ጊዜ ፕሮፌሰር አንድርያስ የትምህርት ክፍሉን በመወከል በዝግጅቱ እንድሳተፍ ጋበዙኝ፡፡
ጉባኤውን ለማዘጋጀት በተቋቋመው ኮሚቴ፥ ፕሮፌሰር ሀብታሙ ወንድሙ፣ ዶ/ር ጄሉ ዑመር፣ ዶ/ር አማረ አስገዶም እና እኔ በጋራ መሥራት ጀመርን፡፡ ከዚያም ዶ/ር አማረ አስገዶም ለጉባኤው ዝግጅት ከአራት ሚልዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ነገረኝ፤ አዲስ የተሾሙት ዶ/ር አድማሱ ጸጋዬም ብሩን እንደሚፈቅዱም በርግጠኝነት ገለጸልኝ፡፡ ወጪው በጣም ከፍ ያለ መስሎ ስለታየኝ፣ ይህን ያኽል ብር ለምን ያስፈልገናል ብዬ ጠየቅኹት፡፡ ዶ/ር አማረ ሲመልስልኝ፣ ከተለያየ የዓለም ክፍል የሚመጡትና ከሀገር ውስጥ የጉባኤው ተሳታፊዎች ከፍለው ስለሚገቡ ወደ ሰባት ሚልዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ተገኝቶ የኒቨርስቲው ሦስት ሚልዮን ብር እንደሚያተርፍ ነገረኝ፡፡ በመቀጠልም ፕሬዝዳንቱን ስለ ጉዳዩ ለማሳወቅ ቀጠሮ እንደተያዘ ነገረኝ፡፡
ኾኖም ኹለት ጊዜ ባካሔድነው ስብሰባ ላይ ዶ/ር አድማሱ ጸጋዬ ሳይመጡ ቀሩ፡፡ በጊዜው ሳይመቻቸው ቀርቶ ነው በማለት ነገሩን ብዙም ትኩረት አልሰጠኹትም ነበር፡፡ በሌላ ጊዜ ዶ/ር አማረን ስለ ጉባኤው ዝግጅት ኹኔታ ስጠይቀው፣ አንተ ከኮሚቴው እንድትወጣ አድርገናል፡፡ በአንተ ምትክ ከፍልስፍና ትምህርት ክፍል ዶ/ር በቀለ ጉተማን አካትተናል አለኝ፡፡ ይኸውም የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት አንተን ስለማይወድኽ ነው አለኝ፤ አክሎም ‹‹እርሱ ከኮሚቴው ካልወጣ በስተቀር ስብሰባው ላይ አልገኝም›› ስላሉና አማራጭ ስለሌን አንተን ከኮሚቴው አስወጥተን በሌላ ለመተካት ተገደናል፡፡ ነገሩ ቢገርመኝ፣ አካዳሚያ ውስጥ መውደድና መጥላት የሚባል ነገር ምን አመጣው በማለት ትዝብቴን ገለጽኹለት፡፡
የሚያሳዝነው ግን፣ በዚህ ታላቅ ጉባኤ የጥናት ወረቀት የሚያቀርቡ ኢትዮጵያውያን፣ የጥናትና ምርምር ግኝታችኹን ለማቅረብ ገንዘብ በ‹‹ዩሮ›› ከፍላችሁ ነው በመባላቸው ጉባኤው የታለመለትን ዓላማ ስቶ መክሸፉ ነው፤ ፈረንጆቹም በዓለም ላይ በፍልስፍና ሥነ ትምህርት ከተዘጋጁ ጉባኤዎች ኹሉ እንዲኽ ዓይነቱ ሥምረት የሌለበት ጉባኤ እንዳልገጠማቸው አምርረው በመናገራቸው፣ ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም ኾኖ ክንዋኔው በብዙኃን መገናኛ ሳይዘገብ እንደተዳፈነ ቀረ፡፡
በፕሬዝዳንቱ በኩል በእኔ ላይ ቅሬታ ማሳደር የተጀመረበት አጋጣሚ ይህ ኾኖ፣ በዋናነት ግን በተለያዩ ብዙኃን መገናኛዎች መንግሥት የሚሠራቸውን ተገቢ ያልኾኑ ድርጊቶች በዐደባባይ መተቸቴንና ሒስ ማድረጌን የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንትም ይኹኑ የውጭ የፖለቲካ ኃይሎች እንዳልወደዱት ግልጽ ነው፡፡
ኢ.ም፡- ይህን ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት ሊወስዱት አስበዋል?
ዶ/ር ዳኛቸው፡- የሥራ ውሌ አልተራዘመም ብዬ ወደ ፍርድ ቤት የመሔድ ሐሳብ የለኝም፡፡ በእኔ እምነት፣ አስተማሪነት የተከበረ ሞያ በመኾኑ፣ በልመና እና በፍርድ ቤት ውሳኔ መምህር ለመኾን መሞከሩ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ በተጨማሪም፣ የኔ ከሥራ መሰናበት በተቀዳሚነት የአካዳሚያው ውሳኔ ሳይሆን፣ በውጭ ባሉት ፖለቲካዊ ኃይሎች የተገፋ ብያኔ እንደኾነና የፕሬዝዳንቱ ሚና ደግሞ ያን የማስፈጸም ጉዳይ እንደኾነ ስለምረዳም ጭምር ነው፡፡ የሳባቲካሉን ጉዳይ ግን ወደሚመለከተው ፍርድ ቤት እወስደዋለሁ፡፡
ኢ.ም፡- በኮንትራት ቅጥር ውልዎ እና በሴኔት ሕጉ ላይ የጥናትና ምርምር ዕረፍት (ሳባቲካል) እንደሚሰጥዎ ሰፍሯል፡፡ ኾኖም በስድስት ዓመት የማስተማር አገልግሎት የሚገኘውን ይህን መብትዎን እንደተነፈጉ እርስዎ ቀደም ሲል ለተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ሲመልሱ፣ ‹‹የጠየቁት ጡረታ ከወጡ በኋላ ነው›› ብለዋልና ለዚኽ ምን ይላሉ?
ዶ/ር ዳኛቸው፡- ከኹሉ አስቀድሞ ይህ ጉዳይ በፍርድ ቤት ሒደት ላይ ነው፡፡ ስድሳ ዓመት (የጡረታ ዕድሜ) ሳይሞላኝ ከሦስት ዓመት በፊት ነው ሳባቲካል ዕረፍት እንዲፈቀድልኝ የጠየቅኹት፡፡ የጠየቅኩበት ሰነድም በእጄ ይገኛል፡፡ ዋናው ቁም ነገር ፕሬዝዳንቱ በኹለት ጉዳዮች ላይ ከእውነት የራቀ መልስ መስጠታቸው በጣም አስገርሞኛል፡፡ አንደኛው፣ ከላይ የጠቀስኹት ስድሳ ዓመት ሳይሞላኝ የዕረፍት ጊዜው እንዲፈቀድልኝ ማመልከቴ ነው፡፡ ኹለተኛው ደግሞ ጡረታ ከወጡ በኋላ ሳባቲካል የተሰጣቸው ሌሎች መምህራን እንዳሉና እርሳቸው እንደሚሉት ከጡረታ በኋላ ሳባቲካል ዕረፍት አይሰጥም ያሉት ነጭ ውሸት መኾኑ ነው፡፡ ይህንም ለፍርድ ቤቱ እንደማቀርበው ስም ጠቅሼ ልነግራችኹ እችላለኹ፡፡
ኢ.ም፡- ወደ አገራዊ ጉዳዮች ልውሰድዎና የቅድመ ምርጫ ሒደቱን እንዴት ገመገሙት?
ዶ/ር ዳኛቸው፡- ብዙ ጊዜ ምርጫውን በሚመለከት ወደ አእምሮዬ የሚመጣው ለጥቂት ጊዜም ቢኾን በእነ አቶ በላይ ፍቃዱ ይመራ የነበረው የአንድነት ፓርቲ መፍረስ ነው፡፡ ይህንንም የምልበት ምክንያት፣ ከወጣት አመራሩ መካከል አቶ በላይ ፍቃዱ፣ አቶ ተክሌ በቀለ፣ አቶ ዐሥራት ኣብርሃ እና ሌሎችም በዚያ አመራር ውስጥ የተሰባሰቡ ሳተናዎች ከጨዋታ ውጪ መደረጋቸው የሐቀኛ ፉክክሩን ጎዳና በመዝጋት የናፈቅንለትን እውነተኛ የምርጫ ውድድር መንፈስ አደንብሾታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ስለምርጫው ውጤትም፣ ብዙ ሰው ከሚለው የተለየ ሐሳብ የለኝም፡፡ ይኸውም ገዢው ግንባር ያለጠንካራ ተፎካካሪ ያንኑ የተለመደውን ከፍተኛ መቀመጫ ይይዛል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ኢ.ም፡- ላለፉት ኻያ አራት ዓመታት ኢትዮጵያን በመምራት ላይ የሚገኘው ህወሓት/ኢሕአዴግ አገሪቱን እና ሕዝቦቿን ወዴት አቅጣጫ እየወሰደ ይገኛል ብለው ያስባሉ?
ዶ/ር ዳኛቸው፡-እኔ እስከሚገባኝ ድረስ በኢሕአዴግ የፖለቲካ ፍልስፍና ወሳኝ የኾነው ቃል ‹‹ብሔር›› የሚለው ነው፡፡ በመሠረቱ የብሔሮች እኩልነት፣ የብሔሮች ራስን በራስ ማስተዳደር የሚለው ጥሪ በራሱ ክፉ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ስናየው ግን ዜጋ እና የዜግነት ብሂልም ተገቢውን አትኩሮትና ቦታ ሊሰጠው ይገባል እላለኹ፡፡ ከዚኽ በፊት በአንድ ስብሰባ ላይ እንዳቀረብኩት፣ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን እንደሚከበረው ኹሉ ወደፊት በቅርብ ጊዜ የዜጋ-ዜጎችንም ቀን እንድናከብር ቢፈቀድልን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀልብ እና የልብ ትርታ የትኛው ላይ እንደሚያርፍ ይታይ ነበር፡፡
በመጨረሻም፣ ዩኒቨርስቲውንም ኾነ የአገራችንን የፖለቲካ ድባብ በተወሰነ ደረጃ ይገልጽልኛል ብዬ ከምለው ከዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ‹‹እውነት ማለት የኔ ልጅ›› ከሚለው የግጥም ስብስብ የሚከተሉትን ስንኞች አቅርቤ እንድጭርስ ብትፈቅድልኝ፡-
የኔ ልጅ፣
እውነት ጽድቅ እንዳይመስልሽ፣ ኲነኔ ነው እውነት ያማል፤
አይታከሙት ደዌ፣ ያከሳል ያጎሳቁላል
ኹሌ አያስከብርሽም፣ አንዳንዴ ሕይወት ያስከፍላል፡፡
እውነቱ ነው ጀግንነቱ፣ ቴዎድሮስ ራሱን ቢያጠፋ፤
ከዙሪያ ገባው እውነት፣ የራሱ ሐቅ ቢገዝፍ፣ የራስ እምነቱ ቢሰፋ፤
ቊርባኑን አላፈርስ ብሎ፣ ከእውነቱ አልተጣላ፤
ማተቡን አልበጥስ ብሎ ነው፣ የወደቀው ከመቅደላ፡፡ …
አቡነ ጴጥሮስ በዐደባበይ፣ በጥይት የተደበደበ፣
ደብር እንደፈታ ሽፍታ
እውነቱና ሕይወቱ፣ ሕይወቱና እምነቱ፣ ብሎት ነው አልፋታ፡፡ …
አጥተውት መሰለሽ ልጄ፣
በላይ ዘለቀ አድር ቢል፣ እጅ ቢነሣ አስመስሎ፣
ጴጥሮስ ለፋሽስት ቢሰብክ፣ የአገር ወገን እውነቱን፤
የአካል የመንፈስ፣ እምነቱን ጥሎ፤
ጊዜ አጨብጭቦ፣ ወርቅ ተሸልመው፤
እንበለ ኃጢአት፣ ቅዱሳን ተብለው፤
በሕይወት እንደሚኖሩ፤
እውነትን ሽረው እንደሚከብሩ፤…
ልጄ፣ እውነት ከሕይወት ይከብዳል፤
በመኖር ከሕይወት ተገኝቶ መልሶ ሕይወትን ይበላል፡፡