>
5:16 pm - Saturday May 23, 9159

ደራሲ አዳም ረታ

Facebook profile - Adam Reta”ደራሲ አዳም ረታ በጥቅምት ወር 2007 ዓ.ም. ከጥቂት አድናቂዎቹ ጋር ተገናኝቶ በነበረበት ወቅት በቀረቡለት ጥያቄዎች መሠረት አንዳንድ ማብራሪያዎችን ሰጥቶ ነበር፡፡ በዚያ ዝግጅት ተገኝተው ለመሳተፍ ላልቻሉ በርካታ አድናቂዎቹ አዳም በአጻጻፍ ስልቱ፣ በመጻሕፍቱና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ በዕለቱ የሰጣቸው መልሶች በዚህ ገጽ ላይ በተከታታይ ይቀርባሉ።” በማለት ደራሲ ኣዳም ረታ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ያስቀመጠውን ልናካፍላችሁ ወደድን፤ መልካም ንባብ።

ጥያቄ 1

የሕጽናዊነት አጻጻፍ ስልት፡ በአንድ ማሕበረሰብ ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች መካከል የሚኖር መረባዊ ትስስርን የሚያጎላ እንደሆነ በተደጋጋሚ ትገልጻለህ። በዚህ መነሻነት በተለይ በተለምዶ “ያ ትውልድ” የሚባለውን የዘመነ አብዮት ወጣት በተመለከቱ ድርሰቶችህ አማካይነት የአሁኑን ዘመን ወጣት ከዚያ ትውልድ አስተሳሰብ፡ አመለካከትና ታሪክ ጋር የማገናኝት ዓላማ አለህ?

አ.ረ

” ያንን ትውልድ ከዚህ ትውልድ የማገናኘትም የማለያየትም ዓላማ የለኝም። እንደግለሰብ የኖርኩት ህይወት ነው። እንደ ደራሲ ግን ያለፈውን ነገር ለማሳየት ብቻ ነው። በርግጥ ያለፈው ዘመን ድርጊት ከአሁኑ ዘመን ድርጊት ጋር ይገናኛል። ቢያንስ በምክኒያትና ውጤት። በሆነ በቀረ መንፈስ residue. ይጥም ይሁን የተበላሸ የሚገናኝበት ነገር አለ። ምን አይነት consiousness እንደነበረ፡ በዚያን ግዜ ስለነበረው ወጣት፡ ስለዘመኑ ስነ ልቦና ፡ በዚያን ግዜ ስለነበረው ማሕበራዊ መስተጋብር፡ ወጣቱን ወደዚያ ምን እንደወሰደው፡ እሱን ነገር የማሳየት ነው።

ብዙ ዓይነት የስነ ልቦና አቀራረብ ልትወስድ ትችላለህ። እስካሁን በስፋት ተቀባይነት ያገኘው አስተሳሰብ ‘በቃ ነቅቶ ነው’ የሚል ነው። ያንን ተጠየቅ ውስጥ ማስገባት ትችላለህ። ፖለቲከኛ፣ ወጣቱ ታሪክ ገብቶት ነው ሊልህ ይችላል። ልብ ወለድ እንደዚህ አይነት በስፋት የታመኑ ሚቲዮሎጂዎችን challenge ያደርጋል። ምክኒያቱም ልብ ወለዶች ወደ ግለሰብ ነው የሚቀርቡት። ከ group discourse አልፈው ግለሰብ ጋር ስለሚመጡ፡ የግለሰቡን የእለት ተለት ህመም፡ የእለት ተለት ስሜት፡ እና ግለሰቡ እንደዛ አይነት የወል አስተሳሰብ (group thinking) ውስጥ ለመግባት እንዴት የራሱን ፍቅር፡ የራሱን ስሜት፡ የራሱን ግዜ ለግሩፕ ሀሳብ እንደሚሽቅጥ ልብ ወለዶች ይነግሩሀል።

ለምሳሌ፡ ሕይወት ተፈራ የጻፈችው መጽሀፍ ውስጥ፡ የሆነ ቦታ እስር ቤት ትገባለች። እስር ቤት ገብታ የሆነ ሰው ይገርፋታል፡ ይደበድባታል። ያ የሚደበድባትና የሚገርፋት ሰው በኋላ ዘመዷ ሆኖ ይገኛል። ይህ የሚያሳየው ምንድን ነው፡ የግለሰቦች ሕይወት ርእዮተ አለሞችን ቆርጦ ያልፋል። ጥሩ ልብ ወለድ ታዲያ እንደዛ አይነት ነገሮችን ይነግርሀል። እነዛ ነገሮች ላይ በጥልቀት ታሰላስላልህ ወይም meditate ታደርጋለህ። ህይወት እነዛ ነገሮች ላይ meditate ሳታደርግ እንደዋዛ ነው ያለፈችው። ምናልባትም እንደመልካም እድል ቆጥራው ይሆናል። ለኔ ግን ያ መልካም እድል አይደለም። ለኔ የሚታየኝ በሆነ መልክ እርስ በርሱ በተሳሰረ ማሕበረሰብ ውስጥ ርእዮተ አለም በጣም በደስታ ራሱን ሲያጠፋ ነው። ያ ሰውዬ እኮ አባቷ ሊሆን ይችላል። እየገደላት ነበር። ሰውዬው ራሱ እንዴት ልጄን እደበድባለሁ ብሎ ሲቆጭ ነበር። ነገር ግን ይህን የፈጠረው፡ የነበረበት ሁኔታ፡ ሆን ብሎ የወሰደው ውሳኔ እንደሆነ ይዘነጋል። እና ሲመስለኝ እሷም ትዘነጋለች። ልብ ወለድ፡ የኔ ብቻ ሳይሆን ጥሩ የሚባል ማንኛውንም ልብ ወለድ ከጻፍክ፡ በዚህ methodology የግለሰቡን ህይወት አውጥተህ የራስህን ፍርድ (judgement) ሳታስገባ፡ የግለሰቡን የህይወት ንቅናቄ እና ጉዞ ካየህ እነዚህ mytheologies፡ በተለይም ፖለቲከኞች ሊገነቧቸው የሚፈልጓቸው mythologies ይፈርሳሉ። ምክኒያቱም የሚቆሙበት መሰረት ያጣሉ። የርስ በርስ ግንኙነቱ ያጠፋቸውናም group mischiefs ይሆናሉ። ይህንን ነው በድርሰቴ ውስጥ ማሳየት የምፈልገው። በኔ ግፊት ሳይሆን ገጸ ባህሪያቱን በመከተል።

አዲስ አበባ፡ ያኔ እንዳሁኑ አይደለም። በእውነት መንደር ነገር ነበር። መሀል ፒያሳ ውስጥ አህያ ሲሄድ ታያለህ። እበት ሊያዳልጥህ ይችላል። ገጠር ነው። እና ያንን የገጠር ወጣት ጥሩ አራዳ ልጆች ሊሸውዱት ይችላሉ። ያንን የማየትና በቅርበት የመረዳት ነገር ነው። ያነሳሁት የህይወት ተፈራ ምሳሌ የሚያሳየው፡ ርእዮተ አለም ራሱን ሲያጠፋ ነው ልትል ትችላለህ። ወይንም ደግሞ በጎ ስራ ነው ልትልም ትችላለህ። ብዙ ደራሲዎች ከተለያየ አንጻር ሊያዩት ይችላሉ። ግን ይህን methodology ሆን ብዬ ለዚህ አልመረጥኩትም። ይሄን ዘመን ለመግለጽ ብቻ አይደለም የተጠቀምኩበት። በታሪክ ውስጥ ማንኛውንም ግዜ፡ ማንኛውንም ክስተት፡በዚህ አይነት መልክ ብናየው ይበልጥ ግልጽ ሊሆን ይችላል።

ጥያቄ 2

በድርሰቶችህ ውስጥ ሰብአዊ ፍጡራን ብቻ ሳይሆኑ ግኡዝ የሆኑ ነገሮችም በስፋት ቦታ ተሰጥቷቸው ሲተነተኑ ይታያል። የዚህ ምክኒያቱ ምንድነው?

አ.ረ.

በምጽፍበት ወቅት ወይም በ ፍልስፍናዬ ውስጥ አለም ለኔ ጠፍጣፋ ነች። ጠፍጣፋ ማለት ተዋረድ የላትም። ጌታ ምናምን የላትም።ይህ ማለት ፍጡራንንም ይጨምራል። አካል ያላቸውም የሌላቸውም ፍጡራን ለኔ እኩል ደረጃ ነው ያላቸው። በሀይማኖት እግዚአብሄር በአንድ ቀን አእዋፋት ፈጠረ በሌላ ቀን የሆነ ነገር ፈጠረ ምናምን ይባላል። Physical ተፈጥሮንም ሆነ የሰው ልጅ ተፈጥሮን አስቦና ግዜ ወስዶ ነው የሰራው።

Adam Reta's bookለሰው ልጅ ብቻ ቦታ በመስጠት ሌሎችን መዘንጋት አይገባም። ስለዚህ flat ወይም ጠፍጣፋ ያልኩት ለዚህ ነው። ሰውም፡ ተፈጥሮም፡ የሰው ልጅ የሰራው እቃም እኩል ደረጃ አላቸው። ስለዚህ ድርሰቶቼን ስጽፍ እቃዎቹም እንደሰዎቹ ቦታ ይኖራቸዋል። በእኩል አይን አያቸዋለሁ። እኩል ስታደርጋቸው ያ ላንተ የተከሰተው እቃ የሚነግርህ ነገር አለ።

ብዙ ግዜ እነዚህን ነገሮች እናሸሻቸዋለን። ተዋረድ እንፈጥራለን። አምላክ፡ አፈር፡ ድንጋይ ምናምን እያልን። ያን ተዋረድ ስለማጠፋ ወይም ለማጥፋት ስለምሞክር ይመስለኛል ያን አይነት አተራረክ የመጣው። በገሀዱ አለም ሰዎች በትናንሽ እቃዎች ይጣላሉ። ይህንንም እምነቴን ቦታ ለመስጠት ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ ላይ ‘ኩሳንኩስ’ የሚል ምእራፍ አለ። ቁሶችን በመውሰድ ሻሽ፡ በር፡ ምናምን ተካተዋል። ቁሶች ውስጥ የሰዎች ልፋት፡ ሀሳብና ፍላጎት፡ ፍቅርም ሊሆን ይችላል አለ። ነገሮችን በመውሰድ እዛ ውስጥ የተቀበረውን ሰብአዊ ስሜት በማውጣት ሊሰራበት ይችላል። እና ቁሶችን አላገልም። ግኡዝ ናችው፡ መዘመር አይችሉም፡ ድርሰት መጻፍ አይችሉም፡ ማፍቀር አይችሉም፡ መጥላት አይችሉም በሚል አላርቃቸውም። ምክኒያቱም ቁሶች ውስጥ ሰዎች አሉ።

ጥያቄ 3

በብዙ ስራዎችህ ውስጥ ልጆች ልዩ ስፍራ አላቸው። ምናልባት ይሄ ነገር ለብዙ አመታት ከሀገርህ ርቀህ በመኖርህ የሚሰማህን የልጅነት ናፍቆት መግለጫ ይሆን? ከሀገርህ ውጪ መኖርህ በድርሰቶችህ ላይ ምን ያሳደረው ተጽእኖ አለ?

አ.ረ.

ከሀገር መራቅ ስለሚባለው ነገር የሚሰሙኝ ስሜቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን እዚህ በምኖርበት ወቅት የሰበሰብኩት መረጃ አለ። የምኖረው አዲስ አበባ ውስጥ ነበር። እና contained space እና social interaction ያለበት ነው። በቀላሉ ልረዳው የምችል አካባቢ ነው። ስለዚህ የዚህን መረጃ ይዤ ነው የሄድኩት።

ብዙ ታሪኮቼ አዲስ አበባ አካባቢ ናቸው። የከተማ ታሪኮች (Town Stories) ናችው። እዛ ከሄድኩ በኋላ ትውስታዬ አለ።እዚህም በምኖርበት ወቅት በባህሪዬ ብዙ አልቀላቀልም።

ነገሮችን ማየት እወዳለሁ። ጥሩ ሲኒማ ካየሁ፡ ክጓደኞቼም ጋር ብሆን፡ ቁጭ ብለን ቡና ስንጣጣ ለሁለት ለሶስት ስአታት ያህል ላልናገር እችላለሁ። ስለሚያውቁ ‘በቃ አሁን ተደብሯል ዝም በሉት’ ይላሉ። ያኔ ነገሮችን በጥልቀት አስተውል ነነር። ያ ጠቅሞኛል። እዛ ከሄድኩ በኋላ ዝርዝሮችን አስታውሳለሁ። እነዛ ዝርዝሮችን cherish አደርጋለሁ። አይጠቅሙም ብዬ አልጥላቸውም። ከተለያየ ክብር ካለው ነገር ጋር፡ ከገንዘብ ጋር ግንኙነት ስሌላቸው ነገሮችን አልንቃቸውም። I keep them. Because they keep you alive in a way. ምክኒያቱም ስታልፍ ስትቀመጥ ተመልሰህ የምታያቸው ነገሮች ናቸው።

ሌላኛው በልጅነቴ ጥሩ ገዜ ነበረኝ። ምናልባት የልጅነት ግዜ ሁልጊዜም ጥሩ ነው ሊባል ይችላል። የልጅነት ጊዜዬን በደንብ አስታውሳለሁ። ደስተኛ ነበርኩ። በጣም ተጫውቼአለሁ። እነዛ ነገሮች They keep you spiritually fit and healthy. ትንሽ መረር ሲልህ የድሮ ሾርባ ትጠጣለህ። ሃሃሃሃ

ጥያቄ 4

በብዙ ታሪኮችህ ውስጥ የምትስላቸው ገጸ ባህሪያት ከማህበረሰቡ የተገፉ፡ ወይም የተገለሉ፡ በራሳቸው ሀሳብ የሚብሰለሰሉና በጥልቀት የሚታዘቡ፡ ናቸው። በነዚህ ገጸ ባህሪያት አማካኝነት በማሕበረሰቡ ላይ ለማቅረብ የምትፈልገው ትችት አለ?

አ.ረ

ስጽፍ ያለውን፡ ያየሁትን ነገር ነው የምጽፈው። ምንም አልለፋም። ዝርዝሩን ለማየት አይኔ እስካየ ድረስ አለም ግልጽ ሆኖ ነው የሚታየኝ። ምንም የሚያስጨንቀኝ ነገር የለም። በምጽፍበት ወቅት ideology ወይም አድልኦ ይዤ አይደለም የምጽፈው። እኔ አለምን ለማየት ዝግጁ ነኝ። ስለዚህ ግልጽ ይሆንልኛል። አጣርቼ የማስገባበት ወንፊት የለኝም። ያየሁትን ወደ ውስጤ ማስገባት እና መልሶ መስጠት ነው።. ያን ደግሞ አንተን ላስከፋህ ወይም ላናድድህ አይደለም። ምንም ነገር ይፋ የማድረግ ወይም የማጋለጥ ነገር አይደለም። ያለ ነገር ነው ስለዚህ ወረቀት ላይ መስፈር አለበት። ወግኜ ወይም እሴት መርጬ፡ ለአንድ ገጸ ባህርይ ላዳላ ብዬ፡ ወይም ከሆነ ወጥመድ ላውጣው ብዬ አልሰራም። አንዳንዴ እኔንም የሚያሳዝነኝ ነገር ይኖራል። ትዝ ካለህ ይጻፋል። የተለየ ብቃት ኖሮኝ ሳይሆን I am just being authentic. ከኔ የተሻለ የማስታወስ ችሎታ ያላቸው ይኖራሉ። ግን ላይጽፉት ይችላሉ። የማይጽፉበት ምክኒያት፡ ወይ ያሳፍራል፡ ወይ በሆነ መልክ ራሳችሁ ናችሁ ሊባሉ ይችላሉ። ያ አደጋ አለ። በመጻፍ ሂደት ውስጥ የመመስገን፡ የመደነቅ ወይም የመዋረድ attitude መያዝ የለብህም። ራቅ ብለህ የሚመጣውን መውሰድ አለብህ።

 

Filed in: Amharic