ለወንድሜ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
የአንተን ጽሁፍ ሀሳብ መነሻ አድርጌ፣ ‹‹ጀማል ማንስ ቢሆን?›› በሚል ርእስ ስር ያነሳሁትን ሀሳብ ተመርኩዘህ፣ የጻፍክልኝን ሶስት አብይ ጥያቄዎች የያዘ አጭር ጽሁፍ አነበብከት፡፡ የዚህ ጽሁፌም አነሳስ እነዚያን ጥያቄዎች ለመመለስ መሞከር ነው፡፡
1. የአንድን ሰው ማንነት ከባለቤቱ ውጭ ያለ ሰው ለእርሱ በሚመስለውና በሚፈልገው መንገድ ለመቀየር መብት አለውን?
በአጭሩ መብት የለውም፡፡ እኔም በቀደመው ጽሁፌ ያልኩት፣ ‹‹ዳንኤል ልብ እንድትልልኝ የምፈልገው፣ አንተ የጻፍከው እውነት አይደለም ማለቴ እንዳልሆነ ነው፤ እኔ የምለው፣ ‹እኔ እውነት ብዬ የተቀበልኩት (አንተ ሀሰት ነው ያልከው) ሀሰት ቢሆን እንኳን፣ አሁን ባለንበት ሁኔታ ከእውነቱ የበለጠ ዋጋ አለው›› ነው፡፡ ስለዚህ የእኔ ሀሳብ የተሰነዘረው ጉዳይ (ታሪኩ) ማህበረሰቡ ውስጥ ከሚያሳድረው ስለምንና ባለንበት ስሱ ሁኔታ ከሚያሳርፈው ተጽእኖ አንጻር እንጂ፣ የሰማእቱን ማንነት (ዜግነቱን፣ ጎሳውን፣ አስተዳደጉን፣ ሀይማኖቱን) በማስረጃ አስደግፌ፣ እውነት ውሸት ብዬ ለመከራከር አይደለም፤ በዚህ ጉዳይ ላይ እንኳን ለአደባባይ ሙግት፣ ለማኪያቶ ወግ የሚበቃ እውቀትም ሆነ መረጃ የለኝም፡፡
በዚህ ረገድ የእኔ ነጥብ፣ በዚህ ሀይማኖትን ተመርኩዞ በደረሰብን ጉዳት፣ ምንም እንኳን አይ.ኤስ ሙስሊሞችን ባይወክልም፣ የገዳዮቹ ሙስሊምነትና እራሳቸውን ትክክለኛ የእስልምና ተከታይ አድርጎ ማየት፣ ሙስሊም ገዳይ ክርስቲያን ተገዳይ የሚል ስሜት መፍጠሩ አይቀርም፡፡ አብዛኛው ህዝብ ደግሞ (የከተማውም ቢሆን) እንደእኔና እንዳንተ ባለቻናል ቲቪ የለውም፤ የኢንተርኔቱንም ተደራሽነት የምናየው ነው፡፡ እና የመጀመሪያው የጀማል ታሪክ ይህንን ሀሳብ የሚያፈርስ በመሆኑ ብዙዎችን አጽናንቷል፤ ቢያንስ በእኔና በዙሪያዬ ስላሉት ሰዎች ስሜት እማኝ ነኝ፡፡ ታሪኩ ፈጣራም ቢሆን እንኳ የፈጠረው በጎ መንፈስ ነው፡፡ እስቲ የጀማልን ኤፍሬምነት ከገለጥክበት ጽሁፍ ስር ያለውን አስተያየት አስተውል፤ በአብዛኛው ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች ወገን ለይተው የሚነታረኩበት ነው፡፡ እኔንም ጣልቃ ገብቼ ሀሳቤን እንድገልጥ ያደረገኝ የኸው ነው፡፡ የአንተም ሆነ የብዙዎች የሀሳብህ ተጋሪዎች ነጥብ፣ ‹‹እውነትና ታሪክ ለምን ይደበቅ?›› የሚል አስተያየት ነው፡፡ እኔ ይህ ድርጊት ከመቸው ታሪክ እንደሆነ፣ ከመቼው ተደብቆ የመቅረቱ አደጋ ሰዎችን እንዳሳሰበ ይገርመኛል፤ ጎበዝ ገና እኮ የሀዘን ድንኳን አልፈረሰም፡፡ ታሪክን የመዘገብ፣ ትላንታችንን ቆፍሮ እውነትን መግለጥ ለሚሻ፣ የሰው ዘር መገኛ፣ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት የሆነች ሀገራችን ያሏት የታሪክ መዛግብት ቢቆጠሩ፣ በክፍለ ዘመን አንድ ወይም ሁለት ቢደርሱ ነው፡፡ ወንድሜ ዳንኤል በዚህ የተነሳ ነው ህሊናዬ፤ ‹‹ታሪክ እንዳይቀበር . . .›› የሚለውን ምክንያት አልቀበል ያለኝ፡፡
ደግሞ እንዲህ በሀዘን ስሜት ውስጥ ተሁኖ የተጻፈ ታሪክ በስሜት የመበረዝ እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ይቅርታ አድርግልኝና ወንድሜ ዳንኤል፣ ከዚህኛው ጽሁፍህ ቀደም ብሎ፣ ‹‹ጎበዝ እየተስተዋለ እንጂ. . ›› በሚል፣ የጻፍከውን ጽሁፍ ከዚህኛው ሳስተያየው፣ ህሊናዬ ስሜታዊነትህን አግዝፎ፣ መረጃህን እንድጠራጠር ነግሮኛል፡፡ እስቲ ከቀደመው ጽሁፍህ ልጥቀስ፣
‹‹ . . . ከኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ጋር ጀማል የተባለ ሶማልያዊ ሙስሊም ክርሲቲያኖችን እረዳለሁ ብሎ፣ አብሮ ተሰውቷል የሚለውን መረጃ ለመቀበል ያስቸግራል፡፡ በመጀመሪያ ሶማልያውያንን ለጥያቄ አይቀርቧቸውም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ጓደኞቼን ትቼ አልሄድም ስላለ፣ ና አብረሀቸው ሂድ ብሎ አስተያየት የሚያደርግ ቡድን አይደለም፡፡ በሊላ በኩል ተጓዦቹ ሲያዙ የሊቢያ ወታደሮች እንደያዝዋቸው እንጂ፣ አይኤስኤስ መሆናቸውን የሚያውቁበት እድል የለም፡፡ የለበሱትም የወታደር ልብስ ነው፡፡ . . . .በዚህ ሁሉ ነገር ጀማል ኢትዮጵያዊ ክርስትያኖችን ለመርዳት እድል የሚያገኝበት መንገድ የለም፡፡ ቢፈልግ እንኳን፡፡ . . . . እንኳን ለመታረድ አብሮ ለመቆየት እድል የለውም፡፡…››
እንግዲህ ወንድሜ ዳንኤል አንተ፣ ስለአሸባሪው ቡድን ባህሪ፣ ስለአካባቢው ሁኔታ አገናዝበህ፣ ንባብና እውቀትክ ተጠቅመህ፣ የጀማልን እውነትነት መቀበል ያስቸግራል ያልከው አስቀድመህ፣ የኤፍሬምን መረጃ ከማምጣትህ በፊት ነው፡፡ በሁለቱ ፅሁፎች መካከል ያለው ልዩነት፣ የመጀመሪያውን ጥርጣሬህና ግምትህን ሁለተኛው ላይ ኤፍሬምን መረጃ አድርገህ ለማስረገጥ መሞከርህ ነው፡፡ በነገራችን ላይ አንድ ኤፍሬም የሚባል ሰማእት መኖሩ ከጀማል ጋር እንዴት እንደሚገናኝ አልገባኝም (ዝርዝሩን የሚቀጥለውን ጥያቅ ስመልስ እመለስበታለሁ)፡፡ እና ወንድሜ ዳንኤል እውነትን ለመግለጥ የሚለውን ሀሳብህን ያልተቀበልኩት በቀደመው የግል ትንታኔህና፣ እውነት ባልከው መካከል ምንም ልዩነት ባለመኖሩም ጭምር ነው፡፡
2. ያልነጠረና ውሸት የሆነ ታሪክን ለምን እናቆየዋለን? በዘመናችን ለምን አናጠራውም?
እውነት ነው ውሸትን ታሪክ ብሎ ማቆየት ይቅርና እውነት ብሎ መቀበል በጎ አይደለም፡፡ ግን በዚህ ጉዳይ ላይ እውነቱ ምንድነው? የቱ ነው?እሲቲ ጉዳዩን በተጠየቅ እንፈትሸው፡፡
መነሻው፣ ‹‹ጀማል የሚባል ሙስሊም የክርሲቲያኖችን መገደል ተቃውሞ አብሮ ሞተ›› የሚለው ነው፡፡ ማፍረሻ ተደርጎ የቀረበው ሀሳብ ጀማል የሚባል ሰው የለም፤ ጀማል የተባለው ኤፍሬም ነው የሚል ነው፡፡
ተጠየቅ 1፡ ኤፍሬም የሚባለው ኤርትራዊ ሰማእት እንደምን ከጀማል ጋር ሊያያዝ ቻለ? ይህ ሊሆን የሚችልበት መንገድ ሁለት ነው፡፡ አንድ፣ የኤፍሬም ፎቶ ጀማል ነው ተብሎ ተቀምጦ ከሆነ፡፡ ሁለት፡ ለጀማል የተሰጠው ታሪክ የኤፍሬም መሆኑ ከተረጋገጠ፡፡ ኤፍሬም ክርስቲያን ነው፤ ሰማእት የሆነው እንደሁሉም ሰዎች ክርስቲያን ስለሆነ እንጂ የሌሎቹን መገደል ተቃውሞ አይደለም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ታሪካቸው ስለማይመሳሰል ሁለተኛው ምክንያት ውድቅ ነው፡፡ ችግሩ የመጀመሪያው (የፎቶ መሳከር) ከሆነ ደግሞ፣ ይህ የሚያረጋግጠው ጀማል የተባለው ኤፍሬም መሆኑን፣ የሰማእታቱን ማንነት መለየት ላይ ችግር መፈጠሩን እንጂ፣ ጀማል የሚባል ሰው አለመኖሩን አያረጋግጥም፡፡ ስለዚህ በምንም መንገድ የኤፍሬም ማንነት መረጋገጥ የጀማልን አለመኖር አያረጋግጥም፡፡ በጀማል አለመኖር እርግጠኛ መሆን የሚቻለው የሰላሳውም ሰማእታት ማንነት ተለይቶ፣ ከመካከላቸው ጀማል የሚባል ሰው ከሌለ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ዲያቆን ዳንኤል ከጻፍከው ውስጥ እውነቱ የኤፋሬም መኖር ብቻ ነው፡፡ ገና ማንነታቸው ያልተረጋገጠ በርካታ ሰማእታት እያሉ ‹‹ጀማል የሚባል ሰው መኖሩ ውሸት ነው ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ ካልንም ከግምት ውጭ እውነት ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ ወንድሜ ዳንኤል፣‹‹ ያልነጠረ ውሸት የሆነ ታሪክ ለምን እናቆያለን?›› ብለህ ለጠየቅከኝ መልሴ፣ የጀማል ታሪክ መቶ በመቶ ውሸት መሆኑ የሚረጋገጠው ሁሉም ሰማእታት ተለይተው ሲታወቁ ብቻ ሆኖ ሳለ ለምን አሁን እርግጠኛ ሆነህ ትናገራለህ? ችኮላው ምንድነው? የኤፍሬም ማንነት ጊዜውን ጠብቆ እንደተገለጠው፣ ሁሉም እስኪረጋገጥ መጠበቅ አይሻልም? ይህ ግን የኤፍሬምን ማንነት ስለአበሰርከን ያለኝን አድናቆት አይቀንሰውም፡፡
3 .የኢትዮጵያውያን የሙስሊሞችና ክርሲቲያኖች የፍቅርና የመግባባት ታሪክ በውሸት ላይ ለምን ይመሰረታል? ሰብአዊነትን በእውነት ላይ እንጂ በውሸት ላይ ለምን እንመሰርተዋለን?
ለዚህ የምሰጠው መልስ አጭር ነው፤ ወንድሜ ዳንኤል የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችና ክርሲቲያኖች የፍቅርና የመግባባት ታሪክ ለምን በውሸት ላይ ይመሰረታል ያልከው፣ የሁለቱን ህዝቦች የአብሮነት ታሪክ ዛሬ ‹‹ሀ›› ብለም መሰረት ልንጥልለት የተዘጋጀን ያስመስለዋል፡፡ የሁለቱ ህዝቦች ታሪክ መሰረቱን ከጣለ አይደለም፣ ጣራውን አልብሶ ካጠናቀቀ ክፍለ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ አሁን የእኛ ትውልድ በዚያ የፍቅርና መተሳሰብ ቤት ውስጥ እየኖረ ነው፡፡ እና የጀማልን ትርክት ለኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችና ክርሲቲያኖች የፍቅርና የመግባባት ታሪክ መሰረት አድርጎ ማሰብ፣ ከልቤ ነው የምልህ፣ እንዳንተ ከፍተኛ የሀይማኖትና ታሪክ እውቀት ካለው ሰው የመጣ መሆኑ አስገርሞኛል፡፡
ሰብአዊነትን በእውነት ላይ እንጂ በውሸት ላይ ለምን እንመሰርተዋለን? ላልከው፣ የሰብአዊነት መሰረቱ እውነት ወይም ውሸት አይደለም፡፡ የሰብአዊነት መሰረቱ ሰው ሆኖ መፈጠር ብቻ ነው፡፡
እንደ ማስገንዘቢያ፤
የሰው ልጅ ነጻነት የመጨረሻው መገለጫ ኅሊና ነው፡፡
ወንድሜ ዳንኤል፣ እንዳነበብከው በአንባቢዎቻችን ከተሰጡት አስተያየቶች እጅግ የሚበዙት ወገናዊነትን መሰረት ያደረጉ፣ ስሜታዊነት የተንጸባረቀባቸው ናቸው፡፡ ይህንን አንተም ልብ ያልከው ይመስኛል፡፡ ለካ በጎሳ፣ በፓርቲ፣ በወንዝ ብቻ ሳይሆን፣ በሀሳብም እየተቧደንን ነው፡፡ ይህንን ዝም ብዬ ማለፍ አቃተኝና ነው እዚህ ላነሳው የወደድኩት፡፡
የሰው ልጅ ነጻነት የመጨረሻው መገለጫ ኅሊና ነው፡፡ የአንድ ሀገር ዜጎች፣ የአንድ ዘር ውላጆች፣ የአንድ እናትና አባት ልጆች ልንሆን እንችላለን፡፡ በመሆኑም የሀገሩ ህግ፣ የጎሳው ልማድና ደንብ፣ የምንከተለው ሀይማኖትና የቤተሰባችን የአስተዳደግ ሁኔታ በየደረጃው ሊጫነን ይችላል፤ በዚህ ሁሉ ተጽእኖ መሀል የተለየን ነጻ ሰብአዊ ፍጡር መሆናችንን የሚያረጋግጥልን ህሊናችን ነው፡፡ ህሊናችን ነገሮችን በራሳችን መንገድ እንድንመረምር ሙሉ ነጻነት ይሰጠናል፡፡ የአንድ ሰው ሀሳብ ከሀሳባችን ጋር ሲሰምር እንደግፈዋለን፤ ሲቃረን ደግሞ ሀሳቡን በሀሳብ እንሞግታለን፡፡ አለመታደል ሆኖ እኛ በዚህ በኩል ብዙ ይቀረናል፡፡ ብዙዎቻችን የጎሳችንንና የሀይማኖታችንን ተጽእኖ አልፈን ከህሊናችን የማሰብ ነጻነት ጋር አልተገናኘንም፡፡ አሁን እኔና አንተ ውይይት ላይ እንኳን ብትመለከት፣ እኔ ያንተን ሀሳብ ስላልተቀበልኩ፣ ሙስሊምና ፕሮቴስታንት መሆኔን እርግጠኛ ሆነው ሀሳባቸውን ሳይሆን ስድባቸውን የገለጹ አሉ፡፡ የአንተንም ሃሳብ ከእስልምና ጥላቻ ጋር አያይዘው ዘለፋ የጻፉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ለምን እንዲህ አደረጉ ማለት አይቻልም፤ ይህ በሁለት ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ አንደኛው፣ ሀሳቡ ካንተ ወይም ከእኔ ሀሳብ የሰመረለት ሰው፣ ለሚቃረኑት ሀሳቦች የሚያቀርበው ስድብና ማንቋሸሽ ነው፡፡ ይህ ሰው የማያውቀው የሌላን ሰው ሀሳብን ማክበርንና ሀሳብ ላይ መሟገትን ነው፡፡ ገዢዎቹ በአንባገነንነት፣ ማህበረሰቡና ቤተሰቡ በ‹‹ተው! ይህን አታድርግ›› ሲሰድቡትና ሲያበሻቅጡት አሳድገውታልና እሱም ከሀሳብህ ተሻግሮ አንተን ይሰድብና ያበሻቅጥሀል፡፡ ይሁን እንጂ እንዲህ አይነቱ ሰው የራሱ ሀሳብ አለው፤ የቸገረው ተግባቦቱ ነው፡፡ ሁለተኛው አይነት ሰው የራሱ ሀሳብ የለውም፤ የሚያስበው እንደአንድ ነጻ ሰብአዊ ፍጡር ሳይሆን፣ በቡድን ነው፡፡ እንደ እንድ ሀገር ዜጋ፣ እንደእንድ ጎሳ አባል፣ እንደአንድ ፓርቲ አባል፣ እንደአንድ ሀይማኖት ተከታይ . . ወዘተ. ያስባል፡፡ እና በምንም መንገድ ከነዚህ ቡድኖች ፍላጎት ጋር የተቃረኑ ሀሳበችን አይቀበልም፤ እንዲያውም መደፍጠጥና ማጥፋትን ያስቀድማል፡፡ በዚህ የተነሳ ይህ ቀድሜ ከጠቀስኩት የበለጠ ለለውጥና መሻሻል እንቅፋት ይሆናል፡፡
የአንድ ማህበረሰብ ጥንካሬና እድገት ከግለሰባዊ ሰብአዊ ነጻነቱ ጋር እጅጉን የተቆራኘ ነው፡፡ የማሰብ ነጻነት ሁለንተናችንን የመመርመር ነጻነት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ብዙ የሚበጁና የማይበጁ ሀሳቦች ወደ አደባባይ ወጥተው ውይይት እንዲደረግባቸው እድል ይሰጣል፡፡ ያን ጊዜ በሰለጠነ መንገድ በሀሳብ ላይ የመወያየት ባህል ያዳበረ ማህበረሰብ፣ የሚበጀውን ሀሳብ እያዳበረ ያድጋል፤ በበጎ ይለወጣል፡፡ እንደእኛ ያለው የማሰብ ነጻነቱን ያላስከበረ፣ የመወያየት ባህሉን ያላዳበረው ደግሞ፣ አዲስ ሀሳብ ብቅ ባለ ቁጥር አሳቢውን ጭምር እየኮረኮመ ባለበት ይረግጣል፤ አንዳንዴም ይዘቅጣል፡፡ እኔ እዚህ ላይ የምለው ነገር ‹‹ሰው የለስላሳ ጠርሙስ ወይም፣ በአንድ ፋብሪካ የተመረተ የሸራ ጫማ አይደለም!›› ነው፡፡ ሰው ተመሳሳይ ሊሆን አይችልም፡፡ 80 (?) ሚሊየን ህዝብ በአንድ ወይም በሁለት ሀሳብ ላይ ይስማማ ማለት እንዴት ይቻላል? ማንም ማንንም ‹‹እንዲህ አስብ›› ሊለው አይችልም፡፡ ፈጣሪም እኮ አላደረገውም! አዳምና ሄዋንን ሲፈጥርና ‹‹አትብሉ›› ሲላቸው እንኳ ትእዛዙን እስከመጣስ የሚያደርስ ህሊናዊ ነጻነት ነበራቸው፡፡ አይገርምም! እና እባካችን ሀሳብ ላይ የመወያየት ባህላችንን እናዳብር፡፡
ቸር እንሰንብት!