>
7:27 am - Tuesday July 5, 2022

አርብን በቂሊንጦ [ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ]

አርብን በቂሊንጦ ከበፍቄ፣ ከአጥናፍ፣ ከተስፋለምና ከፍቅረማርያም ጋር
‹‹ሀሳብ ያለው ሰው ቢታሰርም፣ ሀሳቡ ግን መቼም አይታሰር!››

zonenine6ከትናንት በስትያ ሰኔ 5 ቀን 2007 ዓ.ም፣ ከሰዓት በኋላ ከፍቃዱ በቀለ፣ ኢዩኤል ፍስሐና ንዋይ ገበየሁ ጋር በእስር ላይ የሚገኙ ጓደኞቻችንንና ወዳጆቻችንን ለመጠየቅ ወደቂሊንጦ እስር ቤት አምርተን ነበር፡፡ ከቃሊቲ መነሃሪያ ወደ ቂሊንጦ በሚያመራው ታክሲ ውስጥ የድምጻዊ ጸጋዬ እሸቱ ‹‹ሰንደቅ ዓላማ …›› የሚለውን ሞቅ ያለ ጥዑም ዜማ እያደመጥን፣ ብሎም አብረን እያንጎራጎርን ተጓዝን፡፡ በቂሊንጦም ያው የተለመደው ፍተሻን አለፍን፡፡ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለም ያለባትን እና የምወዳት ስከርፌ ግን ወደውስጥ መግባት አትችልም ተብላ ከአንገቴ ላይ ወልቃ በር ላይ መንጠልጠል ግድ ሆኖባታል፡፡ ከዚሀ ቀደምም መሰል ነገር ደርሶባታል፣ አሁንም ድረስ ‹‹ለምን?›› ለሚለው ጥያቄዬ ግን ‹‹አይቻልም›› ከማለት ውጪ አንዱም ፖሊስ በቂ መልስ ሰጥቶኝ አያውቅም፡፡ አንዳንድ አሰራራቸው ይገርመኛለል፡፡
…ከጓደኞቼ ጋር ተከፋፍለን ወደተለያዩ ዞኖች ዘለቅን፡፡ እኔ ዞን 2 ደርሼ፣ ጦማሪና ጋዜጠኛ በፍቃዱ ኃይሉን፣ ጦማሪ አጥናፍ ብርሃኔን፣ ጋዜጠኛ እና አብሮ አደጌን ተስፋለም ወልደየስን፣ እንዲሁም የሰማያዊ ፓርቲ ወጣት ልጅ የነበረውና ‹‹ወደኤርትራ ሲሄዱ ድንበር ላይ ተያዙ›› ከተባሉት ሶስት ልጆች መካከል አንዱ የሆነውን ፍቅረማርያም አስማማውን አስጠራኋቸው፡፡ ትንሽ ቆዩብኝ፡፡ በህዳር ወር እኔም እዚህ ታስሬ በነበረበት ወቅት የምጠየቅበት ቦታ ላይ ቆሜ በሀሳብ ነጎድኩ፡፡
…ተስፍሽ፣ በፍቄና አጥናፍ መጡ፡፡ በፈገግታ የታጀበ ሰላምታ ተለዋወጥንና ለማውራት የሚያመች ቦታ መርጠን ወጋችንን በእኔ ክስ ተስፋለም ጀመረ – ‹‹የክስህ ጉዳይ ምን ደረጃ ላይ ደረሰ?›› በማለት፡፡ ‹‹ሰኔ 18 2007 ዓ.ም መከላከል ሳያስፈልጋችሁ በነጻ ተሰናበቱ ወይም ተከላከሉ›› የሚል ብይን ለመስጠት መቀጠሩን ነገርኩት፡፡ ከክሱ ጋር በተያያዘ አስቂኝ፣ አስገራሚና አሳዛኝ በሆኑ ነገሮች ላይ ሀሳቦች ካካፈልኳቸው በኋላ ወደእነሱ የክስ ሁኔታ አመራን፡፡ ከክሳቸው ጉዳይ እና እስከአሁን ከነበረው የፍርድ ሂደት በመነሳት በቀጣይ ሊሆን ስለሚችለው ነገር የየግላችንን ግምት እና (…ቆመሮችን) ሳንዘነጋ ተነጋገርን፡፡ ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝም በቅርቡ በአልጀዚራ የቴሌቭዥን ጣቢያ ላይ እነሱን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ላይም ትንሽ ሀሳቦች መለዋወጣችን አልቀረም- ፈገግ እያልን፡፡
የክሳቸውን ሂደት በተመለከተ፣ ተስፋለም ይበልጥ በማድመጥ ላይ አተኮረ፡፡ በፍቄ መልካም ነገርን አስቦ ሀሳቡን ሰዘነረ፡፡ አጥናፍ ለየት ያለ ሀሳቡን (በዚህ ጽሑፍ የማልገልጸውን) ተንተን አድርጎ አካፈለን፡፡ በእርግጥ ጥሩ እይታ ነበር፡፡ ነገር ግን፣ ሁላችንም በአንድ ነገር ላይ ዕምነት ነበረን – ከዚህ በኋላ ያለው የእስራቸው ጊዜ ጊዜ አጭር ሊሆን እንደሚችል፡፡ ማን ያውቃል፣ ተስፋውም ሆነ እምነቱ እውን ይሆን ይሆናል፤ የልብን እውነት እና መሻት የሚያይ ፈጣሪ አለና፡፡
ባለፈው ሳምንት መጠነኛ ህመም ገጥሞኝ መድሃኒት እየወሰድኩ ነበርና ድካም ስለነበረብኝ እኔ እና እነሱን የሚለየውን የሽቦ አጥር በእጄ ይዤ ነበር የማናግራቸው፡፡ አንድ ፖሊስ ግን ከኋላዬ መጣና ‹‹ሽቦውን ልቀቀው፤ ሽቦውን ይዞ ማነጋገር አይቻልም›› አለኝ፡፡ ደስ ይበለው ብዬ ለቀቁለት፡፡ በዚህ ዕለት ከጀርባ ወይም ጠያቂ መስለው ከጎን በመቆም የጠያቂና የተጠያቂን ሃሳብ የሚያዳምጡ ‹‹ከፊል አድምጦ አደሮች›› ባለመኖራቸውም ደስ ብሎኛል፡፡
…ወደዘንድሮው የምርጫ ሁኔታ ወደመነጋገር ገባን፡፡ በታሰሩበት ክፍል ውስጥ ሆነው የምርጫ ክርክሩን በኢብኮ ከተከታተሉት አኳያ ያስተዋሉትን በየተራ ሀሳቦቻቸውን ሰዘነሩ፡፡ በምርጫ ዕለት የነበረውን የመምረጥ ሂደት ከታዘቢነቴ አኳያ የተመከከትኩትን፣ የታዘብኩትን …ወዘተ ነገርኳቸው፡፡ የአሸባሪውን አይ.ኤስ.አይ.ኤስን ድርጊት በመቃመው በመስቀል አደባባይ የተጠራውን ሰልፍ ተከትሎ ‹‹ብጥብጥ አስነስታችኋል›› በሚል ስለታሰሩት፣ ስለተፈረደባቸውና ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት እየተከታተሉ ስለሚገኙ ወጣቶች በጋራ አወጋን፡፡
ምርጫ ቦርድ የፓርላማ 442 መቀመጫዎችን ኢህአዴግ 100% ማሸነፉን ይፋ ካደረገበት ነገር በመነሳት ሰፋ ያለ ውይይት እና መጠነኛ ክርክር አደረግን፡፡ የሀሳብ ልውውጡ በጣም መሳጭ ነበር፡፡በዚህ ወቅት እስር ቤት መሆኔን ፍጹም ዘንግቼው ነበር – የሀሳብ ፍሰቱ አስደሳች በመሆኑ፡፡ [በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከጋዜጠኛ እስከንድር ነጋ፣ ጠበቃ ተማም አባቡልጉ፣ የቅርብ ጓደኛዬ አናንያ ሶሪ …ጋር ብዙ ጊዜ ስንወያይ ከጊዜ ቅንፍ ውስጥ ወጥተን መሰል ተመስጧዊ የሀሳብ ፍሰት ውስጥ እንገባለን፤ በተለይ አናንያ እኔ ጋር ሲያድር ውይይታችን ሳይቋጭ የንጋት ወፎችን ድምጽ ለመስማት እንቃረብ ነበር]
በውይይቶች መካከል ተስፋለም ጣልቃ እየገባ የሚያነሳው ጠንካራ ጥያቄ፣ አጥናፍና በፍቴ ሀሳባቸውን ለማስረዳት እና ለጥያቄዎች መልሶቻቸውን ለመስጠት እጃቸውን በመጠቀም ጭምር ያደርጉት የነበረው እንቅስቃሴ ውስጤ ቀርቷል፡፡ እኔና በፍቄ በ‹‹ዕንቁ›› መጽሔት ኤዲቶሪያል ስብሰባዎች ላይ ከባልደረቦቻችን ጋር የምናደርጋቸውን የሀሳብ ልውውጦችና ክርክሮች አስታወሰኝ፡፡ ተስፋለምም ቢሆን በ‹‹አዲስ ነገር›› ጋዜጣ ኤዲቶሪያል ላይ የሚያደርገው ነገር ነው ብዬ አሰብኩ፡፡ ሶስቱም ቆመው ሀሳቦቻውን በሚገልጹበት ወቅት ትከሻ እና አንገታቸውን በእጆቻቸው ተቃቅፈው ነበር፡፡
ተስፋለምም ከዚህ ንግግሩን ቀጠል አድርጎ ስለኢትዮጵያ ፕሬስ የግሉን ሀሳብ ሰነዘረ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ዴሞክራሲ እውን እንዳይሆን አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የራሳቸውን ጠጠር ስለሚጥሉት የህትመት እና የኤሌክትርኒክስ ሚዲያዎችም አንስተን በጥቂቱ ተነጋግረናል፡፡ ተስፋለምም ‹‹ይሄ ቀን ሲያልፍ ብዙ የምንናገረው ነገር አለ፤ ሰው ማለት …›› በማለት ዞር ብሎ ጓደኞቹን ተመለከተ፡፡ በፍቄ እና አጥናፍም ፈገግ እያሉ በአዎንታ ራሳቸውን ነቀነቁ፡፡ ያዘኑበትን ሁነት እና ግለሰብም አልሸሸጉኝም፡፡ እኔም አልኩ፣ ‹‹የሚዲያ ሀሳባዊ ትግል የግድ ያስፈልገናል! ‹አካፋን አካፋ› ማለት ሳይቻል፣ ሥርዓቱን ፈርቶ እና የግል ምቾትን ብቻ ጠብቆ ማሽሞንሞንን መምረጥ በዚህች ውድ ሀገራችን ላይ ሀሳብን በነጻነት በመግለጽ መብት ላይ ለዓመታት ሲንከባለል ከመጣ ትልቅ ችግር በተጓዳኝ ሌላው ከባድ ቀንቃራ መፍጠር ነው፡፡ ደግሞም ተፈጥሯል፡፡ ስለዚህ…›› ተስፋለምም ‹‹አንተ እና አቤል ዓለማየሁ ‹ኢትዮጵያን ማን ይታደጋት?› የሚለውን ርዕስ ለመጽሐፋችሁ ሰጥታችሁ ነበር፡፡ ርዕሱ በሀሳቤ ይመጣል፡፡›› ካለ በኋላ ‹ኢትዮጵያን እንዴት ነው የምንታደጋት?› ሲል የተለመደ ጥያቄውን ሰዘነረ፡፡ ‹‹ዛሬ ላይ ባለኝ ግንዛቤ እና አረዳድ፣ ኢትዮጵያን አንቀው የያዟትን ዘርፈ ብዙ መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት ስለሀገሩ የሚያስብ እና የሚጨነቅ ማንኛውም ዜጋ በተሰማራበት የሙያ ዘርፍ/የሕይወት መስመር የበኩሉን ሚና በድፍረት መወጣት ሲጀምር …›› አልኩት፡፡
ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ ሥርዓታት አምባገነንነትም አንዱ የጨዋታችን ርዕስ መሆኑንም ቀጠለ፡፡ ከዚህ አኳያ በደርግ እና በኢህአዴግ ዙሪያ ሀሳቦች ተንሸራሸሩ፣ መጠነኛ ክርክሮችም ተስተናገዱ፡፡ ለውጥ ተፈጥሯዊ ሀቅ ነውና የነገዋን ኢትዮጵያን አስመልክቶም ወደፊት ተጉዘን በሀሳብ ቅኝት ተስፋ እና ስጋቶች ላይ ሀሳቦች ተሰነዛዘርን፡፡ ዋው! የሀሳብ ውይይቱ እና ክርክሩ በጣም ደስስስ ይል ነበር፡፡ [በግሌ ሰላማዊ እና መከባበር ላይ የተመሰረተ (ከማያስከብር፣ እኔም ከማላከብረው ስድብ የራቀ) መሰል ሃሳባዊ ውይይት እና ክርክር በጣም እወዳለሁ]
ብቻ ዛሬ በእስር ላይ የሚገኙ ወጣት ጦማሪያን እና ጋዜጠኞች ለዛሬዋም ሆነ ነገዋ ኢትዮጵያ አስፈላጊ ልጆች ናቸው፡፡ [ይህ ጽሑፍ እነሱ ላይ ስላተኮረ እንጂ ሌሎች በእስር ላይ የሚገኙ የህሊና እስረኞች፣ እንዲሁም በእስር ላይ የማይገኙ፣ ለሀገር ቅን ሀሳቢ የሆኑ ዜጎች በሙሉ ለዛሬዋ እና ለነገዋ ኢትዮጵያ ወሳኝ መሆናቸውም ግንዛቤ ውስጥ ይግባልኝ]
በቂሊንጦ የጠያቂ እና የተጠያቂ ሰዓት ከመጠናቀቁ 15 ደቂቃ ቀደም ብሎ ፍቅረማርያም አስማማው እኛ ወዳለንበት ቦታ መጥቶ ያ እውነተኛ ፈገግታውን እያሳየኝ በሽቦ መካከል እጆቻችንን አሾልከን ተጨባበጥን፤ ሰላምታ ተለዋወጥን፡፡ አራዳ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት ተያይተን ስለነበር እሱን በማስታውስ ትንሽ አወጋን፡፡ ‹‹በዚያን ቀን ስለመጣችሁ ደስ ብሎኝ ነበር›› አለኝ፡፡ ‹‹ያው እስካለን ድረስ የፍርድ ቤት ዘገባዎችን መዘገብ ከእኛ ይጠበቃል›› አልኩት፡፡ አራቱም ጎን ለጎን ሆነው ተቃቅፈዋል፡፡ ሳያቸው ደስ ይላሉ፡፡ ያው በዚህ ጽሑፍ ላይ ባልጠቅሰውም ተስፋለም ፍቅረማርያምን አስመልክቶ አንድ ነገር አለኝና ጥያቄ መሰል ሀሳቡን ሰነዘረልኝ፡፡ እኔም መለስኩለት፡፡ በዚህ ሁሉ መካከል ሳቅ እያልን ተረብ ጣል ጣል እንደራረግ ነበር፡፡ በፍቄ ከመጣ ጀምሮ በቀኝ እጁ መዳፍ ላይ በእስክሪብቶ የምታምር አበባ ስሎ አይቸው ነበር፡፡ ልጠይቀው ብዬ በሀሳብ ውይይት ምክንያት ስረሳው ቆየሁ፡፡ በመጨረሻም ‹‹በፍቄ ፍቅር ያዘህ እንዴ፣ መዳፍህ ላይ የሳልካት አበባ ምንድን ነች?›› አልኩት፡፡ ሁሉም ሳቁ፡፡ አጠቃላይ እስርን፣ የፍቅር ህይወትን፣ ትዳርን፣ ልጅ መውለድን አስመልክቶ በእስር ቤት ከሰዎች የተማረውን እና በአንዷለም አራጌ ‹‹ያልተሄደበት መንገድ›› በተሰኘ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ ያነበበውን ጠቅሶ ዘርዘር በማድረግ ነገረንና የታሰሩበት አንደኛ ዓመት ሲሆን ባዘጋጇት የምስጋና ፖስት ካርድ ላይ የሰፈረችዋን ትንሽ አበባ በማስታወስ ከተስፈኝነት ስሜቱ በመነሳት በምልክትነት በመዳፉ ላይ እንደሳላት አስረዳኝ፡፡ አጥናፍም ‹‹በፍቄ ስዕል መሳል ይወዳል›› አለኝ፡፡
‹‹የሰውን ጠይቀህማ አትሄድም፤ የአንተስ የፍቅር ህይወት …›› ሲል ተስፋለም እየሳቀ ጥያቄ ወረወረ፡፡ ሌሎቹም ‹‹የተስፋለም ጥያቄ ትክክል ነው›› አሉ፡፡ በአጭሩ ነገረኳቸው፡፡ ፍቅረማርያም የሚያውቀው ነገር በመሆኑ እያየኝ ሳቅ አለ፡፡ እየሳኩኝም ‹‹የቀረውን ፍቅረ ይነግራችኋል›› አልኳቸው፡፡
‹‹የመጠያየቅ ሰዓት አበቃ›› የሚለው የፖሊሶች ድምጽ በድንገት ተሰማ፡፡ ‹‹በቃ ጨርሱ›› እያሉ የመጠየቂያ እንጨቶችን እየደበደቡ (ድምጹ እንዲሰማ) ተጠያቂና ጠያቂን ማለያየት ጀመሩ፡፡ ሁሉም ‹‹ለሚያውቁን እና ስለእኛ ለሚያስቡት በሙሉ ሰላም በልልን›› አሉኝ፡፡ እኔም ‹‹እሺ፣ አይዟችሁ›› ብዬ ተሰናብትኳቸው፡፡ ተስፋለም ከሄደ በኋላ ድምጹን ከፍ አድርጎ ጠርቶኝ ‹‹ህመምህን አስታም፤ ውሃም ጠጣ›› አለኝ፡፡ ‹‹እሺ›› ብዬ በፈገግታ ከመጠየቂያው ግቢ ወጣሁ፡፡ ‹‹ሀሳብ ያለው ሰው ቢታሰርም፣ ሀሳቡ ግን መቼም አይታሰር!›› በማለት ለውስጤ ነገርኩት፡፡ እነዚህ ወጣት ልጆች ለሀገር የሚጠቅም ብዙ ሀሳቦች አሏቸው፡፡ አካላቸው ቢታሰርም ሀሳቦቻቸውንና አርቆ ዓላሚነታቸውን ማንም ሊነጥቃቸው አይችልም! የጊዜ ጉዳይ እንጂ ከእስር ተፈትተው በሚወዱት የሙያ እና የህይወት መስመር ላይ ዳግም ተሰማርተው እንደምናያቸው ልቤ ያምናል፡፡ ሁሉም ባሉበት ቦታ ላይ ግን ፈጣሪ ዘወትር ይጠብቃቸው፣ ብርታትትና ጥንካሬውን ይስጣቸው ዘንድ ትልቁ መሻቴ ነው፡፡ ሌላ ምን ልበል?
ከፍቃዱ በቀለ፣ ኢዩኤል ፍስሐና ንዋይ ገበየሁ ጋርም አብረን እንደመጣን አብረን ወደመሃል ከተማ ተመለስን፡፡
እንግዲህ በተወዳጁ እና በአንጋፋ የኦሮምኛ ዘፈን አቀንቃኝ አሊ ቢራ የቀደምት ጥዑም ዜማዎቹን በማድመጥ ‹‹አረማ ቦሩ ..ቦሩ ቦሩ›› የጀመርኳትን ጽሑፉ በጎሳዬ ተስፋዬ ‹‹እማማዬ …ኢትዮጵያዬ …›› በሚለው ዜማ አጠናቅቄ እንዲህ አስነበብኳችሁ፡፡
መልካም እሁድ!

Filed in: Amharic