>
4:53 pm - Tuesday May 25, 2184

የድርቁ ተፅኖ ሲበረታ የት ደርሰው ይሆን? [እሳቱ ሰ]

(ከዚህ በታች የቀረበው ታሪክ ከሥነ-ጹሑፋዊ ማስተካከያዎች በስተቀር እውነተኛ ገጠመኝ ነው፡፡ ድርቅ በአገራችን ሰማይ ማንዣበብ እንደጀመረ መጋቢት 2007 ዓ.ም ላይ ገጠመኙን አጋርቻችሁ ነበር፡፡ በወቅቱ ላላነበባችሁት ‪#‎EthiopiaFamine‬ ‪#‎ክፉ_ቀን‬ ዘመቻን ምክንያት በማድረግ በድጋሜ ተለጥፏል፡፡ እነዚህ ባለታሪኮች የድርቁ ተፅኖ ሲበረታ የት ደርሰው ይሆን?)

መጋቢት 12/2007ዓ.ም ጠዋት፤
ባህር ዳር መንገድ ዳር ካለ ካፌ በረንዳ ላይ ከጓደኛየ ጋር ተቀምጠናል፡፡ በሰፊው መንገድ ላይ ባጃጆች ይርመሰመሳሉ፡፡ ሰው በቀኝና በእግራ ይዋከባል፡፡ ይሮጣል፡፡ ሙቀቱ ከደቂቃ ደቂቃ ይጨምራል፡፡ ከጓደኛየ ጋር የልብ የልባችን እያወጋን እያለ አንድ ህፃን ቀኝ እጇን ለልመና ዘርግታ ወደኛ በመቅረብ፡-
“ሰለ ሚካኤል” አለችን፡፡ የሁለታችንም ዓይን ልጅቱ ላይ አረፈ፡፡ ወደ ጥቁርነት ያደላ ሽብሽቦ ለብሳለች፡፡ ትልልቅ ክብ ክብ የብረት የጀሮ ጉትቻዎች አንጠልጥላለች፡፡ በመሃል አናቷ ላይ ወደ ታች የሚወርድ ቁንጮ ተሰርታ ሌላውን ተላጭታዋለች፡፡ ፊቷ በነፋስ የተመታ ቢሆንም ቁንጅናዋን አልሸፈነውም፡፡ የምታሳዝን ቆንጅየ ልጅ ናት፡፡
“ነይ እስቲ ” አላት ጓደኛየ፡፡ እጇን አፏ ላይ ጭና በፍርሃት ተጠጋችን፡፡ ጓደኛየ ያዋራት ጀመር፡፡
“ማነው ስምሽ?”
“ብርቄ”
“ስንት ዓመትሽ ነው?”
“ሰባት”
“ምን ሁነሽ ነው ምትለምኝው?”
“ርሃብ ገብቶ” የልጅቱ ዓይኖች እንባ ሲቋጥሩ አስተዋልሁ፡፡ ዓይኗን ለማየት ድፍረት አጣሁ፡፡ ከጠረጴዛው ላይ የሻይ ማንኪያ አንስቸ የጠጣሁበትን ብርጭቆ መደብደብ ጀመርሁ፡፡ አዎ! በዋግ ኸምራ በተከሰተው ርሃብ ሕዝቡ ልመና መውጣቱን አውቃለሁ፡፡ ገና ልጅቱን ሳያት ከዚያ አካባቢ እንደሆነች ገምቸ ነበር፡፡ ጓደኛየ ማዋራቱን ቀጠለ፡፡
“የት ነው ርሃብ የገባ?”
“ከኛገር ሰቆጣ”
“ከማን ጋር መጥተሽ ነው? የት ነው ያላችሁ?”
“ከዘመዶቸ ጋር መጥቸ፡፡ እናቴም አለች አባይ ማዶ፡፡”
“ምንድን ነው ምትለምኝ? ብር ነው ሚበላ?”
“የተገኘውን! ግን ብር ቢሆን . . .”
በእጀ የያዝኋትን የአንድ ብር ሳንቲም ሰጠኋት፡፡ ፈገግ አለች፡፡ ጓደኛየ ወደ ኪሱ ገብቶ አስር ብር ሲሰጣት ደስታዋ ለማመስገን እንኳን አላስቻላትም፡፡ በፍጥነት ከእጁ ነጥቃ ከፊታችን ተሰወረች፡፡ የምንቀማት ሁሉ ሳይመስላት አልቀረም፡፡ ለደቂቃዎች ጓደኛየ ጋር ሳንነጋገር በዝምታ ቆየን፡፡ በልቤ የጥላሁንን ዘፈን እዘፍናለሁ፡፡
ዋይ ዋይ ዋይ ሲሉ
የርሃብን ጉንፋን ሲስሉ
እያዘንሁ በዓይኔ አይቸ
ምን ላድርግ አለፍኋቸው ትቸ
“አይገርምም ግን?” አለኝ ጓደኛየ ድንገት፡፡
“ያሳዝናል፡፡” በማለት መለስሁለት፡፡ እንደገና ዝምታ በመካከላችን ሰፈነ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ግን የሄደችውን ልጅ የመሰሉ ሁለት ወንድ፣አራት ሴት ልጆች ሁለቱ ሕፃናት ያዘሉ ወደ ተቀመጥንበት ካፌ በመምጣት ለልመና ተበተኑ፡፡ ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ቆንጆዎች ናቸው፡፡ አካላቸውም በርሃብ የተጎዳ አይመስልም፡፡ ካፌ ተቀምጦ ኬኩን የሚገምጥ ሁሉ ልጆችን እየጠራ ያዋራቸዋል፣ ፎቶ ያነሳቸዋል፣ ብር ይሰጣቸዋል፣ ይሰድባቸዋል፣ ያባርራቸዋል . . .፡፡
ከዱር አንባ የፈሰሱ
ለአቅመ አዳም ያልደረሱ፤
ሁሉም ሕፃን-ልጆች ናቸው
ምንስ ሁኘ ምን ላርጋቸው፡፡
የካፌው ዘበኛ ለልመና የተሰማሩ ልጆችን አሯሩጦ ከካፌው አባረራቸው፡፡ ጓደኛየ ዘበኛውን ጠርቶ ለምን እንደሚያባርራቸው ጠየቀው፡፡
“ደንበኛውን እኮ አስመረሩት፡፡ ይሄው ቀኑን በሙሉ እነሱን ጥበቃ ተገትሬ ነው ምውለው፡፡ ሰውም ሰጥቶ እንደ መሸኘት ከፊቱ አቁሞ ወሬ አለመዳቸው፡፡ እነሱኳ ብዙም አይዳፈሩም፡፡” አለ ዘበኛው
“ቢሆንም አንተ ቀስ ብለህ ነው እንዲሄዱ መንገር ያለብህ፡፡ ተቸግረውኮ ነው እነሱም፡፡”
“እሱማ መቸ ጠፋኝ ግን ስራየ ሆኖ ተቸገርሁ እንጅ”
ከዘበኛው ጋር ንግግራችን ሳንጨርስ አንድ ሕፃን ያዘለች እናት ወደኛ ቀርባ በምልክት እጇን ከፍ ዝቅ በማድረግ ለመነችን፡፡ ጓደኛየ የላስቲኩን ወንበር ስቦ እንድትቀመጥ ጋበዛት፡፡ ፈራች፡፡ አንዴ እኔ ላይ-ሌላ ጊዜ ዘበኛው ላይ- ዞር ብላም በአካባቢው ዓይኖቿን አንቀዋለለች፡፡
“ነይ ተቀመጭ! አይዞሽ አትፍሪ!” አልኋት ሳላስበው፡፡ ቀሚሷን በእግሮቿ መካከል ሰብሰብ በማድረግ ተቀመጠች፡፡ ጓደኛየ አስተናጋጇን ጠርቶ ሻይና የሚበላ እንድታመጣላት ጠየቃት፡፡
“ሰቆጣ የት ነው የመጣችሁ?”
“ገጠሩን ነው?”
“አዎ! ምትኖሩበት የነበረው አካባቢ የት ነበር?”
ሁለት አሁን የማላስታውሳቸውን አካባቢዎች ጠራችልን፡፡
“አሁን እንዴት ነው ምትኖሩ? ብዙ ናችሁ ወደዚህ የመጣችሁ?”
“ገሚሱ አባይ ማዶ ነው ያሉት፡፡ ቤተስኪያን ነው የምናድረው፡፡ እኛ 17 ስላሴ ቤተስኪያ ነን፡፡ ሕፃኑም ልጁም ከተቆጠረማ ብዙ ነን፡፡”
“አንቺ ስንት ልጆች አሉሽ?”
“ሰባት፡፡ ወዲህ ከኔ ጋር የመጡት አራት ናቸው፡፡ ሌሎች አባታቸው ጋር ቀርተዋል”
“ድርቁ መቸ ነው የተከሰተው? እኛ በዜናም አልሰማንም?”
“መኸሩን አልዘነበም ነበር በደንብ፡፡”
“አሁን በየመንገዱ ስትለምኑ ሕዝቡ ምን ይላችኋል? መንግስትስ እርዳታ አላደረገላችሁም ወይ?”
ለደቂቃዎች ዝም ካለች በኋላ
“የጎጃም ምድር ደግ ነው፡፡ ሲቸግረን ሁሌም ምንመጣው ወደዚህ ነው፡፡ ሕዝቡም መልካም ነው፡፡ ግን. . .” ብላ ዝም አለች፡፡
“ግን ምን?” የሆነ ቅር ያላት ነገር አለ፡፡
“አሁን ሕዝቡ ሁሉም አንድ አይደለም፡፡ ብዙው ያዝንልሃል-ያለውን ይሰጥሃል፡፡ እናቶች ለልመና እያፈርንም ቢሆን እጃችን ስንዘረጋ ብዙው አያሳፍረንም፤ ይሰጠናል፡፡ ሴቶችም ልጆችን ስጡን እኛ እናስተምርላችሁ፡፡ እናሳድጋችሁ ይሉናል፡፡ እኛ ግን ለሚያልፍ ችግር ልጆቻችን አንሰጥም፡፡ አንዳንዱም ይሰድበናል፡፡ ለማኝ ይለናል፡፡” ብላ ትክዝ አለች፡፡
“ምን ብለው ነው ሚሰድቧችሁ?”
“ያው ከልመና ላያላቅቃችሁ ኢሃዲግን አመጣችሁብን፡፡ እናንተ ናችሁ ለዚህ ያበቃችኋቸው፡፡ አሁንም ተቸግራችሁ ሳይሆን እየሰለላችሁላቸው ነው ይለናል፡፡ መቸ የተራባችሁ ትመስላላችሁ፤ የመንግስት ቅጥረኛ ናችሁ-ይለናል፡፡ ብዙሃኑ ግን ደግ ነው-የለመኑትን አይከለክልም፡፡”
“መንግስትስ መጠለያ እና ምትመገቡት አላዘጋጀላችሁም፡፡”
“የለም፡፡”
በዚህ መሃል አስተናጋጇ ሻይና ቦንቦሊኖ ይዛ መጣችና ጠረጴዛው ላይ አስቀመጠች፡፡
“ያንች ነው ብይ” ሲላት ጓደኛየ ቦንቦሊኖውን ለሁለት ከፈለችና በጀርባዋ ላዘለችው ሕፃን ሰጠችው፡፡
“አንቺ ይሄን ብይ ለሱ ኬክ ታመጣለታለች፡፡” ብሎ ጓደኛየ ከአስተናጋጇ ጋር ተነጋገረ፡፡ ከተገመሰው ቦንቦሊኖ ጫፍ ቁርስ አርጋ ወደ አፏ ሰደደች፡፡ ሻይዋን አማስላ ጠጣች፡፡ ቦንቦሊኖውን ግን መብላት አልቻለችም፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ቆርሳ ወደ አፏ ያስገባችው አልዋጣት ብሎ ጉንጯ ላይ እየተንከባለለ ነው፡፡ ቀና እያለች በሃፍረት ታየናለች፡፡
“ቦንቦሊኖውን አልወደድሽውም?” አልኋት መጨነቆን አይቸ፡፡
“አይ. . .”
“እና ብያ አይዞሽ”
“እንዴው . . .” የሆነ ልትነግረን ወይም ልትጠይቀን የፈራችው ነገር እንዳለ ከሁኔታዋ ያሳውቃል፡፡ በጣም ተሳቀቀች፡፡
“ሌላ ምትፈልጊው ነገር ካለ ንገሪን፡፡ እኛን እንደወንድሞችሽ እይን፤ አትፍሪ፡፡” ጓደኛየ አደፋፈራት፡፡
“ይችን” አለች የተከፈለውን ቦንቦሊኖ አንስታ፡፡ ግራ ተጋባን፡፡
“እ” አልሁ እንድትናገር በምልክት እያሳየኋት፡፡
“ይችን . . . ለልጆቸ ልያዝላቸው . . . እኔ ይበቃኛል፡፡”
እዚህ ላይ – እናት – ከማለት ውጭ ምን ይባላል፡፡ የእናትነት አንጀት እንዲህ ነው፤ ለልጆቹ ሲል ሳይበላ የሚጠግብ፡፡ የእናትነት ጉሮሮ እንደዚህ ነው፤ ልጆቹን እያሰበ የጎረሰው የማይዋጥለት፡፡ ይች እናት ያን ሁሉ ጭንቅ ያሳለፈችው ይችን የቦንቦሊኖ ክፍይ እኔ ከምበላት ለልመና መንገድ ለወጡ ልጆቸ ላቃምሳቸው ብላ ለመናገር ነበር፡፡ በቀጭን ድምጿ አስተዛዝና የጠየቀችን ጥያቄ ጭንቅላቴ ውስጥ እየደጋገመ ያቃጭላል፡፡
“ይችን . . . ለልጆቸ ልያዝላቸው . . . እኔ ይበቃኛል፡፡”
. . . . . . .
በዚች ከንቱ ድልል አለም
መቸም ጠገብሁ የሚል የለም
የተገኘውን እንስጣቸው
ቸርነቱን አንንሳቸው፡፡

Filed in: Amharic