>
12:24 pm - Monday November 29, 2021

ውዳሴ በዕውቀቱ ሥዩም [በፈቃዱ ዘ ኃይሉ]

(በሕዝብ ጥያቄ ካለፈው የቀጠለ :-))

«እስክረታ ድረስ ካልታገልሁ፣ እስክታፈን ድረስ ካልተናገርኩ፤ የረባ ኑሮ ኖርሁ ማለት ይከብደኛል።» ~ በዕውቀቱ ሥዩም

book-design- Bewiketu Siyumየበዕውቀቱን ዝና ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ልመዝነው ሞከርኩ። መጽሐፉ ሊወጣ እንደሆነ ሲነገር ብዙ ሰው ተስገብግቦ፣ “በዕውቀቱ መጣልን” እያለ ክርስቶስ የመጣልን ያህል ደስታውን አወጀ። መጽሐፉ ገና ሳይነበብ የተወደደ መሰለኝ። በዕውቀቱ በከተሜው ዘንድ ሁነኛ ተወዳጅ፣ ዐዋቂ እና ታዋቂ መሆኑን እኔ ራሴው አንድ ምስክር ነኝ። አንዳንዴ ሲበዛ ተወዳጅ የሆኑ ሰዎችን እጠረጥራቸዋለሁ። በዕውቀቱ መስማት ያለብንን ሳይሆን መስማት የምንፈልገውን የሚነግረን (conformist) ይሆንን?

ይህንን ብዬ ሳልጨርስ መጽሐፉ ወጣ። እንደፈረመበት የተነገረኝ መጽሐፍ አውሮጵላን ተሳፍሮ አዲስ አበባ እስኪደርስ መጠበቅ ስላላስቻለኝ እዚሁ ገዝቼ አነበብኩት። እኔ አንብቤ ከመጨረሴ በፊት የዚህኛውም የዚያኛውም የዘውግ ብሔርተኞች በዕውቀቱ ሥዩም ላይ ጦርነት አወጁ። ይህ በዕውቀቱ conformist ይሆንን ለሚለው መልሴ ከፊል መልስ ሰጠኝ።

ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ አሁን ለማስታወስ የማልገደደው አንድ ፈላስፋ ይጠቅስና እንዲህ ይላል። «ፈላስፋው ያሳተመው መጽሐፍ በጣም ተወዳጅ ይሆንና አሳታሚው ይደሰታል። ለፈላስፋው ደውሎ ‘መጽሐፉ በጣም ስለተወደደ በገፍ እየተሸጠ ነው። ስለሆነም ድጋሚ ልናትመው ነው’ ሲለው፣ ፈላስፋው ደንግጦ ‘የቱጋ ነው የተሳሳትኩት?’ አለ።» ቁምነገሩ ብዙኃኑ አዲስ እና አፈንጋጭ ሐሳብ አይወድም፤ የሚወደው ‘የቆምክበት አቋም ትክክለኛ ነው’ እያለ የሚሸነግለውን ብቻ ነው የሚለው ነው። በዕውቀቱ ያንን ባለማድረጉ ወቃሹ በዛ።

በዕውቀቱን በconformistነት መጠርጠር ሀጢያት ይሆናል። እርግጥ በዕውቀቱ የብዙኃንን ቀልብ በቀልድ ለመግዛት መሞከሩ አይካድም። ነገር ግን የማይደፈሩ የሃይማኖት ግድግዳዎችን ለመነቅነቅ ሞክሮ ብዙ አወዛግቧል። ነገር ግን በዕውቀቱ አወዛጋቢ ዐሳቦቹ በቀልድ እየለወሰ ማቅረብ በመልመዱ ግልቡ አንባቢ እየሳቀ (ቡጢ ሳይሰነዝር) ሲያልፍለት፣ ቀሪው ቁምነገሩን ጨብጧል፤ ወትሮም ግልቡ ነው እኔ ያሰብኩትን ካላልክ ብሎ ቡጢ የሚጨብጥ። ይሁን እንጂ በ«ከአሜን ባሻገር» ላይ ከመጨረሻዎቹ ሁለት መጠጥፎች በስተቀር፣ ለማሳቅ ተብሎ የተጻፈ የለም። ግልቦቹ አንባቢዎቹ እስከዚያ ድረስ በትዕግስት ማንበብ ካልቻሉ መጨረሻውን አምሮታቸውን ሳይወጡ ይቀራሉ። በነገራችን ላይ ይህ መጽሐፍ ሪከርድ ይሰብራል ተብሎ (ሪፖርተር እና ፎርቹን ጋዜጣ) የተገመተው የቀልዶቹ አድናቂዎች ብዙ ይሸምታሉ በሚል ነው። እውነትም የመጀመሪያው 20ሺሕ ኮፒ በሁለት ቀኑ አዲስ አበባ ላይ አልቋል። መጽሐፉ የ‘መውጣትና መግባት’ን ወይም የ‘እንቅልፍ እና ዕድሜ’ን ያክል ሳቅ ባይይዝም፣ አወዛጋቢ ሐሳቦችን ይዟል። ይህ ፌስቡክ ላይ ከወዲሁ ይንፀባረቃል። ስለሆነም ግምቱ የመሳካት ዕድል ይኖረው ይሆናል።

ስንቀጥል፣ ውዳሴው ጥቅል ነውና በዕውቀቱ በቀልድ መጻሕፍቱም ውስጥ ሳይቀር የሚገርሙ ኀልዮቶችን እንዳኖረልን በምሳሌ እንመልከት፤

ምሳሌ ፩ – ባሕታዊው፣

‘መውጣትና መግባት’ ላይ አንድ የሃይማኖት አባት ይጠቀሳሉ። ባሕታዊው ‘አምላክ አንድ ነው’ እያሉ ሲያስተምሩ ንጉሡ ጠርቶ ‘አማልክት ብዙ ናቸው ይህንኑ ያስተምሩ’ አላቸውና አሻፈረኝ አሉ። ንጉሡ ምላሳቸውን አስቆረጣቸው። ከዐሥር ዓመት በኋላ አማልክት ብዙ መሆናቸውን ባሕታዊው ደረሱበት ይለንና፣ ‘ነገር ግን ምላሳቸውን ያጡለትን እምነት ላለመካድ በእምነታቸው ፀኑ’ ይለናል። ይሄንን በስንት የእውነተኛ ዓለም ትርክት ልንመነዝረው እንችላለን?

ምሳሌ ፪ – ዐፄ ዮሐንስ እና የመተማ ፍፃሜ

‘እንቅልፍና ዕድሜ’ የሰሙነ ምርጫ 97ን (በሀዲስ ዓለማየሁ ቋንቋ) ስርዓተ-ማኅበር በልቦለድ ቀርፆ አኑሮልናል። እዚያ ላይ አንድ ምሁር ገፀ ባሕርይ ስለዐፄ ዮሐንስ ፍፃሜ የሚሠራውን ጥናት አስታኮ ስለፍርሐት ይተርክልናል። አባቶቻችን በዐፄው መሰዋት ከሞት ጋር ሲተዋወቁ ሰው መሆን ጀመሩ። ፍርሐት የማያውቅ ሕዝብ ሥልጣኔን አይወልድም የሚል ኀልዮት ነው። በመሥመሮቹ መሐል የሚያነብ ከተገኘ መልዕክቱ ጥልቅ ነው። ይህንን ኀልዮቱን ደረጄ ዓለማየሁ የተባለ የ‘ያ ትውልድ ሰው’ ከ20 ዓመት በፊት “ዴሞክራሲ የፈሪዎች ናት’ ሙግት ጋር አመሳስለዋለሁ።

ምሳሌ ፫ – ክንፋም ሕልሞች

‘በራሪ ቅጠሎች’ በሚለው (ቀልድ ብዙም በማያወቁት) የበዕውቀቱ አጫጭር ልቦለዶች ስብስብ ውስጥ ‘ክንፋም ሕልሞች’ የምትል ከማንኩሳ ⇒ደብረማርቆስ ⇒አዲስ አበባ ⇒ሀገረ ማርያም ⇒ቨርጂንያ የሚከንፉ ደብዳቤዎች ስብስብ አለች። ደብዳቤዎቹ የሰው ልጅ መብረሪያ ክንፍ እንጂ ማረፊያ ጎጆ የለሌለው ወፍ መሆኑን የምታረዳ የጥበብ ሥራ ናት። ደብዳቤዋ አካባቢዬ በክንፋ አልባ በራሪ ሰዎች እንደተሞላ እንድታዘብ ታደርገኛለች። እዚያው ጥራዝ ላይ የኢትዮጵያውያን ጦረኝነት፣ ውጤት አልባ ጉባኤ ወዳድነት በቅጡ ተተርከዋል።

ወደአዲሱ መጽሐፉ እንመለስ። አዲሱን መጽሐፉን እንደጠበቅኩት አላገኘሁትም። ከአንድ እንደራሱ በዕውቀቱ ሊቅ ከሆነ ጓደኛዬ ጋር ስናወራ፣ ቅሬታዎቹን ቆጠረልኝ። ይሁን እንጂ ቅሬታዎቹ የሐቅ ግድፈት ላይ አልነበሩም። የኔም ቅሬታዎች ያው ናቸው። ጽሑፎቹ ሙሉ ለሙሉ አዲስ አለመሆናቸው፣ ጋዜጣ ላይ ያነበብናቸው እና ከመድረክ ላይ የሰማናቸው መሆናቸው ብዙ የጠበቅነውን አንሶብናል። ሐሳቦቹ እዚህም፣ እዚያም የሚረግጡ መሆናቸው አንድ ጉዳይ ላይ እንዳንረጋ አድርጎናል። ምናልባት ወደፊት አንድ ወጥ በሆነ ሥራ መጥቶ ይክሰን ይሆናል።

ሰሞኑን (በፊትም) የሚጻፉ ውዳሴ በዕውቀቱዎች በዕወቀቱን በእውቅ ሰው የመመሰል አባዜ ይታይባቸዋል። ዐብይ ተ/ማርያም ቀድሞ በክርስቶፈር ሂችንስ መስሎት ነበር። እኔ ራሴ ባለፈው ከቮልቴርና ትዌይን ጋር፣ ውብሸት የተባለ ፌስቡከኛ ከዐለቃ ገ/ሃና ጋር፣ እና ለሌሎችም ከሌሎች ጋር… መስለውታል። በድጋሚ ዐሳብ በዕውቀቱ በራሱ ምሉዕ ስብእና አዳብሯል እና በማንም የማይመሰል የራሱ ለዛ እና ቀለም ያለው ሰው ሆኗል ባይ ሆኛለሁ።

በዕውቀቱን የኔ-የኔ እያሉ በመሻማቱ ሒደትም ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እንዲህ ነው፣ የለም እንዲህ አይደለም የሚሉ ሙግቶችም አስተውያለሁ። ሙግቶቹ የሚያደንቁትን ሰው አስተሳሰቡ ከእኔ ብቻ ነው የሚገጥመው ከሚል ድርቅና የመነጨ ይመስለኛል። የዘውግ ብሔረተኞቹም በየፊናቸው ብስጭታቸውን ፌስቡክ ላይ መደበቅ ያቃታቸው በዚሁ በዕውቀቱን በራሳቸው ሰልፍ የማሰለፍ ምኞት አለመሳካት ሳቢያ ነው። የተቹት ሁሉ፣ ሐሳቡን በሱ ልክ ምንጭ እየጠቀሱ መሞገት መቻላቸውን መገመት ይከብደኛል።

በዕውቀቱ፣ በእኔ እምነት፣ ነፃ ዐሳቢ ሰው ነው። ስለዚህ እንኳን የእገሌ፣ ወይም የእገሌ ሊሆን “የራሱም አይደለ”።

Filed in: Amharic