>
5:33 pm - Thursday February 2, 2023

አይዞህ ...ተሜ [ነብዩ ሲራክ]

Temesgen Desalegn by Nebiyu Sirakየተባው ሾተል ብዕርህ ፣
አላላውስ ቢላቸው
የእንቢ ላገሬ ስሜትህ ፣
ነዲዱ ወላፈን ሲገርፋቸው
ሃገሬን አልቀም ማለትህ፣
እንቅልፍ ሰላም ቢነሳቸው
እውነትክን እውሸት ማለት ፣
ሰላማዊው ሙግትህ ቢያቅታቸው
“አሸበረ ” ብለው መረጃ ማቅረብ
ተሜን ማኮላሸቱ ቢገዳቸው
ብዕርክን ነውጠኛ ብለው አስገቡህ
መያዣ መጨበጫ ቢጠፋቸው !
ዳሩ ግና …
እጅና እግርን በካቴና እንደማሰር
ህሊናን ማሰር አይቀልም ፣ አይቻልም!

እናም …
አይዞህ ወዳጀ ፣
ቀን አያልፍም ፣ ያልፋል
የደፈረሰው ጠርቶ
የተሸፈነው ይገለጣል
የተንኳሰሰው ይነሳል
አንኳሳሽ የእጁን ያገኛል
ግፍ በግፍ ባይመለስም
ጨቋኝ በታሪክ ይወቀሳል
በሰፈረው ቁና ባይሰፈር
የውርድትን ካባ ይለብሳታል
የጊዜ ወቅት ጉዳይ እንጅ
ይህ አይቀርም ይፈጸማል
የጀግና እናት ካልመከነ
ይህ ይፈጸማል ይሆንማል!

ተሜ … አይዞህ …

የቀራንዮ ጉዞህ ቢያምም
የእማማን አንገት አስደፍቶ አይቀርም
“የኢትዮጵያን እናድን ” ጩኽትህ
“ለእኔ አታልቅሱ !” ቃልህ ይሰምራልም
“ለትንሳኤው ተሰማሩ !” ሰላማዊ ጥሪህ
ከወገንህ እዝነ ልቦና ተኖ አይጠፋም
ጊዜ እስኪያል ያልፋህ እንጅ
ተገፍቶ ተረግጦ መኖርህ አይዘልቅም
ስማኝ ተሜ! እውነቴ ነው የምለህ
የእማማ ጸሎት ምህላዋ አይከሽፍም
እስኪያልፍ መልፋትህ ዘልቆ ቢያምም
በቁጭት ቢያነደን ብንበግንም
ቀኑ ቅርብ ነው ይመጣል
የኢትዮጵያ ትንሳኤ እንደሁ አይቀርም !
አይዞህ ተሜ ቆፍጣናው
ኢትዮጵያ ሃገርህ ሰው አታጣም
እውነት እያደር ሲጠራ
የአርበኝነት ክብርን አታጣም !

ነቢዩ ሲራክ
መጋቢት 26 ቀን 2008 ዓም

( አንተ ጀግና እንኳን ተወለድከ ልልህ ከዚህ ቀደም የቋጠርኩልህን ስንኝ ለልደትህ መታሰቢያም ትሆን ዘንድ እነሆ ለጠፍኳት ! )

Filed in: Amharic