>

ቀዝቃዛው ገሞራ!... (ግማሽ ሰዓት - ከመቃብሩ ስር) [ኣንተነህ ይግዛው]

ገሞራው ተፈጸመ!…

ታላቁ ደራሲ፣ ገጣሚና ባለቃኔ ኃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው) በህመም ሲሰቃይ ቆይቶ አረፈ…


Gemoraw( Baleqine- Hailu GebreYohans )ለ40 አመታት ያህል በተለያዩ አገራት የስደት ህይወትን ሲገፋ የኖረው ገሞራው፣ በስዊድን ስቶክሆልም በሚገኝ ሆስፒታል ህክምና ሲደረግለት ቆይቶ፣ ጥቅምት 30 ቀን 2007 ዓ/ም ከዚህ አለም በሞት ተለየ…

“ሰው አይድን!…” ይላት ነበር ገሞራው – ስዊድንን ሲያሾፍባት…

እሷ ግን፣ ቀልድ አታውቅምና ማሾፉን ችላ ብላ፣ የምርም ስታሰቃየው ኖራ እማይድን ሰው መሆኑን አረጋገጠቺለት፣ ፈጸመቺው!…
.
ዛሬ ማለዳ…
ገሞራውን አሰብኩት…
እያሰብኩት፣ አንድ ወዳጄ ከሳምንታት በፊት የነገረኝ ነገር ትዝ አለኝ…

የገሞራው መቃብር አዲስ አበባ በሚገኘው እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ግቢ እንደሚገኝ ነግሮኝ ነበር…

ማየት ከፈለግኩም፣ ሊያሳየኝ የሚችል ሰው እንዳለ ጠቁሞኝ ነበር…

ዛሬ ማለዳ፣ የገሞራውን ማረፊያ ማየት ፈለግኩ…
.
.

ደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ቅጽር ግቢ ውስጥ…

ከደብሩ የእቃቤት ጠባቂና የመካነ መቃብር ተቆጣጣሪ ፊት ቆሚያለሁ…

“መምሬ ገብረ ዮሐንስ ሰንበቴ የሚያበሉባት የነበረቺዋን ቤት ቢያሳዩኝ ብዬ ነበር?…” ስል በትህትና ጠየቅኩት፡፡

ሰውዬው ባቀረብኩለት ጥያቄ አልተደናገረውም፡፡

ምክንያቱም የጠራሁለት ስም፣ ደብሩን ከመሰረቱት የሃይማኖት አባቶች አንዱ የሆኑትን፣ ዛሬም ድረስ ስማቸው የሚጠራውን፣ የደብሩ ታሪክ ሲነሳ አብረው የሚነሱትን፣ የሊቁን ካህን የመሪጌታ ገብረ ዮሐንስ ተሰማን ስም ነው፡፡

“ምን ፈለግህ?…” አለኝ፡፡

የባለቅኔውን መቃብር ለማየት እንደመጣሁ ነገርሁት፡፡

ሰውዬውን እየተከተልሁ፣ ከቤተ ክርስቲያኑ በስተጀርባ አመራሁ…

ከግቢው የምስራቃዊ የግቢ አጥር ተከልሎ የተቀለሰ አንድ ቤት ላይ ደረስን፡፡

የቤቱ በር በሰንሰለት ታስሮ፣ ባረጀ የጋን ቁልፍ ተዘግቷል፡፡

ቁልፉን ከፍቶ ጨለም ወዳለው ክፍል ጠቆመኝ…

ጭንቅ ጭንቅ እያለኝ፣ እየተርበተበትኩ፣ ፈራ ተባ እያልኩ፣ በቀስታ እየተራመድኩ ገባሁ…
.

ያውና ባለቅኔው!…
ያውና የቀዘቀዘው ገሞራ!…
ያውና!…

Gemoraw (Hailu Gebire Yohans)ዘመኑን ሙሉ ሲንከራተት የኖረው ሃይሉ ገብረ ዮሃንስ፣ የሲሚንቶ ምርጊት ተከናንቦ፣ ዝምታ ውስጥ ተዘግቷል!…

በ1935 ዓ.ም. ከአዲስ አበባው ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የጀመረች የሃይሉ ገብረ ዮሃንስ ህይወት፣ ከብዙ መንከራተት በኋላ ስቶክሆልም ውስጥ አብቅታ፣ የተነሳችበት ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ ተደምድማለች፡፡

የገሞራው የተማሪነት፣ የስደት፣ የባይተዋርነት፣ የመከፋት፣ የማመጽ፣ የመቀኘት፣ ብዙ ክፉና ደግ የማየት፣ ብዙ በጎና መጥፎ የመሆን ረጅም ጉዞ፣ እዚህች ጠባብ ክፍል ውስጥ፣ እዚያ የኮንክሪት ሳጥን ውስጥ ይቋጫል!…

“እኒህ እናቲቱ ናቸው!…” አለኝ ሰውዬው – ከገሞራው ዝቅ ብሎ የሚገኝ መቃብር እየጠቆመኝ፡፡

ወደጠቆመኝ ቦታ ዞርኩ፡፡
የባለቅኔ ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ (ገሞራው) እናት፣ ወ/ሮ አመለወርቅ ሀብተ ወልድ ያረፉበት መቃብር ነው፡፡ ከእናቲቱ አለፍ ብሎ ደግሞ፣ የታላቅ ወንድሙ የበትረ ገብረ ዮሐንስ መቃብር ይታያል፡፡
.

የገሞራውን ተንከራታች ህይወት እያሰብኩ ዝም አልኩ…

የቤተ ክህነት ተማሪነት፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪነት፣ የኮሌጅ ቀን ግጥም ኮከብነት፣ የስርዓት ተቃዋሚነት፣ የመምህርነት፣ የተሳዳጅነት፣ የተመራማሪነት፣ የሰው አገር ሰውነት፣ የታዋቂነት… የገሞራው የብዙ ነገርነት የመጨረሻው ምዕራፍ ይሄ ነው!…

“ታውቃቸው ኖሯል?…” የሚለው የሰውዬው ጥያቄ አባነነኝ፡፡

ባለቅኔውን በስራዎቹ እንጂ በአካል እንደማላውቀው ወይም ዝምድና እንደሌለን ነገርኩት፡፡

ለነገሩ እሱም ቀድሞ ሳይጠረጥር አልቀረም፡፡

እንደኔ ገሞራውን በስራዎቹ ከሚያውቁና ሊጎበኙት ከመጡ ጥቂት ሰዎች በስተቀር፣ ዘመድ አዝማድ ነኝ የሚል ሰው ወደመቃብር ቤቱ ዝር ብሎ እንደማያውቅ ነገረኝ፡፡

ገረመኝ!…

ተገርሜ ሳልጨርስ፣ ሌላ ገራሚ ነገር ጨመረልኝ…

“የቀብሩ እለት እንኳን፣ አስር ሰው አይሞላም የተገኘው!… እንደነገሩ ነው የቀበሩት… ከተቀበረ በኋላም ቢሆን… እንደወጉ ሃውልት ምረቃ፣ ሰልስልት፣ አርባ፣ ሰማኒያ የሚባል ነገር አልነበረም!…”

ቀና ብዬ አየሁት – እልፍ አድናቂ እያለው ያለ ለቀስተኛ ወደ መቃብሩ የገባውን ባይተዋሩን ገሞራውን!…

አሳዛኝ ፍጻሜው ልቤን ሰብሮት እያለ…

ሰውዬው ሌላ ልብ የሚሰብር ነገር ጨመረልኝ…

ገሞራው በስዊድን ህይወቱ ካለፈ በኋላ፣ ቤተሰቦቹ አስከሬኑን ወደ አገር ቤት አምጥተው ሊያስቀብሩት ሲሞክሩ፣ አስከሬኑን አታስገቡም ተብለው እንደተከለከሉ…

የታላቅ ወንድሙ የበትረ የልጅ ልጅ፣ ተስፋ ባለመቁረጥ አስከሬኑን ለማስገባት ለወራት መድከሟን…

በስተመጨረሻም…
አንዲት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን የሆነች ሴት፣ ባደረገችላት ከፍተኛ ርብርብ፣ አስከሬኑ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ መፈቀዱን…

በሬሳ ማድረቂያ ኬሚካል አማካይነት እንዲደርቅ ተደርጎ፣ በስዊድን ተቀምጦ የቆየው የገሞራው አስከሬን፣ ከሁለት ወራት ቆይታ በኋላ ወደ አገር ውስጥ ገብቶ፣ እዚህች ክፍል ውስጥ መቀበሩን ነገረኝ!…
.

የሚወዳት፣ ብዙ የተቆረቆረላት፣ የተቆጨላት፣ የተቀኘላት፣ የኔ የሚላት አገሩ፣ ዞሮ ዞሮ ሲመጣ፣ የኔ ልጅ ብላ ወግ አልተቀበለቺውም!

የአገሩ አፈር እትብቱን እንጂ ቀሪ አካላቱን ለመቀበል አልፈቀደም!

የገሞራው አስከሬን፣ ከአገሩ መሬት ሁለት ክንድ ያገኝ ዘንድ፣ ለወራት መጉላላት ነበረበት!

(እኛ!… በአስከሬን ቂም የምንይዝ ጉዶች!)
.
.

13 አመታት በፊት…

ገሞራው ከኢትኦጵ መጽሄት ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ እንዲህ ብሎ ነበር
.

“ከሃገሬ ከወጣሁ ጀምሮ ለሩብ ምዕተ ዓመት እዚህና እዚያ ስንከራተት የኖርኩበትን ፀሊም ህይወት በማስመልከት የፃፍኳት ‹ሞቼም እኖራለሁ› የምትል ትንግርተኛ ግጥም አለችኝ፡፡ ግጥሚቱን የፃፍኳት እዚህ ያለሁበት ሃገር ውስጥ፤ ሀገሬንና ወገኔን በመታደግ የምፅፋቸውን ምግታራውያን ፅሁፎች መነሻ በማድረግ፤ ባልፈፀምኩት አንዳች ወንጀል፤ ከታላቁ የፍትህ አደባባይ ላይ የፊጥኝ አስረው አቅርበው ‹እብድ ነህ› የሚል መንግስታዊ ውሳኔ በተሰጠበት ማግስት ነው፡፡ እነሱ በሃገሬ የውስጥ ጉዳይ ባይገቡ ኖሮ ባልተነቸፉ ነበር፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ህይወቴ ቀልቡን እንዳጣ ይገኛል…”
.

ምስኪን ገሞራው…

ህይወቱ እንጂ፣ ሞቱና ቀብሩም ቀልቡን እንዳጣ አያውቅም!…
.

እነሆህ አንዲት ዘለላ ግጥሙን…
.

“… እንደ ኪሩብ ሁሉ – ክንፍ አካል ቢኖረኝ፣

መች እጠበስ ነበር – በዚህ ዓለም በቃኝ፣

ስላጣሁ ብቻ ነው – መሸሻ መድረሻ፣

በዚች በሽት ዓለም – የኖርኩ እንደውሻ …”

“… በሥጋዬ ብቻ ውጪ – ሀገር እስካለሁ፣

እወቁልኝ በርግጥ – አልኖርኩም ሞቻለሁ!…”

Filed in: Amharic