>
4:38 pm - Monday December 2, 1765

ኦርቶዶክሱ ራሱን ሁለተኛ ዜጋ ያደረገበት አካሔድ [ኤፍሬም እሸቴ]

እንደ ዳራ

Cross Church Photo ባፐቲስቶች 5.jpg - Adebabayሁለት የባፕቲስት ሚሲዮን እምነት ተከታዮች የሆኑ ፓስተሮች ባለፈው የጥምቀት ሰሞን አገራችንን መጎብኘታቸውን እንዲሁም ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋርም መነጋገራቸውን በፎቶግራፎች አስደገፈው ያወጡት ዜና ያትታል። ዜናውን በማኅበራዊ ድረ ገጾች ከፍተኛ መነጋገሪያ እንዲሆን ያደረገው የሁለቱ ፓስተሮች ጉብኝት ሳይሆን እንገነባዋለን ያሉት የ50ሺህ አብያተ ጸሎት ጉዳይ እንዲሁም የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ናቸው በተባሉት በአፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ላይ (ያውም በፓርላማው መንበራቸው ላይ እንደተሰየሙ) ከዳርና ከዳር ጠምደው ጸሎት ሲያደርጉላቸው የሚያሳየው ፎቶግራፍ ነው። http://www.bpnews.net/46636/layman-plans-for-50000-churches-in-ethiopia

ከዚህም ባሻገር የጉዞ ዘገባቸው ያነሣቸው አስገራሚ ነጥቦች አሉ።

1ኛ. የጉዞ ወጪያቸውን የሸፈነላቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሆኑ፣

2ኛ. ከፕሬዚዳንቱ ጀምሮ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ከመከላከያ ሚኒስትሩ እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሁም ከአየር መንገድ ኃላፊዎችና በአሜሪካ ከኢትዮጵያ አምባሳደር ጋር መነጋገራቸው እና እነርሱም በሁሉም ነገር እንደሚተባበሯቸው ቃል መግባታቸው መገለጹ፣

3ኛ. የተገኙትና ተቃቅፈው ሲጸልዩ ፎቶ የተነሡት በጥምቀት በዓል ላይ ቢሆንም በሌላው ሰው በዓል የራሳቸውን ጸሎት ማድረጋቸው ሳያንስ ለፎቶው የሰጡት መግለጫ እንዲህ ይላል፡- ግርድፍ ትርጉም፡- “የኦርቶዶክስ ክርስትና የጥምቀት በዓል በአዲስ አበባ። ወደ 5 መቶ ሺህ ኢትዮጵያውያን ተካፍለውበታል ይህንን የኢየሱስን ጥምቀት ለማሰብ፤ ነገር ግን በተሳሳተ የነገረ መለኮት ትምህርት የተዘፈቀ … ” ነው። /“… the Christian Orthodox Epiphany festival in Addis Ababa, Ethiopia. About 500,000 Ethiopians attended the celebration marking Jesus’ baptism but steeped in false theology.”/ ስሕተቱ ምን ይሆን?

4ኛ. ከድሮ የትምህርት ቤት ጓደኛቸው ከነበሩት ከአምባሳደር ግርማ ብሩ ጋር በመነጋገር ይህንን ጉብኝት አስፈቅደዋል የተባሉት ኢትዮጵያዊ አቶ ኃይለየሱስ አባተ የተናገሩት አንድ አስገራሚ ንግግር ወዘተ። አቶ ኃይለየሱስ የማጀቱን ባደባባይ እንደተባለው ሁልጊዜው የሚታወቀውን አንድ እውነታ እንዲህ ሲሉ መግለጻቸው ተጠቅሷል።

“For the first time in 3,000 years, it is the first time an evangelical, a Protestant person is the ruler of the country,” Haileyesus said. “This is the best opportunity to get [the Gospel] there. It is up to us to use this opportunity as quickly as possible.” በግርድፉ ሲተረጎም፣- «በ3ሺህ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው አንድ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የአገሪቱ መሪ የሆነው። ይህ ወንጌልን ለማድረስ ትልቅ አጋጣሚ ነው። ይህንን አጋጣሚ በፍጥነት መጠቀም የእኛ ፈንታ ነው።»

ስለዚሁ ጉዳይ ጥናት ያደረጉ የፕሮቴስታንት እምነት አጥኚዎችም ይህንን እውነታ በተለያየ ጊዜ መግለጻቸው ይታወቃል። የጠ/ሚኒስትርነቱን ሥልጣን ከአቶ መለስ ዜናዊ «የተረከቡት» ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በእምነታቸው ጴንጤቆስጤ መሆናቸው የሰጠው ትርጉም እጅግ ሰፊ ነው።

“In particular the relationship between the government and Pentecostalism has taken on a new dimension with the leader of the country, Prime Minister Hailemariam Desalegn, for the first time being not an Orthodox Christian, but a Pentecostal himself.” (Guest Editorial: The Ethiopian Pentecostal Movement – History, Identity and Current Socio-Political Dynamics, PentecoStudies 12.2/2013, page 151)

ቀጥሎ የሚመጣው ጥያቄ ባለሥልጣናት የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ መሆናቸው በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ምንድር ነው? የሚለው መሆኑ ግልጽ ነው። ምንም እንኳን ፖለቲካው ከእምነት ነጻ መሆኑ በአደባባይ ቢነገርም በተግባር ደረጃ ግን የፖለቲካውና በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ቤተእምነቶች ጋብቻ ስር የሰደደ፣ ፖለቲካው በእምነቶቹ ላይ ያለው ተጽዕኖም እጅግ የጠነከረ መሆኑ የአደባባይ ሐቅ ነው። አብዛኞቹ ይህንን “ያላቻጋብቻ” ተቀብለው አብረው ሲኖሩ ጥቂቶቹ ደግሞ ተቃውሟቸውን በግልጽ ከመግለጽ ወደኋላ አላሉም። ለአብነት ያህል ሙስሊሙ ሕብረተሰብ ላለፉት ዓመታት ያካሔደው ሰላማዊና እልህ አስጨራሽ ትግል ምስክር ነው።

ባፐቲስቶች 1.jpg - adebabayፕሮቴስታንትን በተመለከተ ግን “መንግሥት እየተጠቀመባቸው ነው ወይስ በመንግሥት እየተጠቀሙ ነው? ወይስ ሁለቱም የሚያገኙትን ጥቅም በማሰብ አብረው እየተመጋገቡ እየሠሩ ነው?” የሚለው የብዙ ኦርቶዶክሶች በይፋ ያልተነገረ ጥያቄ ነው። ጴንጤኮጥናት/PentecoStudies መጽሔት እንዳተተው “While estimated to account for less than 1 per cent of the population in the early 1960s,1 Protestants were recorded at 5.5 per cent by the 1984 Census and 10.2 per cent by the 1994 Census.2 The 2007 Population and Housing Census counts almost 14 million Protestants, namely 18.6 per cent of the population, next to 43.5 per cent of Christians Orthodox and 33.9 per cent of Muslims.” (page 150-151) የእምነቱ ተከታዮች ቁጥር በዚህ ደረጃ ዕድገት ማሳየቱ ላይ የእምነቱና የፖለቲካው ጋብቻ ድርሻ አለው ወይንስ በእምነቱ ተከታዮች ትጋት ብቻ የመጣ ነው?

ከእምነት አንድነት በፊት የብሔረሰብ አንድነት

ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች በነገሥታቱ ዘመን የነበራቸውን ሥፍራ አሁን ድረስ በስሜት ሲያነሱት መስማት የተለመደ ነው። የ66ቱ አብዮት መፈንዳት ይህንን ሕልም የሚመስል ዘመን በማሳለፉ የኦርቶዶክሶች ፀሐይ እንደጠለቀች የሚገምቱ ኦርቶዶክሳውያን ቁጥር ቀላል አይደለም። የወታደራዊውን መንግሥት ዘመን «ፀረ ሃይማኖት» ከመሆኑ አንጻር ብቻ ሳይሆን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን የኢኮኖሚና ማሕበረሰባዊ የበላይነት ያሰናከለ በመሆኑ ክርስቲያኖች ምንም ድርሻ ሊኖራቸው እንደማይገባ ያሳሰቡ አያሌ ነበሩ። ኮሚኒስታዊ ዘመንም ቢሆን የእንቅስቃሴው ሞተር ክርስቲያኖች መሆናቸው ሳይዘነጋ ፀረ ሃይማኖት በሆነው መንግሥት ዘመንም ቢሆን ክርስቲያኑ ከፖለቲካው መገለልን እንደ አማራጭ አልወሰደም። በዘመኑ የነበሩ ጥቂት ሰባኪዎች የመንግሥትን አካሔድ ባገኙት አጋጣሚ በመንቀፍ አካሄዱ ለአገር መአት የሚያመጣ ኃጢአት መሆኑን በድፍረት በመናገር ሕዝቡን ለመታደግ ከመሞከራቸው በስተቀር።

በዘመነ ኢሕአዴግ ግን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለፖለቲካቸው ያላት አመለካከት “በጠላትነት እና በተቃራኒነት” በመፈረጁ ግልጽም ሆነ ሕቡዕ ተጽዕኖዎች እንዲጣልባት ምክንያት ሆኗል። ኦርቶዶክስን በተቀናቃኝነት የሚፈርጀው ይኸው የፖለቲካ አስተሳሰብ ዘውጋዊነት /ብሔረሰባዊ ማንነት/ ላይ የሚያተኩረው ሌላው ፍልስፍናው ኦርቶዶክሱ አማኝ በእምነቱ አንድነት ብቻ ተሰባስቦ ሃይማኖታዊ ሥፍራውን ለመያዝ ሊያደርግ የሚችለውን እንቅስቃሴ ሁነኛ በሆነ ሁኔታ አምክኖታል። አንድ እምነት ካላቸው ሁለት ግለሰቦች ይልቅ አንድ ዓይነት ብሔረሰብ ያላቸው ሁለት ግለሰቦች በእምነታቸው ሳይሆን በብሔረሰባቸው እንዲተማመኑ እና እንዲተባበሩ በማድረጉ የአንድ እምነት ሰዎች በተለያየ መስመሮች እንዲሰለፉ አድርጓቸዋል። የእምነት አንድነት ሳይሆን የብሔረሰብ አንድነት አሸናፊ ሆኗል። ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም መንግሥት በሚፈልገው መሠረት እንድትተዳደር በብሔረሰብ ተኮር ቤተ ክህነት ተቀርቅባለች።

የዚህ የብሔረሰባዊ ቤተ ክህነት ጉዳይ የአደባባይ ምሥጢር ቢሆንም ብዙ ክርስቲያኖች ግን ጉዳዩ ሲነሣ አይስማማቸውም። ዘረኛ የሆኑ ወይም የተዘረጋው የዘረኝነት ወጥመድ ሰለባ የሆኑ ስለሚመስላቸው አለማንሣቱን ይመርጣሉ። (ማሳሰቢያ፡- ይህንን ጉዳይ ሣነሣ ፀረ ትግራዋይ ተብዬ ልፈረጅ እንደምችል ጠፍቶኝ አይደለም። በዚህ ማስፈራሪያ ዝም የሚባልበት ዘመን ማለፍ አለበት። ለአገራችንና ለቤተ ክርስቲያናችን ስንል ብዬ ስለማስብ እንጂ፡፡) በሌላ አነጋገር በትግራዋዮች የተገነባው ሕወሐት ታማኝ በሆኑ ትግራዋዮች የተገነባ ቤተ ክህነት መሥርቷል። የእርሱን በእምነት ላይ ሳይሆን በብሔረሰብ ላይ ያተኮረ ፍልስፍና የማይቀበሉ አያሌ የትግራይ ሊቃውንት ወደዳር ተገፍተዋል፡፡ የቤተ ክህነትን ሥልጣን ለመቆናጠጥ እምነት ሳይሆን ብሔረሰባዊ ማንነት ዋነኛ መስፈርት በመሆኑ ከመንበረ ፕትርክና እስከ አቃቢትና ዘበኛ ድረስ ያለው ሥፍራ በዚህ መስፈርት ተለክቶ ለሰዎች ተሰጥቷል።

የቅድስት አገር ፍልስፍና ሲፈርስ

ኦርቶዶክስ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን “አገር ብቻ” አድርገው አይመለከቱም። አገራቸውን ከሃይማኖታቸው ለይተውም አያዩም።። ለሃይማኖታቸው የሚሰጡትን ቅድስና ለአገራቸው ሰጥተዋል። ቅድስት አገር ኢትዮጵያ የሚለው አባባል (ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም እንዲል) አገር ማለት ተራራና ሸንተረር፣ ወንዝና ተረተር ብቻ እንዳልሆነ ማሳያቸው ነው። ሊቃውንቱ “ሰብእ ይቄድሶ ለመካን፥ ወመካን ይቄድሶ ለሰብእ፤ ሰው ቦታን ይቀድሳል፥ ቦታም ሰውን ይቀድሳል” በሚለው ትምህርታቸው መሠረት ቅዱሳን በኪደተ እግራቸው የቀደሷት ናትና (ስለኖሩባት፣ ዞረው ስላስተማሩባት፡ ገድል ትሩፋት ስለሠሩባት፡ በጸሎታቸው ሁልጊዜም ስለማይለዩዋት፣ የተቀደሰ አጽማቸው ስለረገፈባት) ኢትዮጵያ የተቀደሰች መሆኗን ያምናሉ ያስተምራሉ። ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች የሚለው የቅዱስ ዳዊት ንግግር አገሪቱ ከሃይማኖቱ እንዳትለይ ሆና የተዋሐደች ያደርጋታል። ለአገር መሥራትም ሆነ ለአገር መሞት እንደ ተራ ግዳጅ ብቻ ሳይሆን እንደ ሰማዕትነት እና እንደ ሃይማኖታዊ ትሩፋት ተደርጎ የሚቆጠረው በዚህ ምክንያት ነው። “ሀገሪቱ ሀገረ እግዚአብሔር፣ ሕዝቡም ሕዝበ እግዚአብሔር” እንዲል።

ታላቁ ሊቅ አለቃ አያሌው ታምሩ ኢትዮጵያን በጌታችን መድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ልብስ፤ መርፌ ባልነካውና ባደገ መጠን አብሮት በሚያድገው የጌታ ልብስ (ኋላም አይሁድ ዕጣ የተጣጣሉበት ልብስ) ይመስሏታል። ሊቃውንት “አልባሲሁሰ ለክርስቶስ መሐይምናን፤ የክርስቶስ ልብሶቹ መሐይምናን/ምእመናን ናቸው” ያሉትን ጠቅሰው ኢትዮጵያም ለእርሱ የተዘጋጀች፣ የተስተካከለች፣ ወጥ-ልብሱ መሆኗን ያስተምራሉ። በክርስቶስ ልብስ ላይ ዕጣ እንደተጣጣሉበትም በዚህ ዘመን የክርስቶስ ልብስ በሆነችው አገር ላይ /ሊቃደዷት/ ዕጣ የሚጣጣሉ  መኖራቸውን አስተምረው አልፈዋል።

በኦርቶዶክሳዊ እምነት ላይ የኮሎኒያሊስቶች ትምህርት

“When the Missionaries arrived, the Africans had the land and the Missionaries had the Bible. They taught how to pray with our eyes closed. When we opened them, they had the land and we had the Bible.” (Jomo Kenyatta)

ኦርቶዶክሳውያን ለአገራቸው ያላቸው አመለካከት ሃይማኖታዊነትን የተላበሰ ሆኖ ለብዙ ዘመን የቆየ ቢሆንም አሁን በተግባር የሚታየው ግን ከዚያ የተለየ ነው። እንዲያውም የአውሮፓ ኮሎኒያሊስቶች በእምነት ስም ሲያስተላልፉ የቆዩት “ስለ ጸሎቱ እንጂ ስለ መሬቱ አትጨነቁ” የሚለው ጊዜ ያለፈበት ትምህርት አሁን በኦርቶዶክሱ ዘንድ መሠረት እየያዘ ነው። አፍሪካውያን ወገኖቻችን ክርስትናን ሲቀበሉ አገራቸውን እንዳጡት ሁሉ ኦርቶዶክሱም ሃይማኖቱን ለመያዝ አገሩን እያጣ በራሱ አገር ወደ ሁለተኛ ዜጋነት እየወረደ ነው። በአገሩ ፖለቲካዊ እና ማሕበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ያለውን ድርሻ ቀስበቀስ እያጣ የዳር ተመልካች ሆኗል። “የአገሪቱን ፖለቲካ በዋነኝነት የሚዘውሩት ሰዎች ከክርስቲያን ቤተሰብ የተገኙ ክርስቲያኖች አይደሉምን” ቢባል “አዎ ናቸው። ነገር ግን ብሔረሰባዊ እምነት እንጂ ኦርቶዶክሳዊ እምነት የሚያራምዱ” አይደሉም። ኦርቶዶክሳዊ እምነት ግን ከብሔረሰባዊነት የላቀ ነው። በቋንቋና ዘር ማንነት የማይቀረቀብ የእምነት ቤተሰብነት ላይ የተመሠረተ ትምህርት ነው። በእምነት አንድነት ብቻ ለይቶ መውደድን የሚቃወም በሥላሴ አርአያ የተፈጠረ ማንኛውንም የሰው ልጅ በእኩልነት እንድንመለከት የሚያስገድድ ሰማያዊ ትምህርት ነው።

ወደ ርዕሰ ጉዳያችን ስንመለስ፣ ኦርቶዶክሳውያን ቀደምት አባቶቻቸው ያቆዩትን ባለአገርነት ቀስ በቀስ እያጡ፣ ከፖለቲካው አደባባይ እየሸሹ የሄዱበት ጉዳይ የኮሎኒያሊስቶች ትምህርት ሰለባ በመሆን እንጂ በሌላ ምክንያት አይመስልም። በምንኖርበት በአሜሪካን አገር ያሉ አፍሪካዊ ዝርያ ያላቸው አሜሪካውያን በፖለቲካ ለመሳተፍ ለዘመናት የቆየ እልህ አስጨራሽ ትግል አካሂደው የመብት ባለቤት ከሆኑ ገና 50 ዓመታቸው ነው። እኛ ኦርቶዶክሶች ግን አባቶቻችን ያቆዩልንን ነጻነት በሰላም አገር እያስረከብን የአፍሪካውያን ወገኖቻችንን ዕጣ ለመቀበል እያጎበደድን ነው። እነርሱ እንኳን ያንን ቀንበር አሽቀንጥረው ከጣሉ ብዙ ዘመን ሆናቸው። ሆነም ቀረም በአገራቸው ፖለቲካ እንዳይሳተፉ ማንም አይከለክላቸውም። “የፖለቲካ ነጻነት ማጣትን/በአገር ጉዳይ አለመሳተፍን፣ ምንቸገረኝነትን፣ ምንግዴነትን፣” ኦርቶዶክሱ ታዲያ ምነው መንፈሳዊነት አድርጎ ቆጠረው? ባፐቲስቶች 2.jpg - adebabay 2

ሃይማኖተኝነት እና ፖለቲካዊ አቋም

ችግሩ ስር የሰደደ ነው። የማንንም ምርምር ሳልሻ በራሴ የታዘብኩትን እንደ ማሳያ ላቅርብ። በአገራችን ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የግሌን ሐሳብ ለማካፈል ከመወሰኔ በፊት ብዙ የራስ-ከራስ-ጋር-ውይይቶች አድርጌያለኹ። ለፖለቲካዊ ጉዳዮች ባዳ የሆንኩበትን ዘመን ባላስታውስም በይፋ ሐሳብ ለመስጠት ግን ግራና ቀኙን ማየት ጠይቆኛል። ሐሳቤን መስጠት ከጀመርኩ በኋላም ብዙ ወንድሞቼ እና እህቶቼ አካሔዴ ትክክል አለመሆኑን ነግረውኛል። ፤አሁን ያንተ የፌስቡክ ጽሑፍ ምን ሊፈይድ ነው? መንግሥት በጽሑፍ ይወድቃል?፤ ብለውኛል። ምክራቸው ከቅንነት እና እኔን ከመጠበቅ አንጻር የተደረገ ነው። ዛሬም ድረስ ይኼንኑ የሚመክሩኝ አሉ።

በሌላኛው ወገን ያሉት ደግሞ “አንተን ብሎ ዲያቆን፤ ፖለቲካህን ከምታወራ ዝም ብለህ መጽሐፍ ቅዱስህን አታስተምርም?” ከሚሉኝ ጀምሮ “ፓለቲካውን ለእኛ ተዉልን፣ እናንተ ቸርቹ ላይ አተኩሩ” እስከሚሉት ድረስ ብዙ ሐሳብ ማስተናገድ የግድ ነው። ይህ ፖለቲካ የሚሉት ነገር በእኔና እኔን በሚመስሉ ዜጎች ላይ ያለውን መዘዝም የዘነጉት ይመስላል። ኢትዮጵያዊነት የእነርሱ ብቻ ነው እንዴ? ዜግነት መብቴን በሃይማኖተኝነቴ ምክንያት ሊገፉት ሲሞክሩ ወንጀል እየፈጸሙ እንደሆነ እንኳን አይገነዘቡም። አንድን ሰው ፖለቲካዊ ሐሳብ አይኑርህ ማለት የዜግነት መብትን መግፈፍ፣ ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ (second-class citizen) ሁን ማለት መሆኑን ልብ የሚሉ አልመሰለኝም።

እንዲህ ያለው ገጠመኝ የእኔ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታቸውን ከምር የሚወዱና የአቅማቸውን ለማገልገል ደፋ ቀና የሚሉ ብዙ ወንድሞችና እህቶችም ዕጣ መሆኑን አሁን አሁን ተረድቻለኹ። በዚሁ ነገር የተሰላቹ አንዳንዶችም የጀመሩትን አገልግሎት ለመስጠት እንቅፋት እንደሆነባቸው አወያይተውኛል። የሚገርመው ነፍሰ ገዳዮችንና ዘራፊዎችን የሚደግፉት ደረታቸውን ነፍተው በሚሄዱበት ዘመን አትግደሉ፣ አትዝረፉ የሚሉት ተሸማቀው መሔዳቸው ነው።

መፍትሔው ወደኋላ ማለት ሳይሆን ሌሎች ሰዎች ከገቡበት ሰመመን እንዲነቁ ማድረግ ብቻ ነው። የአገራችን ጉዳይ የሃይማኖታችንም ጉዳይ ነው። ሃይማኖታችንን በአገራችን ማኖር ስላለብን። የአገራችን ፀር የሃይማኖታችንም ፀር ነው። ሃይማኖቴን አይንካ ምእመናንን ግን እንደፈቀደ ያድርጋቸው ማለት ምን ዓይነት እምነት ነው? “ፍርድ አይጓደል፣ ድሃ አይበደል” ማለት ነው ሃይማኖተኝነት።

ቱርካዊው ፀሐፊ ኤሊፍ ዣፋቅ/ Elif Shafak/ ያለውን እዚህ መጥቀስ ይገባናል። “I don’t have the luxury of being apolitical”። ይህንን በአማርኛ ተርጉሙት ብንባል፡- 1.“ፖለቲካ የማይመለከተው ሰው ለመሆን መቼ ታደልኩና” ወይም 2. “የደላው ፖለቲካ አይንካኝ ይላል።” ወይም “ችግር ፖለቲካ ያናግራል (የቸገረው በቅቤ ይበላል – እንዲል)። ወይም 3. “የቸገረው ፖለቲካዊ ጉዳይ ያገባኛል ይላል” ወይም 4. “ቢደላኝ ፖለቲካ ባላናገረኝ” …. ወዘተ ብለን ልንፈታው እንችላለን። ለአገሩ፣ ለሃይማኖቱ፣ ለማንነቱ ግድ የሚሰጠው ሰው ዝምታን ሊመርጥ እንዴት ይችላል?

የሚኖረን መንግሥት ለእኛ የሚመጥነን መንግሥት ነው

“Every nation gets the government it deserves.” (Joseph-Marie, comte de Maistre)

“እያንዳንዱ አገር የሚኖረው ለእርሱ የሚገባው/የሚመጥነው መንግሥት ነው።” /ባ ጠብቆ ይነበብ/

ይህ ፈረንሳዊ እንዳለው ክርስቲያኖች በአገራቸው ጉዳይ ሊኖራቸው የሚገባቸውን ድርሻ አሳልፈው በሰጡ መጠን እምነታቸውንና ታሪካቸውን፣ ሰብዓዊነታቸውንና ማንነታቸውን የሚያጎድፍ መሪ ይጫንባቸዋል። በሥላሴ አርአያ የተፈጠርን እንጂ በእንስሳት አርአያ የተፈጠርን እስካልሆንን ድረስ ክቡር ለሆነው ተፈጥሯችን የሚስማማ ኑሮ ይገባናል። በጥምቀት የከበረች ሕይወታችንን በኑሮም ልናስከብራት ይገባናል። ክርስቶስ የሞተለት የሰው ልጅ ከእንስሳት ያነሰ ሊኖር አይገባውም። ቅዱስ አምላክ ለቅድስና ፈጥሮናል፣ ክቡር አምላክ ለክብረት እንጂ ለውርደት አልፈጠረንም። የተፈጠርንለት ዓላማ ራሳችንን ማክበርን ያስተምረናል። በዘር የተከፋፈለ፣ በድህነት የደቀቀ፣ ተስፋ ያጣ ኑሮ ይመጥነናል?

ይህ ተረት እንዳይተረትብን እሰጋለኹ። በጣሊያን ፋሺስቶች ዘመን ነው አሉ። መሬቱን እያረሱ፣ ድንጋዩን እየፈረከሱ፣ ተራራውን እየበሱ፣ መንገድ ይሠራሉ። በአድዋ ዘመን በከብት ጀርባ መሣሪያ ጭነው የመጡ ሰዎች፤ ከ40 ዘመን በኋላ በታንክና በአውሮፕላን እንዲሁም በመርዝ ጋዝ ታግዘው ስለመጡ፣ አገሩን ለመቆጣጠር መንገድ መሥራት የግድ ነበር። እና …. በዚያ ዘመን … ድንጋዩን ሲፈነቅሉ፣ … ሲሰባብሩ፣… ያዩ አንድ ሰው፣ ድንጋይ ድንጋዩን እያዩ እንዲህ አሉ ይባላል፦ “ይበልህ!!! አንተም መጎለቱን አብዝተኸው ነበር።”

መንግሥት በፕሮቴስታንቶች ወይስ ፕሮቴስታንቶች በመንግሥት ተጠቀሙ?

የዚህ ጽሑፅ ምክንያት የሆነው የባፕቲስት አምነት አራማጅ ፓስተሮች ደረጉት ጉብኝትና ዘገባቸው እንደመሆኑ በዚያው ሐሳብ ጽሑፌን ላጠቃልል። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እምነቱን ማስፋፋት መብቱ ነው። 50ሺህ ቤተ እምነት ለመሥራት ማቀዳቸው መብታቸው ነው። ተቃውሞ የለኝም በግሌ። የሁሉም ዜጋ መጠቀሚያ በሆነው ፓርላማ የግል እምነታቸውን ማራመዳቸው ግን ስሕተት ነው። አሁን ከዘገዩና ሁለት ፀጉር ካበቀሉ እምነቱን የተቀላቀሉት አባ ዱላ በያዙት ሥልጣን እና ወንበር ያሳዩት ድርጊት የበታቾቻቸው በየጊዜው ሲያደርጉት ያየነው ነው። ጥያቄው የመንግሥት ሥልጣን የያዙት ፕሮቴስታንት ኢትዮጵያውያን በመንግሥት እየተጠቀሙ ነው ወይንስ መንግሥት በእነርሱ ተጠቅሞ ዓላማውን እያከናወነ ነው? የሚለው ነው። በእኔ አመለካከት ሁለቱም ይመጋገባሉ ባይ ነኝ።

መንግሥት የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ቀዝቀዝ እንዲል “ሪፎርምድ” የሆነ ኦርቶዶክስነትን ይፈልጋል። ከዘመኑ ጋር የሚሔድ ለብ ያለ፣ በራድም ትኩስም ያልሆነ ኦርቶዶክስ። ለዚህ ደግሞ በፕሮቴስታንቶች ፊትአውራሪነት የተጀመረው “የሪፎርሜሽን”/የተሐድሶ/ እንቅስቃሴ መልካም አጋጣሚ ነው። ይህንንም ራሳቸው በይፋ የሚናገሩት ሐቅ ነው። የሚከተሉትን ሁለት ጥቅሶች አዲስ ተስፋዬ ከጻፈው ጽሁፍ ላይ ማግኘቴን አስታውሼ ላስነብባችሁ።

  1. “The evangelist is hopeful that the seeds of revival are being planted and nurtured in the estimated 34,000 Orthodox churches in Ethiopia and abroad. So far more than 600 people have successfully completed the two-week course.” /Revival and Persecution in ETHIOPIA፤/http://www.charismamag.com/blogs/189-j15/features/africa/530-revival-and-persecution-in-ethiopia/
  2. “Today, many underground movements are operating within Ethiopian Orthodox Church, some with evangelical and others with Pentecostal convictions. … Some of these movements exemplify attempts at religious innovation, though it is hard to plot their trajectories because of their hidden nature and complex character. Such developments are affecting wide ranging areas of the established structure of the Orthodox institutions, such as Sunday Schools, the mahibers, the monastic centers, and even the local churches in major cities.” /Tibebe Eshete The Evangelical Movement in Ethiopia: Resistance and Resilience 2009፡ ገጽ 61. Bayor University press/

ይህ በሰው ቤት ገብቶ ማንጎዳጎድ በኦርቶዶክሱና በፕሮቴስታንቱ ኢትዮጵያዊ መካከል የሚፈጥረው አለመተማመን፣ መቃቃርና ጥላቻ ለአገራችን የሚፈይደው አንዳች ነገር የለም። ፈረንጆች ባላቸው ንቀት በትምቀት በዓል ላይ እንኳን ተገኝተው ከክርስትና ውጪ የሆነ ነገር እንደተፈፀመ ለመናገር መድፈራቸውን ለጥቁሮች ካላቸው ንቀት ወይም ከገቡበት ድንቁርና አለመንቃታቸውን መመዘን ሲገባን በገዛ ራሳችን ሕዝቦች መካከል አለመተማመንን መፍጠር አይገባም ነበር። አሁንም በአስተሳሰባቸው እና በኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነታቸው የነቁት የፕሮቴስታንት እምነት ሊቃውንት ቁስሉ እንዲጠግግ ማድረግ መቻል እንዳለባቸው ይሰማኛል። ተሐድሶው ላይሳካ ጥላቻ መዝራቱ አይረባንም።

ይቆየን፤ ያቆየን

(ኤፍሬም እሸቴ) (ephremeshete@gmail.com/  Adebabay A

Filed in: Amharic