>

ጉዞ ወደ ኢትዮጵያ አናት፤ ራስ ዳሸን ተራራ ክፍል ፭ [ሙሉቀን ተስፋው - የቀለም ቀንድ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ]

Rasdashn mountenደባርቅ ተከስቻለሁ፡፡ የደባርቅ ከተማ የሊማሊሞ ገደል ጫፍ ላይ የተመሠረተች ከተማ ናት፡፡ ደባርቅ ስያሜዋን ያገኘችው እንዲህ ነው አሉኝ፤ ደባርቃውያን፡፡ ከቆላውም ከደጋውም የተጣሉ ሰዎች ለፍርድ ወደ ጎንደር መሔድ ግድ ይላቸው ነበር፡፡ ከበርሃው የመጡት የሊማሊሞን ገድል አልፈው የሚያርፉበት፣ ከደጋው ቧሒትና ጃናሞራ የሚመጡትም ገደሉን ወርደው ደባርቅ ላይ ያርፋሉ፡፡ ለፍትሕም ይሁን ለበቀል አብረው ሲጓዙ የነበሩት ባላንጣዎች ደባርቅ ላይ ካረፉ በኋላ ይመክራሉ፡፡ አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ሲሸርቡት የነበረውን ሴራ እርግፍ አድርገው ይተውና እርቀ ሰላም ያደርጋሉ፤ ወይ በድካማቸው ተሰላችተው አሊያም በቦታው አዚም፡፡ በዚህም ምክንያት ‹‹ደባ-እርቅ›› ተባለች አሉኝ፤ ደባ- ተንኮል፤ እርቅ- ሰላም ማውረድ፡፡ ቂም በቀሉ ሁሉ ተረስቶ ሰላም (እርቅ) ሆነ እንደማለት፡፡ ምን ያክል ዕውነት ነው የሚለውን ማጣራት ባልችልም ወሬው ግን የሚጣል አልመሰለኝም፡፡

ከዓለም አቀፍ የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ባገኘሁት መረጃ መሠረት የጃናሞራና የበየዳ አካባቢዎች በድርቅ መጎዳት ዳታ አይቼ ስለነበር የድርቁን ጉዳይ ለማጣራት ደባርቅ እንደገባሁ ወደ ጃናሞራ ወይም ደረስጌ የሚሔድ መኪና መፈለግ ግድ ይለኝ ነበር፡፡ በተጨማም ጎንደር ከተማ ባገኘሁት መረጃ በጃናሞራ መንግሥትና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ገዳማቱንና የአብነት ትምህርት ቤቶችን ስለማይረዱ ብዙ ገዳማት ተፈተዋል፡፡ መነኮሳት የሚበሉትን አጥተው ተበትነዋል፡፡ ይህ ጉዳይ አሳሳቢ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ደረስጌ ማርያም አጼ ቴዎድሮስ ጠላቶቻቸውን ሁሉ ድል ካደረጉ በኋላ ቅባዓ ሜሮን ተቀብተው የነገሡበት ቦታ በመሆኑ ወደ እዚህ አካባቢ መሔድ ከድርቁም ባሻገር ታሪካዊውን ቦታ ማየትም ለእኔ ቀላል ግምት የምሠጠው አይደለም፡፡ መኪና በደላላዎች አማካይነት ማፈላለግ ግዴታ ነው፡፡

የሚገርመው ነገር ከደባርቅ ወደ ጃናሞራና ደረስጌ የሚሔዱ መኪናዎች የእቃ ጪነት አይሲዙዎች ናቸው፡፡ አውቶቡስ የለም፡፡ መንገድ በደንብ አልተሠራም፡፡ ፓርኩን ሳይነካ አሁን በአስፓልት የተጀመረ መንገድ አለ፤ ግን ስላላለቀ አገልግሎት አይሰጥም፡፡ ስለዚህ ወደዚህ አካባቢ የሚሔዱ ሰዎች 150 ኪሎ ሜትር ያክል የሚርቀውን መንገድ 150 ብር በመክፈል ከላይ እንደ እቃ ተጪነው ሊጓዙ ግድ ነው፡፡ ከላይ በነፋስና በብርድ መሔድ የማይሹ ግለሰቦች ደግሞ 300 ብር አስቀድመው ከፍለው (ያውም ከተገኘ) ጋቢና ይገባሉ፡፡ ጋቢና የማገኘት እድል አልነበረኝምና 150 ብር ከፍዬ ከላይ ከእቃ መጫኛው ላይ ወጣሁ፡፡

አሁን የአገራችን ማማ ወደ ሆነው የራስ ዳሽን ተራራ እየወጣን ነው፡፡ ሁላችሁም የአገሬ ዜጎች ከእኔ በላይ ከፍታ ያለው ቦታ ላይ አይደላችሁም፡፡ ሁላችሁንም ወደ ታች እየተመለከትኳችሁ ነው፡፡ ራስ ዳሽን (ራስ ደጀን) ከአገራችን ተራሮች ሁሉ በከፍታ የሚልቀው የለም፡፡ ያ ማለት ደግሞ ከፍተኛው ማማ ላይ ለመውጣት እየገሰገስኩ ነው ማለት ነው፡፡ የተራራው ጫፍ ከባህር ወለል በላይ ወደ ዐሥራ አምስት ሺህ ጫማ ያክል ከፍ ይላል፡፡ በሌላ አነጋገር የአገር ውስጥ የአውሮፕላን በረራ ከፍታ ሊደርስ ብዙ የቀረው አይደለም ማለት ነው፡፡ ከደባርቅ ከተማ 36 ኪሎ ሜትሮችን ያክል እንደተጓዝን ሰሜን ሎጂ የሚባል ሆቴል አለ፡፡ የፓርኩ መግቢያ አካባቢ ነው፡፡ “The Highest Hotel In Africa” ይላል፤ ከአፍሪካ ከፍተኛ ቦታ ላይ ያለው መዝናኛ ለማለት መሆኑ ነው፡፡ ለኔ ግን የገባኝ በሌላ ነው፡፡ ስልክ ጉግል አድርጌ ማረፊያ እንዳላቸው ለማረጋገጥ ገና ስመጣ ደውዬ ነበር፡፡ የፈርንጅ አፍ ያላት እንስት አነሳችሁ፡፡ የአልቤርጎ ዋጋ ስጠይቅ ግን ተሸማቀቅኩ፤ ‹‹88 ዳላርስ!›› አለችኝ፡፡ ወይ አቅምን አለማወቅ!

ስንሔድ ነጭ ቀለም ያለው ፈረፈር፣ ገደላማ አምባ፣ አፈሩ የገጠጠ መሬት፣ የደጋ ዛፎች ያሉበት ጫካ… ድብልቅልቅ ያለ እይታ ያለው መልክዓ ምድር ነው የሰሜን ተራሮች፡፡ የጭላዳ ዝንጀሮዎች መቀመጫቸውን የእሳት ፍም አስመስለው መኪናውንም ሰውንም ከምንም ሳይቆጥሩት ይንጎማለላሉ፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ እንዲያውም ከብዛታቸው የተነሳ ሁሉንም አካባቢ ሊሸፍኑት ይችላሉ፡፡ በዝንጀሮች አገር ድርቅ የገባ አልመሰለኝም፡፡

ይህን መንገድ የሚጓዙ መኪናዎች እንደ ጭላዳ ዝንጀሮዎች መጭጨው የሚይዙ ነው የሚመስሉት፡፡ እንደ እቃ የሚቆጠሩ ሰዎችን የጫነችው የጪነት መኪና በሮጠችና ወደ ከፍታዋም እየጨመረ በሔደ ቁጥር የሚመታኝ ነፋስ አእምሮዬን አደነዘዘው፡፡ እንኳንስ ለቀናት መንገድ የሰነበተበትን ሰው ቀርቶ የመንገድ ሁሉ የመጀመሪያው ቢሆንም ፊትንና አናትን የሚወቅረውን ንፋስና ብርድ መቋቋም እጅግ ከባድ ነው፡፡ ከ57 ኪሎ ሜትር በላይ ለመሔድ አልቻልኩም፡፡ ከፊታችን የቧሒት ጭጋግ አለ፡፡ እጅግ አስቸጋሪ የሆነውን መንገድ በእግራችን እንድንወጣ ከመኪናው ውረዱ ሲባል እንደወርድኩ ቀረው፡፡ አዎ! ከጨነቅ በኋላ በጭነት መኪና ላይ ተጭኜ መሔድ (መጨነቅ) ለእኔ የሚቻል አልሆነም፡፡ በጣም ሽንፈት ተሰማኝ፡፡ የጃናሞራ ሰው በእየጊዜው እየሔደ እኔ ስለምን እንዲህ አቅመ ቢስ ሆንኩ?

ብቆጭም ምንም ማድረግ አልችልም፡፡ 150 ብር የከፍልኩባት መኪና ሒዳለች፡፡ ጨነቅ ካለው የማኅበረሰብ ሎጂ በጀርባዬ ተኝቼ አሻቅቤ ወደ ምስራቅ በኩል ተመለክትኩ፡፡ ከተራራው አናት እንደ ቅልጥም ሰባሪዋ አሞራ ስትርቀኝ አየዋት፡፡ ወደ ሰማይ ቀና አልኩ፤ ዕውነተኛዎቹ የቅልጥም ሰባሪ አሞራዎች በእኔ ትይዩ ይዞራሉ፡፡ የቅልጥም ሰባሪ አሞራዎችን ነጮች ‹‹ላመርጌር›› ይሏቸዋል፡፡ ጨነቅ ላይ በብዛት አሉ፡፡ የቅልጥም ሰባሪ አሞራዎች የበግ ወይም የፍየል ቅልጥም ይዘው ወደ ሰማይ ከፍ ብለው ይበራሉ፡፡ ከዚያም ከታላቅ ድንጋይ ላይ ይጥሉታል፡፡ በዚህ ጊዜ ቅልጥሙ ይሰበራል፡፡ የተሰበረው አጥንት ውስጥ ያለውን ‹መቅኔ› ይጠጡታል፡፡ የጃናሞራ ስያሜ ከቅልጥም ሰባሪ አሞራዎች ጋር የተገናኘ ይሁን አይሁን አላውቅም፡፡ ጃናሞራ ማለት ግን የንጉሥ (የራስ) አሞራ የሚል ትርጉም ይሰጣል፤ ጃን (ራስ)፣ አሞራም አሞራ ነው፤ የልዑላን ወይም የራሶች አሞራ፡፡ በዚህ አካባቢ ደግሞ ከቅልጥም ሰባሪ አሞራ የበለጠ ንጉሥ የለም፡፡

በነገራችን ላይ አንድ ጊዜ አንድ ልጅ አገሬን በቅልጥም ጣይ አሞራውና በመቅኔው መስሎ ያጫወተኝን አልረሳውም፡፡ ‹‹ሕወሓት እንደ ቅልጥም ጣይ አሞራ አገራችን እየሰባበራት ነው፤ ከሚሰባበረው ቅልጥም ውስጥ የሚወጣውን መቅኔም የሚጠጣው እርሱ ነው፡፡ ስለዚህ ሕወሓት እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚል ያረጀ ያፈጀ ፍልስፍና አገሪቱን ሰባብሮ ጠጥቷታል›› ነበር ያለኝ፡፡ ይህን ቅልጥም ጣይ አሞራ ሳይ የምሳሌውን አስረጅነት ተገነዘብኩ፡፡ ግን ዕውን አገሬ ይህን ያክል ተሰባብራለች? መቅኔውስ ይጠጣ፤ ችግሩ የተሠበረው ካልተጠገነ ነው፤ የሰይጣን ዦሮ ይደፈን፡፡

ወደ ቀደመው ነገራችን እንመለስ፡፡ ጨነቅ ሜዳዋ ላይ ተሁኖ ወደ ሰሜን ምስራቅ በኩል የተመለከትን እንደሆነ ከፍየል ትንሽ ከፍ የሚሉ ቀንዳቸው ከቁመታቸው የላቀ ዋሊያዎችን እንመለከታለን፡፡ በተለይ ደግሞ በጠዋት ከደረስን፡፡ የዋሊያዎቹ ቀንድ በረጃጅሞቹ እጽዋት (እጸ ጳጦስ የሚባሉ ይመስለኛል) ቁመት አልፎ ይታያል፡፡ በርቀት የማየት ችግር ያለበት ደግሞ ከስካውቶቹ (አጃቢዎች) ማጉያ መነጸር መዋስ ይቻላል፡፡ ትንኟን ዝሆን አሳክሎ ያጎላል መሪሣሪያው፡፡ የአገራችን ብሔራዊ ቡድን ዋሊያዎቹ የተባለው ከዳሸን ተራራ አናት ላይ በሚገኙት ዋሊያዎች ቢሆንም የእግር ኳስ ቡድናችን ግን እንደኔ ጨነቅንም ማለፍ አለመቻሉን ሳስብ ይደንቀኛል፡፡ ቴዲ አፍሮ ‹‹እዳሸን ተራራ አናቱ ላይ›› እያለ የተቀኘውን ኤዲት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

ጨነቅ ላይ ሆነን ወደ ቆላ አዲአረቃይ፣ ዋልድባና ወልቃይት ስንመለከት ያለው ትዕይንት ለመግለጽ የሚያስችል ቃል መፈለግ ጊዜ ከግደል ውጭ እንደማላገኝ አውቃለሁ፡፡ በመንከራተቴ ዘመናት ሁሉ ካየኋቸው ቦታዎች እንደዚህ ውቃቢዬን የሚማርከው ቦታ አላገኘሁም፡፡ ወደ ታች የምንመለከታቸው የተራራ ሰንሰለቶች ለደቦ ተሰባስበው የመጡ ይመስላሉ፡፡ ደራሲው እንዳለው እግዚአብሔር ቸዝ ሊጫወትባቸው የደረደራቸው መጫዎቻ ጠጠሮች ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ ፊት ለፊት ያሉት የተራራ ሰንሰለቶች ንጉሥና ንግሥት ናቸው ብሎ ማሰብ ነው፡፡ ግን ካከአሞራዎች ውጭ ማንም እንዲያርፍባቸው አልፈቀዱም፡፡ ጨነቅ ‹‹ቁርበት መጣያ›› የሚባል ገደል አለ፡፡ የደገኞችን በግ ሌባ አርዶ ከበላ በኋላ በዚህ ገደል ከወረወረው ማረፊያው የአዲአረቃይ ወረዳ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የበግ ሌባዎች በአውጫጭኝ ሌጦው እንዳይገኝባቸው በገደሉ ይወረዉሩታል፡፡ ከዚያም ማን የማንን በግ እንደሰረቅ የሚያውቅ ሰው አይኖርም፡፡ በዚህም ቁርበት መጣያ ተባለ፡፡ አንድ ከፍተኛ ዋጋ ያለው እቃ ከእጅ አምልጦ ቢወድቅ እቃውን ለማምጣት በትንሹ ከአንድ ቀን በላይ የመኪና መንገድ ለመሔድ ያስገድዳል፤ ለዚያውም እቃው ከተገኘና መኪናም የሚወስደን መንገድ ካለው ማለት ነው፡፡ ግን ሁለቱም ምናባዊ ምኞቶች ብቻ ናቸው፡፡ ከገደሉ አናት ላይ ያሉና ከገደሉ በታች ያሉ ሰዎች እየተያዩ የማይገናኙ ናቸው፡፡

የቁርበት መጣያ ገደልን ለማየት የሚሻ ሰው መጀመሪያ በሆዱ ተንበልብሎ ይተኛል፡፡ ሆኖም አንድ የሚታመን ሰው የተኛውን ግለሰብ እግር ወደ ኋላ በደንብ መያዝ አለበት፡፡ ያ ካልሆነ ወደ ገደሉ ከተሔደ በሰዓት 100 ኪሎ ሜትር ቢምዘገዘግም ለደቂቃዎች በአየር ላይ ለመቆየት ይገደዳል፡፡ በሕይወት ስለመትረፍ አለመትረፍ የሚጠይቅ የዋኅ ሰው ይኖራል ብዬም አላስብም፡፡ ማንም ደፋር ነኝ የሚል ሰው ቁርበት መጣያን ቁሞ መመልከት አይችልም፡፡ የገደሉን አስፈሪነት ለመግለጥ በዚህ መልኩ ብሞክር አይከፋም፡፡ ቀጥ ያለ ከሆነ መቶ ሰማንያ ዲግሪ ይለካል ብለውናል የጂኦሜትሪ መምህራችን፡፡ በጂኦሜትሪ ሕግ እጥፍታው (ከርቩ) ከ90 ዲግሪ ከፍ ብሎ ከ180 ዲግሪ ካነሰ ቢያንስ የሚወድ ቀው ነገር መሬት ነክቶ መንከባለል ይችላል፡፡ ቀጥ ያለ ከሆነ ደግሞ 180 ዲግሪ ስለሚሆን ይህም ቢያስፈራም መሬት የመንካት እድል ሊኖር ይችላል፡፡ አንግሉ (እጥፍታው) ከ180 ዲግሪ የበለጠና ከ360 ዲግሪ ያነሰ ከሆነ ስርጉድ አንግል ተፈጠረ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የሚንከባለል ነገር ምንም ነገር ማግኘት ሳይችል በአየር ላይ ሊከሰከስ ይገደዳል ማለት ነው፡፡ ቁርበት መጣያ እንዲያ ነው፡፡ ተጨነቅ ቢለኝ እንጅ ቁርበት መጣያን የገለጽኩት አይመስለኝም፡፡

ጨነቅ አካባቢ አየሩ ይከብዳል፡፡ አየሩ ይበርዳል፡፡ የአየር ግፊት የሚሳሳ ይመስለኛል፡፡ እዚህ አካባቢ የዛሬን አያድርገውና ደርግ ወገራን ሰው የወያኔ ጦር ሲመጣ እዚህ ላይ ሆነው እንዲጠበቁ ያደርግ ነበር፡፡ ሚሊሻዎቹ ውርጭ በበዛበት ቀዬ ያለምንም ጫማ አገርን የሚያፈርስ ጠላት ቀያቸውን ረግጦ እንዳይሔድ ከዝንጀሮዎች ጋር እያደሩ ለመጠበቅ ይገደዳሉ፡፡ ባለባዶ እግር ሚሊሻዎቹ እግራቸው ይነቃል፤ ዝናብ የተጠማ መሬት ይመስል ይሰነጠቃል፡፡ በማግ (ዘሃ) ይሰፉታል፡፡ አሊያ ንቃቃቱ እግራቸውን እስከመጨረሻው ሊያበላሸው ይችላል፡፡

የአካባቢው ሕዝብ አሁንም ያለበት ሕይወት ከትናንት የተሻለ አይደለም፡፡ መሬቱ የተበላ ነው፡፡ ገበሬው አሳረኛ ነው፡፡ ገደላ ገደሉን በመቆፈሪያ በመቆፈር ይዘሩታል፡፡ ገበሬዎች ገደላ ገደሉን በመቆፈሪያ በመቆፈር ሲዘሩ መጀመሪያ መውሰድ የሚገባቸው ጥንቃቄ አለ፡፡ መሬቱ እንኳንስ ለበሬዎች ሰው ሲረግጠውም ተጠንቅቆ ነው፡፡ ለዝንጀሮዎች ብቻ ነው ምቹ የሆነው፡፡ ስለዚህ ቆፋሪዎች ራሳቸውን ከጥፋት ለመታደግ ረጂም ገመድ አዘጋጅተው ከትልቅ ዛፍ ወይም ቋጥኝ ጋር አንደኛውን ጫፍ ካሰሩ በኋላ ሌላኛውን ጫፍ እራሳቸው (ከሚቆፍረው ሰው) ወገብ አስረው ቁፋሮ ይጀምራሉ፡፡ በቀኑ መጨረሻ ሌላ የቤተሰብ አባል መጥቶ ገመዱን በመጎተት ያወጣቸዋል ማለት ነው፡፡ በዚህ ዘመንና በዚህ ጊዜ በእንዲህ ዓይነት ሕይወቱን የሚመራ ገበሬ መኖሩን መስማት ባለሁለት ድጅት እድገት ባላት አገር ላይ ምጸት ነው፡፡ ምንም እንኳ ያገራችን ስም ያጠለሻል ቢባልም ጋዜጠኛ ዕውነቱን ከመናገር አይቆጠብምና ይኼው ገለጽኩት፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ አንድ የሚያሳዝንና የሚያስቅ ነገር ገልጨ ልለፍ፡፡ ዕውነታው የሚያሳዝን ቢሆንም የሰው ልጅ ግብዝ ነውና መሣቁ አይቀርም፤ ለዚህም ነው የሚያሳዝንና የሚያስቅ ያልኩት፡፡ ጉዳዩ ከተፈጸመ ቆየት ብሏል፡፡ ጊዜውንም ማጣራት አልቻልኩም፡፡ የሆነው ግን ይኼ ነው፡፡

ባል ረዢም ገመዱን ይዞ ከቤት ይወጣል፡፡ ለሚስቱ ጀምበር ስታዘቀዝቅ (ፀሀይ ስትገባ) መጥታ ገመዱን እንድትስብ ይነግራታል፡፡ ባልና ሚስት በዚህ ተስማምተው ተለያዩ፡፡ ወደ ማታ ሲሆን ሚስት የባሏ ወገብና ቋጥኙ የታሰሩበትን ገመድ በአንድ በኩል ስትስበው ምንም ሳያስቸግራት ይወጣል፡፡ የገመዱን ጫፍ እስከምታይ ድረስ አላመነችም፡፡ ገመዱ ባዶዉን ነው፡፡ ባሌን ወዴት ጣልከው አትለው ነገር፡፡ ባዶውን ገመድ ስትስብ የተመለከታት ከገደሉ ማዶ ያለ ሰው ድምጹን አሰማ፡፡

‹‹ኧረ ጠዋት ነው ቆርጦ የሔደ!›› አላት፡፡ ባል የታሰረበት ገመድ ተበጥሶ ሕይወቱን ያጣው በጠዋት ነበር ማለት ነው፡፡ ሕይወት እንዲህ ናት፡፡ እና እንደገነገርኳችሁ በገመድ ያልታሰረ ወገቤ ቁርበት መጣያ ገደል አካባቢ ነው፡፡ ገመድ መቁረጥ ሳያስፈልገኝ ወደ ደባርቅ መመልስ ይሻለኛል፡፡

ፓርኩን ከሰው ንክኪ ለማራቅ በሚል በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የሚኖሩ ገበሬዎችን መንግሥት እያስነሳቸው ነው፡፡ ጥቂት ገንዘብ እየሰጠ በደባርቅ ከተማ ‹‹ኮሌጅ ሜዳ›› በሚባለው ሰፈር ነው ያሰፈራቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ የትውልቅ ቀያቸውን ለቀው የሚመጡ ገበሬዎች ራሳቸውን ማቋቋም የቻሉ አይደሉም፡፡ የተሰጣቸውን ገንዘብ ጨርሰው ለችግር እንደተጋለጡ ሰምቻለሁ፡፡ በነበረኝ የጊዜ እጥረት ምክንያት በፓርክ ምክንያት ለቀው ደባርቅ ያሉ ተነሽዎችን አነጋግሬ የደረሰባቸውን ችግር ሁሉ ለማጣራት አልሞከርኩም፡፡ የማኅበራዊ ሳይንስና የኢኮኖሚ ሊቃውንት በዚህ ላይ ትንታኔ የመስጠት ግዴታ የእናንተ ይሆናል፡፡ በተለይ ደግሞ የጎንደር ዩንቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች የመመረቂያ ምርምራችሁን እዚሁ ላይ ብታደርጉት የሚል ምክር አለኝ፡፡

ወደ ደባርቅ ለመመለስ ወይ ከጃናሞራ የሚመልስ የጪነት አሊያም የቱሪስ መኪና መጠበቅ ግድ ይለኝ ነበር፡፡ ቱሪስቶችን ይዛ የመጣች ላንድ ክሩዘር ይዛኝ ተመለሰች፡፡ መንገድ ላይ በፈረስ የሚኳትኑ የፈረንጅ ጎብኝዎች ከነኮተታቸው ከዝንጀሮ ጋር ውድድር የገቡ ይመስላል፡፡ በነገራችን ላይ ዝንጀሮዎችና ዋሊያዎች ከሐበሻ ይልቅ ፈረንጅን ይቀርባሉ፤ ምናልባት አብዛኛው ጎብኝ ፈረንጅ ከመሆኑ የተነሳ ሳይላመዱ አልቀሩም፡፡

ደባርቅ ከተማ ሆቴል እሜት ጎጎ ነኝ፡፡ ነገ የሊማሊሞን ገደልና የተከዜን በርሃ ለማቋረጥ መዘጋጀት አለብኝ፡፡

ደባርቅ፤ ኢትዮጵያ፡፡

Filed in: Amharic