>
11:26 am - Monday November 29, 2021

የሁለት ሳምንታት ጓደኛዬ [አቤል ዋበላ]

Abel Wabelaማዕከላዊ እንደገባኹኝ ከእኔ በፊት በዚያ የነበሩ ሠባት እስረኞች ተቀበሉኝ፡፡ ክፍሏ ከመጥበቧ የተነሳ እኔ እንድተኛበት ያመቻቹልኝ ቦታ ከሽንት መሽኛው ባሊ አጠገብ ነበር፡፡ ለረጅም ጊዜ ይመጣ ይሆን እያልን አንዳንዴ በድፍረት ብዙውን ጊዜ ደግሞ በፍራቻ የምንጠብቀው እስር ስለመጣ ይሆን ወይም ቀን በስራ የዛለው ሰውነቴ አላውቅም እንደገባኹኝ እንቅልፍ ጣለኝ፡፡ ስነቃ መንጋት አለመንጋቱን ማወቅ አልቻልኩም ነበር፡፡ ክፍሉ ጨለማ ነው፡፡
በመተላለፊያው ኮሪደር እና በኛ ሴል መሐል የምትገኝ አንዲት አምፑል የደከመ ብርሃኗ ይተየኛል፡፡ ወደክፍሉ ሳማትር ብርድ ልብስ ለብሰው የተጋደሙ ሰዎች፣ ኩርቱ ፌስታሎች እና በኋላ የሽንት መሽኛ ባሊ መሆኑን የተረዳኹት አንድ ነገር ይታዩኛል፡፡ ያለኹት ፌደራል ወንጀል ምርመራ መሆኑን ስረዳ ምን ያረጉኝ ይሆን የሚለው ስጋት ልቤን ይንጠው ገባ፡፡

አጠገቤ የተጋደመው ቀጭን ረጅም ሰው ብንን ብሎ ተነሳ፡፡ አነሳሱ ስላስደነገጠኝ ብበሽቅም ከማልወጣው የሀሳብ አዙሪት ስለገላገለኝ ደስታ ቢጤ ተሰማኝ፡፡ ፍራሽ ባልነጠፈባት ቀሪ ከሁለት ካሬ በምታንስ መሬት ላይ ቆሞ ይተጣጠብ ጀመር፡፡ ዑዱ እያደረገ መሆኑ ገባኝ፡፡ እኔ ጎን ወደሚገኘው ፍራሹ ተመልሶ ድምጹን ከፍ አድርጎ መስገድ ጀመረ፡፡ ምን አይነት ሁኔታ ውስጥ እንደከተተኝ ወያኔን እያማረርኩኝ ጸሎቱን እስኪጨርስ በትግስት መጠበቅ ጀመርኩኝ፡፡ ከአምላኩ ተገናኝቶ ሲጨርስ ወደግራ እና ቀኝ ተገላምጦ ሲያበቃ ባይተዋር ሰው በጭንቀት እየተመከተው እንደሆነ አስተዋለ፡፡ “አብሽር አብሽር” ብሎ ሰላም አለና ድንጋጤዬን አበረደው፡፡

ስሙ ዚያድ ያሲን ይባላል፡፡ የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር ወታደር ነው፡፡እየቆየው ከሌሌቹ እስረኞች ጋር ስግባባ አንድ ቶፊቅ ያሲን የሚባል አማርኛ፣ እንግሊዘኛ እና ኦሮምኛ አቀላጥፎ የሚናገር አረብኛ ደግሞ በመጠኑ የሚሞክር ፋርማሲስት በቆይታ ከዚያድ ጋር የፈጠሩትን የጋራ መግባቢያ በመንገር ወዳጅነታችን እንዲጎለብት አደረገው፡፡ ከሱማልኛ በቀር ሌላ ቋንቋ ባይችልም ሌበረሽን ፍሮንት ደጋግሞ ከአፉ የማይጠፋ ሁለት የእንግሊዘኛ ቃላት ናቸው፡፡ ቀብሪደሃር ነው የተወለደው፡፡ ገና ልጅ ሳለ ያጋጠመው ትዕይንት የህይወቱን መስመር ቀየረው፡፡ መንደራቸው በእሳት ሲቀጣጠል፣ ህጻናት እና ሴቶች ሲያለቅሱ፣ ወጣት ወንዶች እና ጉልማሳዎች በጥይት ተመተው ወድቀው ማየቱን ለማስረዳት እኔ የምረዳቸውን አማርኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች አለማወቁ አላገደውም፡፡ የተለያዩ ድምጾችን እያወጣ፣ በሰውነቱ የተለያየ ቅርጽ እየሰራ የልጅነቱን ትዝታ ያካፍለኝ ጀመር፡፡ አብረውኝ ከታሰሩ ሰዎች ቀድሞ ወዳጅ አደረገኝ፡፡ ያ በልጅነቱ የተመለከተው ዕልቂት ሁሌም የንግግሩ ማጠንጠኛ ነው፡፡ እናም ያንን እንደተመለከተ የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባርን ለመቀላቀል ብዙ ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ ያኔ የነበረው የፖለቲካ አመለካከት ጥቂት እንደሆነ እና መደበኛ ትምህርት እንዳልተማረ ፈገግ እያለ ያስረዳኝ ነበር፡፡ የማዕከላዊ መርማሪዎች የኦኤንኤልኤፍ አመራር አባል አድረገው ምንም ትምህርት የሌለውን ዚያድ መጠርጠራቸው ማዕረግ መደርደሪያ ትከሻውን እየደበደበ በድንቁርናቸው መገረሙን እየሳቀ ይነግረኛል፡፡ የሚገርመው ስለምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ እና ታሪክ ጥሩ ግንዛቤን ሰባት ዐመታት በፈጀው የደፈጣ ተዋጊነት ጊዜው አዳብሯል፡፡ መተኮስ ስለሚችላቸው ከባድ መሳሪያዎች አውርቶ አይጥግብም፡፡ በእኔ ምንም አለማወቅ ይገረም ነበር፡፡

ከጥቂት ጊዜ በኋላ እርሱም የኔን ታሪክ መጠየቅ ጀመረ፡፡ አየር መንገድ እንደምሰራ ለማሰረዳት ከባድ አልሆነብኝም የከበደኝ የእስሬን ምክንያት መግለጽ ነበር፡፡ እጄን የኮምፒዩተር ኪቦርድ እየደበደብኩኝ ሳስረዳው እስሬ ከኮምፒዩተር ጋር እንደተያያዘ ገባው፡፡ ኢንተርኔት የሚለው ቃል ከአፌ ሲወጣ ግን አደገኛ ሰው መሆኔን የገመተ መሰለኝ፡፡ በደፈጣ ተዋጊነቱ ዘመን ኦኔን ኤል ኤፍ የማረካቸውን ነዳጅ ሊቆፍሩ የመጡ ቻይናዎች ለመመለስ የተደራደረው ቻይኖቹ ለግንባሩ መጠቀሚያ የሚሆን የኢንተርኔት ማሽነሪዎች እንደሰጡ በማድረግ መሆኑን ያስታውሳል፡፡ ከትግል አጋሮቹ የተረዳው ኢንተርኔት ጠቃሚ የመታገያ መሣሪያ እንደሆነ ነው ፡፡ አለሙን በሞላ በወሬ እንደሚሞላም ግንዛቤም እንዳለው በሰፊው ከሚያወራጫቸው እጆቹ አወቅሁኝ፡፡

አንድ ሳምንት ከሌሎቹ እስረኞች ጋር ስምንት ሆነን ከዘለቅን በኋላ ሁሉንም ወደሌላ ክፍሎች ቀይረው እኔ እና ዚያድ ብቻችንን ቀረን፡፡ ወዳጅነታችን እጅግ ጠነከረ፡፡ አሁን ሳስታውሰው ያለቋንቋ እንዲያ መግባባታችን ይገርመኛል፡፡ ለዚያድ ባሬ ያለው ፍቅር፣ የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ያለው ግንዛቤ፣ አምስቱ ሶማሌዎች ተሰብስበው እንዴት “ታላቋ ሶማሊያን” እንዴት እንደሚመሰርቱ፣ ይተነትንልኛል፡፡

በሶማሌ ላንዷ ሀርጌሳ ያሳለፈውን ጊዜ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር ዳውድ ኢብሳን በእጁ አንደጨበጠ በኩራት ደጋግሞ ይነግረኛል፡፡ ብቻችንን ስንቀር የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር የትግል ዘፈኖች ይዘፍንልኝ ነበር፡፡ ቋንቋ በማይገድበው ዜማ የተበደለውን የኦጋዴን ህዝብ ጭቆና እና የታጋዮችን ቁርጠኝነት ያስረዳኝ ነበር፡፡ አንዳንዶችን አብሬው ለማንጎራጎር እሞክር ነበር፡፡ “ወያኖ” የሚል ቃል ያለው እንዴት ወያኔን አባረው የራሳቸውን ሀገር እንዴት እንደሚመሰርቱ የሚገልጽ ዘፈን ዜማው እስካሁን ድረስ በአእምሮዬ ያቃጭላል፡፡
ከዚያድ ጋር የምንጣላው አዲስ የምትመሰረተው ኦጋዴን የምትባል ናዝሬትን(አዳማ)፣ ሐዋሳ እና ድሬዳዋን እንደሚጠቀልል ሲነግረኝ ነው፡፡ “ይሄማ የኢትዮጵያ መሬት ነው” ስለው ሦስቱ ከተሞች ድሮ የሱማሌ መሆናቸውን እና ስያሜያቸው ሌላ እንዳነበረ ስያሜውን እየጠቀሰ ይነግረኛል፡፡ “ሂውማን ራይት” የሚለውን የእንግሊዘኛ ቃል ዚያድ በትክክል ተረድቶታል፡፡ ሂውማን ራይት ካለ ከኢትዮጵያ የመገንጠል ሐሳባቸውን ይቀይሩ እንደሆን እንደምንም ተፍጨርጭሬ ስጠይቀው እኔን ደስ እንዲለኝ ብቻ በሐሳቤ እንደተስማማ ይገባኛል፡፡
ዚያድ ሁሌ ደስተኛ ነው፡፡ ሁሌ ሰላቱን ይሰግዳል፤ ወያኔ በቅርብ ቀን እንደሚወድቅ ደስተኛ ነው፤ ያገኘውን ይበላል፤ እዛው ማዕከላዊ የተማረውን በተለምዶ ‘እንጀራ በወጥ’ የሚባለውን የካርታ ጨዋታ ብቻውን ይጫወታል፤ በየደቂቃው እየተነሳ በበሩ ትንሽ ቀዳዳ በመተላለፊያው ማን ወደ ምርመራ እንደሚሄድ ይመለከታል፡፡

ፀሐይ ስንወጣ ወይ አንዳችን ወደምርመራ ስንሄድ አንድ ባንድ ጓደኞቼን ለያቸው፡፡ ሁሉንም የራሱ የኮድ ስም ሰጣቸው፡፡ በአረብኛ ሳሂብ ማለት ጓደኛ መሆኑን መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡ ዚያድ ይህንን ጓደኞቼ ከታሰሩበት ክፍል ቁጥር እና አንዳንድ ሁኔታዎች በማያያዝ የራሱን መለያ ፈጠረ፡፡ በቀዳዳው አጮልቆ “ሳሂብ ነምበር ናይን ፒው” ካለ በፈቃዱ ለምርመራ እንደተጠራ አውቃለው፡፡ ሳሂብ ነምበር ስሪ፣ ሳሂብ ነምበር ፎር ተስፋለም፣ ሳሂብ ነምበር ፋይቭ ዘላለም፣ እንደሆኑ አውቃለው፡፡ ጋዜጠኛው አስማማው ሀይለ ጊዮርጊስ ደግሞ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ከነበረው ኦኬሎ አኳይ ጋር በመታሰሩ ምክንያት ስሙ “ሳሂብ ኦኬሎ” ነበር፡፡ ከሁሉም የሚያስቀኝ ናትናኤል የነበረበት ክፍል ለመለየት የሚጠቀምበት ኮድ ነው፡፡ ናትናኤል ፈለቀ ታስሮ የነበረው ሽንት ቤት ጎን የሚገኝ ሰባት ቁጥር የሚል መለያ የነበረው ክፍል ውስጥ ነበር፡፡ ዚያድ ናትናኤልን እንደሌሎቹ ሳሂብ ነምበር ሰቭን ሊለው አልወደደም፡፡ ዚያድ ሁለት ሳምንቱን አብረን ቆይተን ወደ ሌላ ክፍል እስኪቀየር ድረስ የናቲ ስም “ሳሂብ ሽንት ቤት” ነበር፡፡

የእኔ እና ዚያድ አብሮነት ከሁለት ሳምንት በላይ አልዘለቀም፡፡ ከእኛ ቀድሞ ተከሶ ወደ ቅሊንጦ ወረደ፤ እኛ ስንከተል ደግሞ ዞን ተለያየን ፡፡ አንድ ሁለት ጊዜ ፍርድ ቤት ስንሄድ አግኝቸው የክፉ ቀን ጓዴን ሰላም ብዬዋለው እንደድሮው ግን ቋንቋ ሳያግደን የሆድ የሆዳችንን አልተጫወትንም፡፡ አሁን በተከሰሰበት መንግስት “የሽብርተኝነት” በሚለው እርሱ ደግሞ “የነጻነት ትግል” ብሎ በሚጠራው ጥፋተኛ ተብሏል፡፡ የሚቀጥሉትን አመታት በእስር ማሳለፉ አልቀረም፡፡ ማዕከላዊ በነበርን ጊዜ የነበራው ተስፋ እና ደስታ ሁሌም አብሮት እንዲቆይ ምኞቴ ነው፡፡

Filed in: Amharic