>
4:05 am - Sunday August 1, 2021

ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን! ክፍል ፯ [ሙሉቀን ተስፋው - የቀለም ቀንድ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ]

Muluken Tesfaw KelemQend Journalist 2አክሱም ለሁለት ቀናት ቆይቻለሁ፡፡ የአክሱም ከተማ እንደ ሽሬ ሁሉ ጽዳትና ውበት ያላት ናት፡፡ አክሱም ዩንቨርሲቲ የሚያስተምር አንድ ወዳጅ አለኝ፡፡ አክሱም እንደገባሁ እንዲያሳየኝ የጠየቅኩት የአክሱም ሐውልትን ነበር፡፡ የአክሱም ሐውልትንና የጽዮን ቤተ ክርስቲያንን በጎበኙ ጊዜ ብዙ ጸሐፍት የተለያየ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ድንቅ የአገራችን ሥልጣኔ ሕያው ምስክሮች ናቸው፡፡ የአክሱም ሐውልቶች ከፊሎቹ ተጋድመዋል፤ ከፊሎቹ ቆመዋል፤ ሌሎቹ ደግሞ እንዳይወድቁ ተደግፈዋል፡፡

አክሱም ላይ ሆኜ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያንን፣ የጎንደር ቤተ መንግሥትን፣ ሳስብ የቆጨኝ በየመካከሉ ለምን የቴክኖሎጅ ጋብ እንደተፈጠረ ነው፡፡ አክሱምና ላሊበላ በተሠሩ ጊዜ አሜሪካ ስለምትባለው አህጉር የዓለም ሕዝብ የሚያውቀው አልነበረውም፡፡ ከ1700 ዓመታት በፊት ያን ያክል ክብደትና ቁመት ያለውን ቋጥኝ ፈልፍለው ያቆሙ አባቶቻችን ስለምን ሥራቸውን ለልጆቻቸው ሳያስተላልፉ ቀሩ? ማናችንም በበቂ ልንመልሰው አልቻልንም፡፡ በ2ኛው ክፍለ ዘመን አዶሊስ ትባል በነበረችው የወደብ ከተማ የመርከብ መሥሪያ ኢንዳስትሪ የነበረን ሰዎች ዛሬ በትዝታ ብቻ የምንቆዝም ሆነናል፡፡ የወዳደቁት ሐውልቶች የአገራችን ውድቀት አመላካች ናቸው፡፡ ሙዚየሙ ውስጥ በጥንታዊው የግእዝ እና የኮይኔ ግሪክ (Koine Greek) ፊደላት በድንጋይ ላይ ተቀርጸው አሉ፡፡ በጥንታዊው ዘመን የአገራችን ሰዎች ውጤት የሆኑ የእጅ ሥራዎች በደንብ አሉ፡፡ እነዚያ ጠንካራ ፍጡሮች ቅርሳቸውን ትተው ጥበባቸውን ግን ይዘው መሔዳቸው ያናድዳል፡፡ ከአክሱም ከተማ በግምት 3 ኪሎ ሜትር ያክል ርቀት የሚገኘውን አጼ ካሌብ ቤተ መንግሥትም አይቻለሁ፡፡ ቤተ መንግሥቱ እንዴት ሊደረደሩ እንደቻሉ ግርምት በሆኑ ትልልቅ ድንጋዮች የተገነባ ነው፡፡ የት ድረስ እንደሚሔዱ የማይታወቁ በአራቱም አቅጣጫ የመሬት ውስጥ መንገዶችም አሉበት፡፡ አስጎብኛችን የመን ድረስ እንደሚደርሱ ነግሮናል፤ ይደርሳሉ ብሎ ማሰብ ግን ይከብዳል፡፡ የአቡነ ጴንጤሊዮን ገዳም ከአክሱ ከተማ ዳር ካለች አንዲት ቀጥ ያለች አምባ አናት ላይ አለ፡፡

የሽሬና የአክሱም ከተማ ንግድ ቤቶች ማስታወቂያዎች በአብዛኛው በአማርኛ የተጻፉ ናቸው፡፡ መጠጥ ቤቶችና ሆቴሎች ላይ የሚከፈቱ ሙዚቃዎች አማርኛ ናቸው፡፡ ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለየ መልኩ የትግራይ ክልል አማርኛ የሚናገር ሰው ብዙ የለም፡፡ በንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ የሌላ ብሔረሰብና ጎሳ አባላት በትግራይ ቆይታዬ አንዳችም አልገጠመኝም፤ የሉም ግን ማለት ላይሆን ይችላል፡፡
የዐብይ ጾም ቅበላ ቀን ነበር፡፡ ‹‹ቦራ የወተት ውጤቶች መሸጫ›› የሚል ቤት ገብቼ እርጎ እንደፈለግኩ በአማርኛ ጠየቅኳቸው፡፡ አስተናጋጇ ፊት ለፊት ገንዘብ መቀበያው ያለውን ሰው አናገረችው፡፡ ሆኖም እርጎው አልቆ ያለው ወተት ለመርጋት ቢያንስ ተጨማሪ ሁለት ሰዓት እንደሚያስፈልገው ገለጸችልኝ፡፡ ምን ማዘዝ እንዳለብኝ በማመናታት ላይ እንዳለሁ አንድ ደንበኛ ገብቶ በትግርኛ ሲያዝዝ ሰማሁት፡፡ ሆኖም የትግርኛ እውቀቴ ብዙም በመሆኑ ማዘዙን እንጅ ምን እንደሆነ ማወቅ አልቻልኩም፤ ወዲያውኑ ግን እርጎ መጣለት፡፡ እኔም ተገርሜ ይህ ለምን እንደሆነ ጠየቅኳት አስተናጋጇን፡፡ ምንም መልስ አልሰጠችኝም፤ ዝም ብላ እርጎውን ለኔም አቀረበችልኝ፡፡ ትንሽ ደነገጥኩ፤ ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያት አልገባኝም፡፡ በትግራይ በነበረኝ ቆይታ በትግራይ ክልል የሚኖሩት ትግሬዎች እና በሌላው ቦታ ያሉት ትግሬዎች ባህሪ አንድ አልሆነልኝም፡፡ በአገራቸው ያሉት ትግሬዎች በአብዛኛው ከሌላ ቦታ ለሚመጣ እንግዳ ክብር አላቸው፡፡ ያን እየተረዳው ስለቆየው ነበር መደንገጤ፡፡

አክሱም የሃይማኖቶች እስር ቤት

ጓደኛዬ እሁድለት ያስተምር ስለነበር ከተከራየበት ቤት አጠገብ ያለ አንድ የዐሥራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ ልጅ የምፈልገውን እንዲያግዘኝ አደረገ፡፡ እዚህ ልጅ ጋር ከተማዋን ለማየት ውስጥ ለውስጥ ስንሔድ በድንጋይ ውርጅብኝ ብዛት የተጠረማመሰ ቤት ስንደርስ ‹‹ይህ የጴንጤዎች አዳራሽ ነው›› አለኝ፡፡ የፕሮቴስታንት አማኞች ቤተ ጸሎት በድንጋይ ተደብድቦ ተጠረማምሷል፡፡ የግቢው በር ያረፈበትን የድንጋይ ቅርጽ እየሠራ ደረመን እንደያዘው ሰውነት አባብጧል፡፡ ይህች የጴንጤዎች ቤት ዩንቨርሲቲው እንደተከፈተ ከአድዋ በመጣ የእምነቱ ተከታይ እንደተገዛች ነው የተነገረኝ፡፡ ሆኖም ግን ቤቷ እስካሁን ድረስ በድንጋይ ከመደብደብ አልቦዘነችም፡፡

አክሱም የሚኖሩ እስላሞች መስጊድ ስለሌላቸው አክሱም ጽዮን አጠገብ ካለ በኮብል ስቶን የተሠራ አደባባይ ላይ ነው የሚሰግዱት፡፡ ይህ አብሮኝ ያለው ልጅ እስላም የአክሱም ትግሬ ነው፡፡ ‹‹እዚህ አገር እስላሙና ክርስቲያኑ አይስማማም፡፡ እስካሁን መስጊድ ለእስላሞች አልተፈቀደም›› አለኝ፡፡ በአክሱም የእስላም መቃብር እንጅ የእስላም መስጊድ አለመኖሩ ምክንያቱ አልገባኝም፡፡ ሆኖም ግን አክሱም የሃይማኖቶች እስር ቤት እንደሆነች ለመረዳት ችያለሁ፡፡

ኦሮሚያና አማራ ዩንቨርሲቲዎች መመደብ አልፈልግም

ብዙ የትግራይ ክልል ተማሪዎች የመሠናዶ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ በአማራና በኦሮሚያ ክልል ባሉ ዩንቨርሲቲዎች መመደብ አይፈልጉም፡፡ አብሮኝ ያለው ልጅ የዐሥራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ የኦሮሚያና የአማራ ክልል ዩንቨርሲቲዎች የደረሰኝ እንደው እያለ ይጨነቃል፡፡ ለምን? አልኩት፤ ይህን ያክል ጭንቀት የፈጠረበትን ነገር ለማወቅ፡፡ ‹‹ሁሉም ሰው ትግሬ አይወድም!›› አለኝ በአጪሩ፡፡ ምንም አላልኩት፡፡ ሆኖም ግን ጓደኞችህን ጥራቸውና ሻይ ቡና ልበላችሁ አልኩት፡፡ ሌሎች ሁለት ልጆች መጥተው ሳቢያን ሆቴል ለስላሳ እየጠጣን አወራን፡፡ ጨዋታችንን ሆን ብዬ ቀደም ሲል ልጁ ወዳነሳው ነጥብ ወስድኩት፡፡ ሦስቱም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች መመደብ አይፈልጉም፡፡ ይህ አክሱም ላይ ያገኘዋቸው ብቻ ሳይሆኑ ወደፊት እንደምናየው አዲግራትና መቀሌ ላይ ያሉ ልጆችም ተመሳሳይ መልስ ሰጥተውኛል፡፡ ይህ ዓይነት አመለካከት በታዳጊ ልጆች ላይ መስተዋሉ (እንዲኖር መደረጉ) እንደ አንድ አገር የመቀጠል እድላችንን አደጋ ውስጥ የሚጨምረው ይመስለኛል፡፡ እዚህ ላይ የስነ ልቦናና የማኅበራዊ ሳይንስ ተመራማሪዎች የራሳችሁን ጥናት ብትጨምሩበት የተሻለ ይሆናል፡፡ በእርግጥ እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ በጥላቻ በተገነባ የጎሳ ፌደራሊዝም ብዙም የሚያስገርም ላይሆን ይችላል፡፡

አድዋ የነጻነትና የባርነት ተቃርኖ ምድር

ሰኞ ከሰዓት በኋላ ወደ አድዋ ሔድኩ፡፡ ከአክሱም አድዋ 24 ኪሎ ሜትር ያክል ነው፡፡ አድዋ የተራሮች አገር ነው፡፡ እነዚያ ተራሮች ሥር የብዙ አባቶቼ አጥንት አለ፡፡ እነዚያ ተራሮች አሁንም የቆሙት ለምስክርነት ይመስላል፡፡ የተሳፈርኩባት ሚኒባስ ከተራራ ሰንሰለቶች ሥር ወደተወሸቀችው አድዋ እየተጠጋች ነው፡፡ የአልመዳ ጨርቃጨርቅን አለፍን፡፡ የአደዋ ተራሮች ሥር ደረሰን፡፡ ሶሎዳ የተባለችው የተራራ ሰንሰለት በቅርበት አለች፡፡ ከሚኒ ባሷ ወረድኩ፡፡

ቀትር ነው፡፡ ሶሎዳ ተራራ ሥር ሆኜ በሐሳብ 120 ዓመታትን ወደ ኋላ ተጓዝኩ፡፡ ‹‹አንተ ተራራ እኔ በኩራትና በትሕምክት እንድሔድ፣ ነጻነቴና ማንነቴ እንዲጠበቅ ስንት ሰው እዚህ መስዋት ሆነ? ጦርነቱ እንዴት ነበር? ለምን ግን የተጠለለብህን ወራሪ ኃይል ተነደህ አላዳፈንከውም? …›› መልስ የሚሰጠኝ ይመስል ለተራራው በምናቤ የምጠይቀው ጥያቄ ነው፡፡ ጊዜን ወደ ኋላ የሚያጠነጥን ግኝት ቢኖር ኖሮ ያኔ የእቴጌ ጣይቱና የእምዬ ምኒልክ ስሜት ምን ይመስል እንደነበር ሶሎዳ አናት ላይ ሆኘ መመልከት ነበር፡፡ የጥቁር ሕዝብ ኩራት፤ እምየ ምኒልክ!

እንደጅል ብቻዬን የሶሎዳ ተራራን አንገቴን ሰብሬ ወደላይ እመለከታለሁ፡፡ የአባቶቼን መስዋትነት አስባለሁ፡፡ ሞባይሌን ከኪሴ አወጣሁት፡፡ እስከ መጨረሻው የድምጹን መጠን ለቀቅኩት፡፡ ከስልኬ የሚያምር ድምጽ ተንቆረቆረ፤

የሰው ልጅ ክቡር- ሰው መሆን ክቡር፣
ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን- ሰውን ሊያክበር፣
በደግነት በፍቅር- በክብር ተጠርቷል
በክብር ይሔዳል- ሰው ሊኖር ሰው ሞቷል
የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነጻነት
ሰው ተከፍሎበታል- ከደምና ካጥንት
ስንት ወገን ወደቀ – በነጻነት ምድር
ትናገር አደዋ ትናገር ትመስክር
ትናገር አደዋ -ትናገር አገሬ
እንዴት እንዴት እንደቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ
በኩራት በክብር በደስታ በፍቅር
በድል እኖራለሁ ይኼው በቅን በቅን
ደሞ መከራውን ያን ሁሉ ሰቀቀን
አደዋ ዛሬ ናት -አድዋ ትናንት
መቼ ተነሱና የወዳደቁት
ምስጋና ለእነሱ ለአድዋ ጀግኖች
ለዛሬ ነጻነት ለአበቁኝ ወገኖች
የጥቁር ድል አምባ አድዋ
አፍሪካ እመየ ኢትዮጵያ
ተናገሪ ተናጋሪ ተናጋሪ
የድል ታሪክሽን አውሪ …..

መለከቱ ይነፋል፡፡ ማንም ጅል ቢለኝ በዚያ ሰዓት ለኔ ምንም አይደለም፡፡ በጂጂ ቀናሁ፡፡ ውስጧን ገልጸዋለች፡፡ የእሷን መረዋ ድምጽ ከቀርነ መለከቱ ጋር መስማት እንዴት ያለ ነገር ነው? ጂጂን አድዋ ላይ ሰማዋት፡፡ የጦርነቱን የተካፈልኩ ያክል ተሰማኝ፡፡ ግን አንቺ አድዋ ስንት ወገን አለቀ? ሰውን ለማዳን ስንት ሰው ሞተ? ጀግኖች ሲሰው አገራችው እንዲህ እንደምትሆን ያውቁ ነበር? ምናለ ጥያቄን ብትመልሽልኝ!!
ነፍሴ ሐሰትን አደረገች፡፡ ከተደሰትኩባቸው ቀናት ይህችን የምትበልጥ የለችም፡፡ የጂጂን ሙዚቃ ማንም ሊያደምጠው ይችላል፡፡ ግን አድዋ ላይ ሆኖ ሲሰሙት የሙዚቃውን ኃያልነት ለመረዳት ይቻላል፤ በትዝታ ጭኖ የአድዋን ጦርነት ያሳያል፤ በቃ ለኔ የተሰማኝ ያ ነው፡፡
ቀብረር እያለኩ ወደ አስፓልቱ ዳር ሔድኩ፤ ውስጤ ሲጀግን ተሰማኝ፡፡ ነጻነቴ የታወጀባት ምድር ናት፡፡ ነገር ግን ወዲያው ደግሞ ነጻነቴን የቀበረው ሰው የፈለቀው እዚህ መሆኑን ሳውቅ ተናደድኩ፡፡ አይ አንቺ አድዋ! በተቃርኖ የተሞላሽ፡፡
ባጃጅ ያዝኩ፡፡ ወደ ከተማ ስሔድ የአድዋ 120ኛ ዓመት የተከበረው ከቀናት በፊት ስለነበር ያን ምክንያት አድርጎ የተከፈተው ባዛር አልተዘጋም፡፡ ከዚያ በኋላ መቆየት አልሻሁም፤ ነጻነቴን ያገኘሁባት፣ ነጻነቴ የተቀበረባት ምድር፡፡ አድዋ ዛሬ ናት፤ አድዋ ትናንትም ናት፡፡
ከመናኻሪያ ወደ ብዘት መኪና ያዝኩ፡፡ ብዘት ወደ አዲግራት መንገድ ነው፡፡ የአድዋን ሰንሰለታማ የሚያምር አስፓልት መንገድ እየሔድኩ ወደ ኋላ ስመለከት ተራሮቹ አሁንም የሚጠሩኝ ይመስለኛል፡፡ የጂጂን ሙዚቃ በኤርፎን ደጋግሜ እያዳመጥኩ በሐሳብና በመኪና በአንድ ጊዜ ተጓዝኩ፡፡ ብዘት ከተማ ልንደርስ ትንሽ ሲቀረን የደብረ ዳሞ መግቢያው በዚህ በኩል ነው ስላሉኝ ወረድኩ፡፡ የሚወስደኝ ባጃጅ ስጠይቅ ደርሶ መልስ አራት መቶ ብር አሉኝ፡፡ ሌላ አማራጭ እየፈለግኩ እያለ ‹‹እዚያች መኪና ውስጥ ያሉ ሰዎች እየጠሩህ ነው›› አንድ ሰው፡፡ ግራ ተጋብቼ ወደ ተባለችው መኪና ስዞር ከደባርቅ እስከ ሽሬ ያመጡኝ ሰዎች ናቸው፡፡

ስሜቴ ተደበላለቀ፡፡ ሰላምታ ሰጥዋቸው፡፡ ወደ አዲግራት እየሔዱ እንደሆነና አብረን እንድንሔድ ጠየቁኝ፡፡ በእጄ ወደ ደብረ ዳሞ እያመለከትኩ ሳላየው እንደማልሔድ ገለጸኩላቸው፡፡ ደብረ ዳሞ ገደላማ አምባ ከአስፓልት ላይ ሆነው ሲመለከቱት በጣም ቅርብ ይመስላል፡፡ ነገር ግን በግምት ከ5 ኪሎ ሜትር በላይ የሚርቅ ይመስለኛል፡፡ ጥሩ የፒስታ መንገድ አለው፡፡ በነገራችን ላይ ትግራይ ክልል ፒስታ መንገድ ያየው ይህችን ብቻ ነው፡፡ ባለመኪናዎቹ ጋር አብረን ወደ ገዳሙ ጉዞ ጀመርን፡፡ በአንድ በኩል ባጃጅ ኩንትራት ውድ ሆኖብኝ ስለነበር የእነርሱን መኪና ስላገኘው ተደሰትኩ፤ በሌላ በኩል ግን ከደባርቅ አንስቶ የሆነው እየታወሰኝ የአጋጣሚ ነገር ነው ብሎ መተው አልቻለኝ አለ፡፡ የሆነው ሆኖ በየትኛውም መልኩ ቢሆን ያለውን አጋጣሚ እየተጠቀሙ መፍትሔ መፈለግ ይሻላል ብየ አሰብኩ፡፡

የደብረ ዳሞ ገዳም ስንሔድ የኤርትራ ድንበር ጥግ ጥጉን ነው፡፡ ገዳሙ ከኤርትራ በግምት ከሦስት ኪሎ ሜትር በላይ የሚርቅ አይመስለኝም፡፡ ትልቅ የቋጥኝ ተራራ አናት ላይ ያለ አድባር ነው፡፡ የደብረ ዳሞ ገዳም በሰባተኛው ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ዘጠኙ የሶሪያ ቅዱሳን ከሆኑት በአንዱ አቡነ አረጋዊ የተገደመ ነው፡፡ ወደ ገደሙ ለመግባት የኤርትራን ድንበር ተጠግቶ በተሠራ መንገድ መጓዝ ይጠይቃል፡፡ ገዳሙ ስንቀርብ ቀጥ ብሎ የቆመ አምባ ስለሆነ ወደ ላይ የተሠሩ መወጣጫ ደረጃዎች ስላሉ እነርሱን እየተከተልን ላጥ ወደላው ገደል ቀረብን፡፡ ከተራራው አናት እስከ ታች ድረስ የሚደርሱ ከከብት ቆዳ ጠፍር የተሠሩ ሁለት ረጃጅም ገመዶች ተዘርግተዋል፡፡ አንደኛው ወፍራም ሲሆን ሁለተኛው ገመድ ግን ቀጭን የሚሳብ ነው፡፡ ከተራራው ጫፍ ላይ ያሉት መነኮሳት በወገባችን እንድናስገባውና ወፍራሙን ገመድ በእጃችን ይዘን እንድንወጣ ነገሩን፡፡

በመጀመሪያ ቀጭኑን ገመድ ከወገቤ ላይ አሰርኩትና እንዲስቡኝ ምልክት አሳየኋቸው፡፡ ከላይ ሆነው እየሳቡ መካከል ላይ ስደርስ ወደ ታች ተመለከትኩ፡፡ በኋላ ላይ ተመልሶ መውረዱን ሳስብ ፍርሃት ተጫነኝ፡፡ አልቻልኩም አልኳቸው፤ ቀስ አድርገው ወደ መሬት መለሱኝ፡፡ የመኪናዋ ሾፌር መጫኛው ውስጥ ወገቡ ገባ፤ መነኮሳቱ ሳቡት፡፡ ሔደ፤ መካከል ላይ አረፈ፤ ተራራው ጫፍ ወጣ፡፡ ከመኪናዋ ጀርባ ከእኔ ጋር የነበረው በተመሳሳይ መልኩ ተራራውን ወጣ፡፡ አለቃቸው አስቀድሞ መውጣት እንደማይፈልግ ስለተናገረ ከታች ተቀመጠ፡፡ እልህ ያዘኝና ሌሎቹ በወጡበት መልኩ እኔም ወጣሁ፡፡

እላይ እንደተቀመጥን ወደታች ስንመለከት ያስፈራል፡፡ ትንሽ እርፍ እንዳልን ሁለተኛ ሆኖ የወጣው ሰው እንቅልፍ ወሰደው መስሎ ተኛ፡፡ ከዚያ ሲስቡን ከነበሩት መካከል አንደኛው አባ ‹‹ልጄ እስኪ እሱን ልጅ እየው›› አሉኝ፡፡ እኔ ደክሞት የተኛ መስሎኝ ነበር፡፡ ለካስ አሞታል፤ የልብ ድካም ይኑርበት አይኑርበት የማውቀው የለም፡፡ ሰውነቱ እየተንቀጠቀጠ በአፉ አረፋ ይተፋ ጀመር፡፡ ደነገጥኩ፡፡ አባ ደግሞ በገመድ ተስበው ወጥተው ስለሞቱ ሰዎች ከዚህኛው ሰው ጋር እያመሳሰሉ ያወጉ ጀመር፡፡ ከዶሮ መካከል ፈንግል አይወራም የሚባለው ተረት እዚህ አልሠራም፡፡ ከሰዎቹ ጋር መገናኘቴን ረገምኩ፡፡ እንሒድ ባልላቸው ይህ ላይፈጠር ስለሚችል ለዚህ ሁሉ ነገር ራሴን ተጠያቂ እያደረግኩ ወደ ታች በቀፎ አስገብተን እናውርደውና ወደ ሐኪም ቤት በቶሎ እንድንወስደው ሐሳብ አቀረብኩ፡፡

ቀፎም የለም፤ ከሞተም እዚሁ ይቀበራል አሉ አባ፡፡ ውሃ ስንደፋበት ቆይተን ትንሽ መለስ አለለት፡፡ እግዚአብሔርን አመስግነን ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ጫፍ ወጣን፡፡ ይህ ቦታ ከተራራው አናት ላይ ሰፊ ሜዳ አለው፡፡ ነገር ግን ዙሪያውን ለማናቸውም አይነት ፍጥረት የማይመች አደገኛ ከደል ነው፡፡ ከብቶችን እንዴት አድርገው እንዳስገቧቸው ባላውቅም ከላይ አግኝተናል፡፡ የመነኮሳቱ መኖሪያ የጥንት ከተማ ይመስላል፡፡ በድንጋይ ግንብ የተሠሩ ብዙ ቤቶች አሉ፡፡ አቡነ አረጋዊ ያረጉበትንንና ዙሪያውን ገደላ ገደሉን ስናይ ደስ የሚል ውበት አለው፡፡ አቡነ አረጋዊ ይህን ቦታ መምረጣቸው ከብዙ መልኩ ሳይጠቅማቸው አልቀረም፡፡ አንደኛ ከሰው ንክኪ ርቀዋል፤ ስለሆነም ስለአምላካቸው ብቻ ያስባሉ፡፡ ሁለተኛው ግን የደህንነት ስጋት አይኖርባቸውም፡፡ ሌባም ቀበሌም አይደርስም፡፡ ሜዳው ላይ ቋጥኞች ወደታች ጠልቀው ተቆፍረው ለዝናብ ውሃ ማጠራቀሚያነት ይውላሉ፡፡

ከተራራው አናት ላይ ተሁኖ ብዙ የኤርትራ የገጠር መንደሮች በቅርበት ይታያሉ፡፡ እንደ አባ ከሆነ ኤርትራውያን ቤተሰቦች የይለፍ ወረቀት ተሰጥቷቸው ወፍጮ እዚሁ ሠፈር እየመጡ ያስፈጫሉ፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እፊታችን ያለውን ተራራ አልፎ እነሱ መሬት ውስጥ መስፈሩን ሰማን፡፡ ከተራራው አናት ላይ ከወጣንበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ታች መውረዱ ሐሳብ ቢሆነንም እላይ መቆየት ግን ያስደስታል፡፡ ጀምበር በአድዋ ተራሮች አናት ሥር እየገባች ነው፤ እኛም ወደ አዲግራት መሔድ አለብን፡፡ የታመመውን ወዳጃችንን ይዘን በወጣንበት መልኩ እነ አባ ቀስ አድርገው ወደ መሬት ላኩን፡፡ መነኮሳቱ በቀን በቀን ብዙ ሰው ሲሸከሙ እየዋሉ ለአገልግሎታቸው እንኳ ገንዘብ የማይጠይቁ ትሁታን ናቸው፡፡

ታሞ በነበረው ልጅ እየቀለድን የፒስታዋን መንገድ ይዘን ወደ አዲግራት ጉዞ ጀመርን፡፡ ሙሉ በሙሉ ጨለማ ነው፡፡ ወደ አዲግራት እንደምትወስደን አባ ባያረጋግጡልን ኖሮ ወደ ኤርትራ የገባን ይመስለን ነበር፡፡ በግምት ለአንድ ሰዓት ተኩል ያክል እንደሔድን የታጠቁ ወታደሮች እንድንቆም በትግርኛ መመሪያ ሰጡን፡፡

አዲግራት፣ ኢትዮጵያ

Filed in: Amharic