>

ከአዲግራት እስከ መቀሌ የመጨረሻ ክፍል [ሙሉቀን ተስፋው]

Muluken Tesfaw KelemQend journalistከደብረ ዳሞ ወደ አዲግራት ስንሔድ የተጠቀምነው መንገድ ወደ ኤርትራ ድንበር የተጠጋ በመሆኑ ከጨለመ በኋላ ይዘጋ ነበር፡፡ ሆኖም እኛ ሳናውቅ ሔድንና የመከላከያ ሠራዊት አስቆመን፡፡ በዕውነቱ ሳናውቅ የኤርትራ ድንበር ውስጥ የገባን መስሎን ነበር፡፡ መከላከያ ሠራዊት ከጠየቀን በኋላ ፈትሾን፤ ባለመኪናዎቹም የሆነ ወረቀት አሳይተው አለፍን፤ ከመሥሪያ ቤታቸው የተጻፈ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምሽት 2፡30 ሲሆን አዲግራት ገባን፡፡

ያደርኩበት ሆቴል የሞይባል ቻርጅ ማድረጊያ ተበላሽቶ ስለነበር ስልኬ ባትሪ ጨርሷል፡፡ አብረውኝ የመጡትን ሰዎች ስልክ ተቀብዬ እነርሱ ሥራቸውን እስኪጨርሱ ድረስ ልጠብቃቸው ተነጋግረን ተለያየን፡፡ በጠዋት ወጥቼ የአዲግራት ከተማን በእግሬ መዞር ጀመርኩ፡፡ የአዲግራት ከተማ ከኤርትራ ከ30 ኪሎ ሜትር ያነሰ ርቀት አለው፡፡ ሕንጻዎቿ የሚገርሙ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ እየተሠሩ ያሉ ረጃጅም ሕንጻዎች አስመራን ወደ ታች እያዩ ለመቆጣጠር የታሰቡ ይመስላሉ፡፡ በእርግጠኛነት የአስመራ ከተማ እንኳን ባይሆን ድንበር አካባቢ ያሉ ኤርትራዉያን የአዲግራትን ሰማይ ጠቀስ ፎቆች በቅርብ ቀን ወደ ላይ አንጋጠው እየተመለከቱ በቅናት እርር ማለታቸው አይቀርም፡፡ አንዳንዶቹ ረጃጅም ፎቆዎች መለስተኛ ኮረብታዎችን ያስንቃሉ፡፡ በአዲግራት ከተማ ውስጥ ለውስጥ በእግሬ የምችለውን ያክል እስከ አምስት ሰዓት ድረስ ዞርኩ፡፡ አንድም ኮብል ስቶን አሊያም አስፓልት ያልተነጠፈ መንገድ አላየሁም፤ አንድም እንኳ በብሎኬት አሊያም በድንጋይ ያልተሠራ የመኖሪያና የመንግሥት መሥሪያ ቤት የለም፤ ቀበሌም ቢሆን፡፡ አውቶቡስ ተራ ፊት ለፊት ካሉ ቁርስ ቤቶች ቀማመስኩ፡፡ ምርጥ ምርጥ ፉል ያዘጋጃሉ፡፡ እዚህ ድረስ ያመጡኝ ባለመኪናዎች ጋር እንደተለያየን ነው፡፡ ስልኬ ባትሪ ዘግቷል፡፡ ደግሞ እኔ እደውላለሁ ብየ ስልካቸውን ተቀበልኳቸው እንጅ ለእነርሱ አልሰጠዋቸውም፡፡ ወደ መቀሌ አብረን እንደምንሔድ ተነጋግረን ነበር፤ ነገር ግን ቃል አፈረስኩ፡፡ እስካላገኙኝ ድረስ እኔም ላላገኛቸው ወሰንኩ፡፡

ስድስት ሰዓት ሲሆን ወደ መቀሌ መኪና ያዝኩ፡፡ ከአዲግራት ጀምሮ እስከ መቀሌ ድረስ አንድም ለዓይን የሚገባ ነገር የለም፡፡ ሁሉም ድርቅ ያለ መሬት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ስንቃጣ ከተባለችው ከተማ ጀምሮ ያለው በድርቅ የተጎዳ ነው፡፡ የታቆሩ የውሃ አካላት ሁሉ ደርቀዋል፡፡ በርካታ የውሃ ማቆሪያ ጉድጓዶች ጥቁር ብለው ይታያሉ፡፡ በትግራይ ክልል በተፈጥሮ ሀብት ሥራ ተራሮች ሁሉ አረንጓዴ እንደለበሱ ተደጋግሞ የሚሰማ ጉዳይ ቢሆንም የአንድ ዓመት ድርቅን ግን መቋቋም የቻሉ አይደለም፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይማ ሕይወት ራሱ ያለበት አይመስልም፤ ጭልጥ ያለ በርሃ ይሆናል፡፡ ድርቁ የከፋ እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ የሚገርመው ግን ወደ ከተሞች ስንገባ የተፈጠረብን ምስል ወዲያውኑ ይጠፋል፡፡ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ሁሉ በነጻ ቢያቀርቡ ያን ያክል ሕንፃዎች መሥራት የሚያስችል አቅም አላቸው እንዴ ያስብላል፡፡ ከእዳጋቡና አንስቶ እስከ መቀሌ ባሉ ከተማዎች የሕንፃ ችግር አላየሁም፡፡

ነጋሽ የምትባል ትንሽ ከተማ ደረስን፡፡ ነጋሽ ከተማ ከላይ የነጋሽ መስጂድ አለ፤ ከአስፓልት ወደ ታች ዝቅ ብላ ማርያም ቤተ ክርስቲያን አለች፡፡ ሆኖም ግን መቶ ሜትር ባትሞላ ርቀት ላይ ያሉት የነጋሽ መስጊድና የማርያም ቤት ክርስቲያን ፈጽሞ አይታያዩም፡፡ ገለጻ እንዳደረጉልኝ ሰዎች ‹‹እንግዲህ እኔና አንተ ነጋሽና ማርያም ነን›› ካሉ ዳግም ላይገናኙ ተለያይተዋል ማለት ነው፡፡
የውቅሮ ከተማ እየበቀሉ ያሉ ሕንጻዎች የሪል ኢስቴት ግንባታ ይመስላሉ፡፡ የወረዳ ከተማ ቢሆንም የሚካሔዱት ግንባታዎች ገራሚዎች ናቸው፤ ደስ ይላሉ፡፡ ከውቅሮ የተወሰነ ኪሎ ሜትሮችን ሒደን ከተራራው አናት ላይ ሆነን መቀሌን ከጫፍ እስከ ጫፍ አየነው፡፡ እንኳን ወደ ሰሜናዊቷ ኮከብ መቀሌ በደህና መጣችሁ የሚል ጥቅስ ባላይ ኖሮ እንዲህ ያለ ከተማ እኛ አገር ያለ አይመስለኝም ነበር፡፡ የመቀሌ ከተማ ስፋት አዲስ አበባን ሳይጨምር ሁሉም የክፍለ አገር ከተሞች የሚበልጡት አይመስለኝም፡፡

በሰሜን በኩል ካለው መናሐሪያ ወርጄ ከተማ ታክሲ ያስኩ፡፡ መቀሌ ያለ አንድ ወዳጄን ደወልኩለትና ተገናኘን፡፡ ሮማናት አደባባይ አካባቢ ምሳ ለመብላት እሔድን እያለ ወደ ተራራው ቀና ብሎ ‹‹መድኃኒ ዓለምን አየኸው?›› አለኝ፡፡ ምናልባት ከተራራው አናት ላይ ቤተ ክርስቲያን ያለ መስሎኝ የታል? አልኩት፡፡ እንደሳስላሴ ወደ ሚባለው ኮረብታ ቀና ስል ቼጎቬራን የሚመስለው የመለስ ፎቶ ቢልቦርድ በትልቁ ይታያል፡፡ ሳቅ ብየ አስተዋልኩት፡፡ የመቀሌን ከተማ መለስ ከጫፍ እስከ ጫፍ እያየ አለ፡፡ ከየትኛም የከተማው ክፍል ብትሆኑ ያን ቢል ቦርድ ታያላችሁ፡፡ በጣም የሚገርም ነው፡፡ ቢል ቦርዱ ያለበት ቦታ ከጣሊያን ጋር በተደረገው የመቀሌ ጦርነት በርካታ ነፍሳት የረገፉበት እንደሆነ ለማወቅ ችያለሁ፡፡ አሁን የመሌ አጽሙ ሳይሆን ምስሉ አርፎበታል፡፡ ፎጋሪዎች ደግሞ ‹‹የሕወሓትን መድኃኒ ዓለም አየኸው?›› እያሉ ይቀልዱበታል፡፡

የከተማውን አብዛኛውን ክፍል ለማየት ቶስ ሒልሰ የተባለው መዝናኛ ጋ መሔድ የግድ ይላል፡፡ ቶፕ ሒልስ ሆኘ ወደ ታች መቀሌን ባስተዋልኩ ጊዜ አዲስ አበባ ብሔራዊ የሚባለውን አካባቢ መሰለችኝ፡፡ ብሔራዊ አካባቢ የሚወጡት ትልልቅ የንግድ ባንኮች ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች እዚያም አሉ፡፡ እዚያ ባለቤቶቹ ባንኮች አይደሉም፡፡ መቀሌ ከአዲስ አበባ የተለየችው ከሕንፃዎቹ ጀርባ ቆሻሻ አለመኖሩ ነው፡፡ በአጪሩ መቀሌ ማለት ብዙ ሃያ ሁለቶች፣ ብዙ ቦሌዎችና ብዙ አያቶች ተሰባስበው በአንድ ላይ ያሉባት ምርጥ ከተማ ማለት ነች፡፡ ያለ ምንም ማጋነን የናዝሬት፣ የአዋሳና የባህር ዳር ምርጥ ምርጥ ግንባታዎች በአንድ ላይ ቢሸከፉ መቀሌን አይስተካከሉም፡፡ ከተማዋን እየዞርኩ ሳይ በጣም ገረመኝ፡፡ መቀሌን ስመለከት ሁለት የተቃረኑ ስሜቶች መጡብኝ፡፡ አንደኛው አገራችን እንዲዚች ያለች ከተማ ባለቤት መሆኗ ደስ አለኝ፡፡ ቶፕ ሒልስ በታች መንገድ ዳር እንዲሁም በተለያየ ርቀት የሞሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካን ጨምሮ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ይታያሉ፤ ይህን ማዬት ያስደስታል፡፡ እንደ አንድ አገር ስናስብ የአገርን እድገት የሚጠላ ስለሌለ፡፡ ምንም ያክል ቢሠራ በሃያ አምስት ዓመት ይህን ያክል ለውጥ መፍጠር እንደሚቻል ለመገንዘብ መቀሌ አሪፍ ማሳያ ናት፡፡ የኢኮኖሚ ምሁራኖቻችንና ፖለቲከኞቻችን የሩቅ ምስራቅ ኤዥያ አገሮችን ልምድ ለመቅሰም እዚያ ድረስ ከሚደክሙ መቀሌን መጎብኘትና ልምድ መወሰድ የሚመከር ይሆናል፡፡ ሕወሓቶችም ቢሆኑ ፖለቲከኞቻችን ሩቅ ሩቅ ከሚያሳዩዋቸው የትግራይን ልምድ እንዲወስዱ ቢያደርጉ መልካም ነበር፡፡

ወዲያው ግን ልዩነቱን ስገነዘብ ግልጽ አፓርታይድ ሆኖ ታየኝ፡፡ መንገዶቹን፣ ሕንጻዎቹን፣ ትምህርት ቤቶቹን፣ ሁሉንም ዓይነት መሠረት ልማቶች ስመለከት ድንበር አቋርጨ ሌላ አገር የገባሁ መሰለኝ እንጅ እዚሁ እኛ አገር እንዳለሁ መቁጠር ከበደኝ፡፡ መቀሌ ከተማ የውስብስብ (ኮምፕሌክስ) ሕንጻዎች ባለቤት ናት፡፡ ቀዳማይ ወያኔ የሚባለው የገበያ አዳራሽ ድንቅ ነው፡፡ በየትኛውም አቅጣጫ ብትሔዱ ምርጥ መንገዶችና ሕንጻዎች ላይ ዓይናችሁ ያርፋል፡፡ ቀበሌ 16 የሚባለው አካባቢ ጥሩ ጥሩ መንገዶች ቢኖሩም መንዶቹ ከመኪናዎች ይልቅ ለወጣቶች አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ የመቀሌ ወጣቶች ቀበሌ 16 መንገዶችን ሁሉ ዘግተው በረንዳ ላይ መጠጥ ሲኮመኩሙ ያስቀናሉ፡፡ መንገዶቹ ዳር ያሉ ዛፍ ሥሮች ሁሉ የበረዳ መጠጫ ቤቶች ናቸው፡፡

ወደ መቀሌ የሔደ ሰው ብዙ ጊዜ ሲያወራለት የምሰማው ሙስና ስለሚባለው ሰፈር በመሆኑ በታክሲ ሔድኩ፡፡ አዲሐቂ ክፍለ ከተማ ነፋሻማው የመኖሪያ አካባቢ መቀሌዎች የሙስና ሠፈር እያሉ ይጠሩታል፡፡ ዩንቨርሲቲው ጫፍ ድረስ በታክሲ ሔድኩና ወደ ሠፈር መካከል በእግሬ ገባሁ፡፡ አጃኢብ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ምርጥ ግንባታ የተጠራቀመበት አካባቢ አላየሁም፡፡ ብዙዎቹ ሕንጻዎች ተሠርተው በዘበኛ ብቻ ይጠበቃሉ እንጅ ሰው አይኖርባቸውም፡፡ ለምን ሰው እንደማይኖርባቸው ስጠይቅ ‹‹ባለቤቶቹ ወደ እናንተ አገር ሒደዋል!›› አሉኝ፡፡ ብዙዎቹ ሕንጻዎች የተገነቡት ለክፉ ቀን መጠባበቂያ ይመስላል፡፡ ይህን ሰፈር ስመለከት ትዝ ያለኝ የፍካሬ ኢየሱስ ትንቢት ነው፡፡ ጥሩ ጥሩ ቤቶች ይገነባሉ፤ ነገር ግን የሚኖሩባቸው ሰው አይኖርም እንዳለው፡፡ እዚህ ያሉ ቤቶች ምናባዊ ውበት አላቸው እንጅ ገጽታቸውን ለመግለጽ እንደሆሜር የሥነ ጽሑፍ ሊቅ መሆን ያሻል፡፡ በዕውነቱ ከሆነ ይህን የመሠለ አገልግሎት የማይሰጥ ሀብት ለማከማቸት ስልሳ ሽህ ሰው መገበር ምንም አይደለም፡፡ በእርግጥ ሰው ለነጻነት እንጅ ለዝርፊያ ባይሞት ጥሩ ነበር፡፡ አቤት የቤቶቹ ዲዛይን! አቤት ግንባታ! አጃኢብ ነው፡፡ የአንዱን ሕንፃ ውበት ለመግለጽ በራሱ ድካም ነው፡፡

ዩንቨርሲቲው ፊት ለፊት የሰማዕታት ሐውልት አለ፡፡ ይህ ሐውልት ማንም አይደፍረውም አሉ፡፡ ለምሳሌ ያክል የከተማው ማስተር ፕላን መንገድ ሲስተካከል በስተደቡብ በኩል ያለውን አጥር በትንሹ ሊፈርስ ሆነ፡፡ እንዴት ተብሎ! የዚህ ግቢ አንዲት ኢንች አጥር መንካት የፈጣሪን ሕግ ከመሻር በላይ የከበደ ነው፡፡ ሆኖም እኔ እዚያው በነበርኩበት ወቅት አጥሮ ተደፍሮ አየሁት፡፡ በአዲስ አበባ ‹‹ቀይ ሽብር›› የሚባለው ሲኖትራክ መኪና ግንቡን ደረማምሶት ተላትሞ ቆሞ ነበር፡፡ ምናልባትም የሕወሓትን የሰማዕታት ሐውልት የደፈረ የመጀመሪያው ‹‹ጀግና›› ሳይሆን አይቀርም፡፡

የአገራችን ምርጥ ምርጥ ነገሮች እዚች ከተማ አሉ፡፡ በመቀሌ ሦስት የመንግሥት ሆስፒታሎችን አይቻለሁ፡፡ የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል ግን አምሳያ የለውም፡፡ እንደ ሕንጻውና ግቢው ማማር ከሆነ እንኳን በሽታን አክሞ ማዳን ነፍስንም መሥራት አይሰነውም፤ ሆስፒታል እንደዚህ እንደሚሠራ በእኛ አገር ያየሁት እዚህ ነው፡፡ የመቀሌን ጠቅላላ ሆስፒታል ወደ ቶፕ ሒልስ መዝናኛ የኩዊሓ ጠቅላላ ሆስፒታል ደግሞ ወደ አየር መንገድ ስሔድ ነው ያየዋቸው፡፡

ቀበሌ 16 ቡና ልጠጣ ስሔድ የዓረናን ቢሮ አየኋት፤ ክርችም ብላ ተዘግታለች፡፡ ሁለት ቀን ያክል በአካባቢው ስመላለስ አንድም ቀን ተከፍታ አላየኋትም፡፡ እዚሁ ሰፈር የሰማውት ነገር ግን ገርሞኛል፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡

አንድ የሕወሓት የናጠጠ ሙሰኛ ሀብታም በወንጀል ተፈርዶበት መቀሌ ማረሚያ ቤት ይታሰራል፡፡ ሰውየው ይታሰር እንጅ እንቅስቃሴው የተገደበ አይደለም፡፡ እስረኛው መኪና እያሽከረከረ ከወደ ውቅሮ አካባቢ ሲመለስ አንድ ሰው ይገጫል፡፡ ተከሶ ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡ ዳኞችም ተገርመው ‹‹ተከሳሽ እኮ ቀድሞ በፈጸመው ወንጅል ታስሯል!›› አሉ፡፡ ልብ በሉ የታሠረ ሰው መኪና እያሽከረከረ ነው የገጨው! ቀበሌ 16 ባሉ ቡና ቤቶችና ግሮሰሪዎች ከብዙ ሰው አፍ የምትሰማ ነገር ነች፡፡

መቀሌን ትቻት ልወጣ የቀሩኝ ሰዓታት ብቻ ናቸው፡፡ የአውሮፕላን የበረራ ጊዜ ከመድረሱ ቀደም ብዬ ወደ ኩዊሓ ታክሲ ያስኩ፡፡ ኩዊሓ የምትባለዋ ከተማ በስም ትንሽ የገጠር ቀበሌ ትመስለኝ ነበር፡፡ የወታደር ካምፕና የተለያዩ ፋብሪካዎችን አልፌ እንደጉድ እንደሙስና ሰፈር አካባቢ ባሉ ቤቶች ያሸበረቀች ሆና አገኘዋት፡፡ ያው እንደነገርኳችሁ በትግራይ የሕንጻ ችግር የለም፡፡ በተፈጥሮ ሀብት ልማት ከተመለሰው የአካባቢ ጥበቃ ይልቅ በግንባታ የተሸፈነው የትግራይ መሬት ልዩ ነው፡፡ ከተከዜ እስከ መቀሌ ድረስ ባሉ ቦታዎች ሁሉ የትምህርት ቤቶች አሠራር የተለየ ነው፡፡ በገጠርም በከተማም አንድም ደረጃውን ያልጠበቀ በእንጨት የተሠራ ትምህርት ቤት አላየሁም፡፡ ቢቻል የሚያምር ፎቅ አሊያ ደግሞ የብሎኬት ግድግዳ አለው፡፡ ይህ ነገር በእርግጥ በሌሎች ክልሎች ስዞር አላየሁትም፡፡ የገጠሩን ብንተወው እንኳ በትልልቅ ከተማዎች ራሱ አብዛኛዎቹ የጭቃ ቤቶች ናቸው፡፡

ኩዊሓን ትንሽ ዘወር ዘወር ካልኩ በኋላ ‹ለጥነኑ› ውኃ ገዝቼ ጠጣሁ (ጥነን አንድ ሰው እንግድነት ሒዶ ቤት ሳይቀምስ ከወጣ አንገቱን ይታመማል የሚባል ልምድ አለ፤ ከዚያም የታመመው አንገቱን እንዲሻለው በሌሊት ሳይቀምስ የወጣበትን ቤት በድንጋይ መደብደብ አለበት)፡፡ እናም እኔ ጥነን ታምሜ ድንጋይ ከምወረውር ውኃ ጠጥቼ መውጣት አይሻልም? ወደ አሉላ አባ ነጋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በእግሬ ጉዞ ጀመርኩ፡፡

የመቀሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከቦሌ አየር ማረፊያ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ልዩነቱ በግርማ ሞገስ አሉ አባ ነጋ እንደ እምየ ምኒልክ ሐውልት ፊት ለፊት ከነፈረሱ አለ፡፡ ምሽት 2፡00 ሲሆን ጥያራው ተነሳ፤ መቀሌን ወደ ታች ተመለከትኳት፡፡ የጎዳና መብራቶቿ መብራቶቿ ጨረቃ ላይ ይዘባበታሉ፡፡
አበቃሁ!!

 

Filed in: Amharic