>
5:52 am - Tuesday July 5, 2022

ሃበሻ በምድር ወገብ የስደት ህይወቱ፣ ያሳዝናል አስተዋሽና መፍትሄ ሰጪ ማጣቱ [ፔን ዘ ኢትዮጵያ ከምድር ወገብ ኡጋንዳ]

Journalist Dereje Begashaw Uganda
በኡጋንዳ ዕድሜያችን እየተበላ ላለን ትክክለኛ ሃገር አልባ ስደተኞች የተሰማኝን ጽፌያለሁ።
ስደት ፋሽን ነው ሊባል ምንም ባልቀረበት  በዚህ ዘመን  ሁለት ሺ ኪሎ ሜትር አቆራርጦ የእግርና  የመኪና ጉዞ አደርጎ ምድር ወገብ ዩጋንዳ የሚገባ ሃበሻ ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም።የስደት ምክንያቱ ብዙ ቢሆንም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች የስደት ዋነኛ ምንጮች ናቸው።በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት በደረሰባቸው ወከባና መሳደድ ወደዩጋንዳ ለሚመጡ ሁሉ ኡጋንዳ በሯ ክፍት ነው!ለዚህም ነው ዛሬ የምስራቅ አፍሪቃ የስደተኞች ማዕከል የሆነችው።ካምፓላ ብቻ ያለ የምስራቅ አፍሪቃ ሃገራት ስደተኛ ከ75 ሺ በላይ ነው። ኤርትራዊያን ከ 10 ሺ እንደማያንሱ ሲነገር ኢትዮጵያዊያን 1 ሺ አካባቢ እንደምንደርስ ስታስቲካዊ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የስደተኛ መታወቅያውን የያዘ ሁሉ ማለቴ ነው።
ከትውልድ አገራቸው እስራትና ሰቆቃ ሸሽተው የወጡ እንዳሉ ሁሉ ለምን እንደወጡ እንኳ ለመመለስ የሚቸገሩ የመታወቅያ ስደተኞችም አሉ። ለሽርሽርና የተሻለ ህይወት ፍለጋ በዩጋንዳ አድርገው ወደሌላ ሃገር ለመጓዝ የሠዓታት በረራ አድርገውም አልጋ ባልጋ የገቡና የስደተኝነት ካባ የደረቡም እንደዚሁ። ዩጋንዳ በዘላቂነት ለመኖር ብለው የመጡ ግን ደርዘን የሚሞሉ አይመስሉኝም።የመኖርያ ፈቃድ ለማግኘት በኬዝ ደራሲያን የተዘጋጀላቸውን ታሪክ ባግባቡ ተጫውተው አሳይለም ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ  የመኖርያ ፈቃድ {ፉል ስታተስ} ለግዜው የሚያኖር ወረቀት ያገኙ በርካቶች ናቸው። ጮማ የሆነ ኬዝ እያላቸው ታሪካቸውን ባግባቡ የሚጽፍላቸውና የሚያስተረጉምላቸው አጥተው ያለመኖርያ ፈቃድ የሚኖሩና ወረቀቱን ለማግኘት ለዓመታት የሚዳክሩም ቀላል ቁጥር የላቸውም።
ካታ ርትራዊያንና ባሁኑ ወቅት ሺ መድረሳችን ቢያጠራጥርም ኢትዮጵያዊያን በዩጋንዳ መሬት ላይ በስደተኝነት ተመዝግበው አቅሙ የሌላቸው በካምፕ በቆሎ ተሰፍሮላቸው የሰቆቃ ህይወት ይገፋሉ።ከ 5 እስከ 8 ዓመት ቆይተውም ዕድላቸው ከቀና  በብዙ ድካምና ተማጽኖ ዩኤን ኤችሲአር ሶስተኛ ሃገር ሊሰጣቸው ይችላል።ገቢ ያላቸው ግን በመረጡት ከተማ ቤት ተከራይተው መኖርና በግል ስራ መሰማራት መብታቸው ነው ።በተለይ የመኖርያ ፈቃድ ያገኙ ስደተኞች በዩጋንዳ ለመኖር ይህ ነው የሚባል ችግር ከመንግስታዊ ተቋማት አይደርስባቸውም። በፈለጉበት ጊዜና ሰዓት በነጻነት መንቀሳቀስ ይችላሉ። በካምፕ መኖር ግን በገቢ እጦት እጅግ ከባድ መሆኑን የቀመሱት ይናገራሉ። በካምፓላ  የሚኖሩ ስደተኞች ግን ወይ ዘመድ አልያም ጓደኛ በወር ከ200 ዶላር ያላነሰ ገንዘብ ከላከቸው ቢያንስ ሳይራቡ ቤት ተከራይተው መኖር ይችላሉ። የስራ ዕድል ላገሬውም ብዙም በሌለበት ካምፓላ ሃብታም ሃበሾች ጋር እየሰሩ ከ100ዶላር ያላነሰ ገቢ እያገኙ የሚኖሩ ጥቂቶች አሉ። ከዛ ውጪ ምንም ገቢ ሳይኖራቸው የከፋ ህይወት የሚኖሩና በረንዳ የወደቁ ፣በጫትና በመጠጥ ሱስ የተዘፈቁ በርካቶች ናቸው። አካላቸው ኡጋንዳ ሆኖ ነፍስያቸው ካናዳን በማሰላሰል ኪሏቸው ያሽቆለቆለና የወጣትነት ውበታቸው የተመጠጠ ወገኖች ቁጥር የዋዛ አይደለም።
”ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል እንደሚሉት” በረሃብና በበሽታ ማቀው እዚሁ አፈረ ተጭኗቸው የቀሩም አሉ።
ወደደቡብ አፍሪካና አውሮፓ ጨደዳ {በደላላ በባህር ወይም በአየር} ለመሞከር ከ5 እስከ 10 ሺ ዶላር ስለሚያስፈልግ ኢትዮጵያዊያን ከዚህ ጨዋታ ውጪ ነን።
የዩጋንዳ መንግስት የሚሰጠው የስደተኞች የመኖርያ ወረቀት{ፉል ስታተስ} ለግዜው ስራ አግኝቶ ሰርቶ ለመኖርም ሆነ የራስን መጠነኛ ቢዝነስ ለማከናወንወይም ወተሻለ 3 ተኛ ሃገር ለመሻገር  እጅግ ወሳኝ ነው።ዘመድ ያለው የካናዳ ፕሮሰስ ዕድል ለመሞከርና ከ4 እስከ 5 ዓመት ደጅ ጥናት {ፕሮሰስ} በኋላ ለመሻገር ወረቀቱ የግድ አስፈላጊ ነው።
ወደሌላ ሃገር ለመሸጋገር የሚያስችል ሌላው መንገድ ጋብቻ ነው ።ውጭ የኖረ ሴት ወይም ወንድ ዩጋንዳ መጥታ ወይም መጥቶ ጋብቻ ፈጽመው   ከ1 አመት እስከ 2 አመት በሚቆይ ፕሮሰስ ወዳሰቡት ሃገር መብረር ይቻላል።
ይህን ዕድል ለመጠቀም ታዲያ ስደተኛው ወይም ስደተኛዋ {ፉል ስታተስ} ሊኖራቸው ይገባል።
 በዩኤን ኤችሲአር ሶስተኛ ሃገር ባሁኑ ግዜ ማግኘት ዘበት አልያም የቶንቦላ ባለዕድል እንደመሆን ይቆጠራል።ጥቂት የማይባሉ የምር ስደተኞች ጉዳያቸውን አይቶ የሚረዳቸውና ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጣቸው  አካል በማጣት ትርጉም የለሽ ህይወት ይኖራሉ። ሃገራቸው መግባት የማይችሉት በተለይ ወርቃማ ዘመናቸው እየተበላ ነው።ራሴንም ጨምሮ።
ኬንያ ያሉ የረጅም ዘመናት ስደተኞች በዩኤንኤችሲአር አማካኝነት መፍትሄ እያገኙ ወደ 3 ተኛ ሃገር ሲሻገሩ ዩጋንዳ ያሉት ግን ከወጣትነት ዘመነ ወደ አረጋዊነት ብቻ ነው የሚሸጋገሩት። ያም አምላክ የለገሳቸው የዕድሜ በረከት ነው።ከ70 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው ስደተኛ አጋጥመውኛል። ዘወትር እንደቤተክርስቲያን የሚመለከታቸው አካላት ቢሮ ቢመላለሱም ያገኙት መፍትሄ የለም።ያበዱ ወገኖችም አይቻለሁ።በቅርቡ በሃኪሞች ቦርድ የውጪ ሃገር ህክምና እንዲያገኝ የተጻፈለት ወገናችን ከስድስት ወር በላይ ተመላልሶ ምንም መፍትሄ ሳያገኝ ህይወቱ አልፎ እዚሁ ቀብረነዋል።
ከ25 ዓመት በላይ በዩጋንዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንንም አነጋግሬያለሁ። በዩኤንኤችሲአር ተስፋ ቆርጠው የዕለት ጉርስና መጠለያ ፍለጋ ሲዳክሩ ኖረዋል።ነገ የሚባል ተስፋ ከአምላካቸው በቀር ማንም አይሰጣቸውም። ኡጋንዳ እንደ ሃገር ከሌሎች ጎረቤት ሃገራት ለስደተኛ ምቹ ናት ለማለት ቢቻልም ያለገቢና ሥራ ለመኖር እጅግ አስቸጋሪ በመሆኗ ለኛ ችግር መፍትሄ ለማግኘት ዓለም አይንና ጆሮውን መቼ እንደሚከፍትና ስንት ዘመን መጠበቅ እንዳለብን የሚነግረን ነብይ ነው ያጣነው።
ኢትዮጵያ ለአፍሪቃ በአርያነት የምትጠቀስ አልነበረችምን? ዛሬ በስደት ዓለምን በማጥለቅለቅ ቀዳሚ ባንሆን ተከታይ መሆናችንን ልብ ልንለው ይገባል። በተለይ የኛ ኢትዮጵያዊያንን ዕንባ የሚያብሰው ተቋም የቱ ይሆን? ስል እየጠየኩ መግቢያ ለሌላቸው የኔ ብጤ ስደተኞች አምላክ በምህረቱ ያስበንና ባለሃገር ያድርገን እያልኩ በመለመን የምድር ወገብ የስደት ህይወታችንን አጭር ዳሠሳ እቋጫለሁ።
ቸር እንሠንብት
ፔን ዘ ኢትዮጵያ ከምድር ወገባይቱ ኡጋንዳ
Filed in: Amharic