>
12:37 am - Thursday July 7, 2022

ደቡብ ሱዳን፤ ነፃነትና ጦርነት ጁባ ላይ [ነጋሽ መሐመድ]

ባንዲራ ሲሰቀል፤ ሲጨፈር-ሲቦረቅ አንጋፋዉ የአማፂያን መሪ ያሉ-ያደረጉት እዉን ሆነ አስኝቶ ነበር። ዳር ግን አልዘለቀም።በጦርነት የኖረችዉ ግዛት ነፃ ሐገርም ሆና ከጦርነት አልተላቀቀችም።የጋራንግ ወራሾች፤የነፃነት ድግስ ፈንጠዝያዉ ሳያበቃ መጀመሪያ ከሰሜን ጠላቶቻቸዉ (ከሱዳን)-አከታትለዉ እርስ በርስ ይዋጉ ገቡ። ደቡብ ሱዳን የዛሬ-አምስት ዓመት የከትናንት በስቲያዉ ቅዳሜ ዕለት የነፃነት መዝሙር ሲዘመርባት፤ የድል ደስታ ፌስታ ሲዘፈን ሲደለቅባት፤ የሠላም፤የእድገት ብልፅግና ተስፋ ሲንቆረቆርባት ነበር።ጁባ።ደቡብ ሱዳን።ዘንድሮ ክላሺንኮቭ-መትረየስ ያስካካባት፤ መድፍ- ሔሊኮብተር ይደቀደቅባት ይዟል።

አዲሲቱ አፍሪቃዊት ሐገር አዲስ ነፃነቷም፤ አዲስ የሠላም ዉሏም ቅንቅን ሆኖባት፤ ለዘንተ-ዓለም እንደኖረችበት አምስተኛ ዓመት የነፃነት በአልዋን በአስከሬን ቆጠራ ዘከረች።የአፍሪቃዉን ጥረት፤ የሐያላኑ ዛቻ ማስፈራሪያ ባከነ። ለምን? እንዴት? መጀመሪያ ሐገር ነበር።ሐገር እሳቸዉንና ብጤዎቻቸዉን አበቀለ።ኮሎኔል ዶክተር ጆን ጋራንግ ደ ማቢዮር። እሳቸዉና ብጤዎቻቸዉ አመፅና ዉጊያን አቀጣጠሉ።ዉጊያዉን ለአርባ ዓመት ያክል አሉት፤ አሉት እና አሉ፤ «ከእንግዲሕ ጦርነት የለም።» 2005 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሮጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።«በዚሕ የሠላም ሥምምነት መሠረት ከእንግዲሕ በንፁሕን ሕፃናት እና ሴቶች ላይ ከሰማይ የሚወርድ ቦምብ አይኖርም።ከእንግዲሕ የደስተኛ ሕፃናት ሳቅና ቡረቃን የምናይ-የምንሰማበት፤ ሰላምና ደስታ ተነፍገዉ የነበሩ ሴቶችን እልልታ የምንሰማበት ሠላም ይሰፍናል።» ጋራግ እንደ ጦር መሪ የተዋጉ-ያዋጉ፤ እንደ ፖለቲከኛ የተመሳጠሩ፤እንደዲፕሎማት የተደራደሩለት ነፃነት ሲታወጅ ለማየት በርግጥ አልታደሉም።

South-Sudan-violence-በስድስተኛዉ ዓመት ጁባ ላይ ባንዲራ ሲሰቀል፤ ሲጨፈር-ሲቦረቅ አንጋፋዉ የአማፂያን መሪ ያሉ-ያደረጉት እዉን ሆነ አስኝቶ ነበር። ዳር ግን አልዘለቀም።በጦርነት የኖረችዉ ግዛት ነፃ ሐገርም ሆና ከጦርነት አልተላቀቀችም።የጋራንግ ወራሾች፤የነፃነት ድግስ ፈንጠዝያዉ ሳያበቃ መጀመሪያ ከሰሜን ጠላቶቻቸዉ (ከሱዳን)-አከታትለዉ እርስ በርስ ይዋጉ ገቡ። ጋራንግ በርግጥ የአማፂ መሪ፤ ፖለቲከኛ፤ ኮሎኔል ወይም የግብርና ዶክተር እንጂ ትንቢት ተናጋሪ አልነበሩም።በ2004 «ነፃነት እርግማን የሆነ ይመስል» ሲሉም ካርቱሞችን ለማዉገዝ አልመዉ እንጂ ተከታይ-የበታቾቻዉን ለማስጠንቀቅ አልነበረም። « ከ(ሱዳን) የነፃነት ጊዜ ጀምሮ ከጦርነት ሌላ-ሌላ ነገር አላየንም።ነፃነት ርግማን ይመስል ከ1955 ጀምሮ ጦርነት ላይ ነን።አንዳዶቻችን በጦርነት መሐል ተወልደን፤ በጦርነት መሐል አድገን፤ በጦርነት መሐል ሸብተናል።» እነሱ እድለኞች ናቸዉ።ሚሊዮኖች እነሱ ያዩትን ሳያዩ አልቀዋልና። ምዕራባዉያን ፖለቲከኞች እና መገናኛ ዘዴዎች ሲላቸዉ የአረቦች እና የጥቁሮች፤ ሲያሰኛቸዉ የሙስሊሞች፤ የክርስቲያኖችና የሐይማኖት የለሾች ይሉት የነበረዉ ጦርነት በአሜሪካኖች ጫና፤ ግፊትና ማስፈራሪያ በአፍሪቃዉያን ትብብር ደቡብ ሱዳን ነፃ ስትወጣ አብቆት ነበር። እልቂት ፍጅቱ ግን አረቦች፤ ሙስሊሞች ወይም ሰሜን ሱዳኖች ከደቡብ ነቅለዉ ከወጡ በኋላ ባሰ እንጂ አላባራም።ለምን? ብዙዎች ብዙ መልስ አላቸዉ።

ተደጋግሞ የሚሰማዉ ግን በ2005 የተፈረመዉ የሠላም ዉል አጠቃላይ (comprehensive) የሚል ስም ይሰጠዉ እንጂ የካርቱም መንግስትን ከማዳከም ወይም ሱዳንን እሁለት ከመግመስ ያለፈ ዓላማና ግብ አልነበረዉም-የሚለዉ ነዉ። ስምነቱ በተለይ በደቡብ ሱዳኖች መካከል የነበረዉን ስር የሰደደ ልዩነት ማጥበብን፤ እንደ መንግሥት ሐገር የመምራት አቅማቸዉን ማጎልበትን ጨርሶ የዘነጋ ነበር። ኢትዮጵያዊዉ የአፍሪቃ ፖለቲካ አጥኚ ፕሮፌሰር መድሕኔ ታደሰም ተመሳሳይ አስተያየት አላቸዉ። ነገሩ አለባብሰዉ ቢያርሱ-እንዲል ገበሬው ሆነና የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች ጁባ ላይ የነፃነት ባንዲራ በሰቀሉ በሁለተኛ ዓመታቸዉ ያን መከረኛ ሕዝብ ከሌላ ጦርነት ማገዱት።ጋራንግ በጦርነት መሐል ተወልዶ-በጦርነት መሐል ያረጀ ያሉት ዜጋቸዉ ካልሞተ በነፃነት ማግስትም ሙት ቁስለኛ ይቆጥራል።የድሕረ ነፃነቱ ጦርነት ከ50 ሺሕ በላይ ሕዝብ ፈጅቷል።አካሉ የጎዶለዉ ከሟቹ እጥፍ ነዉ።ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ተፈናቅሏል።አንድ ሚሊዮን ያክል ተሰድዷል። 12 ሚሊዮን ከሚገመተዉ የሐገሪቱ ሕዝብ 3,9 ሚሊዮን ለረሐብ የታገለጠ ነዉ።የተደፈሩ፤ የተገረፉ፤የታገቱ፤ የተጋዙትን ሴቶች፤ አቅመ ደካማና ሕፃናትን የቆጠራቸዉ የለም።ከየሰወስቱ ትምሕርት ቤት አንዱ ወድሟል። ከ15 ሺሕ እስከ 16 ሺሕ የሚገመቱ ልጆች በማያዉቁት ጦርነት ብረት አንግበዉ ይዋጋሉ። ወትሮም በቅጡ ያልተዘረጋዉ የመሰረተ-ልማት አዉታር ወድሟል።

ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪርና ዋና ባላንጣቸዉ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንት ሪክ ማቸር አምና ነሐሴ የተፈራረሙት የሠላም ዉል ደቡብ ሱዳኖችን ዳግም የሚያረግፍ-የሚያሰድደዉን ጦርነት ለማስቆም ያለመ ነበር።ባለፈዉ ቅዳሜ መከበር የነበረበት የደቡብ ሱዳን አምስተኛ ዓመት የነፃነት በዓል አከበባር ለጁባዉ ወጣት ለሚካኤል አቲት የስምምነቱ ገቢራዊነት መገለጫ፤ የሰላም ተስፋዉ ማብሰሪያ ምልክት ነበር።ግን አልተከበረም።«የበዓሉ አለመከበር ለኛ እንደ አዲስ ሐገር አሳፋሪ ነዉ።ሰወስተኛዉ እና አራተኛዉ ዓመት በዓል በድምቀት ያልተከበረበትን ምክንያት ሰምተን ነበር።አሁን ደግሞ አምስተኛዉን ለማክበር ገንዘብ የለም የሚል ምክንያት ሰማን።በዓሉ ለሌላ ጊዜ መተላለፉ ብቻ አይደለም የደቡብ ሱዳን ግጭት፤ የሐገሪቱ የምጣኔ ሐብት ድቀት በዉጪዉ ዓለም ዘንድ የሚያሰጥን የተበላሸ ሥም ነዉ።» ወጣቱ ድግስ በመሰረዙ መቆጨቱን ሲናገር ከፊል ጁባ በተቀናቃኝ ሐይላት ዉጊያ ትተራመስ ነበር።ሐሙስ።አርብ ቀጠለ።ቅዳሜ አሰለሰ።ትናንት።ዛሬም።ተጣማሪ መንግሥት መመስረታቸዉን ያወጁት የኪር እና የማቸር ሐይላት ርዕሰ-ከተማ ጁባ ዉስጥ በገጠሙት ዉጊያ በትንሽ ግምት ሰወስት መቶ ሰዉ ተገድሏል። በሔሌኮብተር፤ በብረት ለበስ ተሽከርካሪና በመድፍ የተጠናከሩት ሐይላት በገጠሙት ዉጊያ፤ ሰላማዊ ሰዎችም ኢላማ ናቸዉ።

በጁባ የቀድሞዉ የጀርመን አምባሳደር ፔተር ሹማን እንደሚሉት የጁባዉ ግጭት ከታሕሳስ 2013ቱ ጋር ተመሳሳይ ነዉ። «ከጁባ ዉጪ የሠፈሩ ሐይላት ወደ ርዕሠ-ከተማይቱ እየገሠገሡ ነዉ የሚል ዘገባ አለ።ታሕሳስ 2013ም ተመሳሳይ ነገር ነበር ያየነዉ።ሠላማዊ ሰዎችም የጥቃቱ ኢላማ ናቸዉ።ምክንያቱም በፖለቲካ ቡድናት የተከፋፈሉ የተቃዋሚዉ የሪክ ማቻር ወይም የመንግሥት የሳልቫ ኪር ወይም የሌላ ጎሳ አባላት በመሆናቸዉ።» ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ ዛሬ አምስተኛ ቀኑን የያዘዉ ግጭት በ2013 እንደነበረዉ ወደ ሙሉ ጦርነት ይሸጋገራል የሚለዉ ሥጋት፤ አምባሳደር ሹማን እንዳሉት እያየለ ፤ ምክንያቱም እያነጋገረ ነዉ።ፕሮፌሰር መድሕኔ ምክንያቱን እሁለት ይከፍሉታል።ማቀጣጠያ እና መሠረታዊ ብለዉ። ዋና ወይም መሠረታዊዉ ምክንያት ግን ለሁለት ዓመት የተደረገዉ ድርድር በተለይ አምና ነሐሴ የተደረገዉ ሥምምነት ሁሉንም ወገን ያሳተፈ አለመሆኑ ነዉ።እንደ ሁለት ሺ አምስቱ ሁሉ የነሐሴዉ ስምምነትም መሠረታዊ ችግሮችን መርምሮ ዘላቂ መፍትሔ ላይ ከማተኮር ይልቅ የይድረስ ይድረስና ዉሽልሽል ብጤ መሆኑን ፕ/ር መድሕኔን ጨምሮ የተለያዩ የፖለቲከ ታንታኞች ሲያስጠነቅቁ ነበር።ዛሬም ደገሙት። በሳልቫኪር እና በማቸር ሐይላት መካከል የተነሳዉ ጠብ ቢረግብ እንኳን በእስካሁኑ ፖለቲካዊ ሒደት ያልተካፈሉት ሐይላት ቅሬታ ደርጅቶ አዲሲቱን ሐገር ከሌላ ብጥብጥ መዶሉ አይቀሩም።

ለሁለት ዓመታት በተደረገዉ ድርድር የተቃዋሚዉን የሪክ ማቸርን ቡድን ወክለዉ ሲደራደሩ የነበሩት ጄኔራል ታባን ዴንግ ጋይ አሁንም የዉጪ ሐይላት ይድረሱልን ባይ ናቸዉ። «እዚሕ የሚቆጣጠር የለም ማለት ከንቱ ምኞት ነዉ።ሐገሪቱ አንድ ፕሬዝደንት፤ አንድ መንግሥትና አንድ ሕዝብ ነዉ ያላት።ሥለዚሕ በመላዉ ሐገሪቱ ሕግና ሥርዓት ማስከበር የመንግሥት ሐላፊነት ነዉ።እናንተ የመገናኛ ዘዴ ተቋማት ጭምር ሐገራችን ሰላም የምትሻ መሆንዋን ለሕዝባችን በመግለፅ እንድትረዱን አሁንም በድጋሚ እንጠይቃለን።» ለጥያቄዉ የተሰጠ ቀጥታ ምላሽ መኖር አለመኖሩ አይታወቅም። የተቀጣጠለዉ ዉጊያ እንዲቆም ግን መንግሥታት እየጠየቁ፤ የተፋላሚ ሐይላት መሪዎችን እያሳሰቡ ነዉ።ከዋሽግተን፤ ኒዮርክና አዲስ አበባ የሚሰማዉ ጥያቄ-ማሳሰቢያ ከጁባ አልፎ በየጫካዉ ካደፈጡ ሸማቂ አዛዦች ጆሮ መድረሱ አጠራጣሪ ነዉ። የእስካሁኑን ድርድር የመሩት የአፍሪቃ እና የዓለም ሐያል መንግሥታት ስምነቱ ሁሉንም ወገኖች እንዲያካትት እና በተገቢዉ መንገድ ገቢር እንዲሆን ግፊት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።ግፊቱ ግን ፕሮፌሰር መድሕኔ እንደሚሉት ተጨባጭ ርምጃን መጨመር አለበት።እስከዚያ ስንት ደሐ፤ ስንት አቅመ ቢስ ይሞት፤ ይቆስል፤ ይሰድድ ይሆን? ደቡብ ሱዳን- የአሮጌ ዉጊያ ጦርነት ማዕከል ግን አዲስ ሐገር።ጋራንግ እንዳሉት ነፃነት ርግማን ሆኖባት ይሆን?
ነጋሽ መሐመድ

Filed in: Amharic