>
5:13 pm - Sunday April 18, 8877

እቅጭ እቅጯን እናውራ? [ዮና ቢር]

የዘንድሮ ሁለት ተቃውሞዎች ምን ይነግሩናል?

Thinking Man....by Mesfen Mamoዘንድሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ታላላቅ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ተከስተዋል።

የመጀመሪያው ተቃውሞ ለወራት የዘለቀውና አሁንም ሙሉ ለሙሉ ያልበረደው <ቅድሚያ ለኦሮሞ> (‪#‎OromoFirst‬) የተባለው ቡድን ያቀጣጠለው የኦሮሞ ተቃውሞ (‪#‎OromoProtest‬) ሲሆን

ሁለተኛው ደግሞ በወልቃይት የማንነት ጥያቄ የተቀሰቀሰው የአሁኑ የጎንደር ተቃውሞ ናቸው።

እነዚህ ሁለት ተቃውሞዎች ለበርካታ ዜጎች ሕይወት ማለፍ፤ እስርና ስደት ምክኒያት ሆነዋል …. እየሆኑም ነው።

የኢህአዴግ መንግስት የሕዝብን ጥያቄ የሚፈታበት አንድ ብልሃት አለው። ይሄውም መጀመሪያ ሕዝብ ጥያቄ ሲጠይቅ መንግስት ጆሮ ዳባ ልበስ ይላል። ከዚያ ጥያቄው ሲበረታና ወደ ተቃውሞ ሲደረሰ መግደልና አስተባባሪዎችን እስር ቤት ማጋዝ ይጀምራል። ከዚያ በኋላ ጥቂት ጸረ ሰላም ሃይሎች ያስነሱት ሁከት በፖሊስና በሰላም ወዳዱ ሕዝብ ትብብር ከሸፈ ይልና <አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎችን> ምስል በኢቲቪ እያሳየ ያላሉትን ወይም ሊሉ ያላሰቡት ይናገራል። ከዚያ እስረኞቹን ጥቂት ወራት ባስ ካለም አመታት ያስርና ይፈታቸዋል፤ ጥያቄው ተረስቶ ይቀራል። ከዚያ መሪዎቹ ሲፈቱ ይሰደዳሉ። ጫወታው ያበቃል

በዚህ አይነት የጥያቄ አፈታት ዘዴ ኢህአዴግ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተሳክቶለታል።

ከነዚህም መካከል የጋምቤላ መሬት ጥያቄ፤ የቅንጅት የ97 ምርጫ ውጤት፤ የድምጻችን ይሰማ ጥያቄ፤ የአንድነትና የሰማያዊ ፓርቲዎች መፈራረስና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጥያቄ በዚህ አይነት ታፍነዋል።

ኦሮሞዎች!!!

ኦሮሞዎች ለረጅም ጊዜ ሲቃወሙ የመንግስት መልስ ሃይል ነበር።

ኢህአዴግ በሚያራምደው የዘር ፖለቲካ ከታየ የኦሮሞዎች ጥያቄ ትክክል ነው። ኢህአዴግ ግን መልሱ ሃይል ብቻ ሆነ።

በልማት ስም በቂ ካሳ ሳይከፈላቸው ከመሬታቸው የሚፈናቀሉት የኦሮሞ አርሶ አደሮች ሲቆጡ መክረማቸውን ማንም አላሰተዋለም ነበር።

የሃጫሉ ሁንዴሳን <ማላን ጂራ> የሚለውን ዘፈን እየሰሙ ከነፈራቸውን ሲነክሱ መክረማቸውን ማንም አላሰተዋለም ነበር
<ገላን ፊኒፊኔቲ> እያሉ ሲቆጡ መሰንበታቸውን መንግስትም ሌላውም ሕዝብ አላወቀም ነበር።

ከዚያስ?

ከዚያማ እየታሰሩና እየተገደሉም ጥያቄያቸውን የማያቆሙ ሆነው ብቅ አሉ። እየገደላቸው በነጋታው በዝተው ይወጣሉ፤ አንዱን ቦታ ሊያፍነው ሲል ሌላ ቦታ ይፈነዳል። አቃተው። ከዚያ ተሸነፈ። ያሰረውን አስሮና የገደለውን ገሎ ሲያቅተው ጥያቄያቸው ተቀበለ። የኦሮሞዎች ጥይቄ በረድ ሲል ሌላ የዘር እሳት ደግሞ ከላይ ተጫረ።

ጎንደሬ
<አለ ነገር … ዘንድሮ አለ ነገር> የሚለውን የፋሲል ደሞዝን ዘፈን እየሰማ በሬውን ሽጦ ክላሽና ጥይት ሲገዛ ከርሟል።

አይ አገሬ ጎንደር
ሰሜን ጃናሞራ
እህል ዘርቶ ላውሬ
ሰው ገሎ ላሞራ … እያለ ክላሹን ሲወለውል ሰንብቷል።

አይ ሃገሬ ጎንደር
ሰሜን ጃናሞራ
ለጠገበው ጥይት
ለራበው እንጀራ …እያለ ጥይቱን ሲቆጥር ከርሟል።

ጎንደር ክላሹን ወልውሎና ፎክሮ ብቻ ግን አላበቃም። ይልቅ ተቃውሞውን በሃይል በጥፋት መግለጽ ጀመረ። ሰዎች ተገደሉ። ንብረትም ወደመ። ከንብረቱ በላይ የሰዎች መሞት ያንገበግባል።

ሆኖም ግን የወደመው የትግራይ ተወላጆች ንብረት ብቻ ተለይቶ መሆኑ ጉዳይን ከንብረት ውድመት በላይ ትርጉም እንዲኖረው አድርጎታል።

ስለዚህ ብዙዎች ደንገጡ ….አዘኑ። በእርግጥም ያሳዝናል።

ሆኖም ግን ይህ እንደሚመጣ ለማወቅ ጠቢብ መሆን አይጠይቅም ነበር። ለምን ከተባለ መልሱ ኢትዮጵያ የምትከተለው በዘር ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ነው። ስለዚህ አንዱ ዘር ከሌላው የበለጠ ተጠቃሚ ሆኗል ብለው ሌሎቹ ዘሮች ካሰቡ መነሳታቸው አይቀርም።

በፖለቲካ ሳይንስ እንዲህ አይነቱ ስሜት አንጻራዊ በደል (relative deprivation) ይባላል።

አንጻራዊ በደል (relative deprivation) ማለት …

<ጥቂት የተመረጡ ሕዝቦች> ለብቻቸው ሁሉንም ሃብት ሲያገበሰብሱና ሁሉንም ስልጣን ሲይዙ የተቀረው ሕዝብ እንደተገለለ ሲሰማው የሚመጣ የመከፋት ስሜት ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስት በዘረጋው የዘር ፖለቲካ አማካኝነት ጥቂቶች ሲጠቀሙ አብዛኛው ሕዝብ በልቡ ሲብሰለሰል ኖሯል። ይሄንን የሚክዱ ሰዎች ይኖራሉ። ሆኖም ግን እኔ የፈጠርኩት አመለካከት ሳይሆን አብዛኛው ሕዝብ ሲሰማው የኖረው እንዲህ ነው።

ስለዚህ የጎንደር ሕዝብ በትግራይ ተወላጆች ላይ መቆጣቱ በድንገት የተከሰተ ዱብ እዳ አይደለም።

በእርግጥ ትግራይ ሄጄ አይቻለሁ። ገበሬዎቹ እጅግ ድሃዎች ናቸው። የሚያርሱት መሬት ደረቅና ተራራማ ነው። ያሳዝናል። ሆኖም ግን ይህ ገበሬ በስልጣን ላይ ያሉት ልጆቹ ስለሆኑ መቼም አይነሳም ። ምክኒያቱም የትግራይ ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ በተሻለ ስነልቦናዊ ተጠቃሚነት ይሰማዋል።

የኦሮሞ ገበሬ ግን መሬቱን ሲቀማ የሃብትም የስነልቦናም መገለል ይሰማዋል። (Relative deprivation)

የትግራይ ገበሬ ባለፉት ሃያ አመታት የሚያርሰው መሬት ተጨምሮለታል። የኦሮሚያና የአማራ ገበሬ በተለያየ ምክኒያት መሬቱን ተነጥቋል። (Relative deprivation)

ትናንት ምንም ያልነበራቸው የትግራይ ተወላጆች በድንገት ሚሊየር ሲሆኑ ሕዝቡ ታዝቧል። በአንጻሩ ደግሞ የጉራጌ ሕዝቦች ለዘመናት ርስታቸው ከነበረው መርካቶ ቀስ በቀስ ተገፍተው ወጥተዋል። (Relative deprivation)

የትምህርትም የተፈጥሮም ብቃት የሌላቸው ሰዎች ስልጣኑን ይዘው ሕዝቡን ሲያሽቆጠቁጡ ይዋላሉ። እውነተኛ ስልጣን በማን እጅ እንዳለ ሕዝቡ ያውቃል። (Relative deprivation)

ላለፉት ሃያ አመታት እድገቱ ሕዝቡን ተጠቃሚ አላደረገም። ይልቅስ ድህነቱ እንዲበረታ ሆኗል። (Relative deprivation)

ስለዚህ ለትግራይ ልሂቃን አሁን የመጨረሻ የማንቂያ ደውል ተደውሎላቸዋል። ሃብቱ ፍትሃዊ እንዲሆን ካላደረጉ እነሱ ብቻ ሳይሆኑ የትግራይ ተወላጆችም በድምር ጉዳት ላይ ይወድቃሉ።

ከሁሉ የሚያስፈራው ደግሞ አገራችን ሱማሊያ፤ ሊቢያ፤ ሶሪያና የመን እንዳትሆን ነው። ሕዝብን ገሎ መጨረስ አይቻልም። ኢትዮጵያዊ ከሞላ ጎደል አንድ አይነት ሕዝብ ነው። አድዋ ላይ የታየው ጀግንነት ኢትዮጵያዊ ሁሉ በጀግነንት አንዱ ከሌላው የማያንስ መሆኑን ነው። እኛ ብቻ ጀግና ነን ሌላው ብሄር ፈሪ ነው የሚለው አስተሳብ ጅልነት ነው።

አንድነታችን የሚጠበቀው ፍትሃዊ የሃብትና የስልጣን ክፍፍል ሲኖር ነው። ሕዝብ ጥያቄ ሲጠይቅ በፖለቲካ ጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይቶ መፍታት ስልጣኔ ነው። ከረፈደ በኋላ መጸጸትና በኤርትራ ላይ ማላከክ ትክክል አይደለም። ሚጢጢዋ ኤርትራ እንዴት ኢትዮጵያን ማተራመስ ይቻላታል። እውነታው ግን አተራማሹ ኢህአዴግ የሕዝብን ጥያቄ መመለስ አለመፈለጉ ነው።

P.S ይህ ጽሁፍ የትግራይ ሕዝቦችን በሙሉ የሚፈርጅ አይደለም። ሆኖም ግን የትግራይ ሕዝቦች ይሄን አካሄድ በቃ ሊሉት ይገባል። ካለበለዚያ ሕዝብ ሲቆጣ ተጎጂ መሆን ይመጣል።

<የእኔ የእኔ ነው፤ የእናንተም የኔ ነው> የሚል አካሄድ አያዋጣም።

ሕዝብ የመጨረሻውን ንብረቱን ሲቀማ ለመሞትም ለመግደልም አይሳሳም። ኢትዮጵያዊ ደግሞ በሚስቱና በርስቱ ቀልድ አያውቅም።

<ለጸባይ ነው እንጂ ለጸብ የለው ዋንጫ> እንዳለው ዘፋኙ መግባባት ይሻላል። ተው አስተውሉ። አንድነት ይበጀናል። ለአንድነት ደግሞ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት።

በመጨረሻ ከፌስ ቡክ ላይ ባገኘሁት ጽሁፍ ልሰናበት

አባቶቻችን ተጋጭተው ያውቃሉ ነገር ግን ተነጋግረው እንዲያም ሲል ልጅህን ለልጄ ተባብለው ችግራቸዉን ይፈቱ ነበር:: አፄ ቴወድሮስ በጦር ሜዳ ለማረኩት ምኒልክ ልጃቸዉን ዳሩለት፣ የምኒልክ የልጅ ልጅ የነበረው እያሱ ከዮሐንስ የልጅ ልጅ ጋር ተገባ:: ሕዝቡም እንዲሁ በደም የተሳሰረ ነው::

ፍትህ እና ዕኩልነት ከሰፈነ ከሚያጣላን ይልቅ የሚያስተሳስረን ይበዛል! ማስተዋል…ዋሸሁ እንዴ?

Filed in: Amharic