>

ክብደትን የመቀነስ ጥበብ ፤ ካስተናጋጁማስታወሻ የተቀነጨበ [በ.ሥ]

Bewketu Seyoumያኔ ባቡር ሳይወጠን- የሃያ ሁለት ማዞርያ አየር ባስመረት ሽሮ ሳይታጠን -ዓባይን የደፈረው መሪ(ሆስኒሙባረክ)ሳይከነበል-ታምራት ገለታ ቃሊቲን ሳይዳበል- ታምራት ላይኔ ጌታን ሳይቀበል-ካገር ወጣሁ፡፡

አሜሪካ እንደገባሁ በመጀመርያ የፈጸምኩት ተግባር ቢኖር መወፈር ነው፡፡ አትፍረድብኝ፡፡ አሜሪካ ውስጥ ሰው መንቀሳቀስ አቁሟል፡፡ ኑሮ ማለት ከሶፋ ወደ መኪና ፤ከመኪና ወደ አሣንሠር መንፏቀቅ ማለት ሆኗል ፡፡ ሁሉ ነገር የሚፈጸመው online ነው፡፡ ያሜሪካ ገበሬ ራሱ የሚያርሥና የሚያጭድ በላፕቶፑ ይመስለኛል፤ “ገብስዎን ለማጨድ ከፈለጉ አልቢን ማጭድ የሚለው ላይ ክሊክ ያድርጉ ” የሚል ላፕቶፕ ላይ ተጥዶ እየዋለ፤ ገበሬ ነኝ የሚል ስንት ፈረንጅ አለ(ሳልፈልግ ገጠመብኝ)

የሆነ ጊዜ ላይ፤ በዩንበርሲትያችን ውስጥ በሚገኘው ጂም ተመዝግቤ ስፖርት መሥራት ጀመርኩ፡፡ መሮጫ ማሽኔ ላይ ዱብ ዱብ እያልሁ፤ ካጠገቤ ባለው ማሽን ላይ ከሚሠግረው ናይጄርያዊ ጋር ሲያቀብጠኝ ራሴን አወዳድራለሁ ፡፡ መጀመርያ የብሄራዊ ስሜት እየገፋኝ( ከአበበ ቢቂላ አገር መጥቶ እንዴት በቀላሉ ያለከልካል እንዳልባል) ጥርሴን ነክሼ እሄን ሩጫ አስነካሁት ፡፡ እግርና ሳንባ ለብሄራዊ ስሜት ግድ እንደሌላቸው ያወኩት ሃያ ደቂቃ ከሮጥኩ በኋላ ነው፡፡ ሰው ያበበ ግደይን ተሰጥኦ ይዞ እንደአበበ ቢቂላ ካልሆንኩ ብሎ ይሟሟታል? ድንገት ትንፋሼ ብትን ብትን ይላል፡፡ የእንግላል እንዳልወድቅ የማሽኑን መደገፍያ እመረኮዛለሁ ፡፡ ጥቂት ቆይቸ ራሱ ናይጄርያዊውን ሰውየ እደገፋለሁ፡፡ ናይጄርያዊው ሁለት እግር ያለው ፈረስ ማለት ነው፡፡ የማሽኑ ሞተር ከጠፋ በኋላ እንኳ መሮጡን አያቆምም፡፡ በኋላ በጣም መረረኝ፡፡ ትንሽ ፈርገጥ ፈርገጥ ካልኩ በኋላ በጂሙ አዳራሽ ውስጥ በተሰቀለው ቲቭ ላይ የሚተላለፈውን ፊልም ስመለከት ውየ ወደ ቤቴ መመለስ ጀመርኩ ፡፡ ለኔ ጂም ቤት መግባት ማለት የስፖርት ቱታ ለብሶ ሲኒማ ቤት እንደመግባት ሆነ።

ደሞኮ አላፍርም፤ እንደ ሰዎች ሴክሲ ሆኖ መታየት ያምረኛል፡፡ ላፕቶፔ ላይ ቦርጭ የሚያጠፋ ሶፍትዌር ጭኘ ፤ ፎቶዎቼን ሸንቀጥ እያደረግሁ ፌስቡክ ላይ መለጠፍ ጀመርኩ፡፡ ምን ዋጋ አለው፡፡ ባለፈው አንዱ ከኔ ጋር የተነሣውን ፎቶ እንደወረደ ለቀቀው፡፡ ዘውዳለም ታደሰ የተባለ ያዲሳባ ተራቢ ያን ፎቶ አይቶ “ኧረ የኬንያ ፖሊስ መሰልክ ”ብሎ ከተረበኝ በኋላ የገዛ ሰውነቴ እንደ ወህኒቤት ዩኒፎርም ቀፈፈኝ ፡፡ የኬንያ ፖሊስ ይሄን የበቆሎ ገንፎ እየነፋ ፤እንደ ዋርካ ስለሚሰፋ ሌባን መጠቆም እንጂ ሌባን አባርሮ መያዝ አይችልም ይባላል፡፡( ምነው የማይመለከትህን የኬኒያ ፖሊስ ላይ ችክ አልህ? አለኝ አንዱ አሁን በኢኖቦክስ ፡፡ እና ሃያ ሁለት ማዞርያ እየኖርኩ ፤ ሰማንያ ዓመት ለመኖር እያቀድኩ፤ ያዲሳባን ፖሊስን እንድተች ትጠብቃለህ?)
አገሬ በገባሁ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ዘጠኝ ኪሎ ቀነስኩ፡፡ ሸገር ውስጥ ያ ሁሉ ከብት እያለቀ ፤ያ ሁሉ ሥጋ እየተበላ ሰው የማይወፍርበት ምንያት የገባኝ አሁን ነው፡፡ ያዲሳባ የኑሮ ውጣ ውረድ በራሱ የማይፎረሽበት ጅም ነው ወንድሜ ፡፡ መታወቂያ ለማውጣት የሆነ ቢሮ ሂድ፡፡ የሆነች ሴትዮ ትቀበልህና “ ሁለተኛ ፎቅ ሄደህ ክፈል” ትልሃለች ፡፡ እየተቅመደመድህ ትወጣለህ፡፡ እዚያ ስትደርስ አንዱ ይቀበልህና “ ይህን ደረሰኝ ይዘህ አራተኛ ፎቅ ላይ የሚገኘው ሥራ አስኪያጅ ቢሮ ሂድ ፤ ማህተም ያደርግልሃል“ ይልሃል፡፡ እያለከለክህ እዚያ ስትደርስ፤ የባለማህተሙ ጸሀፊ ትቀበልህና “ሥራ አስኪያጁ ለሥራ ወጥተዋል፡፡ እስኪመለሱ ድረስ ሰባተኛው ፎቅ የሚገኘው ካፌ ሻይ ቡና እያልህ ቆይ፡፡”ትልሃለች ፡፡ ያዲሳባ ፎቅ ለወጉ ሊፍት ተገጥሞለታል፡፡ ግን ሊፍቱ ጥቂት ሠርቶ በመብራት ኃይል ስፖንሰር አድራጊነት ወደ እቃ መጋዘንነት ይቀይራል፡፡ሰባተኛው ፎቅ ላይ እስክትደር አንድ ሦስት ኪሎ ቀንሰሃል፡፡ እና እዛ ቁጭ ብለህ ሻይህን ፉት እያልህ ”አተት ሰባት ሰዎችን ገደለ”የሚል ዜና ሲተላለፍ በቲቪ ታያለህ፡፡ ስምንተኛው ያተት ሰማእት አንተ ልትሆን እንደምትችል ታስብና በስጋት ሌላ ሁለት ኪሎ ትቀንሳለህ፡፡ ከዚህ ሁሉ ወደ ጎረቤት አገር ዞር ብየ ለእናት አገሬ ብተርፍላት አይሻልም? ብለህ ማሰብ ትጀምራለህ፡፡ የህይወቴ ቤዛ፤ እንደምነሽ ቪዛ?

ቪዛ ስል የሚከተለው ትዝ አለኝ፡፡

የሆኑ ሽማግሌ እንደነገሩኝ በኃይለሥላሴ ጊዜ ላንድ ኢትዮጵያዊ ቪዛ ማግኘት፤ ወደ ፍኖተ ሰላም የሚሄድ አውቶብስ ትኬት ከማግኘት በጣም ይቀል ነበር፡፡ ሽሮሜዳ አካባቢ በእግርህ እየተንሸራሸርህ ትንሽ ካካፋ ዝናቡ እስኪያባራልኝ ለምን ቪዛ አልጠይቅም? ብለህ ወደ አሜሪካ ኢምባሲ ጎራ ማለት ነው፡፡ አምባሳደሩ በቢሯቸው ተቀብለውህ አሪፍ ቡና እየጋበዙህ ኩኪሱን ገፋ እያደረጉልህ “ አንተ ወጣት ኢትዮጵያዊ ወደ አሜሪካ ለመሄድ ስለፈቀድህ በጆን ኤፍኬኔዲ ስም የተሰማኝን ደስታ እገልጽልሃለሁ፡፡ የማትቸኩል ከሆነ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ፡፡ ለመሆኑ ቪዛውን የት ላይ ብመታልህ ትመርጣለህ? ፓስፖርትህ ላይ ወይስ የቀበሌ መታወቂያህ ላይ? ”
አለቀ፡፡
ዛሬ የኢምባሲ ጥያቄዎች ምን ብለን ጠይቀን እንጣለው የሚሉ ነው የሚመስሉ ፡፡ ለምሳሌ የቺስታ አገር ዜጎች እንደሆንና ገንዘብ ለመሥራት እንደምንሄድ እያወቁ የባንክ ደብተራችንን ለምን እንደሚጠይቁን አይገባኝም፡፡ የዛሬ ምናምን አመት ክበበው ገዳና ተስፋየ ካሳ ከኢምባሲ ኢምባሲ ይንከራተቱ ነበር፡፡ አንዴ ፤ ጀርመን ኢምባሲ ገብተው ጥያቄ በጥሩ መንገድ ሲመልሱ ከቆዩ በኋላ
“ተቀማጭ ገንዘብ ካላችሁ ልታሳዩ ትችላላችሁ?“ ስትል ጠየቀች ጀርመኒቱ፡፡

ተስፍሽ ፈጠን ብሎ መለሰ፡፡

“ጀርመን ደርሰን ስንመጣ ማሳየት እንችላለን”
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሁለቱ ቺስታ ኮመድያኖች እንደማሽላ ኣንገታቸውን ደፍተው ከኢምባሲ ወጡ፡፡ ያካባቢው ጎረምሶች ከበቧቸው፡፡
“ሰጧችሁ?ሰጧችሁ?” አሉ ጎረምሶች፡፡
“አዎ “ አለ ክበበው አንገቱን እንደደፋ “ ፓስፖርታችንን ሰጡን ”

Filed in: Amharic