>
2:30 am - Saturday November 27, 2021

ዝክረ-ግንቦት 20 ሰለባዎች - ሐኪም አጥቶ የሞተው ሐኪም! (ታምራት ታረቀኝ)

«ጦርነት ግድ ሲሆን የሚገባበት ሁኔታ እንጂ እንደ ትልቅ ጀብዱ የሚወደስ ባህል መሆኑ መቆም አለበት፡፡ በተለይም ጦርነቱ የውስጥ ሲሆን ሰላማዊ አማራጮች ሁሉ ከተሟጠጡ በኋላ ብቻ የሚመረጥ መንገድ ሆኖ መታየት አለበት፡፡ የፖለቲካ ልዩነቶችንም በተመለከተ አንዱ ወገን ምንግዜም ቢሆን ፍጹማዊ እውነትን ሊታደል እንደማይችል ተገንዝቦ የሌላውን ወገን ሀሳብ እህ ብሎ ማዳመጥ መቻል ይኖርበታል፡፡ የተቀዋሚ ወገን አየለ ብሎ ቃታ ለመሳብ መጣደፍ ዞሮ ዞሮ ሀገርን በብርቱ የሚጎዳ መሆኑን ከ ቀይ ሽብር ያተረፍነው ትልቁ ትምህርት ነው፡፡ ከከፋ ከከፋ ተቀዋሚን ላጭር ግዜ አስሮ ማቆየቱ ይመረጣል፡፡ ማኦ ዜ ዱንግ እንዳለው የተቀነጠሰን አንገት መልሶ መትከል አይቻልምና፡፡» ይህን ያሉት ፕ/ር ባህሩ ዘውዴ ናቸው፡፡ ያለመቻቻል ፖለቲካ ሰማዕታት፣ መቼም እንዳይደገም በሚል ስያሜ የሰማዕታት ማህበር ባሳተመው መጽፍ ላይ በሰፈረው ጽሁፋቸው፡፡

ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ እነሆ በሚቀጥለው ሳምንት 23 ዓመቱን ያስቆጥራል፡፡ በየአመቱም ሆነ በየምክንያቱ የእርስ በእርሱ ጦርነት አሸናፊነቱን ጀብዱ ይተርካል፣ ይፎክራልም፡፡ ተቀዋሚውን ማጥፋትን እንጂ እህ ብሎ ማዳመጥን ዛሬ ድረስ ሊካነው አልቻለም፡፡ የፖለቲካ ልዩነት ከአንድ ሀገር ልጅነት በላይ ሆኖ በጠላትነት የሚያስተያይ የመሆኑ ነገር እየታደሰ እንጂ እየከሰመ ሊሂድ አልቻለም፡፡ ፋኖ ሆኖ መዋጋትና ቤተ መንግሥት ተቀምጦ ሀገር መምራት ፍጹም የተለያዩ ነገሮች በመሆናቸው ህወሓት/ኢህአዴግ ለ17 ዓመታት የተናገራቸውንና ቃል የገባቸውን ተግባራዊ ማድረግ ተስኖት ሲቃወመውና ሲያውግዘው የነበረውን ድርጊት ለመፈጸም ግዜ አልወሰደበትም፡፡

በደኖ፣ ወተርና አርባ ጉጉ የተፈጸሙ ኢሰብአዊ እልቂቶችን አንድ ብለን፣ የአዋሳውንና የጋምቤላውን ዳስሰን በምርጫ 97 ተሸጋግረን ሰሞኑን በየዩኒቨርስቲዎች የተፈጸመውን ብንቃኝ መነሻ ምክንያቱ መፍትሄ አገኝቷል የተባለው የብሄር ብሄረሰብ መብት እና የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት ጉዳይ ጥያቄ እያስነሳና ተገቢ ምላሽ መስጠት እየተሳነ የተፈጸሙ ናቸው፡፡ ‹‹የሞተው አንድ ሰው ነው፡፡ ያም ቢሆን አድማ መበተኛ መሳሪያ ከቀድሞው መንግሥት ባለመውረሳችን ነው፡፡ እሱም ቢሆን የኢሰፓ አባል ነው፡፡›› የተባለበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የነበረው ተስፋሁን ወርቁን፣ (የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የተመድ ዋና ጸኃፊ የነበሩትና ለኤርትራ መገንጠል በብርቱ የሰሩት ግብጻዊው ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊን አዲስ አበባ መምጣት በመቃወም ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተገደለ ነው) በማን አለብኝነት በጠራራ ጸሐይ በአደባባይ የተገደሉትን አቶ አሰፋ ማሩን፣ በእስር ቤት ተሰቃይተው ሐኪም አጥተው የሞቱትን እውቁን የቀዶ ህክምና ሐኪም ፕ/ር ዓሥራት ወልደየስን፣ እንዲህ እንዲህ እያልን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በየመግለጫው የጠቀሳቸውን የተገደሉና ታፍነው የተሰወሩ ዜጎችን እንዘርዝር ብንል የጋዜጣ ገጽ አይበቃንም፡፡ ከላይ በገለጽኩት መጽኃፍ ውስጥ የሰፈረው የማህበሩ መልእክት እንዲህ ይላል፡፡ «መቼም እንዳይደገም የሚለው ውሳኔ እንደዋዛ መወሰድ የለበትም፣ እያንዳንዱ እንደ ቃል ኪዳን አድርጎ በመውሰድ ሁሌ የሚመራበት መርህ ማድረግ አለበት፡፡ ያጣናቸውን ንጹኃን ወንድም እህት ልጅ፣…የምንዘክረው ሌሎች ንጹኃን ተሰውተው ወገኖቻቸውም እንደኛ በሀዘንና በሰቆቃ ሲያስታውሷቸው እንዳይኖሩ በመታደግ ነው፡፡»

ዶ/ር የራስ ወርቅ አድማሴ በዚሁ መጽኃፍ ውስጥ በሰፈረው ጽሁፋቸው «ከኛ ትውልድ ስህተት በመማር የልጆቻችንን ትውልድ ከፖለቲካ ግድያ፣ ከዘር ማጥፋት ፍጅትና ከስጋትም ጭምር ነጻ በሆነችና ፍትህ በነገሰባት ኢትዮጵያ እንዲኖሩ እንመኛለን፡፡ ይህን ምኞታችንን እውን ካደረግን ደግሞ እሱ ጊዜ የማይሽረውና የማያደበዝዘው ዕውነተኛው የሰማዕታት መታሰቢያ ይሆንልናል፡፡» ብለው ነበር፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ የማህበሩ መልእክትም ሆነ የዶ/ር አድማሴ ምኞት እውን ባለመሆኑ እነሆ ዛሬም የዚህ ዘመን ሰማዕታትን እንዘክራለን፡፡ ነገር ግን በአንድ ግዜ የጋዜጣ ጽሁፍ ሁሉንም መዘከር ባለመቻሉ የዛሬ 15 ዓመት ግንቦት 18/1991 ዓ.ም ግብአተ መሬታቸው የተፈጸመውን ፕ/ር ዓሥራት ወልደየስን እናስታውሳለን፡፡

ሐኪም አጥቶ የሞተው ሐኪም

እለቱ ግንቦት 7/1991 ዓ.ም፣ ቦታው አሜሪካን ሀገር ዋሽንግተን አካባቢ ቨርጂኒያ ውስጥ ነው፡፡ ከተሰበሰበው ሰው መካከል እድሜና ጤና ያዳከማቸው መንፈሰ ጠንካራ ሰው በከዘራና በሰው እየተረዱ ወደ መድረኩ ቀረቡና መነጋገሪያውን በመጨበጥ «ዛሬ ሀቀኛ ኢትዮጵያዊነት፣ የሕዝብ ወገናዊነት ወንጀል በሆነበት ጊዜ አሥራት አንተ ከኢትዮጵያዊነት በስተቀር ሌላ ወንጀል የለብህም፡፡ ዛሬ የእኛ ምስክርነት ለአንተ አያስፈልግም፣ ዓሥራት ከሰማዕታት ጎን ቆመህ ግን የሞትክላትን ኢትዮጵያ እኛ ምድራዉያኑ እንዴት እንደተቀራመትናት የምትጠይቀን፣ ገመናዋን እንዴት እንዳረከስነው የምታጋልጠን፣ በጦርነት አለንጋ ገላዋን እንዴት እንደገነጣጠልናት የምትመሰክርብን አንተ ነህ፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ ጉዳዬ ነው የምንል ዜጎች ሁሉ ዛሬ ከዚህች መራራ ጥያቄ እንደማናመልጥ የምትመሰክርብን አንተ ነህ፡፡ ዓሥራት ዛሬ እንደሚባለው በሐረርጌ ድሬዳዋ ልጅነትህ ወይም በመንዜነትህ ወይም በሸዋነትህ ወይም ስለ አማራነትህ ሳይሆን በቁርጠኛ ኢትዮጵያዊነትህ ነው፡፡ ዛሬ መላው የኢትዮጵያ ልጅ እጅ የሚነሳህ፡፡ ዛሬ በ21ኛው ሳይንሳዊ ዘመን ዘመነ ጥምቀት መግቢያ በር ላይ በማኪያቬሊ ያረጀ ሾተል እንደ ጲላጦስ የሕዝብን ጀግና ለሞት አሳልፎ ሰጥቶ እጅ መታጠብ በሕዝብም ፊት ከተጠያቂነት ከታሪክም ፊት ከኃላፊነት ማናችንም አንድንም» በማለት ተናገሩ፡፡

እኚህ ሰው ብዙም ሳይቆዩ አስራትን ተከትለው ይህችን ምድር የተሰናበቱት ባለቄኔው ሎሬት ጸጋየ ገብረ መድህን ነበሩ፡፡ በዚህ የአስራት አስክሬን አሸኛኘት ሥነ-ሥርዓት ላይ የወቅቱን የተመድ ዋና ጸኃፊ ኮፊ አናን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ተገኝተው ንግግር አድርገዋል ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ወቅት መአህድ በነውጥ ውስጥ ነበር፡፡ ከሰኔ 1988 ዓ.ም ጀምሮ የተባረርነው ወጣቶች ውስጥም ሆነን ከተባረረንም በኋላ መአህድን ለማደስ ባደረግነው ትግል ተሸንፈን አማራጭ ኃይሎች አዳራሽ ፈቅዶልን ስለመጻኢ ተግባራችን በመምከር ላይ ነበርን፡፡ ከእኛ መባረር በኋላ በቀኝ አዝማች ነቅዐጥበብ በቀለ ካቢኔ ላይ ተቃውሞ ያነሱ ወገኖች ደግሞ የመአህድና የፕ/ር ዓሥራት ተቆርቋሪዎች በሚል አዲስ ትግል ጀምረዋል፡፡ ቀድመን እንጠረጥረው የነበረውና ኋላ ተስፋዬ ገብረአብ ያረጋገጠው ቀኝ አዝማች በደህንነት ሹሙ ክንፈ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ሻማዋ እንዳትጠፋ የሚል ምክንያት እየሰጡ መአህድን አለምም የለምም የማይባልበት ደረጃ አድርሰውት የሚቃወሙዋቸውን ሁሉ ገለል እያስደረጉ የተቀመጡበት ግዜ ነበር፡፡

እንደተለመደው እሁድ ማለዳ በቅሎ ቤት በነበረው የአማራጭ ቢሮ አዳራሽ በርካታ ሰዎች ተሰብስበናል፤ አብዛኛው ወጣት ነው፡፡ የፕ/ር መሞት ሲነገር አብዛኛው ያልሰማ ነበርና ቤቱ በለቅሶ ተናወጠ፡፡ ሀዘናችንን ተወጥተን እንባችንን ከአበስን በኋላ ድርጅቱ ምን ያደርግ ይሆን? ሌሎቹ ሰዎችስ መንግሥትስ ምን ያደርጉ ይሆን? እኛስ ምን ማድረግ አለብን? ምንስ ማድረግ እንችላለን? በሚል ሰፊ ውይይት ካደረግን በኋላ አስራትን የሚዘክሩ ጽሁፎች ሥነ-ግጥሞች እንዲዘጋጁ፣ ቀብራቸው በደማቅ ሥነ-ሥርዓት እንዲከናወን፤ አስክሬናቸው ከቦሌ እስከ መኖሪያ ቤታቸው በከፍተኛ ድምቀት ታጅቦ እንዲጓዝ የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ተስማምተንና አቅደን ተለያየን፡፡
እዛም የመአህድና የፕ/ር አስራት ተቆርቋሪዎች በሚል የሚንሳቀሱትን ሰዎች አግኝተን ምን ማድረግ አለብን? ምንስ ማድረግ አንችላልን? የሚለውን ስንነጋገር በእኛ በኩል ከአስራት የቀብር ሥነ ሥርዓት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚያስብ ወገን ካለ እንደማንተባበር ገልጸን ይሄው ስምምነት አግኝቶ እቅድ ተነደፈ፣ ምደባ ተካሄደ፣ ገንዘብ ተዋጣ፣ ሥራ ተጀመረ፡፡
ግንቦት 15/1991 ዓ.ም ከዋሽንግተን ጉዞ የጀመረው የፕ/ር ዓሥራት አስክሬን ግንቦት 17/ቀን 1991 ዓም ከጠዋቱ 4፣30 አዲስ አበባ ይገባል ስለተባለ ሁላችንም ያዘጋጀነውን ጥቁር ጨርቅ ክንዳችን ላይ አስረንና በእጅ የሚውለበለብ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ይዘን በጠዋት ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የሄድነው ፓርቲው በሚያዘጋጀው የአቀባበል ሥነ-ሥርዓት ተካፋይ ለመሆን ነበር፡፡ ነገር ግን አንዳንድ የፓርቲው አመራሮች በቦታው ቢኖሩም ምንም ዝግጅት አይታይም፡፡ በመሆኑም የአስራትን አስክሬን እንዲህ በዝምታ መቀበል ተገቢ አይደለም በማለት እዛው ተመካክረን መፈክር ማሰማት፣ ግጥምና ስነ ጽሁፍ ማንበብ ጀመርን፡፡ ለዚሁ ዓላማ ከመጣው ሰው በተጨማሪ በአካባቢው ለተለያየ ጉዳይ የተገኘው ሰው እየተቀላቀለን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ለቅሶውንም መፈክሩንም አደመቀው፡፡

አስክሬኑን የያዘው አውሮፕላን ግን በተባለው ሰዐት ሊደረስ አልቻለም፡፡ ሰዐታት ባለፉ ቁጥር ሆን ብለው ያደረጉት ነው፣ በጨለማ ሹልክ አድርው ለመውሰድ ፈልገው ነው ከሚለው ጀምሮ የተለያዩ መላ ምቶች ይሰነዘሩ ጀመር፡፡ ይህ ደግሞ ሰዉን ይበልጥ እልህ ውስጥ አስገባው፡፡ በዚህ ሁኔታ ያለምንም ድካም በእልህ ሥነ-ሥርዓቱ ቀጥሎ አውሮፕላኑ 11፡30 ላይ ማረፉ ተሰማ፡፡ በዚህ ወቅት ደግሞ የመአህድ አመራሮች ከመንግስት ጋር በመስማማት አስክሬኑን በፍጥነትና በጸጥታ ይዘው ሊሄዱ ነው የሚል ወሬ ሲሰማ ፈጥነን በመሄድ የመኪና መንገዱን ዘጋን፡፡ አስክሬኑን የጫነው መኪና ብቅ ሲል በለቅሶ፣ በመፈክር፣ በኡኡታ ምድር ተደበላለቀ፡፡ በየትም በኩል መኪናው ሾልኮ እንዳያልፍ በጥንቃቄ በመጠበቅና መንገድ በመዝጋት በቀስታ የእግር ጉዙ ተጀመረ፡፡ በየመንገዱ የሚቀላለው ሰው ቁጥር ጨመረ፡፡ አጃቢ መኪናዎችም ቁጠራቸው እየጨመረ ሄደ፣ የትራፊክ ፖሊሶች ከፊት እየቀደሙ ከቦሌ ወደ መስቀል አደባባይ መምጫውን መንገድ ክፍት አደረጉ፡፡ ጊዜው እየመሸ ሲመጣ ጧፍና ሻማ እየተገዛ ተለኮሰ፡፡ በአካል ያልተቀላቀለው በየፎቁ ላይ ሆኖ መፈክር በመቀበልና በመጮህ ጉዞውን አደመቀው፡፡
የታጋይ ድምጽ ይጮኻል፣ አትነሳም ወይ፣ ማን ይፈራል ሞት፣ ወዘተ ተዜመ፡፡ የደህንነት ሰራተኞች በመካከላችን ተሰግስገው አስተባባሪ ናቸው ብለው ከገመቱዋቸው ሰዎች ጎን ተጣብቀው የሚባለውን ሁሉ እያሉ ይጓዛሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ተጉዘን መስቀል አደባባይ ስንደርስ የሰዉ ብዛት የአንድ ወገን መንገድ ከሚችለው በላይ ሆኖ ነበር፡፡ ስፖርት ኮሚሽን ጋር ስንደርስ ከለገሀር አቅጣጫ አድማ በታኝ ፖሊስ የጫነ መኪና መጣና በቅርብ ርቀት ጥግ ይዞ ቆመ፡፡ ከፊት ይመራ የነበረው ትንሽ የፖሊስ መኪና በጣም ተጠግቶን እንደቆመ አንድ የፖሊስ ባለሥልጣን ወርዶ ወደ እኛ መጣ፡፡ ከቦሌ እስከዛ ድረስ ምንም ያለለን ፖሊስ እዛ ጋር ስንደርስ ችግር ይፈጥርብናል ብለን ባለመገመት ሰው ፖሊስ ሲያይ ስሜቱ ግሎ አላስፈላጊ ነገር እንዳይናገር ስናረጋጋ ፖሊሱ ተበተኑ አለ፣ ሰዉም አንበተንም አለ፣ በዚህ ግዜ ወደ ኋላ ዘወር ብሎ በለው ሲል በመኪናው ዙሪያ በተጠንቀቅ አድፍጠው የነበሩት ፖሊሶች ከመቅጽበት ሰፈሩብንና በዱላ መጠዝጠዝ ጀመሩ፡፡ ለማምለጥ ሲሞከር ደግሞ ከዋና መንገድ ወደ ውስጥ የሚያስገቡ መንገዶች ሁሉ በፖሊስ ተይዘዋል፤ የነበረው ምርጫ አንድም ፊት ለፊት ጥሶ ወደ ለገሀር አንደም ወደ ኋላ ተመልሶ ወደ መስቀል አደባባይ መሮጥ ነበር፡፡ የአስክሬኑን መኪና የሙጢኝ ብለው የሚያለቅሱት ሳይቀሩ ዱላ ቀምሰዋል፡፡ ብዙዎች ተይዘው በመኪና ተጭነው ኮልፌ የተወሰዱ ኢሰብአዊ የሆነ ድብደባና ቅጣት ተፈጸመባቸው፡፡ ቀኝ አዝማችን በሚቃወሙት ላይ ቅጣቱ ለየትም ከበድም ያለ ነበር፡፡

በዚህ ሁኔታ ከመኖሪያ ቤታቸው የደረሰው የፕ/ር አስራት አስክሬን አዳሩን ጸሎተ ፍትሀት ከተደረገለት በኋላ በማግስቱ ግንቦት 18 ቀን 1991 ዓ.ም በከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ታጅቦ ወደ መአህድ ቢሮ አመራ፣ በዛም የተወሰነ ቆይታ ካደረገ በኋላ ስላሴ ካቴድራል እንዳይቀበር በመከልከሉ በባለወልድ ቤተ ክርስቲያን በክብር አረፈ፡፡ ግብአተ መሬቱ ሲፈጸም የሕዝቡ ለቅሶ፣ የተቃውሞ ጩኸት፣ እልህና ቁጭት በቃላት ሊገለጽ የሚችል አልነበረም፡፡ ይህ ያበሳጫቸው የጸጥታ ኃይሎች ከቀብር በመመለስ ላይ በነበሩ ወጣቶች ላይ ተኩሰው አንዱን ወዲያው ሲገድሉት አንዱ ቆስሎ ወደ ሆስፒታል ተወሰደ፡፡ (በኋላ መሞቱ ነው የተሰማው) መአህድ ድረጊቱን ባለማውገዙና ለሞቱትም ሀዘኑን ባለመግለጹ አባላትና ደጋፊዎቹን አሳዘነ፡፡

ፕ/ር አስራት ወ/የስ በቀዶ ህክምና ሙያቸው
• የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ የፈረሰኛ ደረጃ፤
• የዳግማዊ ምኒልክ ኒሻን የፈረሰኛ ደረጃ፤
• የአብዮታዊ ዘመቻ አርማ፤
• ዓለም አቀፍ የወርቅ ሜሪኩሪ በግል አስተዋጽኦ፤
• የቀይ ባህር ኒሻን አንደኛ ደረጃ ተሸልመዋል፡፡

ፕ/ር ዓሥራት ለመጀመሪያ ግዜ ጥርስ ውስጥ የገቡት የከፍተኛ ትምህር ተቋማትን ወክለው በተገኙበት የሰኔው ኮንፈረንስ ላይ የኤርትራን መገንጠል በመቃወም ባደረጉት ንግግር ሲሆን የመአህድ ሊቀመንበር ሆነው በአጭር ግዜ ትግሉን ከዳር ዳር ማቀጣጠል መቻላቸው ደግሞ ጥርስ ነካሳውን ወደ ተግባራዊ ጥቃት አሸጋገረው፡፡ እናም ደብረ ብርሃን ላይ ባደረጉት ንግግር ጦርነት አውጀዋል ተብሎ የመጀመሪያው ክስ ተመሰረተባቸው፡፡ ‹‹ከጎጃም ከመጡ ገበሬዎች ጋር በጽ/ቤታቸው ስለ ጦርነት መክረዋል›› የሚል ሁለተኛ ክስ ተጨመረ፤ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እየተጠሩ በዋስ መለቀቁ ሲበዛባቸው አሁንስ ዋስትና በባንክ ማስቀመጥ ሊኖርብኝ ነው አሉ፡፡ በመጨረሻም ተፈርዶባቸው ወህኒ ወረዱ፤ ህመማቸው እየበረታ ቢሄድም ህክምና ባለማግኘታቸው «ሕክምናውም ቢሆን እኔ ዘንድ ሲደርስ አለው ነገር ይዘገያል» ብለው ነበር፡፡ ህመማቸው ከፍተኛ ደረጃ ከደሰ በኋላ ስንት ህይወት ባሰረዘሙበት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተኙ፣ ቀጥሎም ወደ አሜሪካ ተላኩ፣ ሐኪሙ አጥተው በሽታቸው እንኳን ሳይታወቅ ይህችን ዓለም ተሰናበቱ፡፡

Filed in: Amharic