>

የኢትዮጵያ ትንሣኤ እንዴት? ከሸግግር መንግሰት እሰከ ጠብመንጃ አፈሙዝ!!!![ግርማ ሰይፉ ማሩ]

Girma Seifu Maruኢትዮጵያችን ከሰሞኑ ድርስ የዲሞክራሲ እርጉዝ የሆነች ይመስላል፡፡ በሰላማዊ መንገድ ለውጥ ለምንፈልግ ሰዎች መንግሰት የፖለቲካ ማሻሻያ በማድረግ ሁላችንም አሸናፊ ሆነን የምንወጣበት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እናገኝ ይሆን ብለን እየጠበቅን ነው፡፡ የለም ገዢው ፓርቲ አብቅቶለታል በውስጥም በስብሷል ከውጭም ጫናው በርትቷል ፈንግለን እንጥለዋለን የሚሉም አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ አንድ ዓይነት ውጥረት ተፈጠረ በተባለ ቁጥር “የሸግግር መንግሰት” አቀንቃኞች ናቸው፡፡ እነዚህን ሶስት የዲሞክራሲ ፅንስ ማዋለጃ መንገዶችን በአጭር በአጭሩ ለማየት እሞክራለሁ፡፡ የግሌን አቋም የያዝኩበትን መስመር ትንሸ ሰፋ አድረጌ እምለከታለሁ፡፡

የሸግግር መንግሰት ማቋቋም

ይህን ሃሳብ የሚያቀነቅኑ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ይህ ሃሳብ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው መቼ እንደሆነ የተረዱት አይመስለኝም፡፡ የዚህ ሃሳብ ተግባራዊ መሆን የሚችለው በኢህአዴግ መቃብር ላይ ብቻ ነው ብዬ ባልፍ በቂ ነበር፡፡ የኢህአዴግ መቃብር ደግሞ ከዚህ ቀጥሎ በምንመለከተው ሁኔታ የሚሆን ሰለሚሆን “የሽግግር መንግሸት” ለብቻው የሚቆም አማራጭ አይደለም፡፡ ገዢው ፓርቲ የሸግግር መንግስት ለሚባል አካል ስልጣኑን አስረክቦ ቢለቅ እኔም የምታዘበው ይመስለኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ወግ ቢደርሳቸው የዚህን ያህል የተዓማኒነት ችግር ያለበት መንግሰት እየመራሁ ነው ከሚሉ፣ ፓርላማውም ወግ ደርሶች ጫና ቢያሳድር፣ “ፓርላማው”ን በትኖ አዲስ ምርጫ በህገ መንግሰቱ አንቀፅ 60 መሰረት እንዲከናወን ማድረግ ይችል ነበር፡፡ ለዚህ አልታደልም፡፡ ከዚህ የተለየ ህጋዊ ስርዓት “የሸግግር መንግሰት” ለመመስረት የሚስችል መንገድ የለም፡፡

በጣም ግልፅ ለመሆን ከዚህም ከዚያ በሚውጣጣ የቡድን እና ግለሰቦች ስብስብ “የሸግግር መንግስት” ይመስረት የሚሉ ሰዎች ያላቸውን የቡድን ውክልና ወይም ደግሞ ግለሰባዊ እውቅና መሰረት አድርገው ስልጣን በአቋራጭ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ እመኑኝ እነዚህ ሰዎች በዚህ መስመር ሰልጣን ቢያገኙ ያገኙትን ስልጣን በቀጣይ በሚደረግ ምርጫ ስልጣናቸውን ቢያጡ አሜን ብለው የሚቀበሉ አይሆኑም፡፡ ሰለዚህ በእኔ እምነት “የሸግግር መንግስት ይቋቋም” በሚለው አልስማማ፡፡

ኢህአዴግ በስብሷል የስርዓት ለውጥ መደረግ አለበት

በዚህ ጉዳይ ኢህአዴጎች ባይስማሙ ብዙ ወገን ሊስማማ ይችላል፡፡ ይህን ስርዓት በስብሰሃልና ዞርበል እያልን ከሆነ በጉልበትና በጉልበት ብቻ የሚሆን ነው፡፡ ይህ ጉልበት ደግሞ አንድም በታጠቁ ኃይሎች፣ ወይም ደግሞ ህዝባዊ አመፅን ተከትሎ በሚመጣ የሰርዓት መፍረስ የሚገኝ ውጤት ነው፡፡ መንግሰት አሁን በያዘው ሁኔታ እሳቱን እያዳፈነ፣ የተዳፈነውን እሳት ግን ጭድ ስር እየደበቀ የሚቀጥል ከሆነ አይቀሬው ህዝባዊ ማዕበል እሳት ሆኖ ይበላዋል፡፡ ይህ እሳት ኢህአዴግን ብቻ ሳይሆን እኛም ከእሳቱ ብንተርፍ ወላፈኑ እይለቀንም፡፡ ይህ በሰላማዊ ሽግግር ሊታለፍ ካልቻለ ቀላል የማይባል ቀውስ በሀገራችን እንደሚያስከትል ግልፅ ነው፡፡ ይህ አማራጭ በትጥቅ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች እና ምንአልባት ህዝባዊ አመፅን በመምራት ላይ ያሉ ቡድኖች/ግለሰቦች በሚያደርጉት ስምምነት ቀጣይ የሀገሪቱ እጣ ፈንታ እንዴት ይሁን ብለው ሊነጋገሩ ይችላሉ፡፡ ኢህአዴግ-ሻቢያ- ኦነግ በለንደን እንዳደረጉት ማለት ነው፡፡ ከመንግሰት ጋር ይህ ውይይት ሊደረግ አይችልም፡፡ ሰለዚህ በዚህ አማራጭ ላይ ብዙ ማለት የሚቻል አይመሰለኝም፣ የአሸናፊዎች ፍትህ መስጫ ነው የሚሆነው፡፡ ምን አልባት በዚህ ወቅት እነዚህ አሸናፊ ኃይሎች የሚያቋቁሙት “የሸግግር መንግስት” አንደኛው ትክክለኛው አማራጭ የሚሆን ሲሆን እንደከዚህ ቀደሙ የኢህአዴግ የሽግግር መንግሰት መጪው የሸግግር መንግሰትም አግላይ ላለመሆኑ ምንም ዋስትና ሊኖረን አይችለም፡፡

ባጭሩ በሀይል የስርዓት ለውጥ ይደረግ ሲባል ኢህአዴግ ምንም ታሪክ እንደማይተርፈው መረዳት ያለበት ይሆናል፡፡ በሰፈረው ቁና መሰፈሩ ላይቀር የሚችልበት እድል ሰፊ ነው፡፡ ኢህአዴግ እና ኢህአዴጋዊያን ይህ ክፉ ቀን እንዳይመጣ ከዚህ ቀጥሎ የቀረበውን የፖለቲካ ማሻሻያ በማድረግ ሀገሪቱን ህዝብንም ሆነ እራሳቸውን እንዲጠብቁ መምከር እፈልጋለሁ፡፡

የፖለቲካ ማሻሻያ ማድረግ

አሁን ባለንበት ወቅት በሁሉም ወገን ተቀባይነት ማግኘት ያለበት ሃሣብ ነው ብዬ የማምነው፡፡ አሁን የደረስንበትን ቀውስ ሳናባብስ ነገር ግን ስር ነቀል የፖለቲካ ማሻሻያ በማድረግ ወደምንፈልገው ዲሞክራሲያው ስርዓት ልንሸጋገር እንችላለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህ የፖለቲካ ማሻሻያ የሚገኘው ግን አሁን የተጀመሩት ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው ቀጥለው መንግሰት በልመና/በችሮታ የሚሰጠው ሳይሆን ለዚህች ሀገር መፍትሔ የሚያመጣ መንገድ ነው ብሎ አምኖ ሲቀበለው እና በሂደቱ በቅንነት ሲሳተፍ ነው፡፡ ከመንግሰት በተፃራሪ የቆምን ሀይሎችም የእኛ ብቻ ነው ልክ ከሚለው ግትር አቋም መለሳለስ ሲችሉ እና አንበረከክነው ከሚለው አስተሳሰብ ስንወጣ ነው፡፡

ይህ የፖለቲካ ማሻሻያ ለማድረግ በዋነኝነት ከመንግሰት ውጭ ያሉ ሀይሎች ችግሩ አሁን በስራ ላይ ያለው ህገመንግሰት ተቀዶ መጣል አለበት ከሚለው ፅንፍ ወጥተወ ሰላማዊ ሽግግር ለማድረግ እንደመነሻ የሚያገለግል እጅግ ጠቃሚ የሆነ የፖለቲካ ሰነድ መሆኑን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን ገዢው ፓርቲ በተለይ (የድል አጥቢያ አርበኞች ሳይሆኑ) በትግሉ ወቅት ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉበት ህገመንግሰት ተቀባይነት በማግኘቱ ደስተኞች ሰለሚሆኑ ሂደቱን የተሳካ ያደርገዋል፡፡ ይህም ሆኖ ህገመንግሰቱ ሊሻሻል የሚችል መሆኑ የማሻሻያ አንቀፆች ያሉት ስለሆነ በሂደት የሚሻሻልበት ሂደት መኖሩን መቀበል ደግሞ ለተቃዋሚዎች ተሰፋን የሚያጭር ይሆናል፡፡

ይህ የፖለቲካ ማሻሻያ በሚከናወንበት ጊዜ ሁሉ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግሰት በመደበኛ የእለት ከእለት ስራው ላይ እንዲቆይ በመስማማት ሀገሪቱ ወደ ሌላ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ እንዳትገባ በማድረግ በስልጣን ላይ ያሉትም ቢሆኑ በስልጣን ላይቀጥሉ ቢችሉ የሰነልቦና ዝግጅ ማድረጊያ ጊዜ ያገኛሉ፡፡ ከገዢው ፓርቲ ውጪ ያሉ በሀገር ውስጥም በውጭ የሚገኙ ስልጣን የሚፈልጉ ሀይሎችም ለስልጣን የሚያበቃቸውን በቂ ዝግጅት ከህዝቡ ጋር በማድረግ እራሳቸውን ለማዘጋጀት በቂ ጊዜ ያገኛሉ፡፡ ማን ስልጣኑን ይይዛል የሚለውን ህዝብ ይወስናል፡፡

የፖለቲካ ማሻሻያ ሂደቱን ሊመራ የሚችል ገለልተኛ የሆነ የሸግግር ሂደቱን የሚመራ “የሽግግር ኮሚሽን”የሚቋቋም ሲሆን ይህ ኮሚሽን በዋነኝነት በሀገሪቱ የፖለቲካ ምዕዳሩን ሊያሻሽሉ የሚችሉ ልዮልዮ ደንቦችን እና መመሪያዎችን እንዲወጡ በማድረግ፣ አፋኝ ህጎችን በመሻር/ወይም በምክር ቤቱ እንዲሻሩ በማድረግ ህዝቡ በፖለቲካው በንቃት እንዲሳተፍ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

ይህ ማሻሻያ በልመና የሚገኝ ባለመሆኑ መንግሰት ወደ ትክክለኛውም አማረጭ እሲገባ ድረስ አሁን ያለው ህዝባዊ እንቢተኝነት እና “በቃ” የሚለው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ መንግሰት ይህን አስፈላጊ የፖለቲካ ማሻሻያ እንዲቀበል ማሰገደድ የግድ ይላል፡፡ ምንአልባትም መንግሰት በራሴ አፈታዋለሁ በሚል በሚጠራቸው “ህዝባዊ መድረኮች” ሁሉ በመገኘት ይህን የፖለቲካ ማሻሻያ እንዲያደርግ ግፊት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ መንግሰት “ሕዝባዊ” ብሎ የሚጠራች መድረኮች በአብዛኛው የፓርቲው አባላትና ጥቂት ጥቅመኞች እንደሆኑ በመረዳት በስብሰባው ላይ ሌሎች እንዲገኙ ጥረት ማድረግ ተገኝተውም ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

አሁን በመደረግ ላይ ያሉ እንቅስቃሴዎች መንግሰት ላይ የፈጠሩት ጫና ያለ ቢሆንም መንግሰት በተገቢው መንገድ ምላሻ ለመሰጠት በሚያስገድድ መልክ እንዳልሆኑ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ለምሣሌ ሰላማዊ ሰልፍም ሆኖ ተቃውሞ በተደረገ ማግስት መንግሰት በዚህ ተቃውሞ ላይ የተሳተፉ ዜጎችን እየገደለና በየቤቱ እየዞረ እየለቀመ በማስር ከስራ በማፈናቀል እንቅስቃሴውን ማፈን እንደ አንድ ታክቲክ እየተጠቀመ ስለሆነ ማነኛውም የህዝብ ጥያቄ (ትክክል ባይሆን) ከመንግሰት ወገን መልስ ከመስጠት አልፎ ጥያቄውን በማቅረብ የተሳተፉ ወይም የመሩ ሰዎችን ማሰረን፣ ከስራ መባረርን መቃወም ሲከፋም እንዳይታሰሩ መከላከል፡፡ ከታሰሩም በታሰሩበት ቦታ በመገኘት ተቃውሞ መቀጠል፣ እስኪፈቱ ድረስ በፈረቃ በቦታው በመገኝት ተቃውሞ ከፍ እንዲል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

መንግሰት አሁን የግድ የሚያስፈልገውን የፖለቲካ ማሻሻያ እስኪቀበል ድረስ የተቀናጀ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ህዝባዊ እንቅስቃሴው ከጊዜ ወደጊዜ አድማሱን እያሰፈ ረጅም ጊዜ የሚወሰድ የስራና ትምህርት ማቆም አድማ ማድረግ ሊጨምር ይችላል፡፡ መንግሰት በዚህ ላይ በሚሳተፉ ሰዎች ላይ በሚወሰድ እርምጅ በመቃውም ከላይ በተገለፀው መልኩ ተቃውሞን ማስፋት፡፡

በማነኛውም ጊዜ ሆነ ቦታ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በማነኛውም ዜጋ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ ማድረግ፤በተለያየ ምክንያት የዚህ ዓይነት ችግሮች ሲፈጠሩ ማጋለጥና ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ህዝቡ እንዲተባበር ማድረግ፡፡ መንግሰት ይህን ሰበብ በማድረግ በሰው ህይወት ላይ አደጋ እንዳያደርስ፣ በሰው ህይውት ላይ ለሚደርሱ ጉዳቶች ሃላፊነቱን እንዲወሰድ ማድረግ፡፡

ኢትዮጵያዊያን በዘርና ሃይማኖት ተቧድነው ይጣላሉ ብሎ መገመት አስቸጋሪ ቢሆን መንግሰትን ጨምሮ የተለያዩ ሀይሎች ለቡድናዊ ፍላጎታቸው ማስፈፀሚያ አንድን የህብረተሰብ ክፍል እንደሰብዓዊ ከላለ ለመጠቀም መሞከራቸው አይቀርም፡፡ ማነኛውም ህዝባዊ እንቅስቃሴ በሚደረግበት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እና ኢትዮጵያዊነታችን ከብሔር ማንነታችን ጋር በምንም ሁኔታ የማይጋጭ መሆኑን ማስመስከር ይጠበቅብናል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያዊ ልሂቃን ይህን ጉዳይ ለፖለቲካ ጥቅም ከማዋል እራሳችንን በማራቅ ታሪክ መስራት ይጠበቅብናል፡፡

Filed in: Amharic