>

ዓይን እያየ ወደገደል? ምን ይባላል! [ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም]

profeser Mesfen Weldemariam Quateroበአገዛዙ ወንበር ላይ ተጣብበው የተቀመጡት ሰዎች ሁሉ ብዙ ቢሆኑ ይነጋገሩ ነበር፤ ቢነጋገሩ ሁሉም በየፊናውና በየአቅጣጫው በራሱ ዓይኖች ያየውንና በራሱ ጆሮዎች የሰማውን፣ በራሱ አእምሮ አብሰልስሎ እያቀረበ ክርክር ይፈጠር ነበር፤ ከክርክሩ የሚፈልቀው እሳት ከተለያዩ ሰዎች የሚወረወሩትን ሀሳቦች እያቀለጠ አዲስ መመሪያ ያወጣ ነበር፤ ነገር ግን ተጣብበው የተቀመጡት ተጣብቀው አንድ በመሆናቸው ዓይን የሚያየውና ጆሮ የሚሰማው አንድ ነው፤ አእምሮ ሲጨፈለቅና ሲጣበቅ ሕይወቱን ያጣል፤ ስለዚህም የታየውና የተሰማው ጎዳ ሆኖ ሲቀርብ ውጤቱም ጎዳ በመሆኑ ክርክር የለም፤ ክርክር አለመኖሩ የመካንነት ምልክት ነው፡፡
አገር ተረብሽዋል፤ ሥርዓት ጠፍቷል፤ መደማመጥ ተስኖናል፤ የገነፈለው ስሜት እያቀለጠ ወደሞት ጅረት እየወሰደን እንደሆነ ወንበሩ ላይ ተጣብቀው የተቀመጡት ገና አልተገነዘቡም፤ የዓለም ሕዝብ በሙሉ ተገንዝቦታል፤ በወንበሩ ላይ ተጣብቀው የተቀመጡት በሚገነዘቡበት ጊዜ የሞት ጅረት አጥለቅልቆናል፤ መድኅን የሚመጣው ከሞት በፊት ነው፤ የዱሮ አዝማሪ እንዳለችው፡–

አንጀቴ ተቆርጦ ከሆዴ ከወጣ፣
እንግዲህ ሀኪሙ ምን ሊቀጥል መጣ!

ሳምሶን ‹‹ውጽዒ ነፍስየ ምስለ ነፍሶሙ፤›› ብሎ ምሰሶውን ገፍቶ እንደጣለው ዛሬም በወንበሩ ላይ የተጣበቁት ምሰሶውን ገፍቶ የመጣልና የሦስት ሺህ ዓመታት የኢትዮጵያን ታሪክ ለማፈራረስ ጉልበቱ እንዳላቸው ያምኑ ይሆናል፤ ‹‹ውጽዒ ነፍስየ ምስለ ነፍሶሙ›› ለማለትና ውጤቱንም ለመቀበል ከቆረጡ ያለምንም ጥርጥር በቂ ጉልበት አላቸው፤ ነገር ግን ይህ ጉልበት የተባረከና የተቀደሰ አይደለም፤ ዝናብ እንደሚወርድበት ክምር ጨው ነው፤ ዝናቡ ከጉልበት ቁጥጥር ውጭ ነው፤ በዚያ ላይ አንድ የሁሉም አገር ታሪክ ያረጋገጠው እውነት አለ፤ አሸናፊ ይጠናከራል፤ ተሸናፊ ይዳከማል፤ ሕዝብ ተሸናፊ ሆኖም አያውቅ፡፡

በዚያ ላይ ወደእምነት ደረጃ ከፍ ስንል ኃያል እምኃያላን የሆነ አምላክ አለ፤ በጉልበታቸው የሚታበዩትን ይታገሳቸዋል እንጂ ለመጨረሻ ድል አያበቃቸውም፤ የደካሞቹንም ስቃይና መከራ የሚያበዛው የድል አክሊል አዘጋጅቶላቸው ይሆናል፤ ጉልበተኞች ከዕብሪታቸው ሲጸዱና የእግዚአብሔርን ኃያልነት ሲቀበሉ በነሱ ላይ ድልን ለተጎናጸፉት ያስተምራሉ፤ የጉልበተኛ ሥርዓት ወድቆ የሕግ ሥርዓት ይተከላል፤ አሸናፊም ተሸናፊም በሕግ ጥላ ስር ይተዳደራሉ፡፡

አሸናፊም ተሸናፊም አንድ ዋና ነገር ቦግ ብሎ እንዲታያቸው እመኛለሁ፤ ትግላቸውም ሆነ ውጤቱ የግል አይደለም፤ ከመሀከላቸው የአምባ-ገነንነት ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ቀስ በቀስ ትግሉን የግል እያደረጉ ሄደው በመጨረሻ ድሉንም የግል ያደርጉታል፤ ሌላ ቀርቶ ቤተ-ሰቦቻቸውንም ይረሳሉ፤ አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ የብዙ ሰዎችን ትብብርና ከባድ መስዋእትነትን የከፈሉ ሰዎችን የያዘ ነው፤ እነዚህ በብዙ መንገድ ብዙ ዓይነት መስዋእት የከፈሉ ሰዎች ለሚቀጥሉት ትውልዶች የሚያወርሱት ብዙ ነገር አለ፤ ራሳቸውን ሀብታም ማድረጋቸውንና ሰዎችን እንደፈለጉ ሲቆርጡና ሲፈልጡ መኖራቸውን ማንም እንደውርስ አይቀበላቸውም፤ ዘመን አልፎበታል፤ ታሪክም አይሆንም፤ የተጋድሎ ታሪካቸው፣ ለነጻነት፣ ለእኩልነትና ለአገር ባለቤትነት የሚያበቃና ለተከታይ ትውልዶች ሁሉ አርአያ የሚሆን ታሪክ በኩራት የሚተላለፍ ይሆናል፡፡
በቀል፣ ጭካኔና በስሜት መገዛት ውሎ አድሮ ያጋልጣል፤ የሀብታሙና የተመስገን ተገቢውን ህክምና ማጣትና መሰቃየት በምድርም በሰማይም ያስቀጣል፤ ይህንን ባህል አድርገን እንዳንቀጥል እሰጋለሁ፤ አእምሮአችንን ጡንቻ ብቻ ስናደርገው የማሰብ ሥራውን ያቆማል፤ ጠላት ለሚባለው ሰው የተመኙለት ገደል ላይ ዓይኖችን ተክሎ መራመድ ራስን ወደዚያ ገደል ማስገባት ነው፡፡

Filed in: Amharic