>
5:13 pm - Monday April 18, 7616

ተው እንጂ ከልክም ልክ አትለፉ! [በላይ ማናየ]

Kilinto - Belay Manayeይኸው ሶስተኛ ቀናችን ቂሊንጦ ያሉ ቤተሰቦቻችን፣ ወዳጆቻችን ያሉበትን ለማወቅ ስንመላለስ፡፡ እንሄዳለን፣ ጥፉ ከዚህ እንባላለን፡፡ በፖሊስ ተገፍትረን እንመለሳለን፡፡

ትናንት እስከ ማክሰኞ እናሳውቃችኋለን ብለው ሸኝተውን ነበር፡፡ አልስችለን አለና ዛሬም ሄድን፡፡ በእስር የያዛችኋቸው ወንድም፣ እህት፣ ቤተሰቦቻችን እንዴት ናቸው… አሳውቁን ብለን ለመጠየቅ በጠዋት ሄድን፡፡ ጭራሽ እስከ አርብ ጠብቁ ብለው ነገሩን ደሞ ዛሬ!

የዛሬው ደሞ ይለያል፡፡ የወንድሞቻችንን ሁኔታ አሳውቁን ብለን በጨዋነት በመጠየቃችን እስር፣ ዱላ፣ አሸማቃቂ ስድብ…ምነው ምን በደልን ይህን ያህል? የተጎዱት የኛው ቤተሰቦች፣ የተጉላላነው፣ በሀዘንና በጭንቀት የምንቃትተው እኛው አይደለንም እንዴ?

አሁን የአንተ ኮማንደርነት ምኑ ላይ ነው? አዎ፣ አንተ ሰዎችን ስታስር፣ እናቶችን ስትገፈትር፣ ወጣቶችን በኃይል ስታባርር የነበርኸው ሰውዬ፣ የአንተ ኮማንደርነት ምኑ ላይ ነው? እንዲህ ሰው መናቅ ነው እንዴ ኮማንደርነት?

የዮናታን ተስፋዬ ወላጅ እናት ‹ልጄ እንዴት ሆነ?› ብለው ጠየቁህ በአክብሮት፡፡ ምላሽህ እንዲያ ነው እንዴ? እኒህን በጭንቀት ላይ ያሉ እናት አንገታቸውን በሻርፓቸው አንቀህ ‹ውሰዱና አስገቡልኝ!› አልህ፡፡ ለመሆኑ ‹ሀገሬ የት ነው?› ብለው በምሬት መለሱልህ፡፡ እውነታቸውን ነው! በህግ ጥላ ስር ነው ያለው የሚባል ልጃቸውን ደህንነት ለማረጋገጥ በመጠየቃቸው ‹አስገቡና እሰሩልኝ!› ሲባሉ ምን ይመልሱልህ?

ለመሆኑ ያን አይነት አሰቃቂ የስድብ ቃል ከየት መዝገበ ቃላት አጠናኸው? ምነው በባህላችን እንኳ እናቶች ክቡር አይደሉም እንዴ? እንዴት ነው ያ ሁሉ ስድብ፣ በዚያ ሁሉ ሰው መሃል ከአንደበትህ የወጣልህ? ወይ ጉድ!

ተው እንጂ ከልክም ልክ አትለፉ! ምን አድርገን ነው ይኸን ያህል፡፡ የዚህ ሁሉ ሰው እምባ ጎርፍ ሲወስዳችሁ ከጎርፉ ለመዳን የምትቧጥጡትን ሰንሰለት ባትበጥሱት ምን አለ?!

ወይ አለመታደል

Filed in: Amharic