ነገርን ነገር ያመጣዋል እንዲሉ በቅርቡ አንዲት የተበሳጨች ኢትዮጵያዊ- የኢሕአፓ ታሪክ እያሉ መጽሃፍ ጻፍን በሚሉ ዋሾዎች በመናደድ–በስም ጠቅሳኝ የድርጅቱን ታሪክ ባለመጻፌ ወቅሳኝና ውቀሱት ስትል መልዕክትና ምሬት ፈረንጆቹ ፌስ ቡክ በሚሉት አማካይነት አሰምታለች። ወጣት ናት በሚል ግምት አንቺ ብያለሁና ከተሳሳትኩ ይቅርታ። ብስጭቷ ቢገባኝም ታሪክ መጻፍን በተመለከተ የተንደረደረችበት ግምትና ሌሎችም የሚያሰሙት ትችት በመሰረቱ የተሳሳተ ነው። ላብራራ።
በቅድሚያ ታሪክ ሲባል ምንም ማለት ነው? በደፈናው ታሪክ ተብሎ የሚጻፈው ሀቅን ብቻ የሚያስተጋባ ነው ብሎ መደምደሙ ስህተት መሆኑን ታሪክ ተብሎ ጠባቦችና አምባገነኖችን ለማወደስ የተጻፈውና እየተጻፈ ያለው ምስክር ነው። የገዢዎችን ታሪክ ዋና አድርጎ መጻፉ የተለመደ ነውና ታሪክ የሚባለው ሚሊዮኑን ሕዝብ–ጭቁኖችን ሰርቶ አደሮችን– የማይመለከት ሆኗል። ይህን በተመለከተ ታዋቂውን ቤርቶልት ብሬሽትን በማስተጋባት ( አለና ወይም ከራስ ጋር ጨዋታ በሚለው ግጥም) የሚከተለውን ጽፌ ነበር፡
“የታሪክ መጽሐፍ ይዘቱ ቢቃና፣
ልዑል ራስ ሳይሆን ተራው የሚነሳ፣
ምን ድንጋይ ጠረበ ንጉስ ላሊበላ?
ገባሩ እንጂ ነው ፍዳውን የበላ?
ምኒሊክ በአድዋስ ብቻውን ተዋጋ?
ዮሐንስ ብቻ ነው የሞተ መተማ?
የታሪክ መጽሐፍ ይዘቱ ቢቃና፣
ታሪክ ሰሪ ዋና ያ ተብየው ተራ።
የተራው ሰው ታሪክ ያጣው ጸሐፊ ነው፣
ለመሰራቱማ ታሪክ እኮ እሱ ነው!
ታሪክ ጸሓፊዎች ደራሲነት አልሳካ ያላቸው ናቸው ተብሏል። ሌላ ሰው ደግሞ ታሪክ የሚጻፍበት ቀለም ራሱ ከመዛባት የተበጠበጠ ነው ብሏል። ዕድላችን ሆኖ ደግሞ ኢትዮጵያ ታሪክ ጸሓፊዎች ሳይዋጣላት ዘመን አልፏል። የጊዜያችን ታሪክ ጸሃፊዎችና አዋቂዎች የሚባሉትም ከግል ርብሽብሻቸው ሊላቀቁ ስላልቻሉ የጋራ ቅርስ ሊሆን የሚገባውን ያራቁቱታል። ከታሪክ መማር ይቻላል የሚለው ባዶ ይሆናል–ታሪክ ሳይሆን ዘለፋና ተረት ነውና የሚጻፈው። ታሪክ የግል ተብሎ ከቀረበ ይህ በግል ታሪክነት ደረጃ ሊነበብ ይችላል። የሕዝብና የሀገር፤ የድርጅት ታሪክ ግን የግል ስንክሳር ሊሆን አይችልም፤ አይገባውምም። ታሪክ ብለው የሚጽፉት ሚዛን አልባ፤ ሀቅ አልባ ከሆነም ታሪክን ሊቀብር እንጂ ሊተርክ አልተነሳም።ታሪክ ከተባለም ስለተባለው ታሪክ ጸሐፊው ሆነ ጸሐፊዎቹ በቅድሚያ ጠንቅቀው ማወቅ አለባቸው። ማን ያውራ የነበረ የተሻለ ቢሆንም ለቀቅ እናድርገው ከተባለም “ማን ያውራ? ጠንቅቆ ያወቀ” ማለቱ የግድ ይሆናል። አውቀው የሚያጠፉ ደግሞ የሚደብቁት ጉድ ወይም ወንጀል አለ ማለት ነው። አለበለዚያም ንግዱ ደርቷል ማለት ነው — ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስለኢሕአፓ የባጥ የቆጡን መቸክቸኩ ገንዘብ የሚያስገባ መሆኑ እንደሚታየው ማለት ነው። መተረኩ፤ ዛሬ ስለቀድሞ አጼዎች–በተለይም ምኒልክ ላይ– የሚጻፈው ሁሉ፤ ታሪክ ነው የሚባለው ሁሉ፤ በአፈ ታሪክ የተድቦለቦለ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ኤርትራን የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት የሚያደርግ ታሪክ ተፈጠረ እንጂ አልነበረም። ማን የማንን ብልትና አካል እንደቆረጠም ያን ያህል ጥርት ብሎ የታወቀ ካለመሆኑ ሌላ፤ የሁሉም የዘመኑ የጦርነት ልምድ ሆኖ የነበረ፤ ሊሆን መቻሉም እንዳለ ሆኖ ዛሬ ይህን በመጠቀም የሚጎሰመው የጥላቻ ነጋሪት ከህዝብ ታሪክ ጋር ግንኙነት ያለው አይደለም። ጥላቻን አራጋቢዎቹ ደግሞ ራሳቸው አሶሳ፣ አርባ ጉጉ፣ ወተር-አረካ፣ ጋምቤላ፣ ኦጋዴን ና በደኖ የሚሉትን የአሰቃቂ ግፍ ታሪክ ዛሬም እያደሱ መሆናቸውን መታዘባችን ያለ ነው። ታሪክ ስንል ምን ማለታችን መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል።
በቅርቡ–ማለትም ወያኔና ቅጥረኞቹ–ስልጣን ይዘው መተየብ፣ መጻፍ ከተሰማሩ በኋላ– ታሪክ ተብሎ የተጻፈው ልብወለድና ውሸት ጥቂት አይደለም። ተራራ ያንቀጠቀጠ በሚል በወያኔና ሻዕቢያ ቅጥረኛ የተጻፈውን አምስት ቅጽ ያስታውሷል። በዚህም ቅጽ ያው የኢሕአፓ ታሪክ ተብሎ የወያኔ ውሸት ተስተጋብቷል። ወዲያውኑ ዛሬ ማንነቱ ግልጽ የሆነ የኢሰፓ ካድሬና የቀይ ሽብር ተጠርጣሪ “ነበር” ብሎ ሲተርክ የቆጡን ከባጡ ብቻ ሳይሆን የካቡልን ከወልቂጤ አደባልቆ የጻፈው እንደቁም ነገር ባይቀርብ በሣቅ ያፈርሰን የነበረን ቅዠት ታሪክ ብሎ አሰፈረና በገበያም ቸበቸበ። በዚሁ “ድንቅ ታሪክ” መሰረት እኔም ስሜ ተጠቅሶ በአዲስ አበባ ተገኝቼ በአረመኔው መንግስቱ ላይ የሞት ፍርድ ስንሰጥ (አብሮኝ ነበረ የተባለውም ጓድ ያኔ በአሲምባ ነበር) አጃቢዬ ደግሞ የመኢሶን አመራር ግለሰብ (ደስታ ታደሰ) እንደነበርም ሰፍሮ ነበር። ድንቄም ታሪክ! ሌላው ደግም ምዕራብ ጀርመንና አልጄሪያ (በዘመኑ በአቅዋማቸው ተቃራኒ የነበሩ አገሮች ) ኢሕአፓን መሰረቱት ሲል አውቅኩ ያሉ ደርጎች ደግሞ ድርጅቱ በሻዕቢያ ተቋቋመ ሲሉ ቀላምደዋል። አብዮታችን፣ ትግላችን፣ ምስክርነት፣ ወዘተ በሚልም የውሸት ገበያ ደርቶ ከርሟል። ለነገሩ ታሪክ ያሉት ተረት ተረት መሆኑን በየጊዜው ድርጅቱ ምላሽ ሰጥቷቸዋል።
ታዲያ ለምን እናንተ ታሪክ አልጻፋችሁም ወደ ሚለው ጥያቄ/ክስ በመንደረደር ላይ ነኝ። ስለ ኢሕአፓ ጠላትና ሰምቶ አውሪው ከጻፈው ባሻገር ነበርን–በአባልም በአመራርም ደረጃ– ብለው ታሪክ የሚሉትን ሊጽፉ ሲነሱ እንዲሁ ውጤታቸው የማያምር ሆኖ አለ። ያልተሳካ ትረካ የሆነባቸው ምክንያቶች ደግሞ ከማን ጻፈው? እንዴትስ ተጻፈ? ከሚለው ጋር የተቆራኘ ነውና ዛሬም ቢሆን መሰል ጥረቶችን ደካማ ያደርጋቸዋል። ማለትም የድርጅቱን ሰፊ ታሪክ አንድ ወይም ሁለት ሰዎች የሚጽፉት ሊሆን አይችልም። ሙሉዉን ታሪክ ማለት ነው። ታዲያ ዝም ከሚባልስ ለምን የሚያውቁት ስለሚያውቁት አይጽፉምና ታሪኩ እየተነገረ አይቆይም? አይሟላም? ብሎ መጠየቁም ተገቢ ነው። በተለይም የሚያውቁት በጊዜና በሞት እየተጠለፉ ባለበት ሁኔታ። በመስተዋት መጽሔት በተደጋጋሚ ታሪክ ጻፍን ያሉትን እንደተቸነው ሁሉ (ለምሳሌ የአንደኛው ይድረስ ለባለታሪክ የግለሰብ ስንክሳር እንጂ ታሪክ አልነበረምና) የዚህ አማራጭ ጉድለቱ የሚከተሉት ናቸው፡
1. ጸሓፊዎቹ ካላቸው የፖለቲካ ቁርሾ፤ የግንዛቤ መንሸዋረር ያልተላቀቁ ናቸውና ብዙውን ጊዜ ድርጅቱን የመጉዳት፤ አመራሩን የመወንጀል መነሻ ሃሳብ አላቸውና ሚዛናዊ ሊሆኑ አልቻሉም። ይድረስ ባለ ታሪኩን ጻፍኩ ያለው ግለሰብ ለምሳሌ ወደ ሰራዊት ገብቶ በዚያው ከመቅጽበት የከዳና ደርግን ተቀላቅሎ በደርግም ወንጀል ተካፋይ የነበር ስለሆነ መጽሃፉ ጸረ ኢሕአፓነት ነበር ተልዕኮው። ራሱንም ሲያጋልጥ (በገጽ 237) የሚከተለውን አስፍሯል፡
“ በቀይ ሽብር ሂደት በሕዝብ ሙሉ ተሳትፎና ተግባራዊ እርምጃ እራስን የመከላከሉ ተግባር መኢሶን እስከፈረጠጠበት ጊዜ የቀጠለ ነበር። ዛሬ አንዳንዶቹ እኛ በቦታው አልነበርንም ብለው ሊክዱት እንደሚሞክሩት ሳይሆን እርምጃው ትክክለኛ የመከላከል እርምጃ ነበር። በእኔ እምነት ከሕዝብ ጎን የቆምን ሀይሎች… የአብዮቱን ፍሬ ጠብቀናል። ሕዝባችንን ከገዳይ ጥይት ተከላክለናል።”
የወንጀለኛ ዓይነ ደረቅ ይሏል ይህ ነው! ይህ ከመንግስቱና ሌሎች ያልተለየ ግለሰብ ሕዝብን የፈጀ ሂደትን እያሞገሰ ባለበት ታሪክ ጻፈ ብሎ መውሰድ አይቻልም። ወንጀል ሰርቷልና ድርጊቱን ለመደበቅ በኢሕአፓ ላይ የሀሰት ዘመቻን መዘርገፉም የሚጠበቅ ነው። መጽሃፉ ሲወጣ በቀረቡ ትችቶች ግልጽ እንደተደረገው ሁሉ የክፍሉ ታደሰ መጽሃፍም–እሱም ትግሉን የተሳሳተ ባይና በተወሰኑ አመራር አባሎች ላይ ቂሙን ሊወጣ ያለውን ፍላጎት ከመጽሓፉ ማራቅ ኣቅቶት–የጻፈውን በሀቅም ደረጃ ሆነ በግምገማ ስህተት ሊያደናቅፈው ችሏል። አንጃ ሆነው ድርጅቱን የጎዱ፤ ወደ ወያኔ የኮበለሉ (በረከትና መሰሎች)፤ ድርጅቱን ሰርገው ገብተው እንደነበር የታወቀባቸው ወዘተ ያወቅነውና የነበርንበት ታሪክ ብለው የሚጽፉት በአብዛኛው ከላይ ከጠቅስነው ድክመት ነጻ አይደለምና የነሱን ሀሰት ሀቅ ብለው የሚወስዱ ውሸትን ይጋታሉ። አረመኔዎቹ የደርግ መኮንኖችም ስለኢሕአፓ ሀቅን ይጽፋሉ ብሎ መጠበቅ ሞኝነት ነው።
2. ነበርን አውቅን የሚሉትም ሀቁ ይነገር ሲባል የሚያውቁት ውሱን ነው። ወይም ውሸት ነው። ስለ ኢሕአሠ ያውም በሁለት ቅጽ ጻፋኩ ያለው የበረከት ስምዖን ወዳጅ / ታዛዥ ግለሰብ ሠራዊቱን በደንብ አያውቀውም። ከድርጅቱም ከሠራዊቱም ከተለዩ ከሀያ (ሰላሳ፣አርባ) ዓመታት በላይ ያደረጉ እስከ 1984 ዓ.ም. ድረስ በሜዳ የቆየን ሀይል ታሪክ ሊተርኩ ብቃቱ የላቸውም። ስደት ለውሸት ያመቻልና ስንቱ ነው የትጥቅ ትግል አርበኛ፤ የከተማ ስኳድ አባል፤ የከርቸሌ እስረኛ፤ የስየል ስቃየተኛ ወዘተ ሆኖ/ነበርኩ ብሎ ዛሬ የሚጀነነው፤ የሚቧርቀው። ለዚህም ነው ያልነበሩበትን ጉዳይ እንደነበሩበት አስመስለው በስማ በለው ወይም ከሌሎች መጽሃፍት ገልብጠው ያገኙትን ሲጽፉ መጽሃፋቸው ፍሬ ቢስና ሀቅ አልባም የሚሆነው። የአውሪያቸውን/ነጋሪያቸውን ዕይታና ግምገማ ብቻ እንጂ ሁለገቡን ሀቅ አያንጸባርቁምና። በቅርቡ በወጣ መጽሃፍ ለምሳሌ ግለሰቡ ከድርጅቱ ወጥቶ በአሜሪካ ከርሞ እያለ እሱ በሌለበት የተከሰቱትን ሁኔታዎችና የተደረጉ ስብሰባዎችን ልክ እንደሚያውቅ ሆኖ አቅርቦታል። በየ ስብሰባው ሆነ በየጦርነት አውድማው የነበሩትም ቢሆን በአንድ መልክ አንድን ክስተት አይገመግሙትም። ኢሕአፓን ለማውገዝና አመራሩን ለመወንጀል በሚል ሊጽፍ የተነሳ ሸውረር ያለ የተሳሳተ ግምገማ እንጂ፤ ክስና ቂማቸውን እንጂ። ታሪክ ለመጻፍ ማወቅ መኖር ያስፈልጋል። ከኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ሳይሆን ጠርዙም ያልነበሩ ዛሬ ያን የተማሪ ትግልና ትውልድ በአሉታዊ ተቺና አውጋዥ ሆነው ይወራጫሉ። ለሕዝብና ለሀገር ሲል እንደ ጧፍ የነደደን ትውልድ ተመክሮ ማክበር ሲገባ ማንኳሰስና መዝለፉ ከሰፈነ ያልታደለና የተደየነ ትውልድ መጣ የሚያሰኝ ይሆናል።
3. ለዚህም ነው የኢሕአፓን ታሪክ ግለሰቦች–ያውም የከዱትና የጠሉት– ሊጽፉት አይችሉም፤ ከሞከሩም ፋይዳ ቢስ ወረቀት ጭረሳ ይሆናል የሚባለው። አስር በመቶን እውነት ጨብጠው ዘጠና በመቶን ሳይሆን አይቀርምና ውሸትን በመያዝ መጽሀፋቸውን ለሞቀ ገበያ ያቀርባሉ። እንደተነገረን ወይም እንደሰማነው ማለት እንኳን ይቀፋቸዋል። ወያኔ በኢሕአፓ ላይ የሀሰት ዘመቻ ከማራገቡና ከመደገፉ ሌላ ራሱም በቀጥታ ተሰማርቶበታል።
ግለሰቦች የሚነዱት የቁርሾ መጋዣ እስከሌለ ድረስ ሀቁን ሊጽፉ እንደሚችሉ በቅርቡ ኢሕአፓና ስፖርት ብሎ የወጣው መጽሃፍ (ቅጽ 1) ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የግለሰብ ስንክሳር፤ ቁርሾ መወጫ ወይም ተረት አይደለም።
ስለዚህ በፌስ ቡክ ለጻፍሽልኝ እህቴ መልሴ መበሳጨትሽ ቢረዳኝም፤
1. የኢሕፓን ሙሉ ታሪክ እኔ ብቻዬን ልጽፍ አልችልም። ሁሉን በጥልቀትና በሙሉ ዝርዝሩ አላውቀውም፤ በቀጥታ አልኖርኩትም። ለዚህም ነው ሁሉም በማን ያውራ የነበረ መሰረት የየበኩሉን ቢጽፍ የተሟላ ታሪክ ሊጻፍ ይችላል የምንለው።
2. የድርጅቱን ታሪክ ሊጽፉ የሚችሉት በትግሉ የተሳተፉ አባሎቹ ናቸው–በተለይም አሁንም በድርጅቱና በኢሕአፓ ላይ ቀና አመለካከት ያላቸው፡፡ ይህን ጥረት አመራሩ ሊያስተባብርና ሊያቀናጅ መጣር እንዳለበት ግልጽ ነው።
ታሪክ ጻፍን የሚሉት እነሱ ከለቀቁ በኋላ የቀጠለውን ታሪክ ነበር ማለት እንኳን ቢቀፋቸውም በበኩላችን የተጀመረውን የኢሕአፓ ትግል ዛሬም ቀጥለናልና፡
1/ ታሪካችንን በጋራ ለመጻፍ እየጣርን ነው–የሚቆርቁራችሁና የነበራችሁ የበኩላችሁን አስተዋፅዖ በማድረግ ተባበሩን፤
2/ አሁንም ቢሆን በትግል ላይ ነንና የስምሪታችን ሆነ የጽሁፎቻችን ትኩረት በታሪክ ላይ ብቻ ሊሆን አልቻለም፤
3/ ይህም ሆኖ ግን ታሪኩን ከመዘከር፤ ጥቃትን ከመከላከል፤ ዋሾዎችና የወያኔ ቅጥረኛ ጸሓፊዎችን ከማጋለጥና የድርጅትና የሰማዕትን ስም ከመጠበቅ ሰንፈን አናውቅም (በየጊዜው የወጡትን ጽሁፎችና ጥራዞች እንመልከት)። የአቅማችንን እያደረግን ነው–ይበልጥ ለማድረግም ተነስተናል። የኢሕአፓ ታሪክ በአባሎቹና ሀቀኛ ልጆቹ ይጻፋል ማለት ነው። በጋራ እንቻኮልበት፤ እንረባርብበት። ስለ ቀይ ሽብር መታሰቢያ ሕንጻ (ሙዚየም) የተጻፈውም የሚገርመኝ አይደለም–የወያኔ ንብረት ነው፤ አንዱን ወያኔና ወይም አንጃ አዳንቆ ሀቀኛውን ቢጥል ምኑ ያስገርማል? በዚህ ሙዚየም ለምሳሌ የባቢሌ ቶላ መጽሃፍ በእንግሊዝኛና በአማርኛ ትርጉሙ ለምን አልተቀመጠም ተብላ ሀላፊዋ ስትጠየቅ ስላላገኘነው ነው ብላ ለሰጠችው መልስ መጽሃፉ ቢወሰድላትም ወደጎን ጥላው እንደነበር እናውቃለን። ለእሷ የቡዴና/እንጀራና የሰልፍ ለውጥ ጉዳይ ነው። በጸጋዬ ገብረ መድህን የተተረጎመውን ይህን መጽሃፍ በአዲስ አበባ ብዙ ማተሚያ ቤቶች ማተምም ፈርተው ክልክል ሆኖ ቀርቷል። ሌሎችም ምሳሌዎች አሉ። እነ ደብተራውን ደብዛ ያጠፋ ቡድን የነደብተራውን ውድ ጓዶች ይዘክራል ብሎ መጠበቅም ስህተት ነው። ወያኔ ራሱስ የቀይ ሽብር ሰለባ ሳይሆን የጎን የተባ አራማጅ አልነበረምን?
በአሁኑ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ወያኔ የስልጣን ባለቤት ከሆነም ጊዜ ጀምሮ ጸረ ኢሕአፓ ዘመቻውን እንዳጧጧፈ አለ። ጠላት፤ አማራ፤ በተለይም ኢትዮጵያዊ ብሎ ስሊሚፈርጀውም ነው። በመሆኑም የድርጅቱን ታሪክ ማቆሸሽና መዋሸት የግድ ሆኖበታል። የወያኔን ጸረ ኢሕአፓ ዘመቻ ግንባር ቀደም ሆነው የሚያናፍሱ ቅጥረኞ ጋዜጠኛ በሉን ባዮች አሳዛኝ ፍጡሮች አሉ። በወያኔ አበረታታችነትም መጽሃፍም ጫርን ያሉን አሉ። ወያኔ ለቅጥፈቱ ለከት እንደሌለው ይሉኝታን ከገደሉት አንዱ የሆነውን የስብሐትን የየጊዜ ቅሌት መታዘቡ ይበቃል። የአብዬን ወደ እምዬው ልምድ ሆኗል። ስርዓቶች የፈጠሩትና ያበላሹትን ሁኔታና ችግር በኢሕአፓ ላይ መለጠፉና አልፎም የፈረደበትን ግን መለፈፍ ሳይሆን በተግባር ውድ ሕይወቱን ለሀገር የሰጠውን ቆራጡ ዋለልኝ መኮንን ላይ ስድብ ማውረዱ በወያኔ የሚደገፍ የታሪክ ትቢያዎች እንቅስቃሴ ሆኖ አለ። ነውናም፤ ሲሶ ኢትዮጵያን የሶማሊያ ግዛት ነው ብሎ ሞቃዲሾ የተፈራረመው ወያኔ፤ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ናት ብሎ የጮኸውና ከ 300 ገጽ በላይ ይህንኑ አስረግጦ መጽሃፍ የጻፈው ወያኔ፤ በሱዳን ትዕዛዝ ድልድይ ሊያፈርስ የሞከረና ደቡብ ሱዳኖችን አሳልፎ ሰጥቶ ያስገደለ ወያኔ፤ በተቃርኖ የቆመውንና አሌ ያለውን ኢሕአፓ በትምክህት ፈርጆ ከሻዕቢያ ጋር ሆኖ የወጋ መሆኑ የተረሳ ይመስል ታሪክ ተብዬ ውሸት በሆድ አደሮች እየቀረበ ነው። ኢሕአፓ ስህተቶቹን ማመኑ ብቻ ሳይሆን ራሱ ጠቁሞም ሊያርማቸው ጥሮ፤ ያረመም ሆኖ ሳለ፤ ስለ ድርጅቱ ጻፍን ባዮች ድርጅቱን የስህተት ቋት ከማድረግ ሌላ ለሕዝብና ለሀገር ያደረገውን አስተዋጾ ከቶም የሚጠቅሱ አይደሉም፤ አልሆኑም። ማን የህዝብን መሰረታዊ ጥያቄዎች አስተጋብቶ ሕዝብን ለትግል አሰለፈ? ማን የመደራጀትን ጥቅምና አስፈላጊነት በሰፊው አስተማረ? ማንስ በተጨባጭ ሰፊውን ሕዝብ ቀስቅሶና አደራጅቶ፤ ዴሞክራሲን ዋና ጥያቄ አድርጎ፤ ከሕዝብ ጎን ሆኖ ታገለ? ተሰዋ? ማን የደርግን አረመኔ ስርዓትና ደጋፊዎቹን ታገለ? ማንስ በጠዋቱ ጠባቦችን፤ ወያኔና ገንጣዮችን በሞላ ተቃርኖና የሀገርን አንድነትን ክቡር አድርጎ በመጋፈጥ የገንጣዮች ጥቃት ሰለባ ሆነ? ማንስ የሀገርን ጥቅምና ክብር ለሆድና ሹመት ስል አሳልፌ አልሰጥም ብሎ መስዋዕትነትን ተቀበለ? ማን ማውራት መቀባጠር ሳይሆን በትግል ሜዳ ደፍሮ ተሰልፎ መከራን ተቀበለ? አኩሪ ታሪክ ጻፈ? ይህ ሁሉና ብዙም ሌላ ትውልድን አስተማሪ ጀግንነት ሊተረክ ሲችል ታዲያ ነጋ ጠባ ክስን ውንጀላን መደርደርና የወያኔ ኮራኩርና ዋሾ ቅጥረኛ መሆን ለምን ተመረጠ?
ታሪካችንንማ እናውቃለ– ያውም በዝርዝሩ። ታሪካችንንማ እንፅፋለን–እየጻፍንም ነው ሊገነዘቡ የሚችሉ ካሉ። አያውቁትም የተባለውንም እናውቃለን። ከላይ የተጻፈው ሁሉ ታዲያስ በሰፊው ሀቁን አሳውቁና የሚል ጥያቄን አንሺ መሆኑን አልሳትኩትም። የጊዜ ጉዳይም አለ። ሀሰትም ለረጅም ጊዜ መንገስ አይችልምና ሀቅ ልትነገር ስትነሳ ግሳንግሱን ሁሉ በዝርዝርም በጥቅሉም ምሱን መስጠትና ርቃኑንም ማስቀረት ይቻላል። የትውልድ ታሪክና መስዋዕትነት በቀላሉ የሚያዝና የሚተረክም አይደለም–ተገቢው ክብር፤ ጥልቀትና ሀቅን እንደ ዓይን ብሌን መጠበቅን ይጠይቃል። በቅርቡ ታተምን ባሉ ርባና ቢስ መጽሓፍትና ጽሁፎች ላይ ተገቢውን ሂስ የነበሩና የታገሉ አቅርበው ባዶ አድርገዋቸዋል–ማለትም ታሪክን መከላከሉ ችላ አልተባለም። የእኔም ጸሀፊዋ ያነሳሽው በእንግሊዝኛ የመጻፍ ጉዳይ በአማርኛ ከመጻፍ ያገደኝ ነገርና ሁኔታ የለምና ሚናውና ጥቅሙን መገንዘብ እንጂ የሚወቀስ ሊሆን አይገባውም።
ነገርን ነገር ስላነሳው ይህን ምላሽ ጽፌልሻለሁ። በነገርሽ ላይ አንዳንዱ አኮ በሆድ ይፍጀው ደረጃም የሚቀመጥ ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ አሁንም ድርጅቱ በትግል ላይ ነውና ሁሉንም ዘርግፎ ለማውጣት የምስጢርና የቀጣይ ትግል ማነቆዎች አይፈቅዱለትም። በኢሕአፓ ላይ የሚጻፈው ሀሰት ሁሉ የወያኔ ጸረ ኢትዮጵያ ዘመቻ አካል ነው። የምንጠብቀው ነው። የለም፤ ተኗል፤ ጠፍቷል በሚባል ድርጅት ላይ ይህ ሁሉ ዘመቻ ማስፈለጉም ጥያቄ ሊያስነሳም ይገባዋል። ከእዚህ በተያያዘ ደግሞ ድርጅቱንም ልክ እንደ ደርግና ወያኔ እየጠሉ (ምናልባትም በወያኔ ብርና ዶላር ገፋፊነት) የድርጅቱን ታሪክ ሊቀሙ የተነሱም አሉ። የድርጅቱ ታሪክ ግን ለቅርጫና ሻሞ የቀረበ እይደለም። ያን ትውልድ ያወግዙ ዘንድ ወያኔ እንደቀጠረቻቸው ሁሉ፤ ያን ትውልድ የዘከሩና ያዳነቁ መስለው የድርጅቱን ታሪክ ሊቀሙና ከይሲ ተልኮአቸውን በስልት ከግብ ሊያደርሱም የሚወራጩ አሉ፡፡ ሁሉንም አውቀንባቸዋል፤ ነቅተንባቸዋል። ያለውን ሁኔታ በጥሞናና ሀቀኛውን ታሪክ መሰረት አድርገን ስንመረምረው ኢሕአፓ ለህዝብና ለኢትዮጵያ በመቆሙና በመታገሉ–በመዋደቁ ጠላቶቹ መብዛታቸውን ነው። የኢሕአፓ ጠላቶች የኢትዮጵያ ጠላቶች ናቸው። ይህ በመሆኑም የድርጅቱ ትግል ገና አላበቃም። ከለየላቸው ጠላቶች በተጨማሪና በከፋም ደረጃ የራሱ ጠማሞች ጎድተውታል፤ ታሪኩንም ሊበርዙና ሊያበላሹም ተነስተውበታል። ሌላ ትግል– ቸል የምንለውም ትግል አይደለም።
ስለዚህም የኢሕአፓ ታሪክ በተግባርም በጽሁፍም በድርጅቱና አባሎቹ–በአስፈላጊው ስፋት ባይሆንም– እየተመዘገበ ነው። ሙሉው ታሪክም መጻፊያው ቀኑ ደርሷል። እንደምናውቀው ድርጅቱ ሰፊ ትምህርት ቤት ነበር። አሁንም ነው። የተወሰኑት ለስምንተኛ ክፍል ፈተና ሳይደርሱ ጥለውት ሄደዋል። ወደ አስረኛ ክፍል ዘልቀውም፤ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያም ፈተናም ወስደውም የተነኑ የወደቁ አሉ። በትምህርቱ ገፍተው የጊዜ ጉዳይ ሆኖ የተሸነፉም አሉ። ሌሎች ደግሞ በትምህርቱ እስከዛሬም ቀጥለዋል። እነ እገሌዎች ደግሞ ወደ ጠላትና ፈረንጅ ትምሀርት ቤቶች ገብተው የክህደትና መሀይምነት ዶክተሮች ሆነዋል። አስመሳዮች ደግሞ በትምህርት ቤቱ ሊገኙ ቀርቶ ተስፈኞችም አልነበሩም–ይህ ግን ምላሳቸውን አልገታውም። ኑሮ ከባድ ነው፤ ዝብርቅርቅም ነው። ይህ ቢሆንም ሲኞርም ይሄዱና ፤ ማሪያ ቴሬዛውም ያልቅና፤ ያስተዛዝበናል ያም ጊዜ ያልፍና የተባለው ተፈለገም ተጠላም እውን ይሆናል –ትዕግስትን ቢጠይቅም። ከልብ ኢሕአፓን የሚወዱ ከድርጅቱ – ኢሕአፓ አንድ ብቻ ነውና– ሊተባበሩና የዚህን ሕዝባዊ ድርጅትና ታሪክ በጋራ ሊጽፉ ቢጥሩ የተመረጠ ይሆናል። ቆሻሻውንም ከጫንቃቸው ያነሳላቸዋል። የሚያሳዝነው ግን ሁሉ ሰው ስርየትንና ንጹህነትን ፈላጊ አይደለም። ያደቆነኝ ሰይጣን ይጨርሰኝ ባዮች ወደድንም ጠላንም ብዙ ናቸው።
የኢሕአፓ ሙሉና ሀቀኛው ታሪክ ይጻፋል!
ያለፈውና የነበረውን ከሚለውጡ አስመሳዮች እንራቅ