>

ለግዛው ለገሰ፤ እንደመልስ [ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም]

Prof. Mesfen Welde-Mariamግዛው ለገሰ በጣም መሠረታዊና አንገብጋቢ፣ ጊዜያዊም ጉዳዮችን አንሥቷል፤ በበኩሌ ጉዳዮቹን በማንሣቱ በጣም እያመሰገንሁት አስተያየቴን በአጭሩ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡
‹‹ህወሓት የተቁአቁአመው በአማራ ጥላቻ ነው:: ይህን ሀቅ ሳይቀበሉ ስለነፃነት ማታገል አይቻልም:: ነፃነት ደግሞ የዜግነት መበት እንጂ የወል መብት አይደለም:: ነፃነት በማንነት ትግል አይገኝም::›› ግዛው በጣም መሠረታዊ ነጥብና ሀሳብ አቅርበሃል፤ ነገር ግን ድብልቅልቁ ወጣብኝ!
መነሻ፡–‹‹ሕወሀት የተቋቋመው በአማራ ጥላቻ (ላይ?) ነው፤›› ከዚህ ትነሣና፡–
‹‹ይህንን ሀቅ ሳይቀበሉ ስለነጻነት ማታገል (መታገል?) አይቻልም፤›› ትላለህ፡፡
እንደምረዳው ግልጽ ያልሆነልኝ ግዛው ሁለቱን ዓረፍተ ነገሮች እርስበርሳቸውና እያንዳንዳቸውን ከነጻነት ጋር ያቆራኛቸው እንዴት ነው? የሚል ነው፤ በእኔ አስተሳሰብ ምንም ግንኙነት የላቸውም፤ የአማራን (በአንተው ቃል ለመጠቀም) ጥላቻም ሆነ በአማራ ላይ ያለውን ጥላቻ ይዞ ለነጻነት መታገልም ሆነ ማታገል የማይቻልበት ምክንያት አይታየኝም፤ ነጻነትን ‹‹አማራ›› ከምትለው ጋር አቆራኝተኸዋል! እንዴት ብሎ?
ሁለተኛው ዓረፍተ ነገርህ ለእኔ በጣም ፈር የለቀቀ ነው፤ ለእኔ ነጻነት ሰው ከመሆን የሚገኝ መብት ነው፤ ስለዚህም የሰው ልጆች ሁሉ መሠረታዊ የጋራ (የወል) መብት ነው፤ ከዜግነት ጋር ማያያዝህ በመሠረቱ ትክክል ቢሆንም ነጻነት የሌላቸው ዜጎች በያለበት ይገኛሉ፤ ከዚሁ ጋር አያይዘህ ‹‹ነጻነት በማንነት ትግል አይገኝም፤›› ስትልም በዝቅተኛ ደረጃ ያሉ ማንነቶችን (ለምሳሌ ባል/ሚስት መሆን፣ ክርስቲያን/እስላም መሆን፤ የዚህ/የዚያ ጎሣ አባል መሆን፣ …) ከሆነ ትክክል ትመስለኛለህ፤ በሰውነትና በዜግነት ደረጃ ካየኸው ግን እንለያያለን፤ ለእኔ መሠረታዊው ነጻነት የሚፈልቀው ማንነትን አንደኛ በሰውነት ደረጃ ሁለተኛ በዜግነት ደረጃ እያዩ በመታገል ነው፤ እኩልነት የነጻነት አካል ነው ለማለት የሚቻል ይመስለኛል፤ እኩልነትን ከነጻነት ጋር አቆራኝተህ ለመታገል የምትችለው በሰውነትና በዜግነት ደረጃ ብቻ ነው የምትል ከሆነ አብረን እንቆማለን፤ ሌሎች ዝቅተኞች ማንነቶች ለእኩልነት ቦታ የላቸውም፤ እንዲያውም አብዛኛውን ጊዜ ጸረ-እኩልነት ናቸው! የአንዳንድ ጎሣዎች አቀንቃኞች የጎሣቸው ሥርዓት ‹‹ዴሞክራሲያዊ›› ነው፤ ነጻነት አለበት ይላሉ፤ (በሴቶች ላይ የሚያሳድሩትን ክፉ ጭቆና ይረሱታል!) ይህ ወይ የማያውቁትን ለማሞኘት ነው፤ ወይም ስለዴሞክራሲና ስለእኩልነት፣ ስለነጻነት አለማወቅ ነው፡፡
ግዛው ያነሳኸው ዋና ነጥብ ሁሌም የሚረሳና በጎሠኛነት አረም የተሸፈነ ነው፤ ዜግነት! የአንድ አገርን ሰዎች በሕግ በነጻነትና በእኩልነት አዋኅዶና አዛምዶ የሚይዛቸው ዜግነት ነው፤ በጎሠኛነት ያለው መንገድ የወያኔ ብቻ ነው፤ የወያኔን መንገድ ተከትሎ ወደዜግነት መድረስ የሚቻል አይመስለኝም!
በመጨረሻ አንድ ያነሣኸው ነጥብ አለ፤ ጥላቻ በመሠረቱ ክፉ የአእምሮና የመንፈስ በሽታ ነው፤ በዚህም በሽታ ይበልጥ የሚጎዳው ማኅደሩ ነው፤ ስለዚህም ‹‹አማራን›› መውደድም ሆነ መጥላት፣ ‹‹በአማራ›› መወደድም ሆነ በጥላቻ መታየት ለዜግነት፣ ለአኩልነት፣ ለነጻነትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግዴታ አይደሉም! በተግባር ፍቅርና አብሮ የመኖር ልምዱ መኖሩን ከተለያዩ ጎሣዎች የወጡት ወጣቶች ተጨባጭ ማስረጃዎች ናቸው፤ እንኳን ሰው ነግሯቸውና አይተውም መረዳት የማይችሉ በሥልጣንና በሀብት በተለወሰ ጎሠኛነት የሰከሩትን ለማሳመን አይቻልም፤ በማየት መረዳት የሚቻል ቢሆንማ ኤርትራን አይቶ ልብ መግዛት ቀላል ነበር፤ በፖሊቲካ ጉዳይ ገና በሕጻንነት ደረጃ መሆናችን የሚረጋገጠው ጎሠኛነት በሃያ አምስት ዓመታት ውስጥ እያደገና እየሰፋ፤ ተምረናል የሚሉ ሰዎች የተሰለፉበት የእንጀራ እናት ሆኖ ማደጉና መስፋፋቱ ነው፡፡

Filed in: Amharic