>
8:25 pm - Wednesday February 8, 2023

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከታሰረበት ዝዋይ እስር ቤት ‹የለም› ከተባለ ስድስተኛ ቀን ተቆጥሯል

Temesgen Desalegn 3ፍትህ ጋዜጣ ላይ ለንባብ ባበቃቸው ጽሁፎቹ ‹ህዝብን ለአመጽ የሚያነሳሳ ጽሁፍ ለንባብ አብቅተሃል› በሚል በኢትዮጵያ መንግስት ክስ ቀርቦበት የሦስት አመት እስራት ተፈርዶበት በዝዋይ እስር ቤት የከረመው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ታስሮ ከነበረበት እስር ቤት ቤተሰቦቹ ሊጠይቁት ባመሩበት ወቅት ‹ተመስገን እዚህ እስር ቤት የለም› ከተባሉ ዛሬ ታህሳስ 3/2009 ዓ.ም ስድሰተኛ ቀን ተቆጥሯል፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ህዳር 28/2009 ዓ.ም ወንድሞቹ ሊጠይቁት ዝዋይ እስር ቤት ቢገኙም የእስር ቤቱ አስተዳደር ግን ‹ተመስገን የለም› የሚል ምላሽ በመስጠት አካባቢውን እንዲለቅቁ በማድረግ መልሷቸዋል፡፡ የተመስገን ቤተሰቦች ከዚያ ወዲህ ባሉት ተከታታይ ቀናት ተመስገን የት እንዳለ ለማወቅ ዝዋይን ጨምሮ ሸዋሮቢት፣ ቃሊቲ፣ ቂሊንጦ፣ ማዕከላዊና ሌሎች የፌደራል መንግስቱ እስር ቤቶች ቢያስሱም ተመስገንን ማግኘት አልቻሉም፡፡

ተመስገን ደሳለኝ ዝዋይ እስር ቤት እንደነበረና ከህዳር 28/2009 ዓ.ም ጀምሮ ግን ‹የለም› እንደተባሉና ተመስገንን ማግኘት እንዳልቻሉ በመጥቀስ ለፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ቤተሰቦቹ አቤት ቢሉም ‹‹እኛ ተመስገን ደሳለኝ ዝዋይ እስር ቤት እንደነበር ከምናውቀው ውጭ አሁን የት እንዳለ አናውቅም›› የሚል ምላሽ አግኝተው ተመልሰዋል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ለእስር ከተዳረገ ሁለት አመታት ያለፉ ሲሆን፣ ባለፈው ጥቅምት 3/2009 ዓ.ም በአመክሮ መፈታት ይገባው የነበር ቢሆንም መንግስት ለተመስገን የአመክሮ መብቱን በመንፈጉ በእስር መቆየቱ ይታወሳል፡፡ የዝዋይ እስር ቤት አስተዳደር ተመስገንን አመክሮ ለመከልከሉ ያስቀመጠው ምክንያት ‹አሁን በሀገሪቱ ለሚስተዋለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ያንተ ጽሁፎች አስተዋጽኦ አላቸው› በሚል እንደሆነ ተገልጹዋል፡፡

አሁን ላይ ለጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ታስሮ ይገኝበት ከነበረው እስር ቤት ‹የለም› መባል ምንም የተሰጠ ምክንያት አለመኖሩን ከቤተሰቦቹ ለማረጋገጥ ይቻላል፡፡

በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 21 በጥበቃ ስር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎችን መብት በተመለከተ ይደነግጋል፡፡ በዚህ አንቀጽ ላይ እንደሰፈረው፣ በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቁ ሁኔታዎች፣ በቤተሰቦቻቸው፣ በጓደኞቻቸው፣ በሃይማኖት አባቶቻቸው፣ በህግ አማካሪዎቻቸው እንዲጎበኙ ተደርገው መያዝ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የአሁኑ ሁኔታ ይህን የህገ-መንግስቱ ድንጋጌ በግልጽ የሚጥስ ነው፡፡ መንግስት ጋዜጠኛ ተመስገን የት እንደሚገኝ ለቤተሰቦቹ የማሳወቅና ደህንነቱን የማረጋገጥ ግዴታ አንዳለበት ማስታወስ ያስፈልጋል፡

Filed in: Amharic