>

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላስ??!! (አለማየሁ አንበሴ)

አዲስ አድማስ

“ሃሳቦች አዕምሮን ከአዕምሮ የሚያገናኙ ድልድዮች ናቸው”

adis-adimas-09012017የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላ፣በተለይ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በተቃውሞና በቀውሱ ሰዓት ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው በኮማንድ ፖስቱ ቁጥጥር ስር ከዋሉ ከ24ሺ በላይ
ግለሰቦች መካከል 9ሺ ገደማው ባለፈው ሳምንት ስልጠና ተሰጥቷቸው መለቀቃቸው አይዘነጋም፡፡ ከ2ሺ በላይ የሚሆኑትም ክስ ይመሰረትባቸዋል ተብሏል፡፡ በቀሪዎቹ 12ሺ ግለሰቦች
ላይም ማጣራት እየተደረገ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ፋይዳ፣ ከህዝብ ጋር እየተደረጉ ባሉ ውይይቶች፣የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲያበቃ ስለሚኖረው ሁኔታ (ተስፋዎችና
ፈተናዎች) —– የፓርቲ አመራሮችንና ፖለቲከኞችን አነጋግሮ አስተያየታቸውን አጠናቅሮታል፡፡ ለፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄው ፖለቲካዊ ውይይት ነው፡፡

“ህዝብን ማወያየት አያስፈልግም፤ ጥያቄውን በአደባባይ አቅርቧል”
ተማም አባቡልጉ (የህግ ባለሙያ)

ህዝባዊ ውይይቶች ለምንድን ነው የሚደረጉት? ለምን ያስፈልጋል? ህዝቡ አደባባይ ወጥቶ ግልፅ የፖለቲካ፣ የመብትና የዲሞክራሲ ጥያቄዎችን ጠይቋል፡፡ ለነዚህ መልስ መስጠት ነው የሚያስፈልገው፡፡ የእኩልነትና የመብት ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ ይሄን በአግባቡ መመለስ ነው። ህዝቡኮ እነዚህን ጥያቄዎች በማያሻማ መልኩ በግልፅ ጠይቋል፡፡ ከነዚህ ሌላ ምን ጥየቄ ለመስማት ነው ህዝባዊ ውይይት የሚደረገው? እንደ’ኔ ይሄ አስፈላጊ አይመስለኝም፤ አቅጣጫ ማስቀየሪያ ነው የሚሆነው፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ቢሆን ሀገሪቱን በወታደራዊ ኃይል ስር አስገብቶ እንደማስተዳደር ነው የሚቆጠረው፡፡ ይሄም ቢሆን የህዝቡ ትግል ውጤት ነው፡፡ የእነ ዶ/ር መረራ ጉዲና መታሰር ደግሞ የመድብለ ፓርቲ ስርአቱ ውሸት መሆኑ የተረጋገጠበት ነው፡፡ እኔ እንደዚህ ነው የምረዳው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምንም የጎላ ውጤት አላመጣም፡፡ የህዝቡ የመብት ጥያቄ በፊትም የነበረ ነው፡፡
አዋጁ የህዝብ አንደበት የነበሩ ሰዎችን እንዲታሰሩ አድርጓል፡፡ የፀረ-ሽብር ህጉ ሲወጣም እንዲሁ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ነበሩ የታሰሩት። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለኮማንድ ፖስቱ ሁሉንም ስልጣን የሰጠ እንደመሆኑ መብትን በመገደብ፤ ፀጥ ሊያሰኝ ይችላል። ይሄ ግን ዘላቂ ውጤት አያመጣም። ማዳፈን የበለጠ ነገሮችን ያባብሳል፡፡  ከዚህ ይልቅ መብት ሰጥቶ፣ ህዝብን ነፃ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ወጣቶች አሁን የሚታደኑበትና በፍርሃት የተያዙበት ወቅት ነው፡፡ ይሄ ለሀገራችን የሚበጅ አይሆንም፡፡ ህዝቡ የጠየቀውን ሳያጓድሉ መስጠት ነው ዋናው ቁም ነገር፡፡ ህዝቡን ማወያየት ሳይሆን ህገ መንግስቱን ማሻሻል ካስፈለገ ማሻሻል፣ ምርጫ ቦርድን እንደገና ማዋቀር፣ ፍ/ቤቶችን ነፃና ገለልተኛ አድርጎ ማደራጀት … የመሳሰሉትን እርምጃ መውሰድ እንጂ ህዝቡ በአደባባይ በግልፅ ከተናገረ በኋላ ማወያየት ለምን ያስፈልጋል? የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መፍትሄ እንደማይሆን አውቆ ለፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሄ ማምጣት ነው የሚበጀው፡፡

“ህዝብን ማወያየት ብቻውን መፍትሄ አይሆንም”
ዶ/ር በዛብህ ደምሴ

ከህዝብ ጋር ውይይት ማድረግ ጠቃሚ ነው። ቢያንስ ከህዝቡ ብሶቶቹን መስማት ይቻላል። ዋናው ጥያቄ ግን ከእነዚህ ውይይቶች፣ ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ ተገኝቷል ወይ የሚለው ነው፡፡ ህዝቡ የሚያነሳቸው ችግሮች ሳይሸፋፈኑ ተደምጠው ትክክለኛ መልስ አግኝተዋል ወይ የሚለው ነው ዋናው ጥያቄ፡፡ ለተፈጠረው ችግር ማስታገሻ ብቻ ለማድረግ መሯሯጥ የትም አያደርስም ምክንያቱም ህዝብ የሚጠይቀው በህይወት የመኖር ጉዳይ ነው፡፡ መንግስት ከህዝብ ጋር እንዲወያይ  እኛም ስንጠይቅ ነበር፡፡ ነገር ግን ውይይቱ ሀቀኛ መሆን አለበት፡፡ የህዝብ ብሶት ማዳመጫ መድረክ ሊሆን ይገባል፡፡ ህዝብን ማወያየት ጥሩ ነው፤ ግን ብቻውን መፍትሄ አይደለም፡፡
በኔ እምነት ለኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም ከተፈለገ፤ ተቃዋሚዎች ለሚያነሱትም ሆነ ህዘብ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ገዥው መንግስት ሰፊ ልብ ኖሮት፣ በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይቶ፣ ለችግሮች ሀቀኛ መፍሄት ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ ሰዎችን ማሰር መፍትሄ አያመጣም፡፡ እውነተኛ ውይይት ይደረግ የምንለውም በተደጋጋሚ መሰል በሀቅ ላይ ያልተመሰረቱ ውይይቶች እየተደረጉ ለሚዲያ ፍጆታ ብቻ ሲውሉ ስለምንታዘብ ነው፡፡
በየትኛውም ሀገር ችግር ሲያጋጥም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይታወጃል፡፡ ነገር ግን አሁን በኢትዮጵያ የታወጀው አዋጅ ለኢትዮጵያ ችግር መፍታሄ የሚያመጣ አይሆንም፡፡ ችግሩን መፍታት የሚቻለው በሀገሪቱ ጉዳይ ከፍተኛ ውይይቶች ያለፍርሀት ያለመሸማቀቅ በነፃነት ሲደረጉ ነው፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በራሱ እነዚህን መብቶች ገዳቢ ነው፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለጊዜው ፋታ ሰጥቶ ሰላም አስገኝቶ ሊሆን ይችላል ግን የአዋጁ ጊዜ ከማብቃቱ በፊት ቢያንስ መንግስት ለህዝቡ ጥሩ ተስፋ ማሳየት አለበት። አሁን የሚፈለገውን ያህል ተስፋ በግሌ አላየሁም።  አሁንም ሰዎች ይታሰራሉ፡፡ ቢያንስ ይሄ መቅረት ነበረበት፡፡ የሰብአዊ መብቶች በተግባር እየተረጋገጡ መምጣት አለባቸው፡፡
ዲሞክራሲው ክፍት እንደሚሆን ተስፋዎች መታየት ነበረባቸው፤ እነዚህን እያየን አይደለም፡፡ ከተቃዋሚዎች ጋር ውይይት እየተደረገ አይደለም፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ እኒህን በተግባር ማየት ነበረብን፡፡

“ሁሉም ነገር ከማስመሰል የተላቀቀ ቢሆን መልካም ነው”
ዳንኤል ተፈራ

በአንድ ሀገር ውስጥ ያለ ችግር በውይይት መፈታቱ መልካም ነገር ነው፡፡ ቀዳሚና ተመራጩ መንገድም ይኼው ነው፡፡ ነገር ግን በውይይት መፍታት ሲባል፣ በምን መንገድ የሚለው ጥያቄ መነሳት አለበት፡፡ ህዝን እያወያየን ነው ሲባል  የተወሰኑ ግለሰቦችን ነው ወይንስ በቴሌቪዥን እንደምናያቸው የተለያዩ እናቶችን ነው? ወይንስ በትክክል ጥያቄውን ያነሳው ህዝብ ነው የሚለው መታየት አለበት፡፡ እውነተኛ ውይይት አድርጎ ችግሮችን ለመፍታት ከተፈለገ፣ በዋናነት ባለድርሻዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የፖለቲካ ድርጅቶችና ፖለቲከኞች፣ የሲቪክ ማህበራትና የሀገር ሽማግሌዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህ ጋር የሀገሪቱን ችግሮች ሳይሸፋፍኑ፣ ፍርጥርጥ አድርጎ መነጋገር ነው የሚያስፈልው እንጂ እንዲሁ ዝም ብሎ በቀበሌና በወረዳ “አንተም አንቺም ነይ” ተባብሎ፣ ለሚዲያ ፍጆታ በሚመስል መልኩ ውይይት አደረኩ የሚለው ነገር ብዙም ፍሬያማ አይሆንም፡፡ ሌላው በሙስና ሰዎች እየታሰሩ ነው መባሉ፣ ለኔ አሁንም ያው እንደበፊቱ ነው፡፡ ዝሆኖችን ትቶ ጥንቸሎችን ማሳደድ አይነት ነገር ይመስላል፡፡ የተወሰኑ ሰዎችን አስሮ፣ እንዲህ እያደረግሁ ነው የሚል መልዕክት ማስተላለፍ ብቻ በቂ አይሆንም፡፡ በትክክል ሙስና የሚሰሩት ላይ እርምጃ እንወስዳለን ከተባለ፣ ከላይ ጀምሮ ወደ ታች መውረድ ያለበት፡፡ ከዝሆኖቹ እስከ ትናንሽ ጥሬ ለቃሚ ዶሮዎች ነው መውረድ ያለበት፡፡ ሁሉም ነገር ከማስመሰል የተላቀቀ ቢሆን ውጤት ሊያመጣ ይችል ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡
አሁን ላይ ሆነን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለውጥ አምጥቷል አላመጣም ማለት የምንችል አይመስለኝም፡፡ ዋናው ወደ አዋጁ ያደረሰው ምክንያት ተደራራቢ ችግሮች መኖራቸው ነው፡፡ ችግሮችን ከስር ከስር ገዥው ፓርቲ መቅረፍ ባለመቻሉ የተፈጠረ ነው፡፡ አሁን ዋናው ጥያቄ መሆን ያለበት፣ አዋጁ ለውጥ አምጥቷል አላመጣም የሚለው ሳይሆን፣ ለአዋጁ ምክንያት የሆኑት ችግሮች ከስር ተነቅለው ተቀርፈዋል አልተቀረፉም የሚለው ነው፡፡ ጥያቄዎች በትክክልና በአግባቡ ተመልሰዋል ወይ? ነው ጥያቄው፡፡ እርግጥ ነው አዋጁ ጊዜያዊ ፀጥታ አምጥቷል፤ ያ ዘላቂ እንዲሆን ህዝቡ ያነሳቸውን ጥያቄዎች መመለስ፤ የፖለቲካ ማሻሻያዎችን ማድረግ፣ ነፃ ሚዲያ መፍጠር የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ላይ የሚደረጉ እስራቶችና ወከባዎችን ማቆም … እነዚህ ናቸው ዋና ዋናዎቹ የውጤቶቹ መመዘኛዎች፡፡

“መፍትሄ ለማግኘት ትክክለኛ ችግሩን ማወቅ ያስፈልጋል”
በፍቃዱ ኃይሉ (የዞን 9 ጦማሪ)
(የቀድሞ የ“አንድነት” ድርጀት ጉዳይ ኃላፊ)

በመጀመሪያ ይሄን ሀሳቤን ስሰጥ ለሀገር ይጠቅማል በሚል ቅን እሳቤ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ ምናልባት ጊዜያዊ ፀጥታ አምጥቷል ብዬ አስባለሁ፡፡ ይሄ ጊዜያዊ ፀጥታ ግን ከዘለቄታዊ ሰላም ጋር መምታታት የለበትም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላ በፍርሃትም ይሁን ኮማንድ ፖስቱ እርምጃዎችን የመውሰድ ሰፊ እድል ስላለው፣ በዚያ ፍራቻ ሰዎች ይቆጠባሉ፡፡ ይሄ አንፃራዊ የሆነ ጊዜያዊ ፀጥታ ፈጥሯል፡፡ ግን ዘለቂታዊ ሰላም ይመጣል ወይ በሚለው ላይ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ መንግስት ከሚናገራቸው ነገሮች እንደምንረዳው፣ የተወሰኑ ድክመቶች አሉብኝ ብሎ አምኗል፡፡ ግን ከመልካም አስተዳደር የዘለለ አይደለም የሚለው ትልቅ አወዛጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ የተቃውሞው አንድምታ ግን ያንን አያሳይም፤ ከመልካም አስተዳደር የዘለለ ነው፡፡ መንግስት ያንን መነሻ አድርጎ፣ በዚህ የአዋጅ ጊዜ ውስጥ የካቢኔ ለውጥ አምጥቷል፡፡ በፍ/ቤት ደረጃ የተወሰኑ የሙስና ክስ ፋይሎች ተከፍተዋል፡፡ የአስተዳደር ለውጡ ወደ ታች ይወርዳል እየተባለ ነው፡፡ የብሄር ቅሬታዎችን ለመፍታት ይመስላል፣ በኮታ በሚመስል መልኩ ስልጣን ለማከፋፈል ተሞክሯል፤ በእውቀትም ምሁራን ለማስቀመጥ በዚህ ጊዜ ውስጥ ተሞክሯል፡፡
ግን ትልቁ ነገር መንግስት ችግር እንዳለበት ያወቀ ቢሆንም፣ ችግሩ ምንድን ነው የሚለውን ከህዝቡ ለመጠየቅ አልፈቀደም፡፡ በፊትም አሁንም ይሄ ትልቁ የመንግስት ድክመት ነው፡፡ ከህዝቡ ችግሩን በትክክል አልጠየቀም፡፡ እኔ በአዋሽ 7 በስልጠና ላይ እንደሰማሁት የመንግስት ድምዳሜ የችግሩ ትልቁ መነሻ የመረጃ ክፍተት ነው የሚል ነው፡፡ ማህበራዊ ሚዲያዎችና በውጭ ያሉ መገናኛ ብዙሃን፡- ኢሳትና ኦኤምኤን የሚሰራጩት መረጃዎች የተሳሳቱና ህዝብን ያሳሳቱ ናቸው ብለው ነው የደመደሙት፡፡ የተሃድሶ አላማውም እኔ እንደተረዳሁት፣ ያንን ለማረም ነው የሚመስለው፡፡ “በተሳሳተ አላማ ተሳስተው፣ መንግስትን ያወኩ ሰዎችን ማረም” የሚል ነው ሀሳቡ፡፡ እስካሁን የደረሰው ተቃውሞና ግጭት “የቀለም አብዮት ውጤት ነው የሚል ነበር ሲያስተምሩን የነበረው፡፡ መንግስት ጥፋቱ አለብኝ ቢልም “የውስጥ ድክመቶችን የውጭ ኃይሎች ተጠቅመውበት አመፅ ፈጠሩ” የሚል ነው ድምዳሜው፡፡ ግን ይሄ ከህዝቡ ጋር አለመነጋገር የፈጠረው ክፍተት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ መንግስት አሁን ባለበት ሁኔታ ከህዝቡ ትክክለኛ መረጃ ያገኛል ብዬም አላምንም፡፡ ምክንያቱም ሀቁን በትክክል የሚያንፀባርቁ ሰዎች እየታሰሩና እየተሸማቀቁ፣ የህዝብን ትክክለኛ ስሜት አውቃለሁ ማለት የማይቻል ነው፡፡ በትክክል የህዝብ ድምፅ ሳይሰማ ሲቀር ነው ችግሮች ወደ አመፅ የሚሄዱት፡፡ ተቃውሞውን ካየን በመጀመሪዎቹ ጊዜያት፣ ሰው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሲገልፅ ነበር። ፋብሪካዎችን ማቃጠልና ንብረት ማውደም ወደ መጨረሻው አካባቢ የተፈጠረ ነው፡፡ ይሄ የሚያሳየን ሰላማዊ መንገዶች በተዘጉ መጠን ኢ-ሰላማዊ የሆነ ነገር ይመጣል ማለት ነው፡፡
አሁን በህዝብና በመንግስት መካከል እየተደረገ ነው የሚባለው ውይይትም ቢሆን በሁለት ተመጣጣኝ አካላት መካከል እየተደረገ ባለመሆኑ የሚፈለገው ውጤት ይመጣል ብዬ አላስብም፡፡ አብዛኛው ዘንድ ያለው የሚደርስብኝ ነገር ስለሚያስፈራኝ፣ የልቤን አልናገርም የሚል ስሜት ነው፡፡ መፍትሄ ለማግኘት ትክክለኛ ችግሩን ማወቅ ያስፈልጋል; ግን አሁን በተያዘው አኳኋን ይሄ እየተደረገ አይደለም፡፡ “ችግራችሁ ይሄ ነው፤ በቃ መፍትሄ እሰጣችኋለሁ” ነው እየተባለ ያለው እንጂ ችግራችሁ ምንድን ነው?” እየተባለ ህዝቡ እየተጠየቀ አይደለም፡፡ ከታች ወደ ላይ ሳይሆን ከላይ ወደ ታች ነው እየተወረደ ያለው፡፡ ይሄ ደግሞ መልኩ ይለያይ እንጂ የበፊት አካሄድ ነው፡፡
እኔ መጀመሪያ አዋጁ ሲታወጅ፣ በርካታ ሰው ሊታሰር እንደሚችል ገምቼ ነበር፡፡ የገመትኩትም ሆኖ ከ24 ሺህ ሰው በላይ ታስሯል፡፡ ያልገመትኩት የካቢኔ ለውጡን ነበር፡፡ ለውጡ የመጨረሻው መፍሄት ነው ባልልም ጥሩ ነው፡፡ ምሁራንን አምጥቶ ሚኒስትር ማድረግ በራሱ ችግሮችን ይፈታል ብዬ አላስብም፡፡ በመጀመሪያ በውስጣችን የነገሰው ፅንፍ የያዘ የፖለቲካ ወገንተኝት እንዲቀረፍ መደረግ ነበረበት ብዬ አምናለሁ፡፡ በተረፈ ችግሮቹ በደንብ ታውቀው እስካልተቀረፉ ድረስ የዘለቄታው አጠራጣሪ ነው የሚሆነው፡፡

Filed in: Amharic