>
4:47 pm - Tuesday September 28, 2021

በውስጥ መሥመር ከታማኝ ሰው የደረሰኝ ዜና [በፈቃዱ ዘ ኃይሉ]

(በውስጥ መሥመር ከታማኝ ሰው የደረሰኝ ዜና /ከእስር ቤት የተላከ/)

ananiya-sory-getachew-shibeshi-and-elias-gebiru-by-befeqadu-z-hailu“ሳይከሰሱ የታሰሩት ሁለት ጋዜጠኞች እና አንድ ፖለቲከኛ ድንገት በተጠራ ስብሰባ ላይ በፖሊስ ኃላፊዎች ጠንካራ ትችቶችን ሰነዘሩ”

****

“እኛ የታሠርነውም ሆነ በሀገሪቷ ላይ የታሠረው ቋጠሮ የሚፈታው ነፃነት የመጣ ቀን ብቻ ነው!” ~ ጋዜጠኛ አናንያ ሶሪ

“ኢህአዴግ እና ኮማንድ ፖስቱ ብቻ፡- ለሀገር ተቆርቋሪ አድርጋችሁ አትንገሩን እኛም ስለሀገራችን ጉዳይ ያገባናል ፣ያንገበግበናል!” ~ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ

“ፍቱን ወይም ስቀሉን፣ የግፍ እስረኞች ነን!” ~ ፖለቲከኛ አቶ ዳንኤል ሺበሺ

ማክሰኞ ጥር 30 ቀን 2009 “አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ”ን ተከትሎ በቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ውስጥ በኮማንድ ፖስቱ ታስረው የሚገኙ ወደ 240 የሚጠጉ እስረኞችን “ኮማንድ ፖስቱ እናንተን እንድናነጋግራችሁ እና ሐሳባችሁን ተቀብለን እንድናስተላልፍለት ልኮናል” ያሉ ሁለት የመምሪያው ዋና ሳጅን መርማሪዎች እና ሁለት ኢንስፔክተሮች አነጋገሯቸው ነበር፡፡ ያለ ክስ ተይዘው የሰነበቱት ተሰብሳቢዎቹ እስረኞችም በስብሰባው መዝጊያ ላይ የተሰማቸውን እርካታ በፉጨት እና በደማቅ ጭብጨባ ገልጸዋል፡፡

የተደረገው ድንገተኛ ውይይትም በምሳ ሰዓት ሲኾን በቅድሚያ ቢንያም የሚባለው መርማሪ ፓሊስ ልዑካኑ የመጡበትን አላማ በአጭሩ ተናግረዋል፡፡ በእስር ላይ የሚገኙ እስረኞች በሙሉ መኖር አለመኖራቸውን በሥም ተጠርቶ ከተጠናቀቀ በኋላም እስረኞች፡- ‹‹አለብን›› የሚሉትን ችግሮች እንዲያነሱ ዕድል መስጠት ተጀመረ፡፡ “ተከራይ እና በቤት አከራይ ጉዳይ ተጠርጥረው፤ በስልካቸው ሚሞሪ ላይ የተለያዩ መረጃዎች፣ ማለትም ፎቶግራፎች እና ቪዲዮዎች ተገኝተዋል” ተብለው የተጠረጠሩ እስረኞች ጉዳይ የየራሱን መፍትሔ ያላገኘ ጥያቄ በማንሳት የአየር ጊዜውን እንዳይዙ መርማሪ ቢንያም አሳስቦ ነበር፡፡

በቅድሚያ ሐሳባቸውን ለማቅረብ ዕድል ያገኙ እስረኞችም ያለ አግባብ ከአራት ወራት በላይ መታሰራቸውን፤ እስካሁን ድረስ ግን ምንም ዓይነት ፍትሕ አለማግኘታቸውን፤ በዚህ (ቦሌ ክ/ከተማ) መምሪያ የታሰሩ እስረኞች ጉዳይ አነስተኛ ነው ተብሎ በመርማሪ ፖሊሶች በግልጽ ቢነገርም፡- ከባድ ወንጀል ሠርተዋል የተባሉ እስረኞች ግን ለሥልጠና ተልከው መለቀቃቸውን፤ በዚህ መምሪያ ለታሰሩ እስረኞች ዛሬም ድረስ መፍትሔ መስጠት ባለመቻሉ በመንግሥት ማዘናቸውን እና አሁንም መፈታት እንደሚፈልጉ በጥልቅ የሐዘን ስሜት ውስጥ ሆነው ተናግረዋል፡፡

በዚሁ እሥር ቤት ታስሮ የሚገኘው ጋዜጠኛ አናንያ ሶሪም ሐሳቡን እንዲናገር ዕድል ተሰጥቶት የሚከተለውን ተናግሯል:- “እዚህ እስር ቤት ውስጥ በተለያዩ ጉዳዮች ተጠርጥረን የታሰርን ሰዎች አለን፡፡ ፍቃድ በሌለው መሣሪያ፣ በሚሞሪና በተለያዩ አጥጋቢ ባልሆኑ ምክንያቶች የታሰሩ አሉ፡፡ የፖሊስ አባላት እና ወታደሮችም ጭምር ታስረዋል፡፡ ነገር ግን ምንም አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጣቸው አልቻለም፡፡ ባለፈው በነበረን ሰፊ ውይይት መርማሪ ቢንያም ‘እናንተ በከባድ ወንጀል ተጠርጥራችሁ ቢሆን እዚህ እንደማትገኙ ይልቁንም ሌላ ቦታ እንደምትታሰሩ እናንተም፣ እኛም እናውቃለን፤ ስለዚህ መፍትሔ እስከምታገኙ ትንሽ ታገሱን’ ብሎ ነበር፡፡ ሆኖም እኛ እዚሁ እስር ቤት ታስረን እያለን ሁለት ዙር ሥልጠና የሔዱ ሠልጣኞች “ሠልጥነው“ ተፈትተዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ፍትሕን መስጠት አለመቻላችሁን ነው፡፡ የዘገየ ፍትህ ደግሞ እንደሌለ ይቆጠራል፡፡ ኢሕአዴግ እንኳ፡- ‘አንዱ የመልካም አስተዳደር ችግር ፍትሕ በአፋጣኝ አለመስጠት ነው!’ እያለ በሚለፈፍበት ወቅት ወደ ባሰ የፍትሕ እጦት መግባት እጅግ ምፀት ነው፡፡ እኔና ባልደረባዬ ኤልያስ ገብሩ፡- ‘ከኦነግ እና ግንቦት7 ጋር በመገናኘት ተልእኮ ተቀብላችሁ ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን ልትንዱ ተንቀሳቅሳችኃል!’ በሚል የተለመደ እና ምንም መረጃ ሊቀርብበት በማይችል ከንቱ ውንጀላ እዚህ መጥተናል፡፡ እውነታው ግን እኛ ለሕዝባችን በድፍረት በመከራውም ቀን ቢሆን ከጎኑ ቆመን ድምፁን በማሰማታችን ይህ እንደ ወንጀል ተቆጥሮብን ነው፡፡ እዚህ የተገኘነውም ስለራሳችን ጉዳይ ሳይሆን ስለሀገር እና ሕዝብ ያገባናል ብለን ስለጻፍን፣ ስለተናገርን ነው ዋናው ወንጀላችንም ‘ወጣት መሆናችን ነውዐ’:፡፡

“ኮማንድ ፖስቱ ፊት ለፊት ቀርቦ ሊያናግረን ያልቻለው ለምንድን ነው?! ለእኔ ኮማንድ ፖስቱ በጨለማ የሚሠራ ስውር ኃይል ነው፤ እኛ የማንም ተላላኪ አይደለንም፤ እዚሁ አገራችን ላይ ሆነን በድፍረት ሥራችንን የምንሠራ እንጂ የማንንም አጀንዳ ለማስፈፀም የምንሯሯጥ ጭፍራ አይደለንም፤ በራሳችን ሐሳብ የቆምን ጋዜጠኞች ነን፤ መከራውንም ለመቀበል ስንዝር የማናመነታ ነን፤ የምንሠራውን ጠንቅቀን እናውቃለን፤ ስለ አገራችን ስንልም ወደፊትም ከመናገር፣ ከመጻፍ አንቆጠብም!

“ባለንበት እስር ቤት ውስጥ እኛን ጨምሮ በርካታ እስረኞች ለሕመም ተዳርገዋል፤ በአንድ ክፍል ውስጥ 40 እና 50 ሆነን ታጉረን ነው ያለነው። ይህ እንኳ ከአገሪቱ ነባራዊ እውነታ አኳያ የሚጠበቅ ቢሆንም፤ ቢያንስ ከአእምሮ ሕሙማን ጋር ልንታሰር አይገባም ነበር፡፡ የሰው ልጆች ሆነን ሳለን እንደ እንስሳ እየበላን እና እየጠጣን ብቻ በረት ልንታጎር ባልተገባ ነበር፤ ለዚህ ሁሉ መንስኤው አገሪቱ የገባችበት ቀውስ ሲሆን መፍትሔው ደግሞ ነፃነት ብቻ ነው! እኛ የታሰርነውም ሆነ በሀገሪቱ ላይ የታሠረው ቋጠሮ የሚፈታው ነፃነት የመጣ ቀን ብቻ ነው!”

ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩም የመናገር ዕድል በተሰጠው ጊዜ ተከታዩን ሐሳብ ሰንዝሯል፡- “እዚህ ፖሊስ መምሪያ ውስጥ ከ20 ቀናት አንስቶ አምስት ወራት ያለፋቸው እስረኞች በኮማንድ ፖስቱ ተጠርጥረው ያለበቂ ምክንያት ታስረው ይገኛሉ፤ እዚህ ያለን እስረኞች በመርማሪ ፖሊሶች አንድ ወይም ሁለት ቀናት ቃላችንን ከመስጠት ውጪ እንዲሁ ተቀምጠን ነው የምንገኘው፤ ከባድ በሚባለው የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ የተጠረጠረ ግለሰብ እንኳን በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ የምርመራ ጊዜውን ጨርሶ ምንም ካልተገኘበት ወይ ነፃ ይባላል፤ አሊያም ክስ ይመሠረትበታል፡፡ እዚህ ግን በሁለት ዙር ለሥልጠና የተላኩ እስረኞች ተፈትተው መጥተው ጠይቀውናል፤ ሌላ ለውጥ የለም፡፡ ይሄ መምሪያ ውሳኔ የመስጠት ችግር እንዳለበት እንሰማለን፤ ችግር ካለባችሁ ችግራችሁን ፈትታችሁ ለእኛም መፍትሔ ስጡን፡፡ ይሄ ፖሊስ መምሪያ የሚነበቡ መጽሐፍትን እና ጋዜጦችን እንኳን ለመፍቀድ ያቃተው ነው፡፡ መፍትሔ ለመስጠት ችግሩ ያለው ኮማንድ ፖስቱ ጋር ከሆነም አጣርታችሁ ንገሩን፤ ኮማንድ ፖስቱም ቢሆን በስውር የሚሠራ ኃይል መሆኑ ነው የሚሠማኝ፤ በዚህ ነጥብ ላይ ከአናንያ ጋር ተመሳሳይ ሐሳብ እንጋራለን፡፡ እዚህ በታሰርንበት ቦታ አንድም ቀን አንድም ሰው ከኮማንድ ፖስቱ መጥቶ ያነጋገረን የለም፤ እውነት አለኝ ብሎ የሚያምን ኃይል ተደብቆ ሳይሆን ፊት ለፊት ወጥቶ ነው በሐሳብ መከራከር፣ መሟገት ያለበት፤ በእኔ እምነት፤ ኮማንድ ፖስቱ ፊት ለፊት መጥቶ የማያነጋግረን ነገ ላይ ኃላፊነት መውሰድ ስለማይፈልግ ነው፡፡ መሐል ላይ ሸፍጥ እንዳለ ይሰማኛል የቂም በቀል ውጤትም ነው፡፡ እኛን እዚህ ያሳሰረን ኮማንድ ፖስቱ የነገ ተጠያቂነትን ስለሚፈራ በግልጽ አይታይም ይህንን እናውቃለን፡፡

ዛሬ ሥልጣን ላይ ያለው ኢሕአዴግ ነገ እኮ ሥልጣን ላይ አይኖርም! ገዢ ኃይል ይመጣል፣ ይሔዳል አገር እና ሕዝብ ግን ይቀጥላሉ፡፡ ኢሕአዴግ እና ኮማንድ ፖስቱ ብቻ ለሀገር ተቆርቋሪ እንደሆኑ አድርጋችሁ አትንገሩን፡፡ እኛም የዚችን አገር ዜጎች ነን፡፡

“ስለአገራችን ጉዳይ ያገባናል፣ ያንገበግበናል! ‘መንግሥት አስተማሪ ነው’ አትበሉ! መንግሥት አስተማሪ ብቻ ሳይሆን ተማሪም ጭምር ነው፡፡ መንግሥታት ጥሩ ይሠራሉ፤ መንግሥታት ያጠፋሉ፡፡ በዓለም ላይ ካየነው ከዚህ ረገድ ኢሕአዴግ ቅዱስ ነገር እንዳደረገ አድርጋችሁ አትሳሉብን። እናውቀዋለን! ታሪክ ይፈርዳል! ሳልታሰር ውጪ ላይ ሆኜ የምናገረውን ሐሳብ ዛሬ ስለታሰርኩ የምተወዉ አይደለም! እዚህ እስር ቤትም ሆኜ የማምንበትን እናገራለሁ፡፡ ነገ እኮ ከእስር እንወጣለን! ያኔም በዚህ ያየሁትን ጥሩ እና መጥፎ ነገሮች እንደ ጋዜጠኛ እናገራለሁ፣ እጽፋለሁ… ለእውነት ኑሩ!”

በመጨረሻም የመናገር ዕድል የተሰጠው ለዳንኤል ሺበሺ (የቀድሞ አንድነት ፓርቲ አመራር) ሲሆን ፖለቲከኛው ዳንኤልም ተከታዩን ሐሳብ ሰንዝሯል፦ “አሁን ኢሕአዴግ ችግሮችን ለመፍታት እየሞከረ ያለው ሌላ ችግር በመፍጠር ነው፡፡ ንፁሐንን በማሰር፣ በማንገላታት፣ ፍትሕን በመንፈግ፣ በአጠቃላይ በዜጎች ብሶት ላይ ቤንዚን በማርከፍከፍ ለመፍታት ነው፡፡ ይህ አዋጭ መንገድ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ጠቁመናል፤ ዛሬም መልዕክታችን ይኸው ነው፡፡ ፋብሪካ እንዲቃጠል፣ የሰው ህ ሕይወት እንዲጠፋ…. ወዘተ የማናችንም ፍላጎት አይደለም፡፡ አሁን እዚህ ካለው እስረኛ ውስጥ አንድም እንኳን በእዚህ ዓይነት ወንጀል የተሳተፈ አይደለም፡፡ የአመፅ እና የሁከት ተሳትፎ ያልነበረን ንፁሐን ነን! ለዚህች አገር ከአሳሪዎቻችንም ያነሰ ኃላፊነት አይደለም ያለን፡፡ በሆነ ጊዜ እየመጣችሁ የእስረኛውን ሙቀት እየለካችሁ መመለሳችሁ ፈፅሞ ፍትሕ ሊሆን አይችልም፡፡ ማሰር፣ ማሳደድ እና መግደል መፍትሔ ሊሆን አይችልም፡፡ ለአገሬ የሚጠቅም ሐሳብ አለኝ።

“የሀገሬ ጉዳይ ይመለከተኛል፤ ያገባኛልም። ስለዚህ ፍቱን ወይም ስቀሉን! የግፍ እስረኞች ነን። ጥያቄያችንን መመለስ ካልቻላችሁ ኮማንድ ፖስት የሚባለው መንፈስ መጥቶ ያናግረን፡፡ ይሄ ወጣት በውኃ ውስጥ እንደተጣለ ጨው መሟሟት አለበት ብዬ አላምንም፤ ትናንት የነበረን ስጋታችንን ይዘን ዛሬ ላይ ደረስን። ዛሬም እየተፈፀመ ያለውን ኢ-ሰብኣዊ ድርጊቶችን እቃወማለሁ! መቼም ዝም አልልም! ሐሳቤን፣ አስተያየቴን በድምፄ እና በብዕሬ ከማንፀባረቅ አልቆጠብም! ስለዚህ ጥያቄዬን መልሱልኝ የማትችሉ ከሆነ ለኮማንድ ፖስት አድርሱልኝ፡፡ ከእኛ ከተጎጂዎች እና ፍትሕ ናፋቂዎች ጋር ፊት ለፊት የመነጋገር አቅም እና ሞራል ካላቸው በቀጥታ በአካል ያናግሩን፡፡ ይህንን ጥያቄዬንና መልዕክቴን ለኅሊናችሁ ስትሉ አድርሳችሁ ምላሹን በአፋጣኝ አምጡልኝ፡፡ አመሰግናለሁ!!” በሚል ሐሳብ ያጠናቀቀ ሲኾን፣ ከ240 ያላነሱ እስረኞች ለንግግሩ ደማቅ ጭብጨባንና ምስጋናን ችረውታል፡፡

እስረኞቹን ያነጋገሩት መርማሪ ሳጅኖች እና ኢንስፔክተሮች እጅግ ውስጣዊ ስሜታቸው እንደተነካ በሚያስታውቅ ሁኔታ ‘የተባሉትን ነገሮች በሙሉ መቀበላቸውን እና ለኮማንድ ፖስቱ እንደሚያደርሱ፣ በተቻለ ፍጥነትም ከእነርሱ መፍትሔ ይዘው እንደሚመለሱ ገልጸው እስከ ዛሬ ያለ አግባብ ለተጉላሉት እስረኞችም ማዘናቸውን’ ተናግረዋል፡፡ በዕለቱ የነበረው ውይይትም የእስረኛው መራር ቁጣ የተገለጸበት፣ የመርማሪዎቹ ጥልቅ መሸማቀቅ በግልጽ የተስተዋለበት ሆኖ አልፏል፡፡

ጋዜጠኛ አናንያ ሶሪ እና ኤልያስ ገብሩ እንዲሁም ፖለቲከኛው ዳንኤል ሺበሺ ከታሰሩ ሦስት ወራት እንዳስቆጠሩ ይታወቃል።

Filed in: Amharic