ሶስተኛ ክፍል ስትደርስ ስለ “ጀርም” ትማራለህ። ስትመገብ የኖርከው፣ ያደክበት ምግብ የተበከለ መርዝ መሆኑን ሳይንስ አስተማሪህ ይነግርሃል። ምንም አይመስልህም፤ አሞህ አያውቅማ፤ ሳይንስን ትጠራጠራለህ። ቆሼው አይጨክንብህም ያለውን ይሰጥሃል።
አንተም ታድጋለህ፤ እናትህም ይደክማታል። ቆሼ ጭሮ ቤተሰብ የመመገብ ሐላፊነት ያንተ ይሆናል። ትምህርትህን ታቋርጥና ውሎህ የቆሼው ክምር ላይ ይሆናል። ኑሮ ያስጠላሃል፤ ትደበራለህ፣ ቁሩ ማጨስ፤ ጫት መገረብ ትጀምራለህ። የቆሼው ቦታ ሊቀየር መሆኑን ስትሰማ ህይወት ትጨልምብሃለች። ማን አለህ ያለ ቆሼ?! ማንም ዞር ብሎ አያይህም። መፈጠርህን የሚያውቅ የለም።
በኑሮህ ሲመጡብህ ስጋት ይወርሃል። ደካም እናትህን ምን ታረጋታለህ? ዘርፈህ እንዳታበላት ባትዘርፍም ተጠርጣሪ ነህ። ማንም ከሰው አይቆጥርህም። ምርጫ ሲኖር ትዝ ትላቸዋለህ፤ ቆሼው ስር የወጠርካትን ሸራ ገልጠው ድምፅህ እንደሚያስፈልግ ይነግሩሃል፤ በየስብሰባው እየጠሩ 50 ብር እየሰጡ ሊያታልሉህ ሲሞክሩ እንዳላወቀ ሆነህ ታልፋቸዋለህ፣ 50ብሩ ይጠቅምሃላ፤ ደግሞም ደንቦች መጥተው ቆሼው ስር የወጠርካትን ሸራ ቢያፈርሱብህስ? የት መግቢያ አለህ? የትም!
ከቆሼው ውጪ ሁሉም ጠላትህ ነው። የተመረዘው ምግብ ብቻ ነው ላንተ የሚራራልህ። አንድ ቀን ማታ ከቆሼ ያገኘኸውን ኡፋ ከናትህ ጋር ተቋድሰህ ስትተኛ ሁሉም ነገር በዛው ይጨልማል።
አስቀይሞህ የማያውቀው ቆሼ በመጨረሻ ፊቱን ያዞርብሃል፤ ከእናትህ ጋር አፍኖ ይገልሃል።
ሰው ነህ ግን ከተቆለለው ተራራ ከሚያክለው ቆሼ ታንሳለህ። ታሪክህ ባጭሩ
“ቆሼ ላይ ትወለዳለህ፤ ቆሼ ላይ ታድጋለህ፤ ቆሼ ላይ ትሞታለህ” አለቀ!!