>

‹‹ኢሕአዴግ የሚመክሩት ሳይሆን፣ የሚመከርበት ድርጅት ነው›› (ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ)

‹‹ኢሕአዴግ የሚመክሩት ሳይሆን፣ የሚመከርበት ድርጅት ነው››

‹‹ድርድሩ ለፈረንጆች ዕይታ የሚካሄድ ነው››

(የሐበሻ ወግ መጽሔት ቅፅ 1 ቁጥር 19፣ መጋቢት 2009 ዓ.ም)
Dr Dagnachew Assefaየሐበሻ ወግ መፅሔት በዚህ ሳምንት ዕትሟ በእንግድነት የጋበዘችው ‹‹የአደባባይ ምሁራን›› ከሚባሉት ጥቂት የሀገራችን ምሁራን መሃከል አንዱ የሆኑትን ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋን ነው፡፡ በፍልስፍና መምህርነት ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ በተለያዩ ሚዲያዎች በሚያቀርቧቸው በሳል ፅሁፎቻቸውና ቃለ መጠይቆች የሚሰነዝሯቸው ሃሳቦች ገዢነት የተነሳ ተደማጭነት ያተረፉ መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ የአበሻ ወግ መፅሔት ዝግጅት ክፍል ባልደረባ የሆነው ጋዜጠኛ ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን በወቅታዊው ሀገራዊ ጉዳይ ላይ፣ በተለይም በቅርቡ በኢህአዴግና በተቃዋሚዎች መሃከል እየተደረገ ያለውን ‹‹ድርድር›› በተመለከተ፣ ከዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ጋር አጠር ያለ ቃለምልልስ አድርጓል፡፡ እነሆ፣

የሐበሻ ወግ፡- በቅድሚያ ለቃለምልልስ ፈቃደኛ ስለሆንክ በዝግጅት ክፍላችን እና በአንባቢያን ስም ምስጋና እናቀርባለን፡፡ በቅርቡ በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መሃከል ይደረጋል ተብሎ ቅድመ ድርድር ተጀምሯል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የአንተ አስተያየት ብታካፍለንስ?

ዶ/ር ዳኛቸው፡- እኔም ለዚህ ቃለ ምልልስ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ፤ ይህንን ውይይት የምናደርገው፣ በምን ዓይነት ድባብ ውስጥ ሆነን ነው? የሚለው ወሳኝ ቦታ ይዞ መገለጽ አለበት፡፡ በመሆኑም ሀገራችን ‹‹በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ›› (ማርሻል ሎው) እየተዳደረች ባለችበት በዚህ ጊዜ፣ ግልጽ እና ገደብ የሌለው ወግ ልናደርግ እንደማንችል የታወቀ ነው፡፡ ይህንንም ስንል፤ ‹‹ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም›› በፊትም ቢሆን፣ ‹‹የነጻ ንግግር›› ሁኔታ አጠያያቂ የነበረ ቢሆንም፤ በአሁኑ ጊዜ ግን፣ የንግግር ነጻነት በእጅጉ አደገኛ ወደሆነ ደረጃ ተሸጋግሯል፡፡ ሆኖም የአደገኝነቱ ድባብ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ‹‹መባል ያለበት፣ መባል አለበት፤›› የሚለውን ብሂል በማክበር፣ እንዲሁም፣ ለውይይት የቀረቡት ርዕሶች በቀጥታ የኮማንድ ፖስቱን ትዕዛዝ የማይገዳደሩ መሆናቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ እነሆ ጥሪያችሁን አክብሬ የውይይት ሑዳድ ውስጥ ለመግባት ፈቅጃለሁ፡፡
ሌላው ያለንበት ድባብ አስገራሚ የሚያደርገው፣ በየመገናኛ ብዙኃኑ ባሻቸው ጊዜ ሁሉ፣ እንዲናገሩ እና ለሥርዓቱ ምክር እንዲለግሱ የተፈቀደላቸው ወገኖች እንዳሉ ሁሉ፣ ‹‹ይህን… ወይም ያን … ተናግራችኋል፤›› ተብለው ደግሞ፣ ዘብጥያ የሚወርዱ ዜጎችም እንዳሉ ማስታወስ ይኖርብናል፡፡
ይህን ካልኩ በኋላ፣ ወደ ጥያቄህ ልመለስ፡፡ ጥያቄህ ጠቅለል ሲደረግ፣ ‹‹በኢሕአዴግ እና በተቃዋሚዎች መካከል ስለሚደረገው ‹‹ድርድር›› ምን ታስባለህ? የሚል መሰለኝ፡፡ እኔ ከዚህ በፊትም ጠቀስ እንዳደረግኩት፣ አሁን እየተደረገ ያለውን ተዋስዖ፣ ‹‹ውይይት እንበለው?››፤ ‹‹ድርድር እንበለው?››፤ ወይስ ‹‹ክርክር?›› የሚለውን ከማየቴ በፊት፤ ምናልባት መድረክ እና ሰማያዊ ፓርቲ ካልሆኑ በቀር፣ ከዚያ ውጪ ያሉትን ‹‹በውይይት ሂደቱ ውስጥ አለን፤›› የሚሉትን ፓርቲዎች በጠቅላላ፣ እንደ ተቃዋሚ ፓርቲ አላያቸውም፡፡
ይህም ማለት፣ አንዲት አፍላ ወጣት ‹‹ፍቅረኛዬ ጥሎኝ ስለሄደ፣ ራሴን አጠፋለሁ፤›› ብላ ብትነሳ፣ የሥነ ልቡና አማካሪው በመጀመሪያ ማረጋገጥ ያለበት፣ ‹‹እውነት ልጅቱን የያዛት፣ ፍቅር ነው? ወይስ ሌላ…?›› ብሎ የተስፋ መቁረጧን ሰበብ መመርመር አለበት እንጂ፣ እሷ እንዳለችው ‹‹የፍቅር ጉዳይ›› እንደሆነ አድርጎ ብቻ፣ ምርመራውን እና ሕክምናውን አይቀጥልም፡፡

ከዚህ ምሳሌ ተነስተን፣ ‹‹ተቃዋሚ ፓርቲ ነን፣›› በሚል ማዕቀፍ የቀረቡትን ፓርቲዎች፣ እኛም በጅምላ ‹‹ተቃዋሚ ናቸው፤›› ብለን ከመቀበላችን በፊት፣ ‹‹በርግጥ ተቃዋሚዎች ናቸውን?›› ብለን፣ ሀኪሙ ስለወጣቷ የፍቅር መያዝ እውነተኝነት መጠየቅ ይኖርበታል፤ እንዳልነው ሁሉ፣ እኛም ስለ እነኚህ ፓርቲዎች ተቃዋሚነት መጠየቅ ይኖርብናል፡፡
ሁለተኛው አስገራሚ ነገር፣ ‹‹ድርድር›› የሚለው ቃል ነው፡፡ በእኔ አረዳድ ‹‹ድርድር›› የሚለው ስያሜ፣ ሁለት አንጻራዊ የኃይል ሚዛን ያላቸውን አካላት የሚጠቁም ቃል ነው፡፡ እዚህ ላይ ግን በኢሕአዴግ እና በተቃዋሚ ፓርቲ ተብዬዎች መካከል፣ በምንም መሥፈርት የቀራረበ የኃይል ሚዛን አይታይም፡፡ በመሆኑም፣ በዚህ ሁኔታ ውስጥ፣ ‹‹ውይይት›› እንጂ፣ ‹‹ድርድር›› ሊካሄድ አይችልም፡፡ ይህ ለድርድር የሚሆን የኃይል ሚዛን በሌለበት ሁኔታ፣ ተቃዋሚዎች ከኢሕአዴግ እንዲፈጸምላቸው የሚፈልጉትን ጉዳይ በማመልከቻ ከማሰማት ውጪ፣ ‹‹ይህንን ካላደረግክ፣ እኛም ይህንን ለሥርዓቱ ይበጃል የምትለውን አንዳንድ ነገር እንዳንፈጽም እንገደዳለን›› የሚሉበት መደራደሪያ አቅም የላቸውም፡፡

የሐበሻ ወግ፡- ግን እኮ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የእኛ የኃይል ሚዛናችን ሕዝብ ነው፣ ሕዝብ ከእኛ ጋር ነው እያሉ ነው …

ዶ/ር ዳኛቸው፡- (ሣቅ) ሕዝብ ኃይል እንደሚሆን ምን ጥርጥር አለው?! ሆኖም፤ ሕዝብ ኃይል ሊሆን የሚችለው፣ በመጀመሪያ ደረጃ ‹‹እኔን ይወክለኛል፣ ፓርቲዬ ነው፣›› ብሎ፣ ምሉዕ ይሁንታውን እና ዕምነቱን እንዲሁም ፖለቲካዊ ወገንተኝነቱን ሲሰጥህ ነው፡፡ ይህንን የሕዝብ ይሁንታ ባላገኙበት ሁኔታ፣ ‹‹ሕዝብ ጉልበታችን ነው››፣ ወይም ‹‹አብሮን ይቆማል››፣ የሚለው አባባል፤ ከግምታዊነት እንዲሁም ለራስ ትልቅ ቦታ ከመስጠት በላይ የዘለለ ቦታ አይኖረውም፡፡
በተጨማሪም፣ እኔ አንተን ልጠይቅህ እስቲ? ሕዝብ እነዚህን ፓርቲዎች ‹‹ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው›› ብሎ የሚቀበላቸው ይመስልሃል? ሕዝቡ በተደጋጋሚ የሚያደርገው ጥሪ፣ ‹‹መብታችን ይከበር››፣ ‹‹የህግ የበላይነት ይስፈን››፣ ‹‹ሙስና አንገሽግሾናል››፣ ‹‹የብሔር አድልዎ ይቁም››፣ ‹‹ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ክፍፍል ይኑር››፣ ‹‹የታሠሩ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱልን››፣ … እያለ እንጂ፣ ‹‹ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጋር ተደራደሩ›› ወይም ‹‹ቦታ ስጧቸው፤›› የሚል ጥሪ ሲያቀርብ እስካሁን አልሰማንም፡፡

የሐበሻ ወግ፡– ዋና ዋና የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች (እንደነ ዶ/ር መራራ እና በቀለ ገርባ ያሉ) ታስረው የሚደረግ ድርድር፣ ድርድር አይደለም፤ የሚሉ አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የታሳሪዎቹ መፈታት በቅድመ ሁኔታነት መቀረብ አለበት ይላሉ፡፡ አንተ በዚህ ላይ ምን ትላለህ?

ዶ/ር ዳኛቸው፡- በመሠረቱ እኔ ፓርቲዎች ምን ቅድመ ሁኔታ ይዘው ወደ ውይይት መቅረብ እንዳለባቸው ምክር ሰጪ አይደለሁም፡፡ ሆኖም ግን በዚህ ውይይት እና ድርድር ሂደት፣ ዶ/ር መራራ ጉዲና እና በቀለ ገርባ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎቹም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ የድርድር አካል ሆነው ቢቀርቡ እንደ አንድ ዜጋ ትክክለኛ የፖለቲካ የፍትሕ ጥሪ እንደሆነ አስባለሁ፡፡
የሐበሻ ወግ፡- ግን እኮ፣ አሁን ‹‹እንነጋገር›› ወይም ‹‹እንደራደር›› የሚለውን ጥያቄ ያቀረቡት ተቃዋሚዎች ሳይሆኑ፣ ኢሕአዴግ ራሱ ነው…፤

ዶ/ር ዳኛቸው፡- ሊሆን ይችላል፡፡ ከእሱ በፊት አንድ ነገር ልንገርህ፡፡ እኔ ራሴ በግለሰቦች አነሳሽነት በቤት ውስጥ በተዘጋጀ የመፍትሄ አፈላላጊ በጎ አሳቢዎች ውይይት ላይ ተጋብዤ ነበር፡፡ ይህ ውይይት ‹‹ሀገር ሊፈርስ ነው››፣ ‹‹የእርስበርስ ጦርነት ውስጥ ልንገባ ነው››፣ ‹‹በመሆኑም፣ ከኢሕአዴግ ጋር ተወያይተን አንድ መፍትሄ ላይ መድረስ አለብን››፣ የሚሉ ‹‹ጎበዞች›› የጠሩት ውይይት ነበር፡፡
በእኔ እምነት እንዲህ ዓይነቱ እሳቤ፣ ምንም ዓይነት ተጽዕኖም ሆነ ተፈጻሚነት በኢሕአዴግ በኩል ስለማይኖረው፣ ከአንድ ጊዜ በላይ በውይይቶቹ ላይ አልተገኘሁም፡፡ ለምን? ቢባል፡፡ ዋናው የእነዚህ ኮሚቴዎች ተቀዳሚ ዓላማ፣ ‹‹ለኢሕአዴግ ምክር ብንለግስ አንዳንድ ሕፀፁን ያስተካክላል፤›› ከሚል ዕሳቤ ሲሆን፣ እኔ ግን ኢሕአዴግ የሚመክሩት ድርጅት ሳይሆን፣ የሚመከርበት ድርጅት ነው ብዬ ስለማምን ራሴን ከዚህ ዓይነቱ ውይይት አቅቤያለሁ፡፡
አሁን የሚደረገው ውይይት፣ ከዚህ በፊት ኢሕአዴግ ‹‹አስፈላጊ ነው፤›› ብሎ ያመነበት፣ ውስጣዊ እና ውጪያዊ ግፊት ስለተቀሰቀሰበት ነበር፡፡ አሁን ግን፣ ከአራት ወራት በፊት እንደነበረው ያለ የሕዝብ እንቅስቃሴ በከሰመበት ወቅት፣ የድርድሩ አስፈላጊነት መሬት ላይ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ አዳክሞታል፡፡ በመሆኑም ቀደም ብለው፣ ‹‹ከተቃዋሚዎች ጋር እንወያያለን›› ብለው ቃል ስለገቡ እንጂ፣ ‹‹ሁኔታዎችን በወታደራዊ ኃይል ተቆጣጥረናል፤›› ብለው ስለሚያምኑ፣ ድርድሩ ለፈረንጆች ዕይታ ሲባል ብቻ የሚካሄድ ነው፡፡

የሐበሻ ወግ፡- መልካም አሁን የሚደረገው ውይይት ወይም ድርድር ተደረገ እንበል፤ ስምምነት ላይም ተደረሰ እንበል፡፡ የሚደረስበት ስምምነት (ስምምነት ላይ ከተደረሰ) የሀገሪቱን ሕገ መንግስት የሚቀይር ነው የሚሆነው ወይስ ምንድነው የሚሆነው?

ዶ/ር ዳኛቸው፡- አዎ! ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት አርቅቆና አጽድቆ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መሆን ያቃተው ድርጅት ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት፣ በሀገራችን የፖለቲካ እና የሕግ ሥርዓት ላይ ‹‹የሕግ የበላይነት›› ስለማይከበር ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ስንል፣ በአጭሩ ሁለት ቁልፍ ጽንሰ ሀሳቦችን የያዘ ጉዳይ ነው፡፡ አንደኛው፡- የሚታወቀው የሥልጣን ክፍፍል በነቢብም ሆነ በገቢር ሲኖር ነው፡፡ ሁለተኛ፡- የሕግ የበላይነት ማለት የትኛውም ተቋም፣ ግለሰብ በራሱ ጉዳይ ላይ ራሱ ዳኛ ከመሆን ይልቅ በሦስተኛ ወገን መዳኘት ሲችል ነው፡፡
ከዚህ በመነሳት፣ ኢሕአዴግ ሁለቱንም መሥፈርቶች አያሟላም፡፡ ማለትም፤ ሕግ አስፈጻሚው፣ ሕግ አውጪውን እና ሕግ ተርጓሚውን አሽመድምዶ በሥሩ በማድረግ፣ የሥልጣን ክፍፍል የሚባለውን ብሂል ጥሶታል፡፡ በተጨማሪም ኢሕአዴግ በራሱ በኢሕአዴግ ጉዳይ ላይ፣ ራሱ ዳኛ ሆኖ ስለሚቀርብ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ባልተከበረበት ሁኔታ፣ ሕገ መንግስት ብትቀርጽ ባትቀርጽ፣ ሕገ መንግሥቱ ቢያምር ባያምር ምንም ዋጋ የለውም፡፡

የሐበሻ ወግ፡- እስቲ ደግሞ ስለ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ጉዳይ እንነጋገር፡፡ አንተ የዩኒቨርሲቲዎችን አመራሮች በተመለከተ ከአንድም ሁለት ጊዜ ጠንከር ያለ ትችት ሰንዝረሃል፡፡ በቅርቡ ደግሞ ትምህርት ሚኒስቴር ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አሰያየም በውድድርና በምርጫ ይሆናል ብሏል፡፡ ይኼን ጉዳይ እንዴት ትመለከተዋለህ?

ዶ/ር ዳኛቸው፡- ቢሆን ጥሩ ነው፡፡ ከዚህ በፊትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተደርጎ ያውቃል፡፡ በደርግ ጊዜ መሰለኝ ይሄ የሆነው፡፡ ኢሕአዴግም ከገባ በኋላ ተደርጓል ይመስለኛል፡፡ ዋናው ነገር አንድ የዩኒቨርሲቲ አመራር የሚሆን ሰው፣ ሰፋ ያለ የአስተሳሰብ አድማስ ሊኖረው ይገባል፡፡ በ1960ዎቹ በአሜሪካ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ሦስት ዓመት የፈጀ ክርክር ተካሂዶ ነበር፡፡ ዋናው ነገር፣ አንድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የሚመረጠው ሁለት ዐበይት የሆኑ መስፈርቶችን ሲያሟላ ነው፡፡
አንደኛ፡- በየትኛው የትምህርት መስክ ቢያልፍ ‹‹ስኮላር›› መሆን አለበት፡፡ ይህም ሲባል፣ የተማረበትን መስክ ብቻ የሙጥኝ ብሎ የያዘ ሳይሆን፣ በሌሎች ዲሲፕሊኖችም ሰፋ ያለ መሠረት ያለው እና ራሱን ሁሌም በአእምሯዊ ዕድገት ጎዳና ውስጥ የሚያስጉዝ መሆን አለበት፡፡
ለምሳሌ ያህል፤ በ1960ዎቹ ውስጥ ሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ኮሚቴ ‹‹የሐርቫርድ ኮሚቴ›› የሚባል ተቋቁሞ፣ ሦስት ዓመት የፈጀ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት አድርገው ነበር፡፡ ይህንን ኮሚቴ የመራው የባዮሎጂ ፕሮፌሰር ነበር፡፡ ሆኖም ግን፣ ከላይ እንደጠቀስነው የአስተሳሰብ አድማሱ ሰፊ ስለነበር ከተለያዩ ዲሲፕሊኖች ከመጡ ፕሮፌሰሮች ጋር ሰፋ ያለ ውይይት አካሂዶ እነሆ እስካሁን ድረስ በአብዛኛው ያልተቀየረ ሥርዓተ ትምህርት ለዩኒቨርሲቲው እንዲኖር አድርጓል፡፡ እዚህ ላይ በዩኒቨርሲቲ አመራርነት የሚቀመጥ ሰው፣ የተማረው ትምህርት ሳይሆን፣ ከዚያ በኋላ ራሱን እንደ ስኮላር ሰፋ ባለ መስክ ትምህርት እና እውቀት የቀሰመ መሆኑ ወሳኝ ቦታ ይይዛል፡፡
ሁለተኛ፡- የአስተዳደር ችሎታ እንዲኖረው ያስፈልጋል፡፡ ይህም ማለት፣ ከመሠረቱ በተለያዩ የትምህርት አስተዳደር ሥራዎች በቂ ልምድ ያለው ሊሆን ይገባዋል፡፡
ወደ ሀገራችን ዩኒቨርሲቲ ሁኔታ በምንመጣበት ጊዜ፣ በቀዳሚነት በፕሬዚዳንትነት ለመሾም ሦስት ዐበይት የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች ተቀምጠዋል፡፡ የመጀመሪያው ከገዢው ፓርቲዎች መካከል የአንደኛው አባል መሆን፣ ሁለተኛ፡- አካዳሚው የሚፈልገውን ሳይሆን የመንግሥትን ፖሊሲዎች ለማስፈፀም ዝግጁ የሆነ ሰው መሆኑ ታይቶ፣ እና ሦስተኛው እና ዋናው የብሔር ተዋፅዖ ጉዳይ ከግምት ውስጥ ገብቶ የሚሰጥ ይሆናል፡፡
የዛሬ 70 ዓመት ገደማ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ሥልጣን እንደያዙ፣ የሹመት ጉዳይ እንደ አንድ ወሳኝ የፖለቲካ ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡ ይኸውም፣ ‹‹ሹመት እንደ ቀድሞው በመወለድ ወይስ በችሎታ›› በሚል ርዕስ፣ ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ ሰፋ ያለ ውይይት ከተደረገ በኋላ፣ ‹‹ሹመት በችሎታ›› የሚሉት ወገኖች አሸንፈው፣ ሹመት በችሎታ እንዲሆን ተደርጎ ነበር፡፡ አሁን፣ ከ70 ዓመታት በኋላ፣ ተመልሰን ‹‹ሹመት በትውልድ›› ወደሚለው ተመልሰን ገብተናል፡፡
የሐበሻ ወግ፡- ይበቃናል! በድጋሚ አመሰግናለሁ ዶክተር፡፡
ዶ/ር ዳኛቸው፡- እኔም አመሰግናለሁ!

Filed in: Amharic