>

የዳንኤልና የኤልያስ አንድ መቶ ሀምሣ ቀናቶች (ዳንኤል ሺበሺ)

የ150 የግፍ ቀናት ትውስታ

elias-gebru-17042017daneil-shibeshi-17042017ቀደም ሲል በተከሰስኩበት ክስ በግፍ ለ2አመታት ያህል በማእከላዊ ፣በቂሊንጦ ፣በቃሊቲ ከሴቶች ዞን በስተቀር በሁሉም ዞኖችና ጨለማ ቤቶች ከታሠርኩ በኋላ ተፈትቼ ለግማሽ አመት ያህል እንኳ በወጉ ሳላርፍ ነበር ለአሁኑ እስር የተዳረኩት፡፡

እኔ(ዳንኤል ሺበሺ)እና ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ሕዳር 8 ቀን 2009 ለመገናኘት የተቀጣጠርነው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጦስ የታሰሩ ጓዶቻችንን ለመጎብኘት ነበር ፡፡ በዕለቱ ካቀድነው ጉብኝት በኋላ የምሣ ሰአታችን ረፍዶብን ነበርና ከቀኑ 10:00 ሰአት ገደማ ካዛንቺስ ወዳለው ሮሚና ባርና ሬስቶራንት ጎራ ብለን እየበላን እያለን ከየት መጡ የማይባሉና በቁጥር 8 የሚሆኑ ሲቪል የለበሱ ወጠምሾች ስምንት ሽጉጥ በጆሮ ግንዳችን ላይ ደገኑብን፡፡

በፊት ለፊታችን ጠረጴዛችን ላይ ያስቀመጥነውን ቦርሣችንን ፣ሞባይላችንንና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ ንብረታችንን ሰበሰቡና በሉ ተነሱ! አሉን፡፡ማንነታቸውን ጠየቅናቸው፣ ለመናገር ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ አንደኛው (ሀላፊያቸው መሠለኝ) ከመታወቂያው የራሱ ስም ያለበትን ቦታ በአውራ ጣቱ ሸፍኖ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት ፅ/ቤት የሚለውን ብቻ አሳየን፡፡

እናም ታፍነን ተወሰድን፣ ሠዎቹ ደም የጠማቸው ይመስላሉ፣ ትግስት አልባ ትዕቢተኞች መሆናቸውንም አስተውለናል ፡፡ከካዛንቺሱ ፖሊስ ጣቢያ መጠነኛ ቆይታ በኋላ ወደ ገርጂ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱን ፡፡እዚያ ስንደርስ ሰአቱ ከምሽቱ 3:00 ይሆን ነበር፡፡ ወደ ፖሊስ ጣቢያው ሲወስዱን እኔንና ኤልያስን አብረው አልወሰዱንም፡፡በፖሊስ ጣቢያው ተፈትሼ ንብረት ካስረከብኩ በኋላ ነበር የምሽቱ ተረኛ ፖሊስ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ወዳለበት የወሠደኝ፡፡
በመጀመሪያው ሌሊት እኔ ከታሠርኩበት ክፍል ጎን ያለው ክፍል ሲከፈትና የጋዜጠኛ አናንያ ሶሪን ድምፅ የሚመስል ድምፅ ከፖሊሶቹ ጋር ሲያወራ ሰማሁ በኋላ ሳጣራ ለካስ አናኒያም እንደእኛ ተከርችሟል ፡፡የታሠርነው ለየብቻ ነበር እኔ በመጀመሪያው ክፍል ፣አናንያ ሶሪ በመሀለኛው ፣ ኤልያስ በ3ኛው ክፍል ታስረናል፡፡ ባልሳሳት እኛ ከመግባታችን በፊት ሌሎች እስረኞችን ወደሌላ ክፍል አሸጋሽገው ቦታውን ለእኛ ብቻ አድርገውታል ፡፡

እኔ በክልል ፣በማዕከላዊ ፣በቂሊንጦ ፣በቃሊቲና በሌሎች ፖሊስ ጣቢያዎች ታስሬ የማውቅ ቢሆንም እንደ ገርጂ ፖሊስ ጣቢያ የከበደኝ አልነበረም፡፡ የመሬቱ ወለሉ ባልጩት(ፈረከሳ) ሲሆን ከባድ ቅዝቃዜ ነበረው፡፡ የያዙን ደህንነቶች ለፖሊሶቹ ለብቻችን እንድንታሠር፣ፍራሽ ፣ትራስ ፣ምግብ ፣የመኝታ አልባሳት ወዘተ እንዳይገባ ስላዘዙ ሁኔታው ከባድ ነበር፡፡

ከቅዝቃዜው አንጻር ለመቆም ፣ለመተኛት ፣ለመቀመጥ ሁሉ ከባድ ነበር ፡፡በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለን እሁድ ጠዋት ህዳር 11ቀን 2009 ወደ ቦሌ ፖሊስ መምሪያ ወሰዱን፡፡ የማልረሳው ነገር ቢኖር የገርጂ ፖሊሶች ወደጫነን መኪና መጥተው ደማቅ አሸኛኘት ማድረጋቸውና ከልብ ማጽናናታቸውን ነው፡፡በተያዝኩ ዕለት የደበደበኝ ደህንነት የሚከሰስበት እና የሚጠየቅበት ሕግ መኖሩን አምነው ይሁን እንዲያው ብስጭታቸውን ለመግለጽ ባላውቅም ደህንነቱን እንድከው መክረውኛል፡፡

በቦሌ ክ/ከ ፖሊስ መምሪያ በ መጀመሪያዎቹ የእስር ጊዜያቶች ፖሊሶቹ እኛን በውል ያለመረዳት ሁኔታ ቢታይባቸውም ቀስ በቀስ ወደ ጥሩ ግንዛቤ ላይ መጥተዋል፡፡ ሰብአዊ ክብራችንን ጠብቀው ማቆየታቸውንም መመስከር ይቻላል፡፡ህዳር12ቀን 2009 ሶስታችንም “ከግንቦት 7 እና ከኦነግ ጋር በመገናኘት ሕገ መንግሥታዊ ስርአቱን በሀይል ለመናድ ተንቀሳቅሳችኋል ” የሚል ክስ ተነገረን “አላደረግንም”ብለን ለፖሊስ ቃላችንን ሰጠን፡፡
ሐሙስ የካቲት 9ቀን 2009 ሶስታችንም (ዳንኤል ሺበሺ ፣አናንያ ሶሪ ፣ኤልያስ ገብሩ) ወደ ቂርቆስ ክ/ከ ተዛወርን እኔ ቄራ አካባቢ ወዳለው እሳት አደጋ ፖ/ጣቢያ ተብሎ ወደሚጠራው ተወሰድኩ፣ አናኒያ ካሳንቺስ 6ኛ ፖ/ጣቢያ ኤልያስ ቂርቆስ ቤ/ክ አጠገብ ወዳለው ፖፑላሬ ፖሊሥ ጣቢያ ተወስደን ታሠርን ፡፡

የብተናው ምክንያት ግልፅ ነበር ቀደም ሲል በግቢው ውስጥ በተደረጉ ስብሰባዎች አንኳር አንኳር ጥያቄዎችን በማንሳት የስርአቱ የአስተዳደር ግድፈቶችን እንተች ነበር፡፡ ለምሣሌ ኮማንድ ፖስት የሚባለው ማነው? የት ነው ያለው? መንፈስ ነው ወይስ የሠዎች ስብስብ? ፍትህ ይሰጠን!ፍ ቱን ወይም ስቀሉን! በኮማንድ ፖስቱ ድብደባ ተፈፅሞብናል ፣ጋዜጣ ፣መፅሔት ፣ሬድዮ ፣መፅሀፍ ይግባልን ፤ሕክምና ተከልክለናል የሚሉ ጥያቄዎችን እናነሳ ነበር፡፡ለእነዚህ ጥያቄዎቻችን መልስ ይሆን ዘንድም ለያይተው አሰሩን፡፡

አርብ መጋቢት 15ቀን 2009 ከየታሠርንበት ፖሊስ ጣቢያዎች በድጋሚ ወደ ቦሌው ክ/ከ ፖሊስ መምሪያ ሰበሰቡንና አሰሩን፡፡ በጊዜው ሊፈቱን መስሎንም ነበር ፡፡ ግን እውነቱ የተገላቢጦሹ መሆኑን ብዙም ሳንቆይ ነበር የተረዳነው፡፡
ሰኞ ሚያዚያ 2ቀን 2009 እኔና ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ወደ ማእከላዊ ተወሰድን በእለቱ ስማችን የተጠራው ወደ ፍ/ቤት ከሚቀርቡ ሌሎች እሥረኞች ጋር በአንድ መዝገብ ስለነበር እኛም ፍ/ቤት የምንቀርብ መሥሎን ነበር ፡፡ ግን የተደገሰልን ሌላ ነበር፡፡ በጧቱ ጥሪ ከፍ/ቤት ቀራቢዎች ጋር ስንቀላቀል “አይ! እናንተ ትንሽ ቆዩ “ተባልንና ከሰልፍ ወጣን፡፡ ነገሩ ግራ ስለገባኝ ወደ አንደኛው ኢንስፔክተር ጠጋ አልኩና”እኛ ለምን ተጠራን” አልኩ ሰውየው ትንሽ ትክዝ አለና “አይ! እናንተ የተጠራችሁት ለፍ/ቤት አይመሥለኝም”አለኝ እናስ?የእኔ ቀጣዮ ጥያቄ ነበር ወደ ማእከላዊ ልትወሰዱ ነው አለኝ፡፡ ነገሩ ዱብዳ አልሆነብኝም፡፡

ከ1ቀን በፊት ጭምጭምታ ሰምተን ስለነበር በወሬ ደረጃ የሠማነውን ነገር እውን ሆኖ ከማረጋገጥ ውጪ አዲስ ነገር የለም፡፡ ከዚያም ከጥቂት ደቂቃዎች በሗላ “ዳንኤል ሺበሺ እና ኤልያሥ ገብሩ እቃችሁን ይዛችሁ ቶሎ ውጡ” ተባልን እቃችንን ይዘን ፣በእጅ ካቴና ታሥረን መሳሪያ በታጠቁ አራት ፖሊሶች ታጅበን በተዘጋጀልን መኪና ማእከላዊ ግቢን ለሁለተኛ ጊዜ ረገጥን ፡፡

ማእከላዊ ለሁለታችንም እንግዳ አይደለም ፡፡ ከወሰደን መኪና ወረድንና በአንድ ቢሮ በረንዳ ላይ ቁጭ አድርገውን ሁለቱ መርማሪዎቹ ወደ ማእከላዊ ሀላፊዎች ቢሮ አቀኑ፡፡ ከተወሰነ ሰአታት በሗላ ተመልሠው መጡ፤አቅፈው የወሰዱትን ዶክሜንቶችንና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎቻችንን አቅፈው ሲመጡ በርቀት አየናቸው፡፡ ምክንያቱን ሳይነግሩን አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንሔዳለን አሉን፡፡ ልባችን በደስታ ተሞላ ፡፡ ጓደኛዬ ኤልያስም የመደሰቱ ምክንያት ግልፅ ነበር ለሀገር ይበጃል ብለን በፃፍነውና በተናገርነው ሀሣብ ዛሬ መከሰሳችንና መታሠራችን ሳያንስ ከሰቅጣጭ የማዕከላዊ ግርፊያ ከመዳረግ ለጊዜውም ቢሆን መትረፋችን አስደስቶናል፡፡

የአ.አ ፖሊስ ኮሚሽን ተብሎ ወደሚጠራው ትልቁና ሰፊው ግቢ ደርሰናል፡፡ አጃቢ ፖሊሶች ክላሻቸውን ወድረው በተጠንቀቅ እየጠበቁን እኔ ግራ እጄን ኤልያስ ቀኝ እጁን ለካቴና ሰውተናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ አንድ የሚገርም ነገር ገጠመን፡፡
አንዲት እናት በዘምቢል የሆነ እቃ ይዘው በግቢው ውስጥ ወደ ግራ ወደቀኝ እያሉ በአይናቸው ሲያማትሩና ወደ ጓሮ እስረኞች መጠየቂያ ጋ ሔድ መጣ ሲሉ አየኋቸው እናም ለኤልያስ ‹‹አንተ! የቤቲ እናት አይደሉም እንዴ!?›› አልኩት በአመልካች ጣቴ ወደ እርሣቸው እየጠቆምኩ ኤልያሥም ሆነ እኔ ማመን አቃተን፡፡
የቤቲ እናት! ብለን ጠራናቸው ወደ እኛ ዞር አሉና እርሣቸውም እምባ ያቆረ አይናቸውን እያበሱ ወደ እኛ ሮጠው ሲመጡ አጃቢዎች ተቆጡ መጨበጥ አይቻልም! አሏቸው ኧረ ባክህን ልጆቼ ናቸው ብለው ለመኗቸው፡፡ እሺ ይገናኙ ብለው ፈቀዱላቸው፡፡ እርሳቸውም አይናቸውን እያበሱ “……ልጆቼ አላችሁ!? እኔኮ ማእከላዊ ደርሼ እየተመለሥኩ ነው”አሉን እኛም ተደናብረናል፡፡ እናስ‹‹ ማእከላዊ ምን ተባሉ ብለን ጠየቅናቸው መቼ ነው የመጡት? ሲሉኝ ዛሬ ጠዋት አልኳቸው እንደዛ ከሆነማ ዝርዝሩ ስላልደረሠን ከሰአት ይምጡ›› ተብዬ ቁጭ እንዳልኩ ልጄ ደወለችልኝና “አይ! ዝም ብለሽ እዛ ከምትቀመጪ ለማንኛውም ወደ 3ኛ ዉረጅ ብላኝ ነው የመጣሁት”አሉኝ ፡፡
በዚህ ቅፅፈት ውስጥ መድረሳቸው ለእኛ ትንግርት ነበር ፡፡ የቤቲ እናት ይዘው የመጡልንን ቁርስ በላን ከትላንትና ምሣ በሗላ ስንበላ ይህ የመጀመሪያችን ነበር ምግብ አስጠልቶን ነበርና ምግብም ትኩስ ነገርም በጣም አሰኝቶን ነበር ፡፡በክፉ ሰአት የደረሠን ምግብ እኛ ቁርሣችንን እያጣጣምን ካመጡልን ቡና ሶስት ሶስት ኩባያ ቡና በተቀመጥንበት በጉሮሮአችን ላይ ደፋነው፡፡ አሁን ደስታ ተሠማን የየቤቲን እናት ወ/ሮ ተንሣይን መረቅናቸው እርሳቸውም መረቁን አሁንስ ምን እንላለን ምስጋና አይጉደልባቸው እድሜን ከጤና ጋር ይሥጥልን ልጃቸውም ብትሆን ወ/ት ቤተልሔሜ ነጋሽ(ቤቲ) ከታሠረንበት ጊዜ ጀምሮ ከጎናችን አልተለየችንም፡፡ ታሪክና ፈጣሪ ውለታዋን ይመለስላት፡፡
ወደ ፎቁ የወጡት መርማሪ ፖሊሶችን ይዘው የመጡትን ዶክሜንቶችንና ንብረቶቻችንን እንደነበሩ ይዘው ተመለሡና የመኪናውን ጋቢና ከፍተው ቁጭ ሹፌራቸው ጠሩና ወደ ልደታ ከፍ/ፍ/ቤት ግቢ ንዳው አሉ፡፡
ፍርድ ቤት ከደረስን በኋላ መርማሪዎቻችን ዶክሜንቶቻችንን በደረታቸው አቅፈው ወደ አ.አ ከተማ አስተዳደር ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሮ ገቡ፡፡ እንደተለመደው ከተወሠኑ ሠአታት ቆይታ በኋላ ግራ የተጋቡ መስለው ወጡ እናም ወደ መምሪያ እንሄዳለን አሉ፡፡
መምሪያ የሚሉት የቦሌውን ክ/ከ ፖሊስ ጣቢያ ማለታቸው ነው፡፡ እኛም ዞረን ተመልሰን ወደ ቦሌው መኖሪያችን ደረስን፡፡ ወደ እስረኞች ጊቢ ከመድረሣችን በፊት በውጪ ያገኙን ፖሊሶች በጥያቄ አጣደፉን፡፡‹‹ ምን ተብላችሁ ነው የተመለሣችሁት?›› ከወጣን በኋላ የተፈጠረውን ጭንቀታቸውን ማራገፍ ጀመሩ በቁንጥጫ ፣በሰላምታ ፣በጥቅሻ ደስታቸውን መግለፅ ጀመሩ፡፡
ከዋናው መግቢያ በር ጀምሮ ትንፋሽ ያሳጡንን ፖሊሶችን አልፈን ጠዋት ትተናቸው ወደ ሔድናቸው እስረኞች ስንገባ የግቢው ድባብ ተቀየረ ፡፡ ወደ ማእከላዊ መወሠዳችንን ለመልካም ያለመሆኑን የተረዱ እስረኞች በከባድ ሀዘን ላይ ወድቀው ነበር።
ሁሉም ከየክፍሉ (ከ8ቱም ክፍል) እየተሯሯጡ ወጡና በግቢው ውስጥ የነበሩ እስረኞችን ተቀላቀሉ። በፉጨት፣ በጭብጨባ፣ በጩኸት ተቀበሉን። የተፈታን ያህል ‹‹የእንኳን ደስ አላችሁ›› ሰላምታ መዥጎድጎድ ጀመረ። መተቃቀፍ፣ መሳሳም መለቃቀስ ሆነ፤ ፖሊሶቹም ጩኸቱን እንደረብሻ አልቆጠሩትም።
እነሱም የያዛቸው ነገር ይዞዋቸው ነው እንጂ ከመጮኽ አይመለሱም ነበር። ከደስታ ብዛት የሚመነጭ ጩኸት መሆኑ ገብቷቸዋል።
እኛ ወደ ማዕከላዊ ከተወሰድን በኋላ ሌሎችም ተራ በተራ ሊወሰዱ እንደሚችሉ በመስጋታቸው እንደየሐይማኖታቸው መጸለይ ጀምረው እንደነበር እስረኞቹ ነግረውናል፡፡ዱዓ (ጸሎት )ሲያደርጉ ከነበሩ ታሳሪዎች አንዱ የሆነው አብዱልአዚዝ ከሚል የሚባል ታሳሪ ‹‹ወላሂ እናንተ ከዚህ ከሄዳችሁበት ቅጽበት አንስቶ ዱዓ እያደረግኩ ነበር ….››ሲል ኤልያስ ጣልቃ ገብቶ
‹‹እስኪ እውነቱን ንገረን ለማን ነው ዱዓ ያደረግከው›› ይለዋል፡፡
ዓብዱልአዚዝ እየሳቀ ‹‹ኤላ ወላሂ ለራሴ ነው ዱዓ ያደረግኩት››አለው፡፡እንግዲህ ማዕከላዊ መሄድን እስረኞች እንዴት እንደሚመለከቱት ከዓብዱልዓዚዝ መረዳት የሚቻል ይመስለኛል፡፡
ግቢው በእኛ መመለስ በደስታ፣በአግራሞትና ቀጣዩን ባለማወቅ ስሜት በተደበላለቀበት ሰዓት አንዲት ሴት ፖሊስ መጠበቂያዋ ላይ ተቀምጣ ስታለቅስ ማየቴንም እዚህ ማንሳት ይኖርብኛል፡፡ፖሊሷን ስሜቷን እንደተረዳኋት ለመግለጽ ሁለት እጆቼን ደረቴ ላይ አድርጌ ‹‹አይዞሽ እግዚአብሄር ስለሁሉም ያውቃል እኛ ምንም አንሆንም››ስላት ኤልያስም በጭንቅላቱ በንግግሬ መስማማቱን እየገለጸላት ነበር፡፡ፖሊሶቹ ግን ይህን ያህል ሰብዓዊነት እየተሰማቸው ስርዓቱን ለምን ለማገልገል እንደሚመርጡ ሁልግዜም ግራ ግብት ይለኛል፡፡
ኤልያስ የአፍንጫ ህመሙ እየተባባሰበት በመሆኑና ለማሽተት በመቸገሩ ክሊኒኩ ሪፈር ከጻፈለት ሁለተኛው ወር እየተቆጠረ ነው፡፡ኤልያስ በተጻፈለት ሪፈር ዙሪያ አንድ ቀን ስናወራ ‹‹እኔ ግርም የሚለኝ የክሊኒኩ ሪፈር ሳይሆን ወደየትኛው ፍርድ ቤት ሪፈር እንደሚጽፉልን ነው››በማለት ከልቤ አስቆኛል፡፡እውነትም ከአንዱ ዓቃቤ ህግ ወደሌላው እያመላለሱ ላለፉት 150 ቀናት ያለምንም ፍትህ በተባይ እንድንበላ፣ጤንነታችን አደጋ ውስጥ እንዲገባ አድርገውናል፡፡መጪው ጊዜስ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን ?
የየፖሊስ ጣቢያው መርማሪዎች
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን
ማዕከላዊና ፖሊስ መምሪያው የእናንተን ጉዳይ አንመለከትም በማለታቸው የአደራና ባለቤት አልባ እስረኞች ሆነናል፡፡አሁን የቀረን የአዲስ አበባ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ብቻ ነው፡፡ኤልያስ እንደሚለው ‹‹ይለቁን ወይም ይሰቅሉን››እንደሆነም እናያለን፡፡
የግፍ እስራታችንን 150 ቀናት ስንዘክር የፋሲካ በዓል ጋር በመገጣጠሙም ከትንሳዔው በዓል ጋር የሚቆራኘው ድል አድራጊነት፤ትንሳዔና ፍቅር ለአገራችን ይሆን ዘንድ ጥልቅ ምኞትና ጸሎታችን ነው፡፡

ከጋዜጠኛ ዳዊት ሰለሞን ፌስ ቡክ ገጽ ላይ የተገኘ

Filed in: Amharic