>
5:13 pm - Thursday April 19, 1731

የቡራዩ ጓንታናሞ (አስራት አብርሃም)

የቡራዩ ጓንታናሞ
ክፍል ፩
(አስራት አብርሃም)


ዕለቱ ቅዳሜ ነው። የአረና የአመራር አባል ከሆነው ጓደኛዬ ጋር በመሆን የመድረክ ሰልፍ ለመቀስቀስ በቡራዩ ከተማ ሄደው የታሰሩትን ጓደኞቻችን ለመጠየቅ አስበናል። ነገር ግን ሁለታችንም ቡራዩ በየትኛው የአዲስ አበባ ጫፍ እንደሚገኝ አናውቅም ነበርና ሜክስኮ፣ ሸበሌ ሆቴል አከባቢ አንዱን መወልዊያ አዟሪ “ቡራዩ በየት ነው?” ብለን ጠየቅነው። እርሱም ብዙ ግድ ባልሰጠው ሁኔታ “በመገናኛ በእኩል መሰለኝ” ብሎን አለፈ።
በዚያ መስመር ያሉትን ከተሞች እኔ አውቃቸዋለሁና ቡራዩ በዚያ በእኩል እንዳልሆነ እርግጠኛ ነበርኩ። እርሱ ወደ ሀገሩ የሚሄድበትን መንገድ ነው የጠቆመን! በመሆኑም ቀጥለን አንዱን የታክሲ ሹፌር ጠየቅነው። በአስኮ መስመር መሆኑንና ከሜክስኮ ወደ አውቶብስ ተራ፣ ከአውቶብስ ተራ ወደ አስኮ፣ ከአስኮ ደግሞ ወደ ቡራዩ በታክሲ መሄድ እንደምንችል ነገረን። እኛም እንደተባለነው አድርገን ቡራዩ ከተማ፣ ከፖሊስ ጣቢያው ላይ ደረስን።
ሆኖም ፖሊሶቹ እስረኛቹን ማየት እንደማንችል ስለነገሩን ምግብ ከዚያው ገዝተን ለእስረኞቹ ላክንላቸውና ከዚያ በመኪና ተሳፍረን ወደቤታችን መመለስ ጀመርን። በዚህ ጊዜ አብሮኝ የነበረው ሰው እስረኞቹ ከሰዓት ሊለቀቁ ይችላሉ የሚል መረጃ ሲሰማ፤ “እስከዚያ ቆይተን አብረናቸው ብንመለስ ይሻላል” የሚል ሀሳብ አቀረበና ከመኪናው ወርደን በእግር ወደ ፖሊስ ጣቢያው አከባቢ ሄድን። ባንድ ምግብ ቤት ውስጥ ገብተን ምግብ ነገር አዝዘን እየበላን ሳለ ስልክ ተደወለልኝና ለማናግር ወደ ውጭ ወጣሁ፤ በምግብ ቤቱ ውስጥ የነበረው የቴሌቭዥን ድምፅ ሊያሰማኝ ስላልቻለ ነበር ወደ ውጭ የወጣሁት።
ስልኩን አናግሬ ልመለስ ስል አንዱ ፖሊስ መጣና በቁጣ አነጋር “ና ትፈልጋለህ፤ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ቀጥል” አለኝ።
“ለመሆኑ ምን አድርጌ ነው ወደ ፖሊስ ጣቢያ የምሄደው?” አልኩት።
“ቀጥል ብያለሁ ቀጥል” አለ።
“እንግዲያው መሄዱንስ እሄዳለሁ ነገር ግን ማንነትህን ማወቅ ስለምፈልግ መታወቂያህን አሳየኝ” አልኩት። በዚህ ጊዜ መታወቀያ ተጠየኩ ብሎ እንደማጓራት አደረገው። የሆነ ሆኖ ሌሎች ፖሊሶችም መጡና ወደ ፖሊስ ጣቢያው ገባን።
የፖሊስ ጣቢያው ኮማንደር ተስፋስላሴ ነገራ ነው የሚባለው። ወደ ሆነ ቦታ ስልክ ደወሎ “ጌታዬ አስራት አብርሃም የሚባል ሰው እስረኞች በሀይል ለማስፈታት ሙከራ ሲያደርግ በቁጥጥር ስር አውለኗል።” ብሎ ተናገረ! በአማርኛ ያናገረው ሰው ኦሮምኛ የማይችል ሰው ሊሆን እንደሚችል ገመትኩ፤ እንዲያ ከሆነ ምርኮኞቹ ጋ ሳይሆን እውነተኛ አለቆቹ ጋ ደውሎ ይሆናል። ቆይ ግን፣ እኔ ሀየሎም አርአያ ነኝ! እስረኞችን በሀይል ለማስፈታት የምሞክረው! እነርሱ ናቸው፣ አንዴ እስረኞችን በኃይል አስፈታን፤ ሌላ ጊዜ የመንግስትን ባንክ ጠባቂዎቹ ገድለን ዘረፍን እያሉ ሲናገሩ፤ መፅሐፍ ሲፅፉ፤ ፊልም ሲሰሩ የምናየው! አግአዚ ኦፕሬሽን እና የአክሱም ኦፕሬሽን ማስታወሱ በቂ ነው። የሆነ ሆኖ “እኔን ነው!” በሚል አኳኋን ኮማንደሩን እየተመለከትኩት እያለ ስልኩን ዘጋና መጀመርያ ለጠራኝ ፖሊስ “በለው!” ብሎ አዘዘው። ፖሊሱም ከተቀመጠበት ተነስቶ በጥፊና በእርግጫ ያላጋኝ ገባ። ከስልኩ ወዲያኛው ጫፍ ሆኖ ያናገረው ሰው “በሉት” ብሎ አዟል ማለት ነው። ግደሉት እንኳን አላለ! ከሁኔታቸው እንደተረዳሁት እነርሱ ግደሉት ቢባሉ ወዲያው ይገደሉኝ ነበር!
አራጋው መሀመድ የተባለ ገጣሚ፤
“የጥፋት ቅጥረኛ ዝናር ቢታጠቅም
መግደሉን ነው እንጂ
የገደለበትን ምክንያት አያውቅም።”
ያለው እንደዚህ ዓይነቱ ነው። ኮማንደሩ ይዝትብኝና ይሰድበኝ ገባ፤ “አንተ ብትደፋ ምን እንዳታመጣ ነው! ብትሞት ማንን ትጎዳለህ?! እያለ ስድቡን ያወርደዋል። ወሬው ሁሉ ስለመድፋት፣ ስለመግደል ነው። ምናልባት በደርግ ጊዜ አብዮት ጥበቃ የነበረ ሳይሆን አይቀርም፤መቼም በኦሮሚያ ያለው የመንግስት መዋቅር አንድም በምርኮኛ አንድም በወዶ ገብ የተዋቀረ ነው እየተባለ ሲነገር ነው የምንሰማው። እድሜውም ሳየው ገፍቷል፤ ከፀጉሩ ነጭነት የተነሳ አናቱ ላይ ፈንድሻ የተሸከመ ነው የሚመስለው።
በዚህ ጊዜ እኔ ተናገርከት፤ “ወንጀል ካለብኝ፤ ያጠፋት ጥፋት ካለ አስረህ ወደ ፍርድ ቤት ማቅረብ እንጂ እኔን ማስመታትም ሆነ መስደብ አትችልም” አልኩት። እንደገና ቁጣውን ገንፍሎ “ገና እረግጥሀለሁ” አለ፤ መራገጥ ቁም ነገር መስሎታል!
ከትንሽ ጊዜ በኋላ በመኪና አሳፈሩኝና ከፖሊስ ጣቢያው አስወጡኝ። የቀኝ ዓይኔ አካባቢ በጣም አብጦ ነበርና ምናልባት ወደ ህክምና ሊወስዱኝ ይሆናል ብዬ አስቤ ነበር። ከነበሩበት ሁኔታ ተነስቼ በዚህ ደረጃ ሊያስቡ እንደማይችሉ ስረዳ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ሄጄ እንድታሰር ፈልገው ነው ብዬ ተረጋጋሁ። በኋላ የሆነው ግን ገምቼው የማላውቅ ነገር ሆነ! ወደ አንድ ግቢ ውስጥ “ግባ” ተባልኩ። በዚህ ሀገር መታሰር እንዳለ አውቃለሁ፤ ከፖሊስ ጣቢያ ወጥቼ፣ ወደ ማይታወቅ ቦታ ተወስጄ ልታሰር እችላለሁ ብዬ ግን አስቤ አላውቅም። በዚህ ጊዜ እውነተኛ ፍርሀት ፈራሁ! ከዚህ ቦታ በህይወት የምወጣ አልመሰለኝም ነበር።
(ይቀጥላል)

Filed in: Amharic