>
7:52 pm - Wednesday February 8, 2023

ለትግሉ የሚበጀው የቀድሞ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴን ለቀቅ፣ ህወሓት/ኢህአዴግን ጠበቅ ማድረግ ነው! [አበጋዝ ወንድሙ]

የኢትዮጵያ ተማሪዎ እንቅስቃሴና ከውስጡ ወጥተው ፣ ባለፈው ዘመን ህብረብሔራዊ ትግል ያካሄዱ ወገኖች (ያ ትውልድ ተብሎ የሚጠራው) ላይ የሚካሄደው ያልተቋ ረጠ ወገዛና እርግማን የዘመኑ አንቆቅልሽ ሆኖ ይሰማኛል።

ይህንን ተገቢ ያልሆነ ወቀሳ የሚያካሂዱ ወገኖች ስብሰብ ተደርገው ሲታዩ የሚከተሉትን ይመስላሉ።
– አሁን አሁን፡ ጀማሪ ፖለቲከኞች የሆኑ፣
– በንጉሱ ጊዜ ወይንም በደርግ ዘመን የገዥው ቡድን አካልና መሪ ተዋናይ የነበሩና፣ ግን ዛሬ ተገልብጠው ደርሶ ዴሞክራት የሆኑ የአገርና የህዝብ ተቆርቋሪ ነን ባዮች ፣
– ከህብረብሔራዊው እንቅስቃሴ ውጭ በብሄር ተደራጅተው የነበሩ፣
– ወይንም ጭራሹኑ ምንም ውስጥ ያልነበሩ፣ በግል ኑሮና ትምህርት ተጠምደው ቆይተው የወጣትነትና የትግል አፍላው ጊዜ ያለፈባቸውና፣ አሁን ግን የምሁር ካባ ለብሰናልና ፍርድ ሰጭ ነን ባይ ግለሰቦች በቴክኖሎጂ እድገት አማካይነት፣ ዛሬ ሁሉም በየፊናው ተነስቶ የሚፈነጭበት ድረ ገጽና የመሳሰሉት መድረክ በመፈጠራቸው፣ (facebook, tweeter, blog, paltalk…) ተማርኩ ተመራመርኩ ባዩ ፣ “የባእድ አስተሳሰብ እንዳለ በመቀበል” የሌለ ችግር ፈጥረው አገርን ለችግር ዳረጉ ሲል፣አንዳንዱ የፈጠራ ታሪክ በመፈብረክ የተማሪውን አንቅስቃሴ በ”ጸረ አማራነት” ሲከስ ፣ በተቃራኒው ደግሞ በስልጣን አካባቢ ያሉ ጠባብ ብሄርተኝነት ያሰከራቸው ቡድኖች፣ በህብረብሔራዊ ትግል ስም “የአማራውን የበላይነት ሊያስቀጥሉ የታገሉ” ብለው ሲወነጅሉ ማየት የተለመደ እየሆነ መጥቷል ።

ለኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ መጀመር ምክንያት የሆነው ፣ እንዲሁ የተወሰኑ መሰሪ ወይንም የዋህ ልጆች (እንደ አውጋዡ ይለያያል!) አንድ ማለዳ ተነስተው፣ “እስቲ አንድ የተማሪ አንቅስቃሴ እንጀምርና ሀገር እናምስ!” በሚል የተነሳ ነገር ሳይሆን፣በወቅቱ የሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ የፈጠረው ጉዳይ አንደነበረ ማንም መሳት የሌለበት፣ የግዴታም መቀበል ያለብን ሀቅ ነው ።

ምናልባት እነኚህ ግለሰቦች፣ የኢህአዴግ ዘረኝነት፣ ጭካኔና ሀገርን ከፋፍሎ መግዛት እየከፋ መምጣትና፣ ተያይዞም የደርግ አውሬያዊ ስርዓት አየተረሳ መሄድ፣ በንጉሱ ዘመን የነበረውንና መለወጥም የነበረበትን የፈላጭ ቆራጭና የዃላ ቀር አገዛዝ እንዲረሱና የፊውዳል ስርዓቱን እንዲናፍቁ አድርጎዋቸው ይሆናል። በዚህም የተነሳ ስርአቱን ለመቀየር የተነሳውን የተማሪውን አንቅስቃሴ በጭፍን ማውገዝ፣ የትውልዱን በጎም ሆነ የተሳሳተ ታሪኩን በቅጡ አለመረዳት ወቅቱንም በሚገባ አለመገንዘብም ይሆናል።

የቅርብ ጊዜ ታሪካችንን በቅንነት ካየነው ግን የተማሪው እንቅስቃሴ እንዲሁ አንዴ እመር ብሎ ሃገራዊ አጀንዳ አንግቦ የተነሳ ሳይሆን፣አጀማመሩ ከራሱ ከተማሪው ጥቅም ጋር የተያያዙ ውሱን ጥያቄዎችን በማንሳት በሂደት እያደገ ሃገራዊ ጥያቄዎች ወደ ማንሳት የዘለቀ እንደነበር ማስታወስ ያስፈልጋል። መማር ማለት ማወቅና ማገናዘብ ነውና የእውቀት አድማሳቸው እየሰፋ ሲሄድ ነው፣ ከራስ ውሱን ጥያቄ ባሻገር የሀገራችንን መሰረታዊ ችግር መገንዝብ የጀመሩት ተማሪዎች ፣ “ድህነት ወንጀል አይደለም !” “ መሬት ለአራሹ !” “ የብሄረሰቦች መብት ይከበር !” “የዜጎች አኩልነት የሚከበርባትና የበለጸገች ሀገር አንገንባ” ወደሚል ሃገራዊ አጀንዳ የተሸጋገሩት። ይሄንን ተግባራዊ ለማድረግ ክቡር ህይወታቸውን እስከመሰዋት የደረሰ ወኔ የተላበሱ ወጣት ኢትዮጵያውያን ያካሄዱትን ትግል፣ በትግሉ ሂደት የተፈጠሩ አንዳንድ ስህተቶችን በማጉላት ከነአካቴው እንቅስቃሴውንና ታጋዮቹን በጅምላ መኮነን በምንም መመዘኛ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፣ ፍትሃዊም አይደለም የምለው።

እስቲ እንደምሳሌ አንዱን፡ “የባእድ አስተሳሰብ አምጥተው” የሚለውን ውንጀላ በአጭሩ እንቃኘው ፣

የ”ባእድ አስተሳሰብ” ወደ ኢትዮጵያ አስገብተው የሚለው በጨለማ ዘመን የተነገረ ቢሆን ተቀባይነት ይኖረው እንደሁ እንጂ አሁን ባለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን፣ ያውም ተማርን ተመራመርን ከሚሉት ወገን ሲሰነዘር የሚያሳፍር ይሆናል። የሰው ልጅ ስለ ህብረተሰብ አረዳድም ሆነ ሌላ የሚያፈልቀው እውቀትና፣ በዛ ላይ ተመስርቶ የሚገኙ ተመክሮዎች፣ በአንድ ሀገር ጂኦግራፋዊ ክልል ብቻ መወሰን አለባቸው የሚል አይነት ክርክር ስለሚሆን ብዙም አንደማያስኬድ አጥተውት ነው ለማለትም ይከብዳል።

እንደው የሰነፍ ዱላ መሆኑ ነው አንጂ፣ ዛሬ ሁሉም የሚምልበትና የሚገዘትበት የ”ሊበራል ዴሞክራሲ” አስተሳሰብ ውልደቱ ኢትዮጵያ እንዳልሆነ ሁላችንም እናውቃለን። እኒህ ወገኖች ይሄን በወቅቱ በተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ የበላይነት የነበረውን የፖለቲካ አመለካከት ትክክል ነበር ወይንም የተሳሳተ ነበር ማለቱ ሲበቃ ፣በድፍኑ የባእድ አስተሳሰብ የሚለው ወገዛና ማጥላላት አያዋጣቸውም። ዛሬ በአገራችን አብዛኛው ሕዝብ የሚከተላቸው የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖቶችም አመጣጣቸው ከባእድ ነውና ወደ ጥንታዊውና ሃገራዊ እምነት፣ ምንም ይሁን ምንም እንመለስ የሚል ክርክር ውስጥ እንደማይገቡም ግልጽ ነው።

በወቅቱ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ባብዛኛው ዓለም ለነጻነትና ለፍትህ የሚታገሉ ኃይሎች ተቀባይነት የነበረውን የማርክሲዝም ሌኒንዝም አስተሳሰብ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴና ሌሎች ታጋዮች እንደ ትግል መሳሪያ መጠቀም፣ (ዛሬም ቢሆን የዓለም አንድ አምስተኛ ሕዝብ ያላትና ፣በዓለም በኢኮኖሚ ግዝፈት ከአሜሪካ ቀጥላ ሁለተኛነትን የያዘችው ቻይና፣ አስካሁን ከዚህ ያደረሰኝ ለቀጣዩም አድገቴ ወሳኙ ይሄው የፖለቲካ አረዳዴ ነዉ ማለቷ አንዳለ ሆኖ ) ምናልባት በቅጡ አልተረዱትም፣ ወይንም ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አገናዝበው አለተጠቀሙበትም ይባል እንደሆነ እንጂ፣ እንደው በድፍኑ የ”ባእድ አስተሳሰብ” በሚል ለማጣጣል መሞከሩ አያዛልቅም።

በኢትዮጵያ የነበረውና አሁንም ያለው በብሔረሰቦች መሃል ያለ አድልኦ የተማሪው እንቅስቃሴ የፈጠረው ይመስል፣ ትውልዱ የብሔሮች እኩልነት ይከበር በሚል ያካሄደውን ትግል፣ በሰላም ይኖር የነበረውን ሕዝብ እንደከፋፈለ ተደርጎ የሚነዛ ውንጀላ ከገዥ መደብ አባላት ሲሰነዘርበት፣ ከጠባብ ብሄርተኞች ደግሞ የተማሪው እንቅስቃሴ የብሄርን ትግል የሃገሪቱ ዋነኛ ቅራኔ ነው ብሎ አለመቀበሉ፣ የአማራውን የበላይ ገዥነት ለማስቀጠል የሚደረግ ጥረት ነበር የሚል ሀሰት ይሰራጭ አንደነበር ይታወቃል። በተቃራኒው ደግሞ አሁን አዲሱ ውንጀላ “ለብሄሮች እኩልነት በሚል የተደረገው ትግል ጸረ አማራ ትግል ነበር” ወደሚል አይን ያፈጠጠ ቅጥፈት ተቀይሯል። ይሄ ውንጀላ በጸረ አማራ ፕሮፓጋንዳ ተወልዶና አድጎ አሁን ድረስ የዘለቀው ህወሓት ላይ ቢወሰን ኖሮ ትርጉም ሊሰጠው ይቻል ነበር።

የቀድሞው የተማሪው እንቅስቃሴ ከሌላ ወገኑ የተለየ ኑሮ ያልነበረውን የአማራ ማህበረሰብን አስመልክቶ ምንም አይነት ብዥታ ሳይኖረው ፣ ከሌሎች መሰል ወገኖቹ ጋር በመተባብር በስሙ የሚነግዱትን የገዥ መደብ አባላትና አጋሮቻቸውን ከስልጣን አውርዶ የሁሉም ብሄረሰብ አባላት በአኩልነት የሚኖሩባትን ሀገር እንገንባ ብሎ መታገሉ በምንም መመዘኛ ጸረ አማራ ሊያሰኘው አይችልም።

ዛሬም ቢሆን ሀገሪቱን በዋናነት በሁሉም ዘርፍ ተቆጣጥሮ ህዝብን መከራ የሚያበላውን ዘረኛ የህወሓት አገዛዝ ስንታገል፣ አብዛኛውን የትግራይ ማህበረሰብ አባላት ለትግል አጋርነት አየጠራን፣ የገዥ መደቡ ላይ አነጣጥረን መሆን ስላለበት በጸረ ትግሬነት ሊወነጅሉ የሚፈልጉ የትግራይ ገዥ መደብ አባላትና ደጋፊዎች አንዳሉ ብንገነዘብም፣ እነሱን ፍራቻ ወይንም ለማስደሰት ሲባል የምናድበሰብሰው አውነታ ሊሆን አይችልም።

ዛሬ አገራችን ላይ የተዘረጋውን አስከፊ የህወሓት/ኢህአዴግ ስርዓት አስወግዶ የዜጎች አኩልነትና ዴሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚደረገው ትግል ስኬት አንዲኖረው ከተፈለገ ፣ነጋ ጠባ የቀድሞ የኢትዮጵያ ተማሪዎችን እንቅስቃሴ በማውገዝ የሚገኝ ትርፍ የለምና፣ የሚበጀው ሙሉ ትኩረታችንን ህወሓት/ኢህአዴግ ላይ አድርገን ፣ ከቀድሞው የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ፣ የሀገር ፍቅርን፣ ህብረብሄራዊነትን፣ የአላማ ጽናትን ፣ ላመኑበት ደግሞ፣ ክቡር ሕይወትን እስከመሰዋት ድረስ የዘለቀ ቆራጥነትን ተውሶ፣ ከነበሩት ስህተቶችም ትምህርት ቀስሞ ወደ ፊት መራመድን ነው ።

አበጋዝ ወንድሙ

Filed in: Amharic