>

ሰው ወይም አውሬ፡ እስከ መቼ እንደ አውሬ እያደናችሁን፣ እንደ ሰው እየተሰቃየን እንኖራለን?

Ethiopian Think Tank Group

Nigist Yirgaመጀመሪያ ለዚህ ፅኁፍ መነሻ ከሆነኝ የሰቆቃ ታሪክ የተወሰነ ቀንጭቤ ላካፍላችሁ፡-

“…ሴትነቴን ተመስርተው ጥቃት ፈፅመውብኛል፤ ሴት ሆኜ መፈጠሬን እንድጠላ የሚያደርጉ ተግባራትን ፈፅመውብኛል፣ እርቃኔን አቁመው ተሳልቀውብኛል፣ የእግር ጥፍሮቼን መርማርዎቼ ነቃቅለዋቸዋል። ጥፍሮቼን ከነቀሉ በኋላም ጥፍሮቼ የነበሩበትን ቦታ ቁስል እየነካኩ አሰቃይተውኛል፣…”

በእርግጥ ይህ ነፍስህ ሲዖል ስትገባ የሚያጋጥማት ስቃይና መከራ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ የኢህአዴግ መንግስትን በመቃወምህ ብቻ ተይዘህ መሃል አዲስ አበባ በሚገኘው የማዕከላዊ እስር ቤት የሚያጋጥምህ ነው። ይህ ስቃይ የደረሰባት ንግስት ይረጋ ናት። ይህን አሰቃቂ ተግባር የፈፀሙት ደግሞ የሳጥናኤል መልዓክቶች አይደሉም። በማዕከላዊ እስር ቤት የሚገኙ ወንጀል መርማሪዎች ናቸው። የማዕከላዊ መርማሪዎችና እስረኞች በአንድ ሀገርና መንግስት ስር የሚገኙ ሰዎች ናቸው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሁለቱም በአንድ አምሳል የተፈጠሩ ሰብዓዊ ፍጡራን ናቸው።

ንግስት ይርጋ

ጥያቄ፤ ሰው በሰው ላይ እንዴት እንዲህ ይጨክናል? ሰብዓዊ ፍጡር እንዴት እንዲህ ያለ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ይፈፅማል? ሰው እንዴት በአንድ ግዜ “ሰብዓዊ” እና “ኢ-ሰብዓዊ” መሆን ይቻለዋል? ንግስት ይርጋን እርቃኗን አስቁሞ ሲሳለቅባት የነበረው መርማሪ ፖሊስ እንዴት ማታ የሚስቱን ገላ አቅፎ ያድራል? የእሷን የእግር ጥፍሮች እየነቃቀለና ቁስሉን እየነካካ ሲያሰቃያት የነበረ ሰው ዘወትር ጫማውን ሲያጠልቅና ሲያወልቅ ምንም አይሰማውም? እንዴት በአንድ ግዜ ሰውም፥ አውሬም መሆን ይቻላል?

ወዳጄ… እንኳን “ከፀረ-ሰላም ኃይሎች፥ አሸባሪዎች ጋር በመመሳጠር አመፅና ብጥብጥ ለማስነሳት ወይም የኢህአዴግ መንግስትን ለመጣል ይቅርና እኔን ለመግደል ስትዘጋጅ፣ በጥርጣሬ ሳይሆን እጅ-ከፍንጅ ተያዘች ቢሉኝ በንግስት ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ተግባር ለመፈፀም አቅሙ የለኝም። ይሄ የፍርሃትና ድፍረት፣ የቆራጥነትና ፈሪነት ጉዳይ አይደለም። ይሄ ሰው የመሆንና ያለመሆን ጉዳይ ነው።  በቃ እንደ ሰብዓዊ ፍጡር በሰው ላይ እንዲህ ያለ ኢ-ሰብዓዊ ተግባር መፈፀም አልችልም። በማዕከላዊ እንዳሉት መርማሪዎች የሴት ልጅን ጥፍርና ፀጉር ለመንቀል፣ ወንድ ልጅን ለሦስት ቀናት ሰቅሎ ለማንጠልጠል በቅድሚያ ሰብዓዊነቴን ከላዬ ገፍፌ መጣልና ወደ አውሬነት መቀየር አለብኝ።

የዩንቨርሲቲ ተማሪ ሆንኩ አስተማሪ፣ የቀበሌ ሊቀመንበር ወይም ጠ/ሚኒስትር በማዕከላዊ የሚፈፀመውን ግፍና በደል ከማውገዝ፣ እስር ቤቱ እንዲዘጋ የበኩሌን ጥረት ከማድረግ ወደኋላ አልልም። ባለፈው ዓመት “ከጓንታናሞ እስከ ማዕከላዊ” በሚል ርዕስ አራት ተከታታይ ፅሁፎችን አውጥቼ ነበር። በዚህ ፅኁፍ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ በተሳሳተ እሳቤ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ፣ በዚህ አዋጅ ተከስሰው በታሰሩ ሰዎች ላይ በማዕከላዊ የሚካሄደው የስቃይ ምርመራ ምንም ጠቃሚ መረጃ እንደማይገኝበት፣ ከዚያ ይልቅ እስር ቤቱ የቀይ-ሽብር ማስታወሻ ሙዝዬም መሆን እንዳለበት እና እስካሁን ድረስ በማዕከላዊ የሰቆቃ ድምፅ መሰማቱ እንደ ሀገርና መንግስት ትልቅ የፖለቲካ ኪሳራ እንደሆነ በዝርዝር ለማስረዳት ሞክሬያለሁ። ነገር ግን፣ በማዕከላዊ የሚፈፀመውን ግፍና በደል ለማስቆም ግን ይሄን ማወቅ  ብዙም አስፈላጊ አይደለም።

የሴት ልጅን እግር ጥፍር እየነቀሉ ላለማሰቃየት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው። በማዕከላዊ እስር ቤት የሚካሄደውን የስቃይ ምርመራ ለማስቆምና ይሄን የስቃይ አምባ ለመዝጋት ሰብዓዊ ርህራሄ ብቻውን በቂ ነው። ታዲያ ከሀገሪቱ ጠ/ሚኒስትር እስከ የእስር ቤቱ አዛዥ ድረስ ያሉት የመንግስት ኃላፊዎች እንደ ንግስት ይርጋ ባሉ እስረኞች ላይ የሚፈፀመውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዴት አውቀውና ፈቅደው ዝም አሉ? ኧረ ለመሆኑ ለትኛው አጣዳፊ ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥታችሁ ነው? ምግብ፥ መጠጥ፥ መኖሪያ ቤት፣… መንገድ፥ መብራት፥ ፋብሪካ፥ ንግድ፥ ኢንዱስትሪ፣… መሬት፥ ድንበር፥ ሀገር፣… ሰላም፥ ልማት፥ ዴሞክራሲ፣… ፓርቲ፥ ፖለቲካ፥ ኢኮኖሚ፣… ወዘተ፣ ሰው የሌለበት ነገር ከቶ ምን አለ? ስለ ሰው ልጅ መብትና ተጠቃሚነት ከማሰብ፥ መስራትና ከማውራት በስተቀር ቅድሚያ የሚሰጠው ሌላ ምን አለ? የመንግስት ባለስልጣናት የስብሰባ አጀንዳ፣ የእቅዳቸው ዓላማ፣ የሥራቸው ውጤት፣… በአጠቃላይ የመንግስት የሆነ ነገር በሙሉ ሕዝብ፥ ሰው ላይ ማዕከል ያደረገ አይደለም እንዴ? እና ታዲያ… ሰው ሆናችሁ ለሰውና ሰለ ሰው እየሰራችሁ፣ የሰው ስቃይና መከራ የማይሰማችሁ እንዴት ነው? ስንቱ ኢትዮጲያዊ በማዕከላዊ ሰብዓዊ ክብሩ ተገፈፈ? እንኳን በአካል ለመሸከም በጆሮ ለመስማት የሚከብድ ስቃይ ተፈፀመበት። ይሄን የሰቆቃ ድምፅ ሰምታችሁ እንዳልሰማ ለማለፍ እንዴት ተቻላችሁ?

በንግስት ይርጋ ላይ የተፈፀመውን ስቃይና መከራ ለአንድ የዱር አምበሳ ብነግረው አይሰማኝም፥ አይረዳኝም። ምክንያቱም፣ የዱር አንበሳ እንደ እናንተ ሰው አይደለም፣ ሰብዓዊ ርህራሄ አልፈጠረበትም። ሁለት አንበሶች ሲጣሉ አሸናፊ ለመሆን አንዱ በሌላው ላይ ጥቃት ይፈፅማል። ነገር ግን፣ በምንም ዓይነት ተዓምር ቢሆን፣ አንዱ አንበሳ ተሸንፎ ከወደቀ በኋላ አሸናፊው የእግር ጥፍሩን እየነቃቀለና ፀጉሩን እየነጨ አያሰቃየውም። አንበሳ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ሁሉም እንስሳት የማዕከላዊ መርማሪዎች በንግስት ይርጋ ላይ የፈፀሙትን ግፍና በደል በራሳቸው ዝርያ ላይ አይፈፅሙትም።

በእርግጥ የዱር አንበሳ ንግስትን ጫካ ውስጥ ቢያገኛት ፀጉር ነጫጭቶ፥ ጥፍሬን ነቃቅሎ፣ ስጋዋን በጫጭቆ ይበላታል። ልክ እኛ ሰዎች በግን አርደን ጥፍሩን ነቅለን፥ አጥንቱ ግጠን እንደምንበላው ሁሉ፣ አንበሳም የንግስት ፀጉርና ጥፍር ነቃቅሎ አጥንቷን እየጋጠ ይበላል። ምክንያቱም፣ ሰው፥ በግ እና አንበሳ የተለያዩ የእንስሳት ዝርያዎች ናቸው። አንበሳ የሰው ወይም በግን እንጂ የሌላ አንበሳን ጥፍርንና ፀጉር እየነቀለ ለስቃይና መከራ አይዳርገውም። የማዕከላዊ መርመሪዎች ግን የዱር አውሬ የማይፈፅመውን ግፍና ስቃይ በእህታቸው ላይ ይፈፅማሉ፡፡

ከማዕከላዊ እስር ቤት አዛዥ እስከ ሀገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ያሉ የመንግስት ባለስልጣናት ይሄ ግፍና ስቃይ በሰብዓዊ ፍጡራን ላይ ሲፈፀም አውቀውና ፈቅደው ዝም ብለዋል። ከሰው በስተቀር ሌሎች እንስሳት በራሳቸው ዝርያ ላይ የማፈፅሙትን ስቃይና መከራ በማዕከላዊ ሰው በሰው ላይ እየፈፀመ ይገኛል። ነገር ግን፣ ሰው በሰው ላይ እንዲህ ያለ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ለመፈፀም በቅድሚያ ሰብዓዊነቱን ገፍፎ መጣል አለበት። ይሄ የአንስሳት ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው። ይህን መሰረታዊ ባህሪ “Edmund Leach” እንዲህ ሲል ይገልፆታል፡-

“One thing you can be sure about: it isn’t a matter of instinct. No species could ever have survived at all if it had an unmodified built-in drive to kill off all members of its own kind…. The general pattern in the animal kingdom is that aggression is directed outwards, not inwards. Only in rare situations do animals behave like cannibals or murderers; predators kill members of other species, not their own…” A Runaway World፡ Lec.3: Ourselves and Others, 1967.

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ በማዕከላዊ እስር ቤት የሚፈፀመው ግፍና ስቃይ ሰው የመሆን እና ያለመሆን ጉዳይ ነው። በማዕከላዊ ያሉ መርማሪዎች እንደ ንግስት ባሉ ሰዎች ላይ የስቃይ ምርመራ ከመጀመራቸው በፊት በቅድሚያ የራሳቸውን ወይም የእስረኞችን ሰብዓዊ ክብር ገፍፈው መጣል አለባቸው። በመሆኑም፣ መርማሪዎቹ የንግስትን የእግር ጥፍሮች ከመነቃቀላቸው በፊት ከሰብዓዊ ፍጡርነት ወደ አውሬነት ይቀየራሉ፣ አሊያም ደግሞ ሰብዓዊ ፍጡር የሆነቸውን ሰው እንደ አውሬ ማየት ይጀምራሉ። ምክንያቱም፣ ሰብዓዊ ፍጡር በአምሳሉ ላይ እንዲህ ያለ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ሊፈፅም አይችልም።

በአጠቃላይ፣ እንደ ንግስት የስቃይ ምርመራ የተፈፀመባቸውና ስቃያቸውን የተጋራን በሙሉ ሰብዓዊ ፍጡራን አይደለንም። አሊያም ደግሞ ይህን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የፈፀሙትና አውቀውና ፈቅደው በቸልታ ያለፉት ሰዎች ሰብዓዊ ፍጡራን አይደሉም። ያም ሆነ ይህ፣ ከሁለት አንዳችን ከሰውነት ወደ አውሬነት ተቀይረናል። ስለዚህ፣ ማን ምን እንደሆነ አይታወቅ አንጂ “ሰው” እና “አውሬ” ሆነን ተለያይተናል።

በማዕከላዊ እስር ቤት አሰቃቂ ግፍና በደል የምትፈፅሙ መርማሪዎች፣ ሁኔታውን አውቃችሁና ፈቅዳችሁ ዝም ያላችሁ በሁሉም ደረጃ ያላችሁ የመንግስት የፖሊስ፥ የደህንነትና ሲቭል ባለስልጣናት፣ እንዲሁም በማዕከላዊ ሰብዓዊ ክብራቸው የተገፈፉ ሰዎች ሰቆቃ ያልተሰማችሁ፥ በስቃያቸው የሳቃችሁ፣ እንደ ሰው ሰብዓዊ ርህራሄ ያልተሰማችሁ፥… እስኪ የሆናችሁትን ንገሩን? “አውሬ ነን” ካላችሁ እኛ ሰዎች ነንና እናድናችሁ! “ሰው ነን” ካላችሁ እኛ አውሬዎች ነንና እንሽሻችሁ። “እኛም፥ እናንተም ሰዎች ነን” እንዳትሉን ብቻ….። ያለ ሰብዓዊ ርህራሄ በሰው ላይ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት መፈፀም ሰብዓዊነት ሳይሆን አውሬነት ነው። ሰውነት በራሱ ሰብዓዊነት ነው! “ሰው” ወይም “አውሬ” ብላችሁ ራሳችሁን ለዩልን? ታዲያ እንደ አውሬ እያደናችሁን፣ እንደ ሰው እየተሰቃየን እስከ መቼ አብረን እንኖራለን?

Filed in: Amharic