>

ስለ 40/60 ሁሉም ሊያውቀው የሚገባ (አስራት አብርሃም)

Asrat Abrhaአንድ ተረት አለ፣ ሁለት ድመቶች ባገኙት ስጋ እኩል መካፈል አቅቷቸው ሲጨቃጨቁ አንድ ቀበሮ ይመጣና እኔ ላካፍላችሁ ይላቸዋል። ድመቶቹ እሺ ብለው በሀሳቡ ይስማማሉ። ከዚያ ሆን ብሎ አንዱን ትልቅ አንዱን ደግሞ ትንሽ አድርጎ ይቆርጠዋል። ድመቶቹ እኩል አይደለም ይሉታል። ችግር የለም አስተካክለዋለሁ ብሎ ከትልቁ ደህና አድርጎ በጥርሱ ለራሱ ይጎርሳል። በዚህ ጊዜ ትንሽ የነበረው ተመልሶ ትልቅ ይሆናል። አሁንም አስተካከልኩ ብሎ ከዚያኛውም ጎምዶ ለራሱ ይጎርሳል። ቀበሮው እንደዚያ እንደዚያ እያደረገ ስጋውን ሊጨርሰው ሆነ። ስለዚህ ድመቶቹ በቃ ያንተን ማካፈል ይቅርብን ስጋችንን መልስልን ይሉታል። ይሄማ የአገልግሎቴ ዋጋ ነው ብሎ የተቀረውም ይዞት ሄደ ይባላል። መንግስት በ40/60 የኮንዶምኒየም ፕራግራም ላይ እያደረገው ያለው ነገር ስንታዘብ ከቀበሮው ድርጊት ጋር የሚመሳሰል ነው።
ሁሉም እንደሚያስታውሰው መንግስት የገንዘብ አቅም ላላቸው የሚሆን ከአሁን በፊት ይሰራው ከነበረው ለየት ያለ የኮንዶምኒየም ዓይነት እሰራለሁ፣ ብሎ ነበር 40/60 የኮንዶምኒየም ፕሮግራም የጀመረው። በእርግጥ አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት ከሆነ ይሄ ፕሮግራም ሲጀመር በውጭ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ ቀልብ በመሳብ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘትና የስርዓቱን ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ለማስፋት ተብሎ የተዘየደ ብሎ መጠርጠር የሚቻል ነው። በአገር ውስጥም በርካታ ዜጎች በዚህ ፕሮግራም ላይ ፍላጎት በማሳየታቸው መንግስት ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ እንዲሰበስብ ምክንያት ሆኖታል። ስለዚህ በአንድ ወፍ ሁለት ድንጋይ የመምታት ዓላማ ነበረው፤ ገንዘብ መሰብሰብ እና ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ማስፋት። ይህን ግብ በተወሰነ መልኩ የተሳካ ይመስለኛል። ነገርየው ግን በዚህ አላቆመም። አሁን ከአምስት ዐመታት በኋላ የሆነውን ሲታይ በ40/60 የኮንዶምኒየም ፕሮግራም ተመዝጋቢ ዜጎች ላይ በመንግስት ደረጃ ክህደትና ማጭበርበር ነው የተፈፀመው። እንዴት ለሚለው ጥያቄ
የተፈፀመውን ነገር አንድ ባንድ እንይ፦
የ40/60 ኮንዶምኒየም ፕሮግራም በሐምሌ 2005 ዓ.ም. ምዝገባ ሲጀመር የቤቶቹ ዋጋ
ባለአንድ መኝታ 162, 645.00
ባለሁለት መኝታ 250, 000.00
ባለሶስት መኝታ 386, 400.00 ነበር። በወቅቱ ቤቶቹ በፍጥነት በጥራት እና እንደሚሰሩ፤ በ18 ወራት ውስጥም ከሃያ ሺህ በላይ ቤቶች ሰርቶ እንደሚያስረክብ፤ ቅድሚያ የከፈለ ቅድሚያ እንደሚያገኝ ነበር ቃል የተገባው። ከአራት ዓመት በኋላ የሰራቸው ቤቶች 972 ሲሆን ዋጋቸው ደግሞ እንደሚከተለው ሆነዋል።
ባለሁለት መኝታ 614, 602.00
ባለሶስት መኝታ 735, 241.00
ባለአራት መኝታ 829, 568.00 ሆኗል ነው እየተባለ ያለው።አራት ዓመት ሙሉ ተኝቶበት ከከረመ በኋላ ሶስት እጥፍ ዋጋ ጨምሯል። በዚህ ዋጋማ ከሪል ስቴቶችም መግዛት የሚቻል ነው። እዚህ ላይ ብዙ ጥያቄ ማንሳት የሚቻል ነው። መጀመሪያ ላይ ሙሉ ለሙሉ የከፈሉ ሰዎች በወቅቱ ገበያ ሂሳብ የቤቱን ሙሉ ዋጋ ከፍለዋል። መንግስት በራሱ ችግር ቤቱ ለመስራት ዓመታት ስለፈጀበት ሙሉ የከፈሉት አሁን ተጨማሪ እንዲከፍሉ እየተደረገ ያለበት ምክንያት ፍትሀዊ አይደለም። ወይ ገንዘባቸውን ሲሰሩበት አልቆዩ ወይ መጀመሪያ በማስቀመጣቸው ተጠቃሚ አልሆኑ በሁሉም አቅጣጫ ተጎጂ የሚሆኑበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። ለምሳሌ አንተነህ የሚባል የ40/60 ተመዝጋቢ ከምዝገባው በኋላ ብቻ 120,000.00 ብር ለቤት ክራይ መክፈሉን በፌስቡክ ገፁ ገልፀዋል። እንደ አንተነህ ያሉ ብዙ ዜጎች ቤቶቹ በወቅቱ ባለመሰራታቸው ለተጨማሪ የቤት ክራይ ወጪ ተዳርጓል፤ ገንዘባቸው በባንክ ተይዞ ሌላ ስራ እንዳይሰሩበት ሆኗል። እንግዲህ በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ ነው ሶስት እጥፍ ተጨማሪ እንዲከፍሉ እየተጠየቁ ያሉት። ይህም ሆኖ አሁንም ቤቱን ማግኘት አልተቻለም። የገንዘብ ጭማሪው ብቻ ነው የተነገረው። ምክንያቱም ሙሉ ለሙሉ የከፈሉት ዜጎች ከ17,000 በላይ ሲሆኑ የተሰሩት ቤቶች ደግሞ 972 ብቻ ናቸው።
ከሁሉም በላይ የሚገርመው ነገር ደግሞ ባለአንድ መኝታ የለም መባሉ ነው። ባለአንድ መኝታ ትጥፎ ባለአራት መኝታ የሚባል አዲስ ፕሮግራም ገብቶበታል። በባለ አንድ መኝታ የተመዘገቡት ዜጎች ከዕጣው ውጭ እንዲሆኑ ተድርጓል። 100% ከፍለው የነበሩት ዜጎች ገንዘባው መንግስት አራት አመት ነግዶበት አላውቃቸው ብሏቸዋል በዚህም ምክንያት ተስፋቸውን ወኃ በላው ማለት ነው። የሚገርመው ነገር የቤቶች ኤጀንሲ በየጊዜው ያወጣው በነበረው ሪፖርት በክራውን 224 በሰንጋ ተራ ደግሞ 100 በድምሩ 324 ባለአንድ መኝታ ቤቶች እየገነባ እንደሆነ ነበር የሚገልፀው። አሁን ታዲያ እነዚህ ቤቶች በተአምር ባለአራት መኝታ ሆነው ተገኙ ማለት ነው?! ይሄ በመንግስት ደረጃ የተፈፀመ ትልቅ ቅጥፈት ነው ሊባል የሚችለው።

ይሄ ነገር አንድ ታሪክ አስታወሰኝ። ሰውየው አካለ ጎደሎ በመሆኑ ዘመዶቹ የታጫትን ሴት እንዲያመጡለት ይልካቸዋል። ሙሽራዋ በበቅሎ ተጭና መጣች። ሙሸራው እጀ ቆራጥ መሆኑን ስትመለከት ምን ዓይነት ጉዱ ነው የማየው አለች በመገረም። ሙሽራው ቁጭ ባለበት ሆኖ የለበሰውን ጋቢ ገለጥ አደረገና የተቆረጠውን እግሩን እያሳየ ይሄ ብትይ ምን ልትይ ነው አላት ይባላል። መንግስታችንም እኛ እድሜውና ጤናው ይስጠን እንጂ ገና ብዙ ነገር ያሳየናል። እስካሁን ካስገረመን በላይ ሊያስገርመን እንደሚችል ከአያያዙ መገምት የሚቻል ነው።

በባለ አንድ መኝታ የተሰራው ቅሸባ እንደሽፋን የዲዛይን ለውጥ ስለተደረገ ነው የሚል ምክንያት ነው የሚቀርበው። እንዴት ነው ባአንድ መኝታ እሰራለሁ ብሎ ውል ገብቶ ገንዘብ ተቀብሎ ከአራት ዓመት በኋላ ውል ላልገባው በፕሮግራሙ ላልነበረ ባለአራት መኝታ ሰራሁ የሚባለው! ሌላው ደግሞ ባለአራት መኝታ ሰርቻለሁ ባለሶስት የሆናችሁ መውሰድ ትችላላችሁ ካልወሰዳችሁት ግን መንግስት ይወስዳል የተባለው ነገር ነው። እዚህ ላይ ነው ያለው ሚስጥሩ መንግስት እነዚህ ቤቶች ለታማኝ ካድሬዎቹ ለመስጠት ያለውን ሀሳብ ነው የሚያሳየው። በዲዛይን ለውጥ ብቻ ቢሆን ኖሮ ባለአንድ የሆኑትን ወደ ባለሁለት ባለሁለቶቹ ደግሞ ወደ ባለሶስት ባለሶስቶቹ ደግሞ ባለአራት እንዲወስዱ ማድረግ ይችል ነበር። ምንም እንኳን ይሄም በራሱ ተገቢ ባይሆንም አሁን ከተደረገው ግን የሚሻል ነው።

ቅድሚያ የከፈሉ ቅድሚያ ያገኛሉ የሚለው መርህም በግልፅ ነው የተጣሰው። በውሉ ላይ በግልፅ እንደሚያሳየው ቀድሞ የተመዘገበ፣ ቀድሞ ሙሉ የከፈለ በየደረጃው ቅድሚያ እንደሚያገኝ ነበር። አሁን እየሆነ ግን በሂደት ሙሉ የከፈሉትን 11,000 ተመዝጋዎች ነው በእጣው ውስጥ እንዲካተቱ የተደረገው። ለመንግስት ሰራተኞች የተወሰነ ፐርሰንት ቅድሚያ ያገኛለሁ በሚል ስሌት አሁንም ለታማኝ ካድሬዎቹ እድል አመቻችተዋል። አጠቃላይ የሆነው ሁሉ ሲታይ መንግስት እንደ መንግስት እምነት የሚጣልበት እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው። ሌላው 100% ሲባል እንዴት ነው የትርጓሜ ችግር ያለው ይመስላል። አንድ ሰው በቅድሚያ 40% ሲከፍል መንግስት ደግሞ 60% የባንክ ብድር እንደሚያመቻችለት ነው ውሉ ላይ የተገለፀው። ይሄ ሰው 100% አልከፈለም ማለት እንችላለን ወይ። እኔ እንደሚመስለኝ የፕሮግራሙ ዓላማም የተወሰነ ገንዘብ ግለሰቡ ይሸፍናል ቀሪው ደግሞ መንግስት በብድር መልክ ሸፍኖ ዜጎች የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ማድረግ ነው። በራሳቸው ሙሉ ለሙሉ መሸፈን የሚችሉ ዜጎች መንግስት ቤት የሚሰራላቸው ምክንያት የለም። መንግስት ማድርግ የነበረበት ለእነዚህ ዜጎች መሬት ማመቻቸትና ከፈለገም የቤቱን ዲዛይን መስጠት ነው። በራሳቸው ጊዜ ይሰሩት ነበር። የመሬት ችግር እንጂ የመስራት ችግር ያለባቸው አይደለም።

አሁንም ቢሆን አሁን ባለው የስራ አፈፃፀም ቤቶቹ ለልጅ ልጅ ካልሆነ በስተቀር በቅርብ የሚደርስ ነገር አይደለም። ሪፖርተር እንደዘገበው መንግስት የኮንዶምኒየም ቤቶች ለመስራት በባጀት ችግር ምክንያት ችግር እንደገጠመው እየተነገረ ነው። ስለዚህ ሙሉ ለሙሉ የከፈሉ ዜጎች መንግስት የቤት መስሪያ ቦታ ብቻ እንዲሰጣቸው መጠየቅ ነው ያለባቸው። አለበዚያ ገንዘባቸው በየጊዜው ዋጋው እየወረደ በብላሽ ባንክ ውስጥ መበስበሱ ነው። በተለይ በገንዘቡ ሌላ ስራ መስራት የሚችሉ ዜጎች ይሄ ጉዳይ በጥብቅ ነው ማሰብ ያለባቸው።

ባለአንድ መኝታ ቤት ተመዝጋቢዎች ደግሞ የጋራ ኮሚቴ ማቋቋምና መንግስት መጠየቅ አለባቸው። ጉዳዩም ወደ ፍርድ ቤት ነው መሄድ ያለበት። ምክንያቱም ፕሮግራሙ አሁን በታደለው የክራውንና የሰንጋ ተራ ኮንዶምኒየም በግልፅ የታጠፈ በመሆኑ ከዚህ በኋላም በሌሎች ኮንዶምኒየም ባለአንድ መኝታ እንዳለማወቅ አይቻልም። ስለዚህ ተመዝጋዎቹ ጉዳዩን ወደፍርድ ቤት መውሰድ ነው ያለባቸው የሚል እምነት ነው ያለኝ። ምክንያቱም መንግስት ቤት እየሰራሁላችሁ ነው በማለት ለአራት ዓመታት ያህል ገንዘባቸውን ሲጠቀምበት ቆይቷል። ሌላ አማራጭ እንዳይፈልጉ አድርጓቸዋል።

መንግስት በኮንዶምኒየም ቤቶች ፕሮግራም ብዙ ዜጎች ተጠቃሚ እንዳደረገ ሁሉ በቀላሉ መስተካከል የነበረባቸው ጉዳዮች ባለመሰራታቸው ዜጎች ለእንግልትና ለመከራ፣ ላም አለኝ በሰማይ ዓይነት አጉል ተስፋ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓል። ለምሳሌ የቤት ተነሺዎች በተነሱበት ቦታ ላይ በሚሰራው ኮንዶምኒየም ቤት እንዲያገኙ የማይድረግበት ምክንያት ግልፅ አይደለም። በመሰረቱም መንግስት ራሱ ቤት ከመስራት ጉዳይ እጁን አውጥቶ ዜጎች ቤት የሚያገኙበት ሌላ የተሻለ መንገድ ነው መፈለግ ያለበት።

Filed in: Amharic