>

የቀንድ-አውጣ ኑሮ፡ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ወጣ፣ የፀረ-ሽብር ሕጉ መጣ!

ethiothinkthank

ላለፉት አስር ወራት በሀገሪቱ ላይ ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በዛሬው ዕለት ተነስቷል። በእርግጥ መንግስት አዋጁ የተቀመጠለትን ዓላማ እንዳሳካ ገልጿል። ይሄን የተለመደ ፕሮፓጋንዳ ወደ ጎን በመተው የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በተጨባጭ ያመጣው ለውጥ ከወደፊቱ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ አንፃር እንዴት ይታያል? በዚህ ፅሁፍ ከአስቸኳይ ግዜ አዋጁ መነሳት ጋር ተያይዞ ያሉትን አንዳንድ ሁኔታዎች በአጭሩ እንዳስሳለን።

መነሻ ይሆነን ዘንድ በመጀመሪያ የራሱን የግል ገጠመኝ ላካፍላችሁ። አንዳንዶቻችሁ እንደምታውቁት የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ከመታወጁ በፊት ታስሬ ነበር፡፡ የታሰርኩበት ዕለት መስከረም 20/2009 ዓ.ም ሲሆን የተከሰስኩበት ወንጀል “ሕዝብን ለአመፅ የሚያነሳሱ ፅሁፎችን ፅፈሃል፣ የጦር መሳሪያ በመኖሪያ ቤትህ ውስጥ ይገኛል” በሚል ወንጀል ነበር። በወሊሶ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ እያለሁ መስከረም 28/2009 ዓ.ም የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ታወጀ። በማግስቱ ፖሊስ ጣቢያ ሊጠይቁኝ ከመጡ የስራ ባልደረቦቼ አንዱ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ መታወጁን ነገረኝ። እኔም እንደ ልማዴ በብጣሽ ወረቀት ላይ ማስታወሻ ያዝኩኝ። የማስታወሻው ጭብጥ የሚከተለው ነበር፡-

“ከስሙ መረዳት እንደሚቻለው “የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ” የአጭር ግዜ መፍትሄ ነው። ሕዝቡ እያነሳ ላለው የመብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት ጥያቄ ዘላቂ ምላሽ ለመስጠት አያስችልም። ሆኖም ግን፣ አዋጁ ትግባራዊ በሚሆንባቸው ቀጣይ ወራት ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል ዘዴ ለመቀየስ በቂ ግዜ ነው። በመሆኑም፣ የኢህአዴግ መንግስት የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ሕዝቡ ለሚያነሳቸው ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት ማድረግ አለበት።”

መስከረም 30/2009 ዓ.ም የወሊሶ ከተማ ፖሊሶች በታሰርንበት ክፍል ውስጥ ድንገተኛ ፍተሻ በማድረግ ከላይ የተጠቀሰውን ማስታወሻ ከኪሴ ውስጥ ወሰዱ። ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ይህን ፅሁፍ እንደ ማስረጃ በመጥቀስ “የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን በመጣስ አመፅ ቀስቃሽ ፅሁፎችን በመፃፍና ለማሰራጨት ሲሞክር እጅ-ከፍንጅ ተይዟል” በሚል ተከሰስኩ። በዚህ ምክንያት ጉዳዩ በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በተቋቋመው ኮምንድ ፖስት መታየት አለበት በሚል ጥቅምት 17/2009 ዓ.ም ወደ ጦላይ ተወሰድኩ። ከዚህ ገጠመኝ በመነሳት ብዙ ነገር ማለት ይቻላል። ከእነዚህ ውስጥ እስኪ የተወሰኑትን ነጥቦች በማንሳት እንመልከት።

በመጀመሪያ ደረጃ እኔ የታሰርኩት በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 29 መሰረት ሃሳብና አመለካከቴን በነፃነት ስለገለፅኩ ሲሆን የተከሰስኩት አንቀፅ ደግሞ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ነው። በእርግጥ የፀረ-ሽብር አዋጁ በወጣ የመጀመሪያ አመስት አመታት ውስጥ ብቻ 10 ጋዜጠኞች ሲታሰሩ 57ቱ ደግሞ ለስደት ተዳርገዋል። የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ከወጣ በኋላ ደግሞ ይሄው አፈና ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠሉ ይታወቃል። የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ ደግሞ የፀረ-ሽብር አዋጁ የቀድሞ አገልግሎቱን መስጠት ይጀምራል። በመሆኑም፣ የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት እንደ ቀድሞ ይታፈናል። ዛሬ ላይ አስቸኳይ ግዜ አዋጁ ተነስቷል፡፣ አምባገነንነት ግን ይቀጥላል።

በድጋሜ ከላይ ወደተጠቀሰችው ፅሁፍ ስንመለስ፣ አንዲት ብጣሽ ወረቀት ለከፋ ስቃይና እንግልት ዳርጋኛለች። ከሁሉም በላይ የሚቆጨኝ ግን በስጋቴ እውን መሆኑ ነው። ከፅሁፉ ጭብጥ መረዳት እንደሚቻለው፣ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ሀገሪቱ ላጋጠማት ፖለቲካዊ ችግር ዘላቂ መፍትሄ መፈለግ ይቻል ነበር። በእርግጥ ከአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በስተጀርባ ያለው ምክንያት የኢህአዴግ መንግስት አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ያለበት ችግር ነው። አዋጁ ተግባር ላይ በዋለባቸው አስር ወራት የኢህአዴግ መንግስት እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመቅረፍ በሚያስችል መልኩ ሥር-ነቀል ለውጥና መሻሻል ለማምጣት ያደረገው ጥረት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

በመሆኑም፣ ¨Crisis is the best opportunity to miss” እንደሚባለው፣ የኢህአዴግ መንግስት ከፀጥታና አለመረጋጋት ችግሩ መንስዔ የሆኑትን ችግሮች በመለየት ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የሚችልበትን ምቹ አጋጣሚን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት የገዢው ፓርቲ አመራሮችና ደጋፊዎች ዘንድ የሚስተዋለው የተዛባ አመለካከት ነው። አብዛኞቹ የመንግስት አመራሮችና ደጋፊዎች በተለያዩ የሀገራችን አከባቢዎች የታየው አመፅና ተቃውሞ፣ እንዲሁም ይህን ተከትሎ የተከሰተው የፀጥታና አለመረጋጋት ችግር በፀረ-ሰላም ኃይሎች እና አፍራሽ አጀንዳ ባላቸው ሚዲያዎች፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎች፥ ጋዜጠኞችና የመብት ተሟጋቾች፣ እንዲሁም በገዢው ፓርቲ ውስጥ ባለው የኪራይ ሰብሳቢነት፥ ጠባብ ብሔርተኝነት እና የትምክህት አመለካከት ምክንያት እንደሆነ ሲጠቅሱ ይሰማል። የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ግን ዜጎች ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ የሚወጡት “በሚያገኙት እና ማግኘት በሚገባቸው” መካከል ያለው ልዩነት ይበልጥ እየሰፋ በመሄዱ ምክንያት እንደሆነ ይገልፃሉ።

ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ወደ ሁከትና ብጥብጥ፣ ብሎ ወደ ግጭትና አለመረጋጋት ሊያመራ የሚችልበት ምክንያት ግን የመንግስት አፀፋ እርምጃ ነው። የሕዝብ ጥያቄ ከፖለቲካዊ መብትና ነፃነት፣ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ጋር የተያያዘ ነው። ሕዝቡ የሚያነሳውን ጥያቄ መንግስት በአግባቡ ተቀብሎ ተገቢ ምላሽ የሚሰጥ ከሆኑ የአደባባይ አመፅና ተቃውሞ ወደ ሁከትና ብጥብጥ አያመራም፡፡ በተቃራኒው፣ የሕዝቡን ጥያቄ በኃይል ለማፈን ጥረት የሚያደርግ ከሆነ ግን የህዝቡ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ወደ ግጭትና አለመረጋጋት ያመራል።

ከአስቸኳይ ግዜ አዋጁ መታወጅ በፊት በነበሩት አመታት ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን በአመፅና ተቃውሞ ካልሆነ በስተቀር በመደበኛ የፖለቲካ አካሄድ እንዳይጠይቁ ተደርገዋል። መደበኛ የተባሉት መንገዶች በሕገ-መንግስቱ ላይ በግልፅ የተቀመጡ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ፤ አንቀፅ 29፡- “የአመለካከትና ሃሳብን በነፃ የመያዝና የመግለፅ መብት”፣ አንቀፅ 30፡- “የመሰብሰብ፥ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት”፣ እንዲሁም አንቀፅ 31፡- “የመደራጀት መብት” በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው።

ሆኖም ግን፣ ከላይ የተጠቀሱት ዴሞክራሲያዊ መንገዶች ከሞላ-ጎደል በፀረ-ሽብር ህጉ ተገድበዋል። ስለዚህ፣ በአመፅና ተቃውሞ ካልሆነ በስተቀር ዜጎች ሃሳብና አመለካከታቸውን፣ ቅሬታና አቤቱታቸውን ሊገልፁ የሚችሉበት መንገድ የለም። ባለፈው አመት በኦሮሚያ፥ አማራና በደቡብ ክልሎች የታየው ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ዋና ምክንያቱ የፀረ-ሽብር አዋጁ ነው። በዚህ ምክንያት ዜጎች “የተሻለ መብትና ነፃነት፣ እንዲሁም ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ይገባናል” የሚል ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ለማንሳት የሚችሉበት መተንፈሻ ቀዳዳ ሲያጡ በአመፅና ተቃውሞ አደባባይ ወጡ። በእነዚህ ዜጎች ላይ የተወሰደው የኃይል እርምጃ ሁኔታውን እያባባሰው በመሄዱ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ታወጀ።

በዛሬው ዕለት የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ሲነሳ ለአመፅና ተቃውሞ መነሻ የነበረው የፀረ-ሽብር አዋጁ ወደ ቀድሞ ተግባሩ ይመለሳል። ይህ ደግሞ በተራው ለሌላ አመፅና ተቃውሞ ይወልዳል። “ይህን አመፅና ተቃውሞ ዳግም በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ መቆጣጠር ይቻላል ወይ”? የሚለውን ወደፊት አብረን እናያለን። ለአሁኑ ግን የቀድ-አውጣ ኑሮ ይቀጥላል፡፡ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ሲወጣ የፀረ-ሽብር ሕጉ መጣ፣ ነገደ ቀንድ-አውጣ ከቤት እንዳትወጣ!

Filed in: Amharic