>
11:32 am - Monday November 29, 2021

በትግራይ አለመረጋጋት አለ! (ኣብርሃ ደስታ ከመቀሌ)

ጓዶች ህወሓቶች በጣም ደንግጠዋል። ባሁኑ ሰዓት በብዙ የሑመራ አከባቢዎች፣ ማይጨው (ሽኮማዮ)፣ ዓዲጎሹ (ተከዘ)፣ ሐውዜንና አፅቢ ህዝቡን ለመቆጣጠር ፖሊሶችና ምልሻዎች ተሰማርተዋል። ትናንት ማታ (ቅዳሜ ማታ) አቶ መሰለ ገብረሚካኤል (የዓረና ስራ አስፈፃሚ አባልና የምዕራባዊ ዞን የዓረና አስተባባሪ) ፊታቸው በሸፈኑ ታጣቂዎች ወደ ፖሊስ ጣብያ ተወስደው ምርመራ ተደርጎባቸዋል። ትናንት ቅዳሜ በእንዳ አብርሃ ወ አፅብሃ የዓረና ልሳን ለህዝብ ሲያድሉ የነበሩ የዓረና አመራር አባላት አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ፣ አቶ ኃይለኪሮስ ታፈረና መምህር ይልማ ኩኖም በህወሓት አስተዳዳሪዎች ክፉኛ ተደብድበው ሆስፒታል ገብተዋል።

አሁን የእንዳ አብርሃ ወ አፅብሃ አከባቢ በፖሊሶች እየተጠበቀ ነው። ሁለትና ከሁለት በላይ ሁኖ መንቀሳቀስ ተከልክሏል። ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ አይፈቀድም። በአፅቢ ወንበርታ ላለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ለመግታት የተቃውሞው መሓንዲስ የተባለውን አቶ ሕድሮም ሀይለስላሴን በሰበብ አስባቡ ለማሳሰር ዝግጅት መጀመሩ ከህወሓት ፅሕፈትቤት መረጃ ደርሶኛል። በሐውዜን ከተማ ዓረና ተብሎ የተጠረጠረ ሁሉ ድብደባ ተፈፅሞበታል። ከሐውዜን እንዲወጣም እየተደረገ ነው። አሁን እሁድ ግንቦት 24, 2006 ዓም ከምሽቱ 2:00 ጀምሮ በእግሪሓሪባ መንደር ብዙ ቁጥር ያላቸው ፖሊሶች ተሰማርተዋል። አቶ ሙኡዝ ፀጋይ የተባለ ያከባቢው የዓረና አስተባባሪ ቤት ተከቧል። መንቀሳቀስ አይችልም። በያንዳንዱ የእግሪሓሪባ መኖርያቤት በር ሦስት ፖሊሶች ይገኛሉ። ዛሬ በህዝቡና አስተዳዳሪዎች አለመግባባት ተፈጥሮ ነበረ። ባጠቃላይ ባሁኑ ሰዓት በትግራይ አለመረጋጋት አለ። ይህን ሁሉ ችግር እየፈጠረ ያለ ግን ህወሓት ራሱ ነው። ከሰለማዊ ተቃውሞ ዉጭ ምንም ዓይነት ዓምፅ በሌለበት ህዝቡ ሊያምፅ ይችላል በሚል ስጋት ብቻ የፀጥታ ሃይሎች እያሰማራ ነው። ህዝቡም ተደናግጧል። እኛ ግን ብዕር እንጂ ጠመንጃ አልያዝንም።

 

Filed in: Amharic