>

መለኛው ምኒልክና የዘመናዊ ወፍጮ አገባብ [ቋጠሮ]

Emye Minilik Henok Yeshitila 06042016አጼ ምኒልክ የተወለዱት በ1836 ነኅሴ 12  ቅዳሜ ቀን ነበር። በህይወት ቢኖሩ ትናንት ነሃሴ 12 2009 ዓ.ም የ173 ዓመት ልደታቸውን ያከብሩ ነበር ማለት ነው፡፡ ሰሞኑን አብዛኛው ኢትዮጵያዊው የእኚህን ድንቅና የጥቁር ህዝብ የነጻነት ቀንዲል የሆኑ መሪ ገድል እየዘከረ 173ኛ የልደት ቀናቸውን እያከበረ ይገኛል፡፡ የዚህችም ጽሁፍ ምክንያት ይኽው ነው። የጸሃዩን ንጉስ ዕለተ-ውልደት መዘከር።
አጼ ምኒልክ በዘመነ ንግስናቸው በርካታ የስልጣኔ መሰረት የሆኑ ተግባራትን ፈጽመዋል። ስልጣኔን ወደ ሃገር በማስገባትና በማስፋፋት የአጼ ምኒልክን ያህል ተጠቃሽ መሪ የለም። ይሁን እንጂ አጼ ምኒልክ የውጭውን ስልጣኔ ለማስገባት ሲሞክሩ ህዝቡ አልቀበል እያለ ይቸገሩ ነበር፡፡  ለምሳሌ ወፍጮን ለማስገባት በሞከሩበት ወቅት ከመኳንቱና ከቀሳውስቱ ጠንከር ያለ ውግዘትና ተቃውሞ ነበር የገጠማቸው። መለኛው ንጉስ ግን የገጠማቸውን ተቃውሞና ውግዘት በጥበብ አክሽፈውታል። ያከሸፉበት ዘዴ ደግሞ ብልህነታቸውን ከማሳየቱም ባሻገር አስቂኝ ነበር።
ጳውሎስ ኞኞ  “አጼ ምኒልክ” በተሰኘው መጽሃፉ ገጽ 337 ላይ የዘመናዊ ወፍጮን አገባብ ታሪክ እንዲህ ሲል አስፍሮታል፦
የወፍጮ መኪና በኢትዮጵያ ውስጥ ለማቋቋም አስቸጋሪ ነበር።የሸዋው ንጉስ ሳህለ ሥላሴ በ1835 ገደማ አንድ በውሃ የሚሰራ ወፍጮ አስመጥተው ባስተከሉ ግዜ፤ ቀሳውስቱ ወፍጮ የሰይጣን ስራ ነውና በወፍጮው አስፈጭቶ የበላ የሰይጣን አገልጋይ ነውና አውግዘናል በማለታቸው ወፍጭው ፈራርሶ ወደቀ። ከዚያ ዘመን ቀደም ብሎም አቡነ ሰላማ አጼ ቴዎድሮስን ወፍጮ እንዲገባ ባማከሯቸው ግዜ “ የሴቶቹን ክንድ ምን ልናደርግበት ነው?” ወፍጮን ከለከሉ። አጼ ዮሃንስም “በጉዞ ላይ እህል የሚፈጩ ሴቶችን ከማጓጓዝ የሚገላግለን ነው..” ብለው ወፍጮ ቢያስተክሉም በንጉስ ሳህለ ስላሴ እንደደእሰው ሁሉ በእሳቸውም ላይ የሰይጣን ፈጪ ነው ተብሎ ስለተወገዘ ቀረ።
በኋለኛው ግዜ የማንኛውንም ውግዘትም ሆነ ተቃውሞ አሸንፈው ወፍጮን ያቋቋሙት ምኒልክ ናቸው። በአድዋ ዘመቻ ጊዜ ጓዙን ያበዛው የፈጪና የወፍጮ ጭነት መሆኑን ያወቁት አጼ ምኒልክ ለግላቸው ብዙ እህል የሚፈጭ ወፍጮ እንዲያስመጣላቸው እስቲቬኒን አዘዙት። ወፍጮውም መጥቶ በ1993 ተተከለ። ወፍጮው የሚፈጨው በሰይጣን ሳይሆን በሰው መሆኑን ለማሳየት ምኒልክ ራሳቸው ወፍጮ ቤት እየሄዱ በአስፈጪነት ተካፋይ ሆኑ። በግብር ጊዜም መኳንቱና ቀሳውስቱ ሰይጣን በፈጨው ዱቄት የተጋገረ እንጀራ አንበላም ሲሉ፤ ምኒልክ ደግሞ በእጅ በተፈጨ ዱቄት የተጋገረ እንጀራ አልበላም ይሉ ጀመር። ምክንያታቸውንም ሲያስረዱ “..ፈጪይቱ በምትፈጭበት ግዜ ንፍጧ ሲመጣ ተናፍጣ ወዲያው ተፈጫለች። ኩሷን ጠርጋ ወዲያው ትፈጫለች..።ለዚህ ነው በንጹህ ድንጋይ የተፈጨውን ዱቄት የምወደው…” ይሉ ጀመር።
በኋላም በዘመነዊ ወፍጮ በተፈጨ ዱቄት የተጋገረ ….መብላት እየተለመደ ሄደ…።
ከዚህ የምንረዳው አጼ ምኒልክ በዛን ዘመን ከነበረው ህዝብ ምን ያህል የቀደሙና አለጊዚያቸው የተፈጠሩ ድንቅ ሰው መሆናቸውን ነው።
በሞቱ ጊዜ በልጃቸው በንግስት ዘውዲቱና በህዝብ ከተገጠመላቸው ግጥም(ቅኔ) ጥቂት ስንኞችን አካፍዬ ጽሁፌን ልቋጭ።
በህዝብ ከተገጠመላቸው
አጼ ምኒልክ ሲሞቱ..
ምነው አትሄዱ ከፍታቱ፡
እናንተ ሰዎች ክፋታችሁ፡
አለማስቀበራችሁ። (ዓለም አስቀበራችሁ)
ምኒልክ መጓዙን የምትጠይቁኝ
ፊትም አላለፈ ኋላም አይገኝ።
በልጃቸው በንግስት ዘውዲቱ ከተገጠመላቸው፡
33 አመት የገዛንበቱ ፤የበላንበቱ፤ የጠጣንበቱ
የታሣስ ባታ ለት ተፈታ ወይ ቤቱ? (ታህሣስ 3)
ብትታመም ልጅህ እጅግ ጨነቀኝ
ስትሞትስ አልሞትም እኔ ብልጥ ነኝ፤፡
ወልደውኛል እንጂ እኔ አልወለድኩዎ፤
አንጀቴን ተብትበው ምነው መያዝዎ።
አሳዳጊዬ አንቱ አላውቅም እናት፤
ምነዋ ሞግዚቴ እንዲያል ክዳት።
ምልክቱ እንዲህ ነው የንጉስ ሞት ሃዘን፤
ጣይቱ ስትጨልም ጨረቃ ደም ስትሆን ።፤
ከወርቅ ጸዳል የሚያበራው የእምዬ ምኒልክ ገድል ከሃገራችን ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ጥቁር ህዝቦች መኩሪያ ነው።
Filed in: Amharic