>
1:47 pm - Sunday September 19, 2021

ኢትዮጲያዊ ግን በመንግስት የተተመነለት ዋጋው ስንት ነው? [ታምሩ ተመስገን]

the-most-important-question-mark… ሀበሻ በስደት ሳለ ይገደላል፡፡ እንደ አውሬ ይታረዳል፡፡ የማይነጋ ተስፋውን በስደት ሲያሳድድ ውቂያኖስ ውስጥ ሰምጦ ይሞታል፡፡ የእናቱን ደሳሳ ጎጆ የአባቱን የጎበጠ ትክሻ ለማሳረፍ ያልፍልኛል ብሎ ሀገር ሲያቋርጥ በየበርሃው ድፍት ብሎ ይቀራል፡፡ ከፎቅ ይወረወራል፡፡ ለግርድና ይጋዛል፡፡ አያቱ ቀና ብሎ እንዲሄድ የታገለለትን ሀገር አባቱ ሲረከብ ልጀቹ አንገታውን በሀፍረት ደፍተው እንዲሄዱ ሆነዋል፡፡ ስለምን ብለህ መብትህን ጠየክ ብለው ፍርድ ቤት ያቆሙሃል፡፡ እስር ቤት ይውረውሩሃል፡፡ እስር ቤቱ ያቃጥሉታል፡፡ አንተም ሞተህ በድንህ የማን እንደሆነ ለመለየት እስኪያስቸግር ድረስ በእሳት ጋይቷል፡፡

ለምን ድንበሬ ተነካ ብለህ ከአደባባይ ስትወጣ በየህንፃዎቹ ላይ አልሞ ተኳሾችን ይሰይምና ሬሳህን መንገድ ላይ ሲዘራው ይውላል፡፡ ጭካኔ ብቻ ውስጣቸው ያረገዙ ሀይሎችን ይበትንና ቤትህ ድረስ እየገቡ የት የምታውቀውን ድንበር ነው ድንበሬ ድንበሬ እያልክ እምትቃወም ሲሉ ሬሳህን ከደጃፍህ ላይ አጋድመውት ይሄዳሉ፡፡

ቆይ መንግስት ለኢትዮጲያዊ የተመነው ዋጋው ስንት ነው? ከአሜሪካዊው ከእንግሊዛዊው ከፈረንሳዊው ወይም ከሌሎች ህዝቦች አንፃር ሲወዳደር ማለቴ አይደለም ይልቁንስ ከዶሮው ከበጉ ከበሬው ከላሙ ከውሻው በቃ ከእንስሳት ዋጋ ጋር ሲነፃፀር ዋጋው ስንት ነው? በግ እኮ እንዲሁ በስለት ተወግቶ አይገደልም፡፡ ላሙ እኮ እንዲሁ ባልሞ ተኳሾች በሚዘንብበት ጥይት ህይወቱን አያጣም፡፡ ዶሮው እኮ እንዲሁ በጭካኔ ታንቆ አይገደልም፡፡ ውሻው ላይ እኮ ጦር አይዘምትበትም፡፡ መንግስት እኛን እንደዚህ ሲጨክንብን ዋጋችንን ስንት አድርጎት ይሆን?

ዜናው ሁሉ ሽብር፡፡ ብስራቱ ሁሉ እስር፡፡ አዋጁ ሁሉ ከልከላይ፡፡ ታሪኩ ሁሉ ሞት፡፡ ሹሙ ሁሉ ሌባ፡፡ ስልጣኑ ሁሉ ደም የጠማው፡፡ ምሩቅ ሁሉ ኮብልስቶን ፈላጭ፡፡ ታሪክ ሁሉ ከአክሱም ወደ ኮብል ስቶን ያዘቀዘቀ፡፡ ግንባታው ሁሉ ከላሊበላ ወደ ፍርስራሽ ኮንዶሚኒየም የዘቀጠ፡፡ ጎጆው ሁሉ የዘር ትርምስ፡፡ ስራው ሁሉ የጀበና ቡና፡፡ መቼ ነው ኢትዮጲያዊነት እንደዚህ ዋጋው ያሽቆለቆለው? መታሰቢያው ሁሉ የወመኔ፡፡ ሸንጎው ሁሉ የፍቺ፡፡ ፋብሪካው ሁሉ የጌሾ፡፡ መንገዳችን ሁሉ የውጭ ዜጋ መተላለፊያ፡፡ መቼ ነው እንደዚህ ከአዘቅቱ የወረድነው?

ነፃ አውጭው ሁሉ የተስፋ ዳቦ፡፡ ትግሉ ሁሉ የውሃ ሽታ፡፡ ህዙቡ ሁሉ ባለ ጎጥ፡፡ ቅድመ አለም ማንነቱን የአንድነቱን ቀለም ሀበሻነቱን የዘነጋ፡፡ ኢትዮጲያዊ ግን በመንግስት የተተመነለት ዋጋው ስንት ነው?

Filed in: Amharic