>

«ኩሽ ወይስ ኢትዮጵያ?» - የቆየ ጥያቄ በአዲስ ጠያቂ አንደበት [ኤፍሬም እሸቴ]

ኦፕራይድ (www.opride.com) የተባለ ድረ ገጽ በኦገስት 2017 ባቀረበው አንድ ቃለ ምልልስ በጀርመን አገር በታተተመ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ ተሳትፈዋል የተባሉ አንድ ፓስተር አቅርቧል። በንቲ ኡጁሉ ቴሶ (Rev. Benti Ujulu Tesso) የተባሉት ፓስተር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለው «ኢትዮጵያ» የሚለው ስም ቆዳቸው የጠቆሩ ሰዎች ሁሉ ስም በመሆኑና አነጋገሩና ትርጉሙም አዎንታዊ ሳይሆን አሉታዊ በመሆኑ «ኩሽ» ወደሚለው ትርጉም መመለሱን ጠቅሰዋል። ሙሉውን ቃለ ምልልስ ለማንበብ ከዚህ (ሊንክ https://goo.gl/UKkf3G ) መመልከት ይቻላል።
By Efrem Eshete Adebabayእ.አ.አ በ1976 የታተመ «ጉድ ኒውስ ባይብል» ኢትዮጵያ የሚለው ስም የዛሬዋን መልክዐ ምድራዊቷን ኢትዮጵያን ሳይሆን የዛሬዋን ሱዳንን የሚመለከት በመሆኑ ማስተካከያ ማድረግ አለብኝ በሚል መነሻ ገሚሱን ክፍል ሱዳን ብሎ ተክቶ አሳትሞ ነበር። ይህንን ጉዳይ የተረዳው ቅዱስ ሲኖዶስም ስለነገሩ ማብራሪያ በመጠየቅ ብዙ ከቆየ በኋላ ትርጉሙ ስሕተት መሆኑን ከአሳታሚዎቹ ጋር በመተማመን እና ድጋሚም በዚህ መልክ እንደማያሳትሙ በመወሰን ጉዳዩን ሊቋጭ ችሏል። ወረቀትና ምን የያዘውን አይለቅም አንደሚባለው በወቅቱ የታተሙት «ጉድ ኒውስ» ባይብሎች ግን በተገቢው መንገድ ከአንባቢያቸው እጅ (አብዛኛውም በታዳጊው ዓለም) በመግባት ሱዳን ሱዳን ሲሉ ኖረዋል።
ይህ ጉዳይ በቀላሉ መታለፍ እንደሌለበት የተረዳው ቅዱስ ሲኖዶስ ለአማንያኑ ባወጣም መግለጫ ላይ በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ በመስጠት ዋና ዋና ጥያቄዎች ላይ ምላሽ ሰጥቷል። የፓስተር በንቲ ጥያቄም የከረመ ጥያቄ በአዲስ ጠያቂ ከመጠየቁ ውጪ ጥያቄውም መልሱም የከረመ ነው።
ይሁንና የፓስተር በንቲ ጥያቄ «ኢትዮጵያ» የሚለው ቃል እና ኢትዮጵያዊነት የሚለው መለያ የጥቃት ዓላማ በሆነበት በዚህ ዘመን የነሣ ጥያቄ በመሆኑ የተለየ ትኩረት ማግኘቱ የግድ ነው። ምላሸችን ግን ያው ነው። ከዚህ ቀደም ተደጋግሞ የተባለው ነው። ዝርዝሩን ከዚህ ላይ ተመልከት ( https://goo.gl/NiEEAx )።
የጀርመን ኢቫንጄሊካል ቸርች ለምን ይህንን አደረገች? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ጥያቄ ነው። ወደ ትልቅ ሴራ ትንተና ውስጥ ሳንገባ የጀርመን ቤተ ክርስቲያን በተለይም በኦሮሞ የቆየ አክራሪ የመገንጠል እንቅስቃሴ ውስጥ በቄሶቿ አማካይነት የነበራትን ሥፍራ በቅጡ የሚተነትን ጥናት ያስፈልገናል (ኖሮም እንደኹ አላውቅም)። የኦሮሞ ምሁር ናቸው የተባሉት ፓስተር በንቲ ስለ ጥናታቸው ያብራሩበት ድርጊት በርግጥ ሳይንሳዊ ጥናት ነው ወይስ ፖለቲካዊ ትንታኔ የሚለው በቅጡ መታየት አለበት።
ለማንኛውም ስለ ኢትዮጵያዊነት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥብቅና መቆሟ የሚገባ ቢሆንም ሌላውም ኢትዮጵያዊ እና ነገሩ የሚያገባው ማንኛውም ተቋም፣ ምሁር እና የእምነት አካል ስለ ጉዳዩ የራሱን የቤት ሥራ መሥራት ይኖርበታል። በዚህ ጉዳይ ከነገረ ሃይማኖት ምሁራን (ቲዮሎጂያን) ጋር «በአደባባይ» የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት እንሞክራለን። እዝከዚያው ግን ቅዱስ ሲኖዶስ ከሁለት አሥርት በፊት ለ«ጉድ ኒውስ ባይብል» አሳታሚ የሰጠውን ምላሽ እንድታነቡ በመጋበዝ ላብቃ። (ሊንኩን ከዚህ ታገኛላችሁ – https://goo.gl/yk9uMM )
ይቆየን
ኤፍሬም
አደባባይ ድረ ገጽ Wednesday, August 30, 2017
Filed in: Amharic