>
5:13 pm - Sunday April 20, 3490

የሀገር ውስጥ ጉልቤና የዲያስፖራ ጉልቤዎች

ኢህአዴጋውያን፣ ጃዋራውያንና በግንቦት 7 ዙሪያ ያሉ

አቤነዘር  ይስሃቅ

=> የሀገር ውስጥ ጉልቤ ቴዲ አፍሮ ላይ በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ ጉልበቱን ያሳያል። የቂም በቀል ሥራውን ላለፉት 12 ዓመታት ለመወጣት አንዴ በሀሰት ክስ ሲያስረው፣ ሌላ ጊዜ ከሀገር እንዳይወጣ ጉዞውን ሲያስተጓጉል ሌላ ጊዜ የሚያዘጋጀውን ኮንሰርት ሲሰርዝ አሁን ላይ ደርሷል። የአሁንም ስራው የበፊቱ ቅጥያ ነው። የዱርዬ ቡድን ተግባር። ከዱርዬዎች የሚጠበቅ። ይሄ የአምባገነኖች ባሕሪ ስለሆነ ብዙም አያስገርምም።

=> በውጪ ያሉ የዲያስፖራ ጉልቤዎች (በዋናነት በግንቦት 7 ዙሪያ ያሉ) ደግሞ አንድን አርቲስት ከኢህአዴግ መሪዎች ዕኩል የኢትዮዽያ ሕዝብ ጠላት አድርገው የተጋበዘበት ኮንሰርት ላይ እንዳይዘፍን ያስደርጋሉ። አሁንም “ገና ምን አይተህ. . .” እያሉ አርቲስት ጎሳዬ ተስፋዬ ላይ እየዛቱ ነው። “በኢትዮዽያ ሕዝብ ሥም ይቅርታ በልን” እያሉ ነው። እነዚህም ያው በሰፈራቸው ጉልበተኛነታቸውን ምስኪኖች ላይ እያሳዩ ነው።

ሳሞራ የኑስን እና አርቲስት ጎሳዬ ተስፋዬን በአንድ ሚዛን ላይ ዕኩል አስቀምጠው እየፎከሩ ነው። “ይቅርታ ካላልክ ልክህን እናሳይሀለን” እያሉት ነው። ይሄንንም የሚያደርጉት “ለነጻነትና ለዲሞክራሲ” ሲሉ መሆኑን ሊያሳምኑህ ይሞክራሉ። አስቂኝ ነው።

=> በተመሳሳይ ሁኔታ ጃዋራውያን ከዚህ በፊት ቴዲ አፍሮ አጼ ሚኒሊክን አድንቋል በሚል በጥላቻና ቂም በቀል ተነሳስተው ከበደሌ ጋር ያዘጋጀውን ኮንሰርት ሊያቀርብ ሲል ከኦህዴድ ጋር ተባብረው ማሰረዛቸው ይታወቃል። እነዚህም ከጥላቻቸው በተጨማሪ ጉልበተኝነታቸውን ለማሳየትና ተደማጭነታቸውን ለማስፋት ሲሉ ቴዲን ኢላማ አድርገው ተንቀሳቅሰዋል። “ቴዲ አፍሮ ይቅርታ ይበለን” ሲሉም ነበር።

ጃዋራውያን ይሄንን ነገር ያደርጉት “ለኦሮሞ ሕዝብ ሲሉ” መሆኑን ሲናገሩ ነበር። አስቂኙ ነገር ኢህአዴግ አንድ ከኦሮሞ ብሔር የሆነ አርቲስትን “ለምን ይሄንን ዘፈን ዘፈንክ” ብሎ ሲያስር “ሀሳብን የመግለጽ መብት ተጣሰ” ብለው እሪሪ ለማለት የሚቀድማቸው የለም። እነሱ ግን ቴዲ አፍሮ “ለምን አጼ ሚኒሊክ አደነቀ” ብለው ለማፈን ሲሯሯጡ ነበር። ወደፊትም ተመሳሳይ ነገር ከማድርግ አይመለሱም።

ለተቃዋሚዎች በኩል ያለው ላይ ለማተኮር:- Boycott መጥራት አንድ የትግል አካል መሆኑ ይታወቃል። ግን በማን ላይ? ለምን አላማ? የሚለው ነገር በደንብ መታሰብ አለበት። የBoycott ዘመቻ ሲካሄድ የዘመቻው ዓላማና ስፋት፣ ለነጻነትና ለዲሞክራሲ ለሚደረገው ለትግል ምን ያህል አጋዥ እንደሆነ፣ ምን ያህል አምባገነኑን መንግስትና በዙሪያው ያሉትን በዝባዦች ላይ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር፣ ለሕዝብ የሚያስገኘው ጥቅም ምን እንደሆነ . . . አስቀድሞ ማሰብና በዝርዝር ማየት ያስፈልጋል።

ለዕውነተኛ ነጻነትና ለዕኩልነት ተብሎ የሚጠራ Boycott በዕልህና “ማንነቴን አሳያለው” በሚል አስተሳሰብ አይደረግም።

 

 

Filed in: Amharic