>
5:16 pm - Saturday May 23, 5170

የኢትዮጵያ መፃዒ እድል (ደርብ ተፈራ)

ቆስቁሰው ቆስቁሰው ያቃጠሉት ክምር፤
ብቻውን አይነድም ቆስቋሹን ሳይጨምር፡፡
የኢትዮጵያ መፃዒ እድል ግን እንደ ዜጋ እጅጉን ያሳስበኛል፡፡ የብሄር ፖለቲካችንም መዳረሻ አስተዳደራዊ ሲዖል ሳይሆን አይቀርም፡፡ አንድ ሰሟ የማይታወቅና የአሁኑ አገራዊ የጥላቻ ፖለቲካ አውሎ ነፋስ ያስፈራት ዘፋኝ በነጠላ ዜማዋ ቆስቁሰው……ስትል ገጠመች፡፡
.
የብሄር ብሄረሰቦችን ጥያቄ ለመመለስ ተብሎ የተነደፈው የዘውግ ፌደራሊዝም አቅጣጫውን የሳተ ይመስላል፡፡ የመንደር ፖለቲካ አራማጆችም ለእውነተኛ ነፃነት ሳይሆን ለስልጣን ጥማቸው ማርኪያ የማንነት ዜማ ማዜማቸውን ቀጥለውበታል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች አድስ የማንነት ጥያቄዎች እየቀረቡ ነው፡፡ የጎሳ ኢንተርፕረነሮች እዚህም እዛም ብቅ ብቅ ሲሉ አስተውለናል፡፡ ከ1990ዎቹ የስልጤ ማንነት ጥያቄ እስከ ቅርቡ የቅማንት ጥያቄ ብሎም በተለያዩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክፍሎች የተነሱት የማንነት ጥያቄዎችም ያላቸው አንድምታ ወደፊት ከማንነት ጋር በተያያዘ የተወሳሰበ የፖለቲካ ችግር እንደሚፈጠር ነው፡፡ በምሳሌነት የወልቃይት ጠገደን ጉዳይ ማንሳት እንችላለን፡፡ በፌደራሊዝማችን ቀመር ኢትዮጵያ ውስጥ ክልሎች የሚዋቀሩት ማንነትን፣ ቋንቋን፣ የህዝብ አሰፋፈርን እና ፈቃደኝነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ነው ካልን ለምን የተለያዩ ማህበረሰቦች ቅሬታ ያነሳሉ? የሚነሱ ቅሬታዎች ህገ-መንግስታዊነት የሌለው አሰራር እንዳለ አመላካች ይመስሉኛል፡፡ ስለዚህ ህገ-መንግስቱ መሬት ላይ ይውረድ!
በብሄረሰቦች መካከል ያለው ጥላቻ መስመር እያለፈ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የፖለቲካ ትኩሳት ብቻ ሳይሆን ደዌ ነው፡፡ ለእርስ በርስ እልቂት በር የሚከፍት የሳጥናኤል ፖለቲከኞች ድርጊት ነው፡፡
.
ብታምኑም ባታምኑም ልክ እንደ ትናንቱ ዛሬም ኢትዮጵያ ታማለች፡፡ እነሆ ቂም ያረገዘው የአገራችን ፖለቲካ ‹‹ልምድ በሌላቸው አዋላጆች›› አማካኝነት ከብዙ ድካም በኋላ በአስጨናቂ ምጥና መከራ ታጅቦ እልፍ አዕላፍ ከሃድዎችን ወልዷል፡፡ እናት ኢትዮጵያም እነዚህን ጉዶች በደከመ ጉልበቷ ተሸክማ በስተመጨረሻ በክፉኛ ህመም ተጠቅታለች፡፡ የፖለቲካ ባህላችን አጥፍቶ መጥፋትን መገለጫው ካደረገ ውሎ ማደሩንም ልብ ይሏል፡፡ ‹‹እንኳን ዘንቦብሽ እንድያውም ጤዛ ነሽ እንድሉ ግለሰቦች ለፖለቲካ ያላቸው አሉታዊ አመለካከት ብሎም ተሳትፏቸው የፖለቲካ ጫወታው በህገ ወጦች የሚመራ ሲሆን የበለጠ መሰረት ይይዛል፤ ጥላቻቸውም መወሳሰቡ አይቀርም፡፡ ስለ ፖለቲካ ካነሳን ማንም ሰው ከፖለቲካ ሸሽቶ ማምለጥ እንደማይችል ማወቅ አለብን፡፡ ሁላችንም ፖለቲከኞች ነን፡፡ እኔም፣ አንተም፣ አንቺም፣ እርስዎም ፖለቲከኞች ነን፡፡ ምሁራን እንደሚሉት ከሆነ ፖለቲካ…ማን ምን ይገባዋል እንደትና መቼ የሚል ውሳኔ ማሳለፍ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ታላቁ የግሪክ ፈላስፋ አርስቶትል እንደሚለው ሰው የፖለቲካ እንሰሳ ነው፡፡ በቀን ተቀን ህይወታችን ውስጥ ውሳኔዎችን እንወስናለን፡ ቤተሰባዊ፣ ማህበረሰብ አቀፍ ብሎም አገራዊ ውሳኔዎች ላይ ተሳታፊ ስንሆን ደግሞ የበለጠ ፖለቲከኛነታችን ያሳብቅብናል፡፡
.
በአገራችን የፖለቲካ መድረክ ብቅ ያለው ብሄርን መሰረት ያደረገ ፖለቲካ የተሳሳተ አካሄድ ጭፍን አስተሳሰብን የሚያበረታታ ነው፡፡ የሰውን ልጅ ከሌሎች እንሰሳት ለመለየት ምክንያታዊነትን በዋነኝነት እንደ መስፈርት እንጠቀማለን ነገር ግን የሰው ልጅ ከምክንያት ዓለም ለመውጣት ከታተረ ፈፅሞ ደስተኛና ትክክለኛ ህይወት መኖር አይችልም፡፡ እንደ አሳማ መብላት፣ የስሜት ፈረስ መጋለብ እንድሁም ለሌሎች አለማሰብ ሰውን ከእንሰሳት ጋር የሚያመሳስሉት እንጅ ከእንሰሳት ማህበር ወይም መንጋ የሚነጥሉት አይደሉም፡፡ ስሜትና ሆድማ እንሰሳትም አላቸው፡፡ ምክንያታዊነት ግን ለሰዎች ብቻ የተሰጠ ፀጋ ነው፡፡ የአገራችን የፖለቲካ ሰማይ ላይ የስሜት አውሎ ንፋስ በርትቷል፤ ብዙዎችን እየመታም ነው፡፡ ከነፋሱ ማንም አያመልጥም፡፡ ለጊዜው መጠለያ አግኝተን ከንፋሱ ራሳችንን ታድገን ቢሆንም ሩቅ መንገድ ግን አንጓዝም፡፡
.
ኢትዮጵያ ውስጥ የታሪክ ምሁራን እውነትን ሳይሆን በግል አመለካከትና ፍላጎት የታሸ ታሪክ ነው የሚያቀርቡልን፡፡በእንቅርት ላይ ጆሮ ገድፍ የሆኑብን ደግሞ ታሪክን እየቆራረሱ ለራሳቸው ጥቅም የሚያዉሉ የፖለቲካ ልሂቃን ናቸው፡፡ የዛሬ መሰረት የተጣለው ትናንት እንደመሆኑ መጠን ነገም በዛሬ ተፅዕኖ ስር ናት፡፡ ስለዚህ ትናንት የሆነውን እንጅ እንድሆን የፈለጉትን ለምን ይደሰኩራሉ? ለምንስ ታሪክ ይዘርፋሉ? መልሱን ለማዎቅ ብዙ መሄድ አያስፈልግም፤ ታሪክ የሚቆራርሱት የፖለቲካ ትርፍ ስላለው እንጅ ከቶ ከዚህ ሌላ ምን ምክንያት ሊኖራቸው? ለምሳሌ ዘጠና ዘጠኝ በመቶ መልካም ገፅታ ያለው ታሪክ አንድ ፕርሰንት መጥፎ ክስተት ስላለው ብቻ ታሪኩ መቆሸሽ የለበትም፡፡ በጠርሙስ ሙሉ ወይን ላይ አንድ ጠብታ መርዝ ሲጨመር ምን እንደሚሆን ይታወቃል፡፡ ወደ ታሪክ ስንመጣ ግን ይህ ነገር ሊሆን አይገባም፡፡ ኢትዮጵያ የምትባለው አገር ከተመሰረተችበት ሽዎችም ይሁን መቶዎቹ ዓመታት ጀምሮ ብዙ መጥፎና በጎ የታሪክ ገድሎች ተፈፅመዋል፡፡ ይህ አንዱ የታሪካችን ገፅታ ነው፡፡
.
የሌሎች አገራትን ተሞክሮ ብንዳስስ የምናገኘውም እውነታ በአገራት የግንባታ ወይም የምስረታ ሂደት የሚደስት ብሎም የሚከፋ ወገን እንደሚኖር ነው፡፡ ሐያላን የአለም አገራት፡- እነ አሜሪካ ብሎም ሌሎች የአውሮፓ አገራት ጀርመንን ጨምሮ የተመሰረቱት እኮ በደም እና በጠብ-መንጃ (ብረት) ነው፡፡ በአገራት የግንባታ ሂደት ውስጥ ብዙ ውጣ ውረዶች ግፍና በደሎች መኖራቸው ዓለም አቀፍ እውነታና ልምድ ነው፡፡
.
እናንተ መጤ ናችሁ ከዚህ ውጡ ብሎም እነ እከሌ ድሮ እንድህ አድርገውናልና ታሪካዊ ጠላቶችችን ናቸው በማለት እርስበርስ መናቆር አገርን ያፈርሳል እንጅ የተሻለች ኢትዮጵያን አይፈጥርም፡፡ ጥላቻዉ ‹‹ሁሉ በሁሉ›› ላይ ተነስቶ እንድንተላለቅ እንዳያደርገን ያሰጋል ፡፡ ይህን እኩይ ተግባር አስቀድመን ለመከላከል ዝግጁ መሆን አለብን፡፡
Filed in: Amharic