>

የሕዝበ ውሳኔው ሕጋዊ ውጤት፤ ምርጫ ቦርድ ሳይኖር ምርጫ አለን? (ውብሸት ሙላት)

የሕዝበ ውሳኔው ሕጋዊ ውጤት፤
የቅማንት ሕዝበ ውሳኔ አስገዳጅ ነው?
ምርጫ ቦርድ ሳይኖር ምርጫ አለን?
(በውብሸት ሙላት)

የቅማንት ማኅበረሰብ ራሳቸውን በራሳቸው ለሚያስተዳድሩበት የአስተዳደር እርከን ምሥረታ ጋር በተያያዘ የአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ዞን የሚገኙ 12 ቀበሌዎች ላይ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሔድ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ኃላፊነቱን አስተላልፏል፡፡ ምክር ቤቱም በእነዚህ ቀበሌዎች ላይ ሕዝበ ውሳኔ እንዲያካሂድ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትእዛዝ አስተላልፏል፡፡

ቦርዱም ሕዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ የጊዜ ሰሌዳ በማዘጋጀት ለሕዝብ ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህም መሠረት የሕዝበ ውሳኔ አስፈጻሚዎች ሥልጠና ይሰጣል፡፡ የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ ይደረጋል፡፡ ስለ ድምጽ አሰጣጡ ለሕዝብ ገለጻ ይደረጋል፡፡ ድምጽ የሚሠጡ ሰዎች ምዝገባ ይደረጋል፡፡ መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ሕዝበ ውሳው ይከናወንና በማግስቱ ውጤት ይፋ ይደረጋል፡፡ መስከረም 15 ቀን ለፌደሬሽን ምክር ቤት ውጤቱ ይተላለፋል፡፡

ከላይ የተገለጸውን ሒደት ተከትሎ የተከናወኑ በርካታ ሕዝበ ውሳኔዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ተከናውነዋል፡፡ በተለይም ኦሮሚያ እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው እንዲሁም ኦሮሚያና ደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች መካከል በተለያዩ ወቅቶች ተከስተው የነበሩ ግጭቶችን ለመፍታት ሕዝበ ውሳኔ ተደርጓል፡፡

በሰሜን ጎንደር ዞን በአስራ ሁለት ቀበሌዎች የሚከናወነው ግን ከዚህ በፊት ከተደረጉት በሁለት ሁኔታዎች ይለያል፡፡ የመጀመሪያው ሕዝበ ውሳኔው በአንድ ክልል ውስጥ የሚገኙ አስተዳደር ወሰኖችን ለመለየት የተዘጋጀ በመሆኑ ነው፡፡ እስከ ዛሬ የተከናወኑት በሁለት ክልሎች መካከል የተከናወኑ ናቸው፡፡ሌላው ልዩ ሚያደርገው ደግሞ እንደ አዲስ የሚመሠረትን የአስተዳደር ክልል ለመወሰን ሲባል የሚደረግ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ቀበሌን፣ወረዳን ወይም ዞን እንደ አዲስ ለማዋቀር በአካባቢው የሚኖረውን ማኅበረሰብ ፍላጎት ለማወቅ ሲባል ውዝበ ውሳኔ ማድረግ አልተለመደም፡፡

እንግዲህ በ1999ኙ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ላይ የቅማንት ማኅበረሰብ እንደ ራሱን ችሎ ባለመቆጠሩ እና ሌሎች ተጨማሪ ገፋፊ ምክንያቶች የማንነት ይታወቅልኝ ጥያቄ ተነስቶ በ2007 ዓ.ም. የአማራ ክልል ምክር ቤት ‘ማንነቴ ይታወቅልኝ’ ያለውን ማኅበረሰብ ሕዝበ ውሳኔ ሳያደርግ በራሱ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ የስልጤ ብሔረሰብ ማንነቱ ከታወቀበት ሒደት አንጻር ይህ ዓይነቱ አካሄድ በጣም ‘ሊበራል’ የሚባል ነው፡፡

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አንድ ማኅበረሰብ በብሔርነት፣ብሔረሰብነት ወይንም ሕዝብነት ዕውቅና የሚያገኘው ተያያዥነት ባላው በአንድ አካባቢ ሠፍሮ ሲገኝ ነው፡፡ በአንድ አካባቢ ሠፍሮ መገኘቱ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር እና የቡድን መብቶቹን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲችል ያግዘዋል፡፡ የቅማንት ማኅበረሰብም ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት የአስተዳደር እርከን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት እነዚህ አስራ ሁለት ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩትን ሕዝቦች ወደየትኛው አስተዳደር መካለል ይፈልጉ እንደሆን ለማወቅ ሲባል ይመስላ የአማራ ክልል ሕዝበ ውዝበ ውሳኔውን የፈለገው፡፡

በአገራችን በተለይም የአስተዳደር ድንበሮችን ለመለየት እና ነዋሪዎች ወደየትኛው አስተዳደር መካለል እንደሚፈልጉ ለማወቅ ሲባል በርካታ ሕዝበ ውሳኔዎች መደረጋቸው ይታወቃል፡፡ ከዚያም ሕዝበ ውሳኔ የተደረገበት አካባቢ አብዝኃኛው ሰው ወደሚፈልገው አስተዳደር ይጠቃለላል፡፡ ይህ እንግዲህ በሕዝቦች መካከል ሊፈጠር የሚችልን ግጭት ለማስወገድ ሲባል የሚተገበር ሕገ መንግሥታዊ መፍትሔ መሆኑ ነው፡፡

ይሁን እንጂ እስካሁን በዚህ መንገድ ሕዝበ ውሳኔ የተደረገባቸው አካባቢዎች የታሰበውን ውጤት እያስገኙ አይደለም፡፡ ለዚህ ዋና ማሳያው ደግሞ በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መካከል ተደርገው የነበሩትን ሕዝበ ውሳዎች ባለማክበር በየጊዜው የተፈጠሩት ግጭቶች ናቸው፡፡ በዚሁ 2009 ዓ.ም. ብቻ እንኳን በሁለቱ ክልሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ በመሆኑም የሕዝበ ውሳኔ ጉዳይ ተገቢ ፍተሻ ያስፈልገዋልና የዚች ጽሁፍም ማጠንጠኛ ይኼው ነው፡፡
በኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 መሠረት ምርጫ ለአምስት ዓቢይ ዓለማዎች ሊከናወን ይችላል፡፡ እነዚህ የፌደራልና የክልል የሕዝብ ተወካዮችን ለመምረጥ ሲባል ‘ጠቅላላ ምርጫ’ ይደረጋል፡፡ ሌላው፣ የቀበሌ፣የወረዳ እና እንደሁኔታው የዞን ተወካዮችን ለመምረጥ የሚደረጉ ‘የአካባቢ ምርጫ’ በመባል የሚታወቀው ነው፡፡

ሦስተኛው ደግሞ፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተጓደሉ የምክር ቤት አባላትን ለመተካት ወይንም ቀድሞ ሕዝቡ የመረጠውን ወኪል ካወረደው በኋላ በምትኩ የሚመረጥበት ‘የማሟያ ምርጫ’ ለማከናወን ምርጫ ይደረጋል፡፡
አራተኛው፣የምርጫ ቦርድ በተለያዩ ምክንያቶች አንድ የምርጫ ጣቢያ ላይ ችግር ተከስቷል ባለ ጊዜ የሚደረግ ‘የድጋሜ ምርጫ’ ነው፡፡

የመጨረሻው የሕዝብን ፍላጎት ለመለካት እና የሕዝብን ውሳኔ ለማወቅ ሲባል የሚደረገው እና ‘ሕዝበ ውሳኔ’ በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ትኩረትም የመጨረሻው ነው፡፡
ከምርጫ ሕጉ እንደምንረዳው የሕዝበ ውሳኔ የመጨረሻ ግብ ‘የሕዝቡን ፍላጎት መለካት’ እና ‘ውሳኔውን ማወቅ’ ነው፡፡ የምርጫ ሕጉ በምን በምን ጉዳይ ላይ የሕዝብን ፍላጎት መለካት ያስፈልጋል? በምን ጉዳይስ ላይ በተወሰነ አካባቢ የሚኖርም ይሁን በአጠቃላይ የአገሪቱ ሕዝብ ውሳኔ ይሰጣል? ለሚለው መልስ አይሰጥም፡፡

በሕገ መንግሥቱ መሠረት የሕዝብን ፍላጎት ለመለካት እና የሕዝብን ውሳኔ ለማወቅ ሲባል እንደሚደረግ በመግለጽ ያልፈዋል፡፡ አዋጁ፣ ትርጓሜ በሰጠበት በአንቀጽ 2 እና በድጋሜም አንቀጽ 32(1) ሁለት ጊዜ ይሄንን ሐሳብ በተመሳሳይ አጻጻፍ አስቀምጦታል፡፡ ይሁን እንጂ፣አንቀጽ 32(2) ላይ እንደ አንድ ፍንጭ የተቀመጠው የሕዝብን ፍላጎት መለካት ወይንም ውሳኔውን ማወቅ የሚፈልግ አካል ሲኖር የሚከናወን መሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት አንድ አካል ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ሲጠይቅ የሚፈጸም እንጂ በአዋጁ ላይ በዝርዝር በምን በምን ጉዳይ ላይ እንደሚደረግ አስቀድሞ አልተወሰነም፡፡

ቀጣዩ ጥያቄ የሚሆነው ሕገ መንግሥቱ በምን በምን ሁኔታዎች ላይ ሕዝበ ውሳኔ እንዲጠራ ይጠይቃል? የሚለውን መለየት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 8 ላይ የሕዝብ ሉዓላዊነት ስለሚገለጽበት ሁኔታ ሲደነግግ ብሔሮች፣ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በወኪሎቻቸው ወይንም በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት እንደሚገለጽ ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም፣ ሕዝብ በቀጥታ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከሚወስንባቸው መንገዶች አንዱ ሕዝበ ውሳኔ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ሕዝበ ውሳኔ ሊደረግባቸው የሚችሉ ሁለት አጋጣሚዎች ሕገ መንግሥቱ ላይ አሉ፡፡ በአንቀጽ 39 መሠረት ከአገሪቱ ለመገንጠ እና አንቀጽ 47 ላይ በተገለጸው አዲስ ክልል በሚመሠረትበት ጊዜ ናቸው፡፡ ኋላ የስልጤ የማንነት ጉዳይን በሚመለከት የፌደሬሽን ምክር ቤት በሰጠው ውሳኔ ላይ ደግሞ ማንነቴ ይታወቅልኝ የሚል ማኅበረሰብም ሲኖርም ሕዝበ ውሳኔ ሊደረግ እንደሚችል መረዳት ይቻላል፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ ደግሞ ከአንቀጽ 48 ላይ መገንዘብ እንደሚቻለው የድንበር አከላለል ለውጥ በሚኖርበት ጊዜ የፌደሬሽን ምክር ቤት የሕዝቡን ፍላጎት እና አሠፋፈር መሠረት በማደረግ ውሳኔ ለማሳለፍ ሕዝበ ውሳኔ ሊያደርግ እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ ለነገሩ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤትን ለማጠናከርና ሥልጣን እና ኃላፊነቱን ለመዘርዘር የወጣው አዋጅ ላይ ሰፋ ባለ ሁኔታ ተገልጿል፡፡

እነዚህ በሕገ መንግሥቱ እና በፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ላይ የተገለጹት ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ፣ከእነዚህ ውጭ ሕዝበ ውሳኔ ማድረግን የሚገድብ ሕግ እስከሌለ ድረስ በሌሎች ጉዳዮችም ላይ ቢደረጉ ከሕግ ጋር ጠብ አይኖረውም፡፡

በአማራ ክልል የሚከናወነውም ሕዝበ ውሳኔም ከላይ ከተገለጹት ከየትኛውም ውጭ ቢሆንም እንኳን ዞሮ ዞሮ የአስራ ሁለቱ ቀበሌ ኗሪዎች ወደ የትኛው አስተዳደር ውስጥ መተዳደርን እንደሚፈልጉ ለማወቅ የሚደረግ ጥረት ነው ማለት ይቻላል፡፡

ቀደም ብሎ እንደተገለጸው የሕዝብን ፍላጎት ለማወቅ እና ሕዝብ እንዲወስን ሲባል ሕዝበ ውሳኔ ይደረጋል፡፡ ይህ አገላለጽ አንድ አይቀሬ ጥያቄን መልስ ለመስጠት ይረዳል፡፡ ጥያቄውም፣በሕዝበ ውሳኔ የታወቀ ፍላጎት እና/የሕዝብ ውሳኔ ከሕግ አንጻር አስገዳጅ ነውን? የሚለው ነው፡፡ መልሱን ለማግኘት ሁለት አቅጣጫ እንከተል፡፡

የመጀመሪያው በሕገ መንግሥቱ የሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግባቸው የተቆረጡትን ጉዳዮች ይመለከታል፡፡ በእነዚህ ላይ የሚሰጠው የሕዝብ ውሳኔ አስገዳጅ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፣አንድ መንግሥታዊ ተቋም (ክልል/ምክር ቤት ወዘተ) የሕዝብን ፍላጎት ማወቅ በመፈለጉ የሚደረግ ከሆነ አስገዳጅነት ላይኖረው ይችላል፡፡ በአማራ ክልል የሚከናወነው ሕዝበ ውሳኔም ከሁለተኛው ምድብ ውስጥ የሚካተት ነው ማለት ይችላል፡፡ ዝርዝሩን ወደ ኋላ እንመለስበታለን፡፡

በእኛ አገር የተከናወኑት ሕዝበ ውሳኔዎች የታለመላቸውን ግብ እያሳኩ አይደለም ብለናል፡፡ ሕዝቡ ከወሰነም በኋላ መልሶ ግጭት ሲከሰት እየተስተዋለ ነው፡፡ ለእዚህ ደግሞ በአጠቃላይ የሕዝበ ውሳኔ አደራረግ ሥርዓቱ እና ሕጉ ጋር የሚያያዙ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህን መቅረፍ እስካልተቻለ ድረስ በትክክል እንዲፈቱ የታሰቡበትን ግብ ላያሳኩ ይችላሉ፡፡ ችግሮቹን ተራ በተራ እንመልከታቸው፡፡

የሕዝበ ውሳኔ ሲደረግ ብዙ ጊዜ ለሕዝቡ ሁለት አማራጮች ይቀርባሉ፡፡ ለምርጫ አመች በሆነ መልኩ ቀድመው ይቀረጻሉ፡፡ ለሕዝብም ይተዋወቃሉ፡፡ በተለይ ምርጫዎቹ ወደ አንድ ወገን እንዳያደሉም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ለምሳሌ ኤርትራ ተደረገ እንደተባለው እና የተባለውም እውነት ነው እንበልና “ነጻነት” ወይስ “ባርነት” በሚል መንገድ ምርጫ አይቀርብም፡፡ መቼም ማንም ጤነኛ ሰው “ባርነትን” ሊመርጥ ስለማይችል፡፡ ከዚህ አንጻር አማራጮቹ ለምን እንደተመረጡ የሚያሳይ ማብራሪያም ጭምር ውሳኔ ከመሰጠቱ ቢያንስ ከሳምንታት ወይም ከወራት በፊት ቀደም ብሎ ሕዝብ እንዲያውቃቸው ማድረግን ሕጋዊ ግዴታ አድርገውታል፡፡ በኢትዮጵያ የሚደረጉ ሕዝበ ውሳኔዎች አማራጮቹ ምን መምሰል እንዳለባቸውም ሆነ ከምን ያህል ጊዜ በፊት ለሕዝብ መድረስ እንዳባቸው የሚገልጽ ሕግ የለም፡፡

ሁለተኛው ችግር የሚያያዘው እንደሌሎች ምርጫዎች በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን አማካይነት ሕዝበ ውሳኔው ለሚመለከታቸው ትምህርት አለመሥጠት እና ክርክሮችን አለማድረግ ነው፡፡ ለሕዝበ ውሳኔ የቀረቡትን አማራጮች የሚደግፉና የሚቃወሙ ከእነ ምክንያታቸው ለመራጩ ማስረዳትና የምርጫ ዘመቻም ሳይቀር መደረግ አለበት፡፡

በአማራ ክልል የሚደረገው ሕዝበ ውሳውም አማራጮቹን አስቀድሞ በማሳወቅ የምርጫዎቹን ጥቅምና ጉዳት ማስረዳት መራጩ ውሳኔውን በጥልቅ እንዲያጤነው ይረዳዋል፡፡ በውሳኔያቸውም ውለው ሲያድሩ መጸጸት እንዳይኖርም ይረዳል፡፡ በውሳኔ መጸጸት ከእንደገና ተመልሶ ግጭት እየፈጠረ መሆኑን ማስተዋል አይገድም፡፡ ይህን ለማሳካት ደግሞ ሕዝበ ውሳኔዎች ከመከናወናቸው በፊት ሕዝቡ የሚወስነው ነገር የሚኖረውን ጥቅምና ጉዳት አስቀድሞ እንዲያጤኑት ማድረግ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም፡፡

በሰሜን ጎንደሩም ጉዳይ ቢሆን በእነዚህ ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖረው ሕዝብ ይህንኑ የሚረዳበት መድረክ ቢዘጋጅላቸው በቀበሌዎቹ የሚኖረው መራጭ ከአማራው ሕዝብ ጋር አብሮ መኖርም ሆነ ሌላ መመሥረት የሚኖረውን ጥቅምና ጉዳት አስቀድመው እንዲያውቁት ማድረግ ተገቢነት አለው፡፡

በእነዚህ ቀበሌዎች የሚከናወነው ሕዝበ ውሳኔ ግቡ የቅማንት ማኅበረሰብ ማንነቱ ከታወቀ እንደቡድን ማንኛውንም አስተዳደራዊ እርከን የመመሥረት መብት ስላለው ነው፡፡ እነዚህ የአስተዳደር እርከኖች እንዴት እንደሚመሠረቱ ከደቡብ ብሔሮች ብሔሰቦችና ሕዝቦች ውጭ ያሉት ክልሎች፣ በውስጣቸው የሚገኙት ነባር ብሔረሰቦች ቁጥራቸው ዝቅተኛ ስለሆነ፣ ወይ መሥርተዋል፤ አሊያም ትተዋቸዋል፡፡ መመሥረት ቢፈልጉ ደግሞ እንዴት ጥያቄያቸውን እንደሚያቀርቡ፣ ለማን እንደሚያቀርቡ፣ ምን ምን ሁኔታዎችን ማሟልት እንዳለባቸው ወዘተ የሚያሳይ ሕግ የላቸውም፡፡

የደቡብ ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት ስላለው፣ የዞንም ይሁን የወረዳ አመሠራረት ጥያቄ እንዴት መስተናገድ እንዳለበት፣ ይህንን ምክር ቤት ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባሩን ለመወሰን በወጣው አዋጅ ላይ ተገልጿል፡፡ ሥነ ሥርዓቱ ከክልል ምስረታ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ልዩነቱ ጥያቄውን ያቀረበው በአስተዳደራዊ መዋቅር ተደግፎ ከሆነ (ለምሳሌ ልዩ ወረዳ የነበረው ልዩ ዞን መሆን ቢፈልግና ጥያቄው የቀረበው የወረዳው መስተዳደር ቢሆን) የመስተዳድሩ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ከደገፈው ወይንም ጥያቄውን ያቀረበው፤ ሕዝቡ ከሆነ (5% የሚሆነው ስምና ፊርማ አስፍሮ) ሕዝቡ በአብላጫ ድምፅ ሲደግፈው እና የክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤት ሲወስን ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

ከላይ የቀረበውን እንደመነሻ በመውሰድ በአማራ ክልል እንዴት ሊሆን እንደሚችል እንመልከት፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ቁምነገር ቢኖር በብሔሩ ስም የተጠራ ክልል (ትግራይ፣አፋር፣ኦሮሚያ፣የኢትዮጵያ ሶማሌ) ሆኖ የዚህን ክልል ያህል የብሔረሰብ ዞኖች እና ልዩ ወረዳ የሌለ መሆኑን ነው፡፡ ሦስት ልዩ ዞን እና አንድ ልዩ ወረዳ መኖሩን ያጤኗል፡፡

የሆነው ሆኖ፣ ከክልል በታች የሚገኙ የአስተዳደር እርከኖችን የማቋቋም ሥልጣን የክልሎች እንጂ የፌደራል አለመሆኑን የፌደሬሽን ምክር ቤትም ሥልጣን እንደሌለው በቅርቡ በአፋር ክልል በአብኣለ ወረዳ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችን አስመለክቶ በሠጠው ውሳኔ ላይ ተገልጿል፡፡ ስለሆነም፣ የሕዝበ ውሳኔውን ውጤት መሠረት አድርጎ ማለትም ከፌደሬሽን ምክር ቤት ተቀብሎ ለሚሠጠው ውሳኔ በግብዓትነት ይጠቀምበታል ማለት ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በእነዚህ ቀበሌዎች የሚኖረው ሕዝብ የሚሠጠውን ውሳኔ መሠረት በማድረግ እና ሌሎችም ሁኔታዎች ከግምት በማስገባት የመወሰን ሥልጣን አለው፡፡ ውጤቱን ለውሳኔ መነሻ እንጂ አስገዳጅነት ላይኖረው ይችላል ብሎ መከራከርም ይቻላል ማለት ነው፡፡

ሌላው በውሳኔው መሠረት ለብቻቸው ተለይተው ራሳቸውን ማስተዳደር የሚጀምሩት ብሔረሰቦች ቀድሞ ከነበሩበት ዞን ወይንም ወረዳ ፍትሐዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል ሊያደርጉ እንደሚችሉ አስቀምጧል፡፡ ክልል ሲመሠርቱ ያልተቀመጠውን፣ በደቡብ ክልል ውስጥ ዞንና ወረዳ (ልዩም ይሁን አይሁን) ሲመሠርቱ የንብረት ክፍፍል እንዲደረግ ያስቀምጥና ስለተግባራዊነቱም የብሔረሰቦች ምክር ቤት እንደሚከታተል ገልጿል፡፡ ይህ እንግዲህ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሕግ አልወጣለትም፡፡

በእርግጥ የፌደሬሽን ምክር ቤት የአስተዳደር እርከኖችን የመመሥረት ሙሉ በሙሉ የክልል ሥልጣን ነው ይበል እንጂ፤ የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 89(1)፣ መንግሥት በዴሞክራሲያዊ መርሆች ላይ በመመሥረት ሕዝቡ በሁሉም ደረጃዎች ራሱን በራሱ የሚያስተዳደርበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያለበትን ስለመሆኑ ተቀምጧል፡፡

ከዚህ አንጻር ማንኛውም የብሔርነት፣ የብሔረሰብነት ወይንም ደግሞ የሕዝብነት ዕውቅና ያገኘ ማኅበረሰብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን ተግባራዊ የሚያደርግበትን አስተዳደራዊ መዋቅር የመመሥረት ገደብ የሌለው ሕገ-መንግሥታዊ መብት እንዳለው የፌደራሉም የክልሎችም ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 (3) ላይም ጭምር ተደንግጓል፡፡

ራስን የማስተዳደር ሙሉ መብት ከክልልም ወደታች የሚወርድ ከሆነ ይህ መብት ውጤታማ እንዲሆን ያልተማከለ አስተዳደር ተግባራዊ መሆን አለበት፡፡ ለቅማንት ማኅበረሰብም ራሱን በራሱ ማስተዳደር የሚችልበት ወረዳ ወይንም ዞን ሲመሠርት በአስተዳደር እርከኑ ውስጥ ተግባራዊ የሚሆኑ እና በክልሉ ሕገ መንግሥት መሠረት የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው የመጨረስ፣ በተወሰኑ መልኩ የሥልጣን ባልተቤት ለመሆን ያስችላቸዋል፡፡

ይህ አስተዳደራዊ ራስ ገዝነት በፌደራሉ በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 50(4) ከተገለጸው አንጻር ሙሉ በሙሉ የክልል ጉዳይ እንጂ የፌደራል አይደለም ማለት ይህንን ድንጋጌ ሥራ ላይ ለማዋል የፌደራሉ መንግሥት ምንም ሚና የለውም እንደማለት ነው፡፡

ጠቅላል ሲደረግ ወረዳዎች እንዴት እንደሚመሠረቱና እንደሚታጠፉ፣ ድንበራቸው እንደሚካለልና እንደሚደካ በየትኞችም የክልል ሕገ መንግሥት አለመገለጹ፤ መሥፈርቶቹን አንዳንድ ክልሎች በአዋጅ (ለምሳሌ ደቡብና ኦሮሚያ) ሌሎቹ ደግሞ ለአስፈጻሚው አካል መተው (ለምሳሌ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና አማራ) ጉራማይሌ በመሆኑ በአንድ ወቅት ልዩ ወረዳ የነበረን፣ በሌላ ጊዜ መደበኛ ወረዳ ሲከፋም በማጠፍ ከሌላ ጋር መቀላቀል ሊከተል ይችላል፡፡ከዚህ አኳያ የአማራ ክልል የአጠፋቸው ልዩ ወረዳ ወይንም ዞን ባይኖርም ደቡብ ክልል ላይ ግን ተከስቶ ነበር፡፡

የቅማንት ማኅበረሰብንም በተመለከተ በልዩ ወይንም ወደበኛ ዞን፣በልዩ ወረዳ ወይንም በመደበኛ ወረዳ ደረጃ ማቋቋም ሙሉ በሙሉ የክልሉ እንጂ የፌደሬሽን ምክር ቤት እንደማይሆን ቀድሞ በአብአላ ወረዳ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች የልዩ ወረዳ ጥያቄን ውድቅ ባደረገበት ውሳኔ ላይ እንደተቀመጠ አይተናል፡፡

የሕዝበ ውሳኔው የታሰበለትን ግብ እንዲያሳካ፣ለአያሌ ዘመናት አብረው እና ተዋህደው በኖሩት በአማራ እና በቅማንት ሕዝቦች መካከል ያለው አብሮነት ስሜት እንዲጎለብት ከላይ የተጠቆሙትን አንከኖች ማስተካከል አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብን ለመገንባት ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ በተለይ ሕዝበ ውሳኔው የሚደረገው በአጭር ጊዜ ውስጥ፣አርሶ አደሩም በከፍተኛ ሁኔታ በግብርና ሥራ የሚጠመድበት ወቅት መሆኑ እንዲሁም የፌደሬሽን ምክር ቤት በሥራ ላይ ሳይሆን ብዙዎቹ የምርጫ ቦርድ አባላትም የሹመት ጊዜያቸው ባለፈበት ሁኔታ ሕዝበ ውሳኔ መደረጉ አሁንም ሕገ መንግሥታዊ መፍትሔነቱን ውጤታማ እንዳይሆን ሳንካ ሊሆንበት ይችላል፡፡

Filed in: Amharic