>
4:53 pm - Wednesday May 25, 8472

ራዕይ ኢትዮጵያ 2020 (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም)

 

ከተለያየ የትምህርትና የሥራ መስክ የመጡ ቢሆንም ከዚህ በፊት የተናገሩት ሁሉ በአንድ ነገር ላይ ይስማማሉ፡- አሁን በተያዘው መንገድ መቀጠል አንችልም፤ የያዝነው መንገድ ወደ ‹‹ክፉ ዕድል›› ወደ‹‹መዓት›› ወደ‹‹ውድቀት›› የሚያመራ መሆኑ ተገልጾአል፤ ለእኔ የአዘቅቱ መንገድ የሚታየኝ እንደሚከተለው ነው፤ በሸምበቆ አጥር የተለያዩና የሚተራመሱ ጎሣዎችን ጭኖ የሚከንፍ ባቡር ይታየኛል፤ ነጂው መትረየሱን ይዞ ፊቱን አዙሮ የተቀመጠው ወደሚነዳበት አቅጣጫ ሳይሆን ወደተሳፋሪዎቹ ነው፤ ተሳፋራዎቹ የሚያዩት ወደፊት ነው፤ ነጂው የሚያየው ወደኋላ ነው፤ ስለዚህም ነጂው ገደሉን ስለማያይ ይበልጥ የሚያስፈራው የተሳፋሪዎቹ ትርምስ ነው፤ ተሳፋሪዎቹን የሚያስፈራቸው የሚታያቸው መትረየስና ገደል ነው፤ በባሩ ላይ ያሉ ተሳፋሪዎች ሁሉ በባቡሩ ፍጥነት ላይም ሆነ አቅጣጫው ላይ ምንም ዓይነት ቁጥጥር የላቸውም፤ የባቡሩ ነጂ ተሳፋሪዎቹ የሚያዩትን አያይም፤ እንዲነግሩትም አይፈልግም፤ የነጂውና የተሳፋሪዎቹ አስተሳሰብ ለየቅል ነው፤ አይነጋገሩም፤ ተሳፋሪዎች በዝምታ ነጂውም ባለማወቅ ወደማያየው ገደል ውስጥ ለመግባት ቆርጠዋል፤ ባቡሩን አቁም ብለው ቢጮሁ መልሱ መትረየስ መሆኑን ያውቃሉ፤ በዝምታ አብሮ ገደል መግባት ነው፤ በዚህ አጣብቂኝና የፍርሃት ቆፈን ተይዘናል፤ ከተረዳንለት ነጂውም አጣብቂኝና የፍርሃት ቆፈን ውስጥ ነው፤ ነጂውና ተሳፋሪዎች ካልተነጋገሩ ባቡሩም፤ ተሳፋሪዎችም፤ ነጂውም ከገደሉ ማምለጥ አይችሉም።

እንግዲህ መሣሪያ የያዘውም ይፈራል፤ መሣሪያ ያልያዘውም ይፈራል ማለት ነው፤ የሁለቱም ጠላት አለመተማመንና መሣሪያው ነው፤ አለመተማመንን ሳናጠፋ መሣሪያውን ማጥፋት አንችልም፤ ሳንነጋገር አለመተማመንን ማጥፋት አንችልም፤ ልባችን ከቂምና ከበቀል ካልፀዳ ተነጋግረን መግባባት አንችልም፤ ባቡሩ እውር ድንብሩን እየሄደ ገደል የሚገባው ለዚህ ነው።

Filed in: Amharic