>
10:04 pm - Wednesday February 1, 2023

የግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ አመጣጥ፤ (በውብሸት ሙላት)

ግሼን ደብረ ከርቤ እንዴት እና መቼ እንደደረሰ፤
የዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን የማይሽረው ሚና፤ 

የዚህ ጽሑፍ ምንጭ ‘’መጽሐፈ ጤፉት’’ ስለሆነች በቅድሚያ ስለመጽሐፏ ጥቂት ነጥቦችን ማንሳቱ ተገቢ ነው፡፡ ግሼን ደብረ ከርቤ ማርያም፣ለመስከረም 21 ንግሥ የሄደ ሰው ስለዚች መጽሐፍ ላይሰማ አይችልም፡፡ በዕለቱ በአደባባይ ስትነበብ፣ስትተረክ፣ስትተረጎም ትውላለች፤በደብሩ ሊቃውንት፡፡ እኛም ስለዚች መጽሐፍ ከልጅነታችን ጀምረን ስትጠራ የሰማነውና የማናውቀው በአንስታይ ጾታ ስለሆነ የተለመደው አጠራር መጠቀም ተመርጧል፡፡

የመጽሐፈ ጤፉት ስያሜ የመነጨው ከጽሑፉ ደቃቅነት ነው፡፡ ፊደላቱ እንደጤፍ ቅንጣት ቢያንሱ፣ድቅቅ ቢሉ “መጽሐፈ ጤፉት” ተባለች፡፡ የመጽሐፏ ይዘት ወይም መጠን ግን ትንሽ አይደለም፡፡ሙሉው የብራና መጽሐፍ ዳጎስ ያለ ነው፡፡

መጽሐፈ ጤፉት በአንድ ጊዜ፣አልተጻፈችም፡፡ ይሁን እንጂ ብዙው ክፍሏ በአንዴ የተጻፈ ይመስላል፡፡ የመጽሐፈ ጤፉት ደራሲም ታላቁ ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ መሆኑን ለማወቅ ብዙ አዳጋች አይደለም፡፡ የተጻፈበትን ሁኔታም፣የደራሲውንም ማንነት በተመለከተ መጽሐፉን ያነበበ ማንም ሰው ይሄንን በቀላሉ ይረዳዋል፡፡

ለዚህ ጽሑፍ በምንጭነት ያገለገለው በመሪጌታ የማነ ብርሃን ተተርጉሞ፣በግሼን ደብረ ከርቤ ደብር ሰባካ ጉባኤ አማካይነት በ2006 ዓ.ም. የታተመው ነው፡፡ መጽሐፏ የተወሰኑ ቦታዎች የምትሸጥ ቢሆንም በሶፍት ኮፒም ትገኛለች፡፡

በመጽሐፈ ጤፉት ላይ፣ መስቀሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተሰቀለበት በኋላ ጠፍቶ እንዴት፣የት እና መቼ እንደተገኘ ተገኘ ተገልጿል፡፡ ወደ ግብጽ መቼና እንዴት እንደተወሰደም ተተርኳል፡፡ ከግብጽ እንዴት ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ፣ ግሼን ደብረ ከርቤ እንዴት እንደደረሰ እና የነገሥታቱ በተለይምም የዓፄ ሰይፈ አርዓድ፣የዓፄ ዳዊት ካልእ እና የዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ ሚና ምን እንደነበር ተወስቷል፡፡

ግሼን ከደረሰ በኋላ እንዴት እንተቀመጠ፣የት እንደተቀመጠ፣ለመስቀሉ ደኅንነትና ጉዳት እንዳይደርስበት ምን መደረግ እንደሚገባ ትዕዛዛት ተላልፈዋል፡፡ የደብሩና የአምባሰል አስተዳዳሪ (የዣንጥራሩ) ግንኙነት ምን መሆን እንዳለበትም ንጉሣዊ ድንጋጌዎች አሉት፡፡ በወቅቱ፣ከአምስት መቶ በላይ የሚሆኑ የነገሥታቱ ቤተሰቦች በአምባው ላይ ይኖሩ ስለነበር እነሱንም የሚመለከት ሕግጋት ተሠርቷል፡፡

ታሪኩንም ደንቡንም የጻፈው ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ነው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ፣ መስቀሉ ከግብጽ እንዴት እንደመጣ፣ግሼን እንዴት እንደደረሰ፣ቤተ ክርስቲያናቱ ስለታነጹበት ሁኔታ፣መስቀሉ እንዴት እንደተቀመጠ የሚያትቱን ክፍሎች እዚያው በደብሩ እያሉ የተጻፉ ይመስላል፡፡ የመስቀሉን የቀደመ ታሪክ እንዲሁም የደብሩን እና የዣንጥራሩን ግንኙነት ደግሞ ኋላ ከደብረ ብርሃን (ከዋና ከተማው) ሆኖ በሌላ ጊዜ የላካቸው ይመስላል፡፡ እስኪ ስለመስቀሉ የሦስቱን ነገሥታት ሚና በቅድሚያ እንመለከት፡፡

ዓፄ ሰይፈ አርዓድ (1328-1356)፤
ንጉሡ፣ ወደ ምስር (ግብጽ) ወርደው እንደነበር መጽሐፈ ጤፉት ላይ ተገልጿል፡፡ የሔዱትም በዘመቻ መልክ ነው፡፡ የወቅቱ የግብጽ ንጉሥ (መርዋን አልጋዲን) ከኢትዮጵያ ጋር በሃይማኖት አንድ በሆኑት በእስክንድርያ ሕዝበ ክርስቲያን ላይ አገዛዙን ከማጽናቱ ባለፈ የእስክንድርያውን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሚካኤልን (47ኛው ሊቀ ጳጳስ) ስላሰራቸው ለማስፈታት ወደ ግብጽ ዘምቷል፡፡

የግእዙ ንባብ እንዲህ ይላል፡፡

“ወሶበ ሰምዓ ንጉሠ ኢትዮጵያ ሰይፈ አርዓድ ከመ ኰንንዎ መኳንንተ ተንባላት ለዝንቱ አብ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ወሞቅሕዎ፡፡ ቀንዓ ቅንዓተ መንፈሳዊተ በእንተ ዘዘኮነ እስክንድርያ ወኢትዮጵያ አሐተ ሃይማኖተ፡፡ ወወረደ ብሔረ ግብፅ ዘምስለ ብዙኃ ሠራዊት፡፡”

ታሪከ ነገሥቱም ቢሆን ንጉሡ ወደ ግብፅ መውረዳቸውን ይገልጻል፡፡ ልዩነታቸው የታሰሩት ሊቀ ጳጳስ ስም ላይ ብቻ ነው፡፡ በታሪከ ነገሥቱ የሊቀ ጳጳሱ ስም አባ ማርቆስ ነው፡፡

ዓፄ ሰይፈ አርዓድም ግብፅ ወርደው ለመርዋን አልጋዲን ጳጳሱን ከእስር እንዲፈታ ካልሆነ ግን በመካከላቸው ፍቅር እንደማይኖር ስለጻፈላቸው ከእስር ፈቷቸው፡፡ ንጉሡም ለሊቀ ጳጳሱ እጅ መንሻ ወርቅ ልከው ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡ ስለሆነም፣በመጽሐፈ ጤፉት መሠረት በዐፄ ሰይፈ አርዓድ ዘመን መስቀሉ አልመጣም፡፡ ይሁን እንጂ፣ታሪኩ ከላይ በቀረበው መልኩ ተካትቷል፡፡

ዓፄ ሰይፈ አርዓድም በ1328 ዓ.ም. ነግሠው 28 ዓመታት ከገዙ በኋላ እንዳረፉ መጽሐፏ ገልጻለች፡፡ ቀጥሎም ልጃቸው ውድም አስፈሬ ለ10 ዓመታት ነግሷል፡፡

ዳግማዊ ዓፄ ዳዊት (1366-1397)፤

መጽሐፈ ጤፉት፣ እንደመጽሐፍ የተጻፈችበት ምክንያትን እንዲህ በማለት ይጀምራል፡፡

“… ንዌጥን በረድኤተ እግዚአብሔር ሕያው ዘከመ ተረከበ መስቀለ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ መንግሥቱ ለዳግማዊ ዳዊት….ወዘከመ መጽአ ውስተ ብሔረ ኢትዮጵያ በመዋዕለ መንግሥተ ወልዱ ዘርዓ ያዕቆብ፡፡ ወቦአ ውስተ ደብረ ነገሥት አሀገረ አምባሰል፡፡”

የአማርኛ ትርጉሙም እንዲህ ነው፡፡ “በዳግማዊ ዳዊት ዘመነ መንግሥት የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል እንደተረከቡ፤ልጃቸው ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ በነገሡበት ዘመንም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ አምባሰል ደብረ ነገሥት እንደገባ (እንደተቀመጠ) እንናገራለን፡፡”

ከዚህ የምንረዳው ዓፄ ዳዊት መስቀሉን ከግብፆች ተረክቧል፡፡ ይኹን እንጂ፣በዓጼ ዳዊት ዘመን ወደ ኢትዮጵያ አልገባም፡፡

ታዲያ ዓፄ ዳዊት ተረክበውት ከነበረ፣ ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ እስኪነግሥ (ቢያንስ ለ35 ዓመታት ያህል የት እንደነበር አሁንም በመጽሐፈ ጤፉት በዝርዝር ተተርኳል፡፡ ታሪኩም በአጭሩ እንዲህ ነው፡፡

የምስሩ ንጉሥ፣ ዓፄ ሰይፈ አርዓድ መሞቱን ሲሰማ በድጋሜ ጳጳሱን አሰሯቸው፡፡ በዚህን ጊዜም ከምስር ሕዝበ ክርስቲያን በተጨማሪ የሮም፣የቁስጥንጥንያ፣የሶሪያና አርመን ክርስቲያኖች በግብፁ ንጉሥ ድርጊት ምክንያት መስቀሉን መሳለም እንዳልቻሉ እና የኢትዮጵያን ንጉሥ እንዲረዷቸው ጥያቄ አቀረቡ፡፡

ይኼን የሰማው፣ ለሃይማኖቱ ቀናተኛ የሆነው ዳግማዊ ዳዊት ወደ ግብፅ ዘመተ፡፡ ንጉሡም ካርቱም በደረሰ ጊዜ የዓባይን ወንዝ ወደበርሃ እንዲፈስ በማድረግ አቅጣጫውን እንዲቀየር አደረገው፡፡ ግዕዙ እንዲህ ይነበባል፡፡ “ወሶበ በጽሐ ኀበ ካርቱም ወጠነ ከመ ይሚጦ ለፈለገ ዓባይ ከመ ይክልኦሙ ማየ ፈለገ ዓባይ…”

የዓፄ ዳዊትን አድራጎት የሰማው የግብፁ ንጉሥ፣ የመርዋን አልጋዲን ልጅ አህመድ፣ ጳጳሱንም ሆነ ሌሎች እስረኞች ከእስር ለቀቃቸው፡፡ በመቀጠልም ጳጳሱንና የየአገራቱን ሕዝበ ክርስቲያን፣ ዓፄ ዳዊትን ዓባይ እንደቀድሞው እንዲፈስ እንዲሁም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለእጅ መንሻ የሚሆን ወርቅ በመላክ ጭምር አስለመኑ፡፡

ዓፄ ዳዊት ግን ጉዞውን ሳያቆም ወደ አስዋን ወረዱ፡፡ ወርቁንም ሳይቀበል መልሶ ላከ፡፡ የውሃውንም ፍሰት አላስተካክልም አለ፡፡ ይልቁንም “መስቀሉን ስጠኝ” በማለት መልዕክት ሰደደ፡፡ “ወንጉሠ ምስርሰ አህመድ ወመኳንንተ ተንባላት ተሐውኩ ብዙኃ በምክንያተ ዝንቱ፡፡” ይላል ግዕዙ፡፡ “በዚህም ምክንያት የአሕዛቡ የምስር ንጉሥ አህመድና መኳንንቱ ፈጽመው ታወኩ፡፡” የንጉሡን ቁርጠኝነት ሲያውቁ መስቀሉን፣ሉቃስ የሣላቸውን ሰባት የእመቤታችንን (የማርያምን) ሥዕሎች ዮሐንስ ወንጌላዊ የሣለውን ሥዕል ጨምሮ ላከ፡፡

ይህም የተደረገው መስከረም 10 ቀን ነው፡፡ ንጉሡም በዚህ ቀን ታላቅ በዓልን አደረገ፡፡ በዚህ ብቻ ሳይበቃም፣ ከመስከረም 17 ጀምሮ ለ7 ቀናት ታላቅ በዓልም ተደረገ፡፡ ከዚህ በኋላም፣ እነዚህን ቅርሶች በመያዝ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ላይ ሳለ፣ስናር የተባለ ቦታ ላይ ዓፄ ዳዊት በድንገት አረፈ፡፡ ያረፈው፣ ጥቅምት 9 ቀን ነው፡፡ ሰላሳ ዓመት፣ከ6 ወራት፣ከ9 ቀናት ገዝቶ ሞተ፡፡

በመሆኑም፣ዓፄ ዳዊት መስቀሉን የተረከበው በ1397 ዓ.ም. መስከረም 10 ቀን ሲሆን የሞተው ደግሞ በዚሁ ዓመት (ሱዳን ውስጥ) ስናር ላይ ነው፡፡ ከዚያም፣ጣና፣ ዳጋ እስጢፋኖስ ተቀበረ፡፡ (ዓፄ ዳዊት ያረፉበትን ዓመት በተመለከተ በርካታ መጽሐፍት ላይ ልዩነት እንዳለ ያጤኗል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ላይ ግን እንዳለ የመጽሐፈ ጤፉት ነው የተገለጸው፡፡)

ታሪከ ነገሥቱ በበኩሉ ባዝራ (በቅሎ) ግምባራቸው ላይ ረግጣ እንደገደለቻቸው ይገልጻል፡፡ መጽሐፈ ጤፉት፣ በምን ምክንያት እንደሞቱ ባይናገርም፣ሊሞቱ ሲሉ በዚሁ ስናር በተባለው ቦታ ጥቅምት 9 ቀን ለልጆቻቸው የመንግሥትን ሥርዓትና ወግ ጽፈው እንዳረፉ ይናገራል፡፡ ከመሞታቸው በፊት እንደሚሞቱ ያወቁት ምናልባት የባዝራዋ ጎድቷቸው ነገር ግን በቅጽበት ባለመሞታቸው ሊሆን ይችላል፡፡

ይሁን እንጂ ንጉሡ ሲሞቱ ቅርሶች አብረው አልመጡም፡፡ ዘርዓ ያዕቆብ እስኪነግሥ ድረስ እዚያው ስናር እንደቀሩ አሁንም መጽሐፈ ጤፉት ትነግረናለች፡፡ በዳዊትና በዘርዓ ያዕቆብ መካከልም ሌሎች ልጆቹ እንደነገሡም እንዲሁ ተተርኳል፡፡

በመሆኑም፣መስቀሉንም ሆነ ሌሎቹ ቅርሶችን ዓፄ ዳዊት ተረክቧቸው ነበር፡፡ ነገር ግን በንጉሡ ድንገተኛ ዕረፍት ምክንያት ስናር ላይ ቀሩ፡፡

ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ (ከ1427 ጀምሮ)፤

ዓፄ ዳዊት በስናር አርፎ በዳጋ እስጢፋኖስ ሲቀበር መስቀሉ እና ሌሎቹ ቅርሶች እዚያው ስናር እንደቀሩ ተገለጿል፡፡ ዓፄ ዳዊት በሕይወት በነበረበት ወቅት “ይነብር መስቀልየ በዲበ መስቀል” የሚል ህልም ዐይቶ እንደነበር ተጽፏል፡፡ ትርጓሜውም “መስቀሌ በመስቀል ላይ ይቀመጣል፤” ነው፡፡

ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብም በ1427 ዓ.ም. ነገሠ፡፡ ኋላ ላይ እንደ አባታቱ ህልም ተገለጠለት፡፡ ይህ የኾነው ደግሞ በነገሠ በ15 ዓመቱ ነው፡፡ 1442 ዓ.ም. መሆኑ ነው፡፡ ህልሙም፣ “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል” የሚል ነው፡፡ ትርጓሜውም “መስቀሌን በመስቀል ላይ አኑር/አስቀምጥ!” የሚል ነው፡፡ ለአባታቱ በትንቢትነት፣ወደ ፊት በሚፈጸም መልኩ የታየው ህልም፤ ለዘርዓ ያዕቆብ በትእዛዝነት ተገለጠ፡፡

ንጉሡም ከሊቃውንቱ ጋር በመመካከር፣ስለ ህልሙ ሲያወጣና ሲያወርድ አንድ ዓመት አለፈ፡፡ ከዚያም፣ሊቃውንቱና የመንግሥቱ አማካሪዎች ፍቹን ነገሩት፡፡ “ወእሙንቱኒ ይቤሉኒ እስመ መስቀለ ክርስቶስ አምኃሁ ለአቡከ ሀሎ በእደ መኰንነ ተንባላት ዘመካ መዲና” ብለው ለገሩኝ ሲሉ ራሳቸው ንጉሡ ተናግረዋል፡፡ ትርጓሜውም፣ “እነሱም ይኽማ ለአባትህ እጅ መንሻ ሆኖ የመጣው የክርስቶስ መስቀል በመካ መዲናው ሹም እጅ አለና አምጣ!” ሲልህ ነው ይሉታል፡፡

ከዚያም ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብም “ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት” በማለት ወደ መካ መዲናው ሹም ዘመቻ ጀመሩ፡፡ የመካና መዲናው ሹም ስምም ‘ጋፍሔር’ ይባላል፡፡ በዚያን ዘመን የነበረው የምስሩ ንጉሥ ደግሞ ‘አሽረፍ’ ነበር፡፡ ከጽሑፉ መረዳት የሚቻለው ጋፍሔር፣በንጉሥ አሽረፍ ሥር የነበረ ገዥ መሆኑን ነው፡፡

ጋፍሔርም፣የዘርዓ ያዕቆብን መምጣት ሲሰማ “የአባትህ ገንዝብ በእጄ አለና ተቀብለህ ወደ አገርህ በሰላም ተመለስ” የሚል መልዕክት ላከለት፡፡ ዘርዓ ያዕቆብም መስቀሉን፣ ሰፍነጉን፣ ከለሜዳውን፣ ሥዕሎቹን፣ የቅዱሳኑን አጽም እና ሌሎችንም በመቀበል ከነሠራዊቱ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ ለሦስት ዓመታት ያህል በየተራራው በመዞርና በማሳረፍ እንደ ህልሙ ለመፈጸም ንጉሡ ጥሯል፡፡ ከሦስት ዓመታት መንከራተትና ልፋት በኋላ እስከ ዓፄ ይኩኖ አምላክ ድረስ ደብረ ነጎድጓድ፣ቀጥሎም ደብረ ነገሥት የተባለችው የአሁኗ ግሼን ደብረ ከርቤ አምባ ላይ ደረሰ፡፡ የተራራውን ግርጌ በመከተል ሦስት ጊዜም ዞራት፡፡ድጋሜ ከመልአክ በህልም ትእዛዝ ከተቀበለ በኋላ ከወቅቱ ጳጳሳት ከአባ ሚካኤል እና ከአባ ገብርኤል ጋር በመሆን ወደ አምባው በ1446 ዓ.ም. መስከረም 21 ቀን ገቡ፡፡

ከአምባው ላይ ቀደሞ በ514 ዓ.ም. በዓፄ ካሌብ ዘመን፣በአባ ፈቃደ ሥላሴ፣የናግራን መነኩሴ አማካይነት የተተከሉ የማርያምንና የእግዚእብሔር አብ ቤተ ክርስቲያናት ስለነበሩባቸው የእግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያንን ድጋሜ በማሳነጽ በመሠረቱ ሥር መስቀሉንና ሌሎቹን ቅርሶች አስቀመጣቸው፡፡

የቤተ ክርስቲያኑ ግንባታም ሦስት ዓመታት ፈጅቷል፡፡ ቤተክርስቲያኑ የነበረበት ቦታ ርጥበት ያለበት ስለነበር ርጥበቱን የሚያጠፋ አፈር አድርገውበታል፡፡ ለመስቀሉ እና ለሌሎች ቅርሶች ማስቀመጫ ይሆን ዘንድ አርባ ክንድ ወርድ፣ርዝመትና ከፍታ ያለው ጉድጓድ በማስቆፈር እና ዙሪያውን በመገንባት ርጥበቱም እንዲጠፋ በሰማንያ ስምንት ግመሎችና በመቶ አጋሰስ ከኢየሩሳሌም አፈር በማስመጣት ለግንባታው ውሏል፡፡

ከዚያም መስቀሉን፣ሥዕላቱን፣የቅዱሳኖቹን አጽም፣ሰፍነጉን፣ጅራፉን፣ከለሜዳውን ወዘተ በምን ሁኔታ እንደተቀመጠ በዝርዝር ተገልጿል፡፡ የእነዚህ ቅርሶች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ለጉዳትም ለመቅሰፍትም ስለሚሆን ጊዜው እስኪደርስ ማንም እንዳያወጣቸው ትእዛዝ ተበጅቷል፡፡ በተለይ መስቀሉ በተለያዩ ሁኔታ ከተዘጋጁ ድርብርብ ሳጥን ውስጥ ሌላ የወርቅ እና የዕንቁ ሳጥን በማዘጋጀት በውስጡም በሰንሰለት በማሰር በአየር ላይ ብቻ እንዲረብ (እንዲጠለጠል) መደረጉን ተጽፏል፡፡

መስቀሉም ሲመጣ፣ እንደሰው እንዲቆም አድርገው የውጮቹ ጠቢባን ሰገባ እና እግር እንዳዘጋጁለትም ተገልጿል፡፡ በመጨረሻም፣የጉድጓዱ አፍ ተዘግቶ በላዩ ላይ ድጋሜ የእግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን ታነጸ፡፡ የማርያምን ቤተክርስቲያንም እህቱ ዕሌኒ (ሚስቱ አይደለችም) በድጋሜ አሳንጻው አብረው በ1449 ዓ.ም. መስከረም 21 ቀን ተመረቁ፡፡ ቅዳሴ ቤታቸው በድጋሜ ተከበረ፡፡

ሲጠቃለል፣መስቀሉንና ሌሎች ቅርሶችን ዓፄ ዳዊት በ1397 ዓ.ም. መስከረም 10 ቀን ተረክቧል፡፡ ነገር ግን፣ስናር ላይ ሲደርስ ስላረፈ እነዚህ ቅርሶችም እዚያው ለ46 ዓመታት ይህል በአሕዛብ እጅ ሰንብተዋል፡፡ ኋላ ላይ በ1443 ዓ.ም. ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ ከነበሩበት ቦታ በመስመጣት በ1446 መስከረም 21 ቀን አምባሰል፣ደብረ ነገሥት (ደብረ ከርቤ ብለው የሰየሟት) ደርሷል፡፡ ንጉሡም አብሮ በመሔድ፣ቤተክርሰቲያኑንም አሳንጿል፡፡ ሥርዓቱንም አብጅቷል፡፡

መስቀሉ መስከረም 21 ቀን ግሼን ደብረ ከርቤ ደረሰ፡፡

ቤተ ክርስቲያናቱ ከእንደገና ታንጸው፣መስቀሉም በክብር ተቀምጦ ክበረ በዓሉ የተከናወነው መስከረም 21 ቀን ነው፡፡

መስከረም 21 ቀን ምን ጊዜም ግሼን ትከበራለች፡፡

ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብን ክፍሉን ከጻድቃኑ ጋር ያድርግለ

Filed in: Amharic